የቅዱስ ያሬድ 1500ኛ ዓመት መታሰቢያ በዓልን አስመልክቶ ማኀበረ ቅዱሳን በግዮን ሆቴል ባዘጋጀውና ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን በተገኙበት አውደ ጥናት ላይ የቅዱስ ያሬድ ሕይወትና ሥራዎቹ በተባበሩት መንግሥታት የትምህርት የሳይንስና የባሕል ድርጅት /UNESCO/ ለማስመዝገብ የሚደረገው ጥረት ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት ተገለጸ፡፡
ቅዳሜ ግንቦት 10 ሙሉ ቀን በተደረገው በዚህ ዐውደ ጥናት ላይ ብፁዕ አቡነ ዲዮስቆሮስ የደቡባዊ ትግራይ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ፤ ከየአድባባራቱና ገዳማት ጥሪ የተደረገላቸው ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን፤ የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ምሁራን፤ ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች የተገኙ ሲሆን በብፁዕነታቸው ጸሎትና ቃለምዕዳን ዐውደ ጥናቱ ተከፍቷል፡፡
ብፁዕ አቡነ ዲዮስቆሮስ በሠጡት ቃለ ምዕዳን ማኅበሩ የቅዱስ ያሬድን 1500ኛ መታሰቢያ በዓልን ማዘጋጀት በመቻሉ አመስግነው በአሁኑ ወቅት በቅዱስ ያሬድ የዜማ ትምህርት ከፍተኛ እውቀት ያላቸው አባቶች ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተመናመነ መምጣቱንና በሀገረ ስብከታቸው ከሚገኙ 1000 ገዳማትና አድባራት ውስጥ በጣም ጥቂት የድጓ መምህራን ብቻ እንደሚገኙ ገልጸዋል፡፡ ይህም አሳሳቢነቱን ከፍ ስለሚያደርገው ከፍተኛ ጥረት መደረግ እንደሚገባው አሳስበዋል፡፡
በባሕልና ቱሪዝም ሚኒስቴር የሚኒስትሩ ተወካይ የሆኑት አቶ ወርቅነህ አክሊሉ ባቀረቡት ንግግር “ቅዱስ ያሬድ ወደር ያልተገኘለትና ዓለምን ያስደመመ የዜማ ጥበብ ባለቤት እንደመሆኑ የሥራ ውጤቶቹ ዘመን ተሻጋሪ ሆነው እሰካለንበት ዘመን ከነውበታቸውና ከነክብራቸው ሊደርሱ ችለዋል፡፡ ተሸናፊነትን ያሸነፈ የትእግስት ተምሳሌት በመሆን አንድን ስጋዊም ሆነ መንፈሳዊ ተግባር ከዳር ለማድረስ ያለመታከት መሥራትን በማሳየት ለተስፋ ቆራጭ ትውልድ የሕሊና ትንሳኤ አብነት ተደርጎ ሊቆጠር የሚችልና የሚገባውም ታላቅ ሊቅ ነው” በማለት ገልጸዋል፡፡
በተጨማሪም የቅዱስ ያሬድ ሥራዎች ድንበር ተሸጋሪነት ሲገልጹ “ቅዱስ ያሬድን ባሰብን ጊዜ የዘመን ውሽንፍር ያልገደባቸው ድርሰቶቹን እንደናስብ ስለሚያደርገን ዛሬም ድረስ በዚህ ሊቅ የሥራ ውጤቶች እንደ ኢትዮጵያዊነታችን እንኮራበታለን፡፡ የሌሎች ሀገሮች ህዝቦችም እንዲያውቁትና ይህ ጥበብ ድንበር ተሻጋሪ እንዲሆን ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመተባበር እንሰራለን” ብለዋል፡፡
በአውደ ጥናቱ ላይ አምስት ያህል ጥናታዊ ጽሑፎች የቀረቡ ሲሆን ከእነዚህም መካከል ሊቀ ኅሩያን በላይ መኮንን የቅዱስ ያሬድ ልደቱ፤ እድገቱ፤ የማኅሌታዊና የምናኔ ሕይወቱ በሚል ርዕስ ጥናታቸውን አቅርበዋል፡፡
ዲያቆን ሰሎሞን ወንድሙ በበኩላቸው የቅዱስ ያሬድ ዜና ሕይወቱ በተለያዩ ጸሐፍት ሥራዎች ሲዳሰስ በሚል ርዕስ ባቀረቡት ጥናትም በተለያዩ ጸሐፊያን የልደት ቀኑ፤ የእናትና አባቱ ስም፤ በስጋ ማረፉን ወይም መሰወሩን፤ የመምህራኖቹ ስም፤ . . . ወዘተ የመሳሰሉት ጉዳዮች ወጥነት ኖሯቸው መስተካከል እንደሚገባቸው መረጃ በማጣቀስ አቅርበዋል፡፡
ዲያቆን ያረጋል አበጋዝ ኦርቶዶክሳዊ ስብከት ከቅዱስ ያሬድ ድርሳናት አንጻር በተሰኘው ጥናታቸውም አንድ ኦርቶዶክሳዊ ስብከት ሊያሟላቸው ከሚገባቸው መሠረታዊ ነጥቦች አንጻር የቅዱስ ያሬድን ድርሰቶች በመመዘን አቅርበዋል፡፡
ሊቀ ጠበብት ተክሌ ሲራክ ባቀረቡት ጥናትም አራቱ የዜማ ዐበይት መንገዶች በሚል አጠር ያለ ዳሰሳ አቅርበዋል፡፡ የቤተልሔም፤ የቆሜ፤ የአጫበርና የተጉለት ዜማዎችን በትውልድ ቅብብሎሽ በመከፋፈል ለማሳየት ጥረት አድርገዋል፡፡ በተለይ የተጉለት ዜማ በመጥፋት ላይ እንደሚኝና በአሁኑ ወቅት አንድ አባት ብቻ እንደቀሩና ለትውልድ ለማሸጋገር ብዙ መሰራት እንዳለበት ጠቁመዋል፡፡
የመጨረሻው ጥናት በሙዚቃው ዘርፍ ባለሙያ የሆነውና በቅዱስ ያሬድ ሥራዎች ላይ ከፍተኛ ምርምር እያደረገ የሚገኘው ሠርፀ ፍሬ ስብሐት የቅዱስ ያሬድ ዜማ በባሕላዊውና በዘመናዊው ሙዚቃ ያለው ተጽእኖ በማስመልከት አጠር ያለ ጥናታዊ ዳሰሳ አድርገዋል፡፡
በቀረቡት አምስት ያህል ጥናቶች መነሻነት የጉባኤው ተሳታፊ በሆኑት ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን አስተያየቶችና ጥያቄዎች ተስተናግደዋል፡፡
የውይይቱ መቋጫ የሆነውም የቅዱስ ያሬድ ታሪክና ሥራዎች በተባበሩት መንግስታት የትምህርት የሳይንስና የባሕል ድርጅት /UNESCO/ ለማስመዝገብና ለዓለም ለማስተዋወቅ ጥናቶች እንዲጠኑ በማድረግና በማስተባበር አንድ እልባት ላይ መድረስ እንዲቻል ከጠቅላይ ቤተ ክህነት፤ ከሊቃውንት ጉባኤ፤ ከሊቃውንት አባቶች፤ ከባሕልና ቱሪዝም ሚኒስቴር፤ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲና ከሙዚቃ ባለሙያዎች እንዲሁም ከማኅበረ ቅዱሳን የተውጣጣ 17 አባላትን ያቀፈ ኮሚቴ እንዲዋቀር በማድረግ ዐውደ ጥናቱ ተጠናቋል፡፡