የ ቆሙ መቃብሮች

መጋቢት 16 ቀን 2005 ዓ.ም.

በመ/ር ስምዓኮነ መላክ

ሰዎች ሲሞቱ ወይም ነፍሳቸው ከሥጋቸው ሲለይ በክብር የሚያርፍበት ቦታ መቃብር ይባላል፡፡ መቃብር የሚላው ቃል የጎደጎደ ምድር ተብሎ ይተረጎማል፡፡ መዝ.14፥4፣ ኢሳ.22፥16 ሲዖልንም መቃብር ሲል ይገኛል፡፡ መትሕተ ታሕቲት ናትና፡፡

በማን ጊዜ እንደተጀመረ ባይታወቅም የሚቀበሩት በርስትነት በያዙት ቦታ ነበር ዘፍ.13፡፡ ያ ልማድ ሆኖልን ዛሬም በአዲስ ኪዳን የምንኖር ክርስቲያኖች እንደ አባቶቻችን ሁሉ በቤተ ክርስቲያን ዙሪያ እንቀበራለን፡፡ ስለምን ቢሉ ሥጋውን ደሙን የበላንበትና የጠጣንበት ብቸኛዋ ርስታችን በምድር ቤተ ክርስቲያናችን ናትና ነው፡፡

የቀደመው ርስት በዋጋ ይገዛ ነበር የዛሬዋ የምእመናን ርስት ቤተ ክርስቲያን ዋጋዋ የክርስቶስ ደም ነውና ደሙ በነጠበበት ቦታ ብቻ ስትሠራ ትኖራለች የምእመናን መቃብር በጌታ ደም የተገዛ እንጂ በሰቅል በተመዘነ ወርቅ የተገዛ አይደለም፡፡ ይህም የጌታ ደም ከሁሉ በላይ የከበረ እንደሆነ የምእመናንም መቃብር የከበረ መሆኑን ያመለክታል፡፡

ለዛሬው ግን መቃብርን ያነሣነው ከአቤል ሞት ጀምሮ እስከ ጌታ ዳግም ምፅአት የማያቋርጥ ታሪክ ያለውን ጀግና ባለ ታሪክ መቃብርን ታሪኩን ለትውልድ ልናስተዋውቅለት ሳይሆን መምህራችን ኢየሱስ ክርስቶስ ስለቆሙ መቃብሮች የተናገረውን ቃል ማስታወስ ስለሚገባ ነው፡፡

መድኀኔ ዓለም ኢየሱስ ክርስቶስ ስብከት በጀመረ በመጨረሻው ዓመት በመቅደስ ተገኝቶ ለሕዝቡና ለደቀመዛሙርቱ ተናገረ፡- “ታላቅ ሸክም ማሰር ሰለሚችሉት መሸከም ግን ስለማይወዱት ስለ ጻፎችና ፈሪሳውያን ነበር የተናገረው፡፡

ለብዙዎች ብዙውን ኀጢአታቸውን በፍቅር የሸፈነው ጌታ ስለ ወንጀለኞች ሲጠየቅ ዝም የሚለው አምላክ ዮሐ.8፥11፣ ሉቃ.7፥47 በቤተ መቅደሱ አደባባይ በተሰበሰበው ሕዝብ መካከል የእነዚህን ታላላቅ የኦሪት አገልጋዮች በደል መዘርዘር ጀመረ፡፡ ተመክሮ ያልተመለሰን ሰው በአደባባይ ሊወቅሱት ይገባልና ጌታ በቅዱስ ወንጌል እንደተናገረው “ቢሰማህ ብቻውን አድርገህ ብቻህን ሆነህ ምከረው ባይሰማህ ካንተ ጋር ሁለት ሆናችሁ ምከረው….. እነርሱንም ባይሰማ ለቤተ ክርስቲያን ንገራት” ማቴ.18፥15-17 ብሎ በእግዚአብሔር ጉባኤ ላይም የማይገባ ነገርን አድርገዋልና መገሰጽ ስለሚገባቸው በታላቅ ቃል ገሰጻቸው 1ቆሮ.5፥5 በመጽሐፍ ቃልህ እውነት ነው ተብሎ የተነገረለት መምህር ነውና ዮሐ.17፥17 እነርሱን ከውስጥ እስከ ውጭ ሊገልጹ በሚችሉ የተግሣፅ ቃላት ገሰፃቸው፡፡

በዘመኑ የነበሩ መምህራን አባቶቻቸው በሠሩት ኀጢአት የተጸጸቱ ለመመሰል አባቶቻቸው የገደሏቸው የነቢያትን መቃብር በኖራ እየለሰኑ ይሠሩና ያሠሩ ነበርና ያንኑ የሠሩትን ልስን መቃብር እየተመለከተ “የተለሰነ መቃብር የምትመስሉ” ሲል ተናገራቸው ይህ መቃብር ቢከፍቱት ለአፍንጫ የሚከረፋ ለዐይንም የሚከፋ ነገር አይታጣበትም፡፡ ሥጋው ተልከስክሶ አጥንቱ ተከስክሶ፣ እዡ ፈሶ ሲታይ ከውጭ የተለሰነ ውበቱን ያጠፋዋል፡፡  አብረውት እንዳይኖሩ ያስገድዳል በዚህ ረጅም ዕድሜው እንደላዩ ሁሉ ውስጡ አምሮ አያውቅም፡፡

ዘመኑን ሁሉ ሕይወት በሌላቸው ነገሮች የተሞላ ሆኖ ይኖራል እንጂ፡፡ ከዕለታት ባንዱ ስንኳን ንጹህ ነገር ክርስቶስን ቢያገኝ በሥጋ የሞተው በመንፈስ ግን ሕያው የሆነው ጌታ በትንሣኤ አሸንፎት ይዞ ማስቀረትም አይቻለው ብሎ ባዶውን ቀርቶ ይሄው እስከዛሬ ያለ ክርስቶስ ይኖራል፡፡ በእውነት ክርስቶስ በመቃብር መስሎ የተናገረበት ነገሩ ምን ይመስላችኋል? ለጊዜው የሚያመለክተው በዚያ ዘመን እስከ ክርስቶስ ወደ መቃብር መውረድ ድረስ በሰው ልጆች ላይ ሙስና መቃብር በሥጋቸው ወደ ሲዖል መውረድ በነፍሳቸው የግድ የነበረባቸው መሆኑን ያመላክታል፡፡

በዘመኑ ባለ ጊዜ ሆኖ ሞት ውጦ መቃብር ተረግጦ የማስቀረት ኀይል ነበረውና፡፡ ያንን የሚገልጽ ሲሆን ፍጻሜው ግን ከውጭ ለሰው መልካም መስለው ስለሚታዩት ከውስጥ ግን ለእግዚአብሔር የሚመች በጎ ተግባር የሌላቸው ሰዎች እንዲገሰጹበት የተጻፈ ነው፡፡

ከውጭ ሲያዩአቸው ይጸልያሉ ይጾማሉ በጾምና በጸሎት ብዛት በገድልና በትሩፋት ጠውልገው ይታያሉ ስመ እግዚአብሔርን ጠርተው ይምላሉ ሐሰቱን እውነት ያስመስላሉ በልባቸው የሌላውን የእግዚአብሔር ቃል አንሥተው ሲናገሩ በቂሳርያ ከተመሰገነው ጴጥሮስ ይበልጣሉ ዝምነታን በማያውቀው አንደበታቸውም ደግመውና ደጋግመው ስሙን ሲጠሩ ከጳውሎስ በላይ ሰባኪ ይመስላሉ ከውስጣቸው ግን እንዲህ አይደሉም፡፡ አመጽንና ሽንገላን ተሞልተዋል፡፡ በክፉ ምኞታቸውና አስቀያሚ በሆነው መሸታቸው የገዛ ነፍሳቸውን ገለው የገዛ ሥጋቸውን መቃብር አድርገው ቀብረዋል፡፡

በወይንና በአረቂ አልሰከሩም እንጂ በኀጢአት ሰክረው ወድቀዋል፡፡ ከመብልና ከመጠጥ እንጂ ክፉ ተግባራቸውን ከመተው የማይከለክሉ ይልቁንም በሞተ ሥራ የተሞሉ የቆሙ መቃብሮች ሆነዋል ስለዚህም መቃብር ውስጥ ያሉ ሙታንን ስንኳን የማይጠላ ጌታ ለተለሰኑ መቃብሮችም በቤተ መቅደሱ አደባባይ ቆሞ አሳምረው የለሰኑአቸው ልስን መቃብሮችን አሻግሮ እየተመለከተ ሁሉም ወደ መዳን የሚደርሱበትን ሕያው መልእክቱን አስተላለፉ፡፡

ወንድሜ ሆይ! አንተስ እንዳምን ነህ? ከውስጥህስ ምን ይገኛል? እግዚአበሔር አንተን ክርስቲያን አድርጎ ሐዋርያት ከሰበሰቧት አንዲት ማኅበር አባል ሲያደርግህ ምን ዓይነት ዓላማ እንደነበረው ታውቃለህ? ጨለማውን ዓለም ካንተ በሚወጣው የመንፈስ ቅዱስ ብርሃን ሊሞላው፣ ሕይወት አልጫ ለሆነችባቸው ማጣጫ ሊያደርግህ ማቴ.5፥12-13 በአሕዛብ መካከል ስሙን አሸክሞ ሊልክህ ሐዋ.9፥5 ዓላማ ስላለው ነው፡፡

የታመሙትንና በአጋንንት ተይዘው የሚሰቃዩትንም የሚፈውሳቸው ለምጻሞችን የሚያነጻቸው የረከሱትን የሚቀድሳቸው አንተን መሣሪያ አድርጎ እንደሆነ ታውቃለህ? አንተ ግን ለዚህ ዓላማ የተጠራህ መሆንህን የረሳህ ትመስላለህ፡፡ በአለባበስህና በከንፈርህ ብቻ እግዚአብሔርን ታመልካለህ ቀን ቆጥረህ ደማቅ በሆኑ የዓመትና የወር በዓላት ብቻ ለእግዚአብሔር ትዘምራለህ በሌላው ቀን ግን ትጠፋለህ ቃሉን ታውቃለህ እንደ ቃሉ መኖር ግን ተስኖሃል ከውጭ እንጂ ከውስጥ የሚታይ ነገር የሌለህ መጥፎ ሰው ሆነሃል፡፡ በክፉ መሻትህ እየወጋህ ሕያዊት ነፍስህን ገለህ የቆመ መቃብር ሆነሃታል፡፡

የማይታይ የተሰወረ የማይገለጥ የተከደነ አለ ይመስልሀልን? ከአምስት ሺህ አምስት መቶ ዓመት ቆይታ በኋላ ተከድኖ ይኖር የነበረ መቃብር መገለጡን በጌታ ደም ድብቅ ምሥጢሩን ከረጅም ዓመታት በኋላ ማጣቱን እንዳትረሳ ማቴ.27፥57 አንተ ሆይ! ሳይነግሩት የሰውን ማንነቱን የሚያውቅ ጌታ አንተንስ ቢገልጥህ? ዮሐ.2፥25 ከላይ የተለሰነ ኖራህን ቢያነሳብህስ? የቆመው መቃብርነትህ በጌታ ቃል የሞተውን ሳይሆን ሕያው የሆነ አልዓዛርን የሚያስገኝ ይመስልሃል? ብታምን የልቡናህን ትንሣኤ ዛሬ ታየ ዛሬም የተለሰነው መቃብር በር ላይ ቆሞ ይጣራል በውስጥህ ያሉት ሙታን አካሎችህ ዛሬ ድምጹን የሚሰሙበት ጊዜ ደርሷል እርሱም አሁን ነው ዮሐ.5፥25፡፡

የሚያሳዝነው ነገር ተዘግቶ ተለስኖ መቀመጡ ነው እንጂ የተከፈተ መቃብርማ ለብዙዎች የሚያስገርም ምስጢር ተገኝቶበታል እኮ! ሉቃ.24፥12 መላእክቱ የከበቡት የጌታ ደቀ መዛሙርት የጎበኙት ያ ቅዱስ መቃብር ባዶም ቢሆን ለመጀመሪያ ጊዜ ትንሣኤውን የሰበከ እርሱ ነበር፡፡

ወንድሜ ሆይ! የቆመ መቃብር ብትሆንም ለእግዚአብሔር ቃል የተከፈተ ልብ ካለህ እውነት እልሃለሁ ስላንተ ወዳንተ ወደመቃብሩ መላእክቱን ያዝልሀል ለደቀ መዛሙርቱ ሳይቀር የሚደንቅ ጥበብን ይገልጥብሃል ለጌታችን ቃል የተከፈተ ልብህ ዝቅ ብለው ቢያዩትስ የጌታ ልብስ ብቻ እንጂ ሌላ ምን ይገኝበታል፡፡ ከእውቀት፣ ከጥበብህ ከቅድስና የተለየሁ ባዶ ሰው ነኝ ብለህ ብታምን እንኳን እግዚአብሔር ባዶነትህን ለምስክርነት ይሻዋልና ከላይህ ላይ ያለ ልስንህን አስወግደው፡፡

አለበለዚያ የክፉዎች አጋንንት ማደሪያ መሆንህን አትርሳው፡፡ ማቴ.8፥28 ከዚያ በፊት ግን አሁን ዕድል አለህ፡፡ እንደውጪ ሁሉ ውስጠኛውንም የመቃብር ክፍል ማጽዳት ትችላለህ፡፡ አንተ እኮ! ዕድለኛ ነህ፡፡ የአባትህ ድምጹ እስከመቃብር ድረስ ዘልቆ ይሰማል ቅዱስ የሆነው ደሙ በመቃብር ያሉትን ሳይቀር መቃብራቸውን ከፍቶ ይቀድሳል እንዳትረሳ! ይሄ ዕድል ላንተም ተሰጥቶሃል፡፡ ደግሞም አንድ ነገር አለ እግዚአብሔር ለሕዝቡ የገባው ቃል ኪዳን አለ መቃብሩን ከፍቶ ለሞቱ አጥንቶች ሕይወትን ሰጥቶ የሚያኖርበት ጊዜ አለ ይሄ ቃል ኪዳን ላንተም የተገባ ቃል ኪዳን ነውና አትፍራ ምን አልባትም ይሄ ቃል ኪዳን ላንተም የተገባ ተስፋ አትቁረጥ፡፡

በዙሪያህ ሆነው ከመቃብሩ ደጃፍ ድንጋዩን ማን ያንከባልልናል የሚሉም ይኖራሉ ድንጋዩ ታላቅ ቢሆንም ጊዜው ሲደርስ እግዚአብሔር መላኩን ልኮ አንተ ባልጠበቅከው ሰዓት ሊያነሣው እንደሚችል አትጠራጠር፡፡ መቃብር ብዙ ኀያላንን ይዞ ማስቀረቱ የተገለጠ ነው፡፡ እነ ዳዊት እነሶምሶን፣ ዮፍታሔ፣ ጌዴዎን ሌሎችም ኀያላን መቃብር ያድራሉ ደራሲዎቹ የደረሱላቸው ተራኪዎቹ የተረኩላቸው ዜመኞቹም ያዜሙላቸው ጀግኖች ሁሉም ከመቃብር አላመለጡም ምድራዊ ፍጥረት ሥጋዊ ደማዊ ሰውነት ሁሉም የመቃብር ምርኮኞች ሆነዋል፡፡

አንተ ሆይ! ባንተም ውስጥ ስንት ኀያላን የእግዚአብሔር ቃላት ተቀብረው ቀርተዋል መሰለህ? እነ አባ ጳውሊ ከዓለም ወጥተው የኮበለሉባቸው እነ አባ እንጦንስ ሥርዓተ መላእክትን የተላመዱባቸው ይሄ ግዙፍ ዓለም የተከናወነባቸው እነዚያ ሰባሪ ቃላቶች አንተ ዘንድ ሲደርሱ ግን ሳይሠሩ ቀብረህ አስቀርተሃቸዋል፡፡

እውነት እልሃለሁ አዲስ ሆነህ የምትሠራው በቅዱስ ቃሉ ነውና ቃሉን ጠብቅ ብታምንም ባትምንም በክፋት ብትሆን ሳትወድ በግድ “መቃብር ሆይ ይዞ ማስቀረትህ ወዴት አለ?” ሆሴ.13፥14፣ 1ቆሮ15፥55 ተብለህ መጣልህ አይቀርምና ይህ የፈጣሪህ ድምጽ ወዳንተ ባደረበት ቅጽበት ወዲህ በፈቃድህ ንስሓ ግባ ይሄ ጊዜ ለሌላ ለምንም የተመደበ አይደለም የንስሓ ብቻ ነው፡፡

“እነሆ መቃብራችሁን እከፍታለሁ ከመቃብራችሁም አወጣችኋለሁ ወደ እስራኤል ምድርም አገባችኋለሁ መቃብራችሁን በከፈትሁ ጊዜ ከመቃብራችሁም ባወጣኋችሁ ጊዜ እኔ እግዚአብሔር እንደሆንሁ ታውቃላችሁ” ሕዝ.37፥12-13፡፡

ቅድስት

መጋቢት 12 ቀን 2005 ዓ.ም.

በአባ አሥራተ ማርያም ደስታ

የማቴ.6፥16-24 ምንባብ በአንድምታ ትርጓሜ
ቁ.16. በምትጾሙበት ጊዜ እንደ ግብዞች አትሁኑ፡፡ እነዚያ ፊታቸውን አጠውልገው ግንባራቸውን ቋጥረው ሰውነታቸውን ለውጠው ይታያሉና፡፡ እንደ ጾሙ ሰው ያውቅላቸው ዘንድ የወዲህኛውን ውዳሴ ከንቱ አገኙ የወዲያኛውን ዋጋቸውን አጡት ብዬ በእውነት እነግራችኋለሁ፡፡ 

ቁ.17. እናንተስ በምትጾሙበት ጊዜ ራሳችሁን ተቀቡ ፊታችሁን ታጠቡ የተቀባ የታጠበ እንዳይታወቅበት አይታወቅባችሁ ሲል ነው፡፡ ይህስ በጌታ ጾም ምን ውዳሴ ከንቱ አለበት ይኸውስ በከተማ ነው በገዳም ቢሉ በከተማ ነው እንጂ በገዳምማ ምን ውዳሴ ከንቱ አለበት ይህም ሊታወቅ ዳንኤል እኔ ዳንኤል ሦስት ሳምንት ሙሉ ሳዝን ማለፊያ እንጀራ አልበላሁም ሥጋና ጠጅም በአፌ አልገባም ዘይትም አልተቀባሁም ብሏል፡፡ እናንተስ ራሳችሁን ተቀቡ /ፍቅርን ያዙ/ ፊታችሁን ታጠቡ፣ ንጽሐናን ገንዘብ አድርጉ ወይም ትሕትናን ያዙ፣ በንስሓ እንባ ታጠቡ፡፡

ቁ.18. እንደ ጾማችሁ ሰው እንዳያውቅባችሁ ሁሉን መርምሮ ከሚያውቅ ከሰማያዊ አባታችሁ በቀር ነው እንጂ ተሠውራችሁ ስትጾሙ ተሰውሮ የሚያያችሁ ሰማያዊ አባታችሁ በጻድቃን በመላእክት በኀጥአን በአጋንንት መካከል ዋጋችሁን ይሰጣችኋል፡፡

በእንተ ምጽዋት
ቁ.19. እህሉን ነዳያን ከሚበሉት ብለው አኑረውት ነቀዝ ቢበላው፣ ልብሱን ነዳያን ከሚለብሱት ብለው አኑረውት ብል ቢበላው ወይም ነቀዝ ቢያበላሸው ምቀኝነት ነውና ዳግመኛ ለክፉ ቀን ይሆነኛል ብሎ ማኖር እግዚአብሔርን ከዳተኛ ማድረግ ነው፡፡ በዝናብ አብቅሎ በፀሐይ አብስሎ አይመግበኝም ማለት ነውና አንድም ምንም እጅ እግር ባያወጡለት ገንዘብ ማኖር ጣዖት ማኖር ነውና ኅልፈት ጥፋት ያለበትን ምድራዊ ድልብ አታድልቡ፣ ብል የሚበላውን ነቀዝ የሚያበላሸውን ሌቦች ግንቡን አፍርሰው ግድግዳውን ምሰው የሚወስዱትን ከሚወስዱበት ቦታ አታድልቡ፡፡

ቁ.20. ኅልፈት ጥፋት የሌለበትን ሰማያዊ ድልብን አድልቡ እንጂ፡፡ ብል የማይበላውን ነቀዝ የማያበላሸውን ሌቦች ግንቡን አፍርሰው ግድግዳውን ምሰው የማይወስዱትን ከማይወስዱበት ለእናንተ በሰማይ መዝገብ ሰብስቡ፡፡

ገንዘባችሁ ካለበት ዘንድ ልቡናችሁ ከዚያ ይኖራልና አንድም ውዳሴ ከንቱ ያለበትን ምጽዋት አትመጽውቱ አጋንንት በውዳሴ ከንቱ የሚያስቀሩባችሁን ሳይሆን የማያስቀሩባችሁን ምጽዋት መጽውታችሁ፣ ምጽዋታችሁ ካለበት ልቡናችሁ ከዚያ ይኖራልና፡፡

ቁ.22. የሥጋህ ፋና ዓይንህ ነው ማለት የሥራህ መከናወኛ ዐይንህ ነው፡፡ ዓይንህ ብሩህ የሆነ እንደሆነ አካልህ ሁሉ ብሩህ ይሆናል ዐይንህ የቀና እንደሆነ ሥራህ ሁሉ የቀና ይሆናል፡፡

ቁ.23. ዐይንህ የሚታመም የሆነ እንደሆነ አካልህ ሁሉ ጨለማ ይሆናል ማለት ዐይንህ ግን ያልቀና እንደሆነ ሥራህ ሁሉ ያልቀና ይሆናል፡፡ ባንተ ያለ ብርሃን ጨለማ ከሆነ ጨለማህ እንደምን ይሆን? በተፈጥሮ የተሰጠህ ዓይንህ የታመመ ከሆነ ጨለማ እንደምን ይጸናብህ ይሆን የታመመው ዓይንህ እንደምን ያይልሃል?

ቁ.24. አንድ ባሪያ ለሁለት ጌታ መገዛት አይቻለውም፡፡ ከፍለን መጽውተን ከፍለን ብንኖር ምነዋ ትሉኝ እንደሆነ ይህም ባይሆን ማለት እገዛለሁም ቢል አንዱን ይወዳል ሌላውን ይጠላል፣ ላንዱ ይታዘዛል ለሌላው አይታዘዝም እንጂ፡፡ እንደዚህም ሁሉ እናንተም ለእግዚአብሔርና ለገንዘብ /መታዘዝ/ መገዛት አይቻላችሁም፡፡

ቁ.25. ስለዚህ ነገር ለነፍሳችን ምን እንበላለን ምን እንጠጣለን ለሥጋችን ምን እንለብሳለን ብላችሁ አታስቡ መብል መጠጥን ለነፍስ ሰጥቶ ተናገረ የበሉት የጠጡት ደም ይሆናል፡፡ በዚህ ምክንያት ነፍስ ከሥጋ ተዋሕዳ ትኖራለችና፣ ልብስን ለሥጋ ሰጥቶ ተናገረ ምንም የምታፍር ነፍስ ብትሆን አጊጦ ከብሮ የሚታይ ሥጋ ነውና ነፍስን እምኀበ አልቦ አምጥቼ ሥጋን ከአራቱ ባሕርያት አዋሕጄ የፈጠርኋችሁ ለእናንተ ምግብ ልብስ እንደምን እነሳችኋለሁ ለማለት እንዲህ አለ፡፡

ቁ.26. ከፍለን መጽውተን ከፍለን ካላኖርን ምን እንመገባለን ትሉኝ እንደሆነ ዘር መከር የሌላቸውን በጎታ፣ በጎተራ፣ በሪቅ የማይሰበስቡትን ሰማያዊ አባታችሁ የሚመግባቸው አዕዋፍን እዩ ማለት አዕዋፍን አብነት አድርጉ ከተፈጥሮተ አዕዋፍማ ተፈጥሮተ ሰብእ አይበልጥምን? ለኒያ ምግብ የሰጠ ለእናንተ ይነሣችኋልን?

ዘወረደ

መጋቢት 12 ቀን 2005 ዓ.ም.

በአባ አሥራተ ማርያም ደስታ

የዮሐ.3፥10-21  ምንባብ በአንድምታ ትርጓሜ

ቁ.11. ራሱን ከዮሐንስ አግብቶ፡፡ ያየነውን፣ የሰማነውን እናስተምራለን ብዬ እንድናስተምር በእውነት እነግርሃለሁ፡፡ ምስክርነታችንን ግን አትቀበሉም፡፡

ቁ.12. ምድራዊ ልደታችሁን ስነግራችሁ ብነግራችሁ ያልተቀበላችሁኝ ሰማያዊ ልደታችሁን ብነግራችሁ እንደምን ትቀበሉኛላችሁ፡፡ ለዚህ ምክንያት አለው በጥምቀት፣ በንፍሐት ይሰጣል፡፡ ለዚያ ግን ንቃሕ ዘትነውም ባለው ነው፡፡ ምክንያት የለውምና፡፡  

ቁ.13. ወደ ሰማይ የወጣ የለም፣ ወደ ሰማይ የወጣው ከሰማይ የወረደው ክርስቶስ ነው እንጂ፡፡ ይህንስ ለምን ይሻዋል ቢሉ የወጣውም የወረደውም አንድ አካል አንድ ባሕርይ ነው ለማለት ሰማያዊ ሀብትን ሰማያዊ ዕውቀትን ገንዘብ ያደረገ የለም፣ ሰማያዊ ሀብትን ሰማያዊ እውቀት ገንዘብ ያደረገ ከሰማይ የወረደው ክርስቶስ ነው እንጂ፡፡

ቁ.14. ሙሴ እባብ በምድረ በዳ እንደ ሰቀለ እንዲሁ የሰው ልጅ ክርስቶስ ይሰቀል ዘንድ አለው፡፡ ጌታ መሰቀሉ ስለምን ነው ቢሉ ትንቢቱ ምሳሌው ሊደርስ ሊፈጸም፡፡ ጌታ እስራኤልን መና ከደመና አውርዶ ውኃ ከጭንጫ አፍልቆ ቢመግባቸው ከዚህ ምድሩ ብቅ ሰማዩ ዝቅ ቢልለት፣ ከደጋ ላይ ቢሆንለት የወርጭ ሰደቃ እያበጀ ውኃውን እያረጋ መና መገብኳችሁ ይላል እንጂ ይክልኑ እግዚአብሔር ሠርዓ ማዕድ በገዳም ቆላ ቢሆንማ ባልተቻለውም ነበር ብለዋል፡፡ ጌታም የርሱን ከሃሊነት የነርሳቸውን ሐሰት ለመግለጥ ሙሴን አውርዶሙ ቆላተ ሐራሴቦን አለው፡፡ ነቅዐ ማይ የሌለበት በረሐ ነው፡፡ ይዟቸው ወርዷል መናም ዘንሞላቸዋል፣ ውኃውም ፈልቆላቸዋል፡፡ ነገር ግን ነዘር የሚባል እባብ እየነከሰ ይፈጃቸው ጀመር፡፡ ሙሴን ከኛ ስሕተት ኃጢአት አይታጣምና ወደ እግዚአብሔር አመልክትልን አማልደን አሉት፡፡ ወደ እግዚአብሔር ቢያመለክትላቸው ድሩቶን ብርት /ነሐስ/ አርዌ /እባብ/ አስመስለህ ሠርተህ ከሚገናኙበት አደባባይ ከእንጨት ላይ ስቀልላቸው ያልጸናባቸው መልኩን አይተው የጸናባቸው ድምጹን ብቻ ሰምተው ይዳኑ አለው እንዳዘዘው አደረገው፡፡ ያልጸናባቸው መልኩን አይተው የጸናባቸው ድምጹን ብቻ ሰምተው ድነዋል፡፡ አርዌ ምድር የዲያብሎስ፤ አርዌ ብርት የጌታ ምሳሌ፤ በአርዌ ምድር መርዝ እንዳለበት በዲያብሎስም ፍዳ ኃጢአት አለበት፡፡ በአርዌ ብርት መርዝ እንደሌለበት በጌታም ፍዳ ኀጢአት የለበትም፡፡ ጽሩይ እንደሆነ ጌታም ጽሩየ ባሕርይ/ በባሕርዩ ንጹሕ/ ነው፡፡ አርዌ ብርት በአርዌ ምድር አምሳል መስቀሉ፣ ጌታም በአርአያ እኩያን ለመስቀሉ ምሳሌ፡፡ ተቅለቈ ምስለ ጊጉያን ከክፉዎች ተቆጠርኩ እንዲል፡፡ ይህንም ሊቁ ከመ ይደምረነ ምስለ ነፍስ ጻድቃን ከጻድቃን ነፍስ ይደምረን ዘንድ ብሎ ተርጉሞታል፡፡ መልኩን አይተው ድምጹን ሰምተው የዳኑ በአካል ያዩ ከቃሉ ሰምተው ያመኑ የዳኑ ድምጹን ብቻ ሰምተው የዳኑ ከርሱ በኋላ በተነሡ መምህራን ሰምተው ያመኑ የዳኑ የምእመናን ምሳሌ፡፡

ቁ.15. በእርሱ ያመነ ሁሉ እንዳይጎዳ ለዘለዓለም ይድን ዘንድ እንጂ፡፡ አይጎዳም ይድናል እንጂ፡፡

ቁ.16. አንድ ልጁን ለሁሉ ቤዛ አድርጎ እስከ መስጠት ደርሶ እግዚአብሔር ዓለሙን ወዶታልና፡፡ በእርሱ ያመነ ሁሉ እንዳይጎዳ የዘላለም ደኅንነት ያገኝ ዘንድ ነው እንጂ፡፡ በርሱ ያመነ ሁሉ አይጎዳም የዘላለም ደኅንነት ያገኛል እንጂ፡፡

ቁ.17. እግዚአብሔር በዓለሙ ሊፈርድበት ልጁን ወደዚህ ዓለም አልሰደደውም፡፡ እርሱ ስለካሠለት ያድነው ዘንድ እንጂ አስቀድሞ ያልተፈረደበት ሆኖ ሊፈርድበት አልሰደደውም፡፡ ተፈርዶበታልና ከተፈረደበት ፍርድ ሊያድነው ነው እንጂ፡፡ በሥጋው ሊፈርድበት አልላከውምና ተኀደገ ለከ ኀጢአትከ ተኀደገ ለኪ ኀጢአተኪ እያለ ሥርየተ ኀጢአትን ሊሰጥ ነው እንጂ፡፡

ቁ.18. በእርሱ ያመነ አይፈረድበትም፡፡ በእርሱ ባላመነ ግን ፈጽሞ ይፈረድበታል፡፡ በአንድ በእግዚአብሔር ልጅ አላመነምና፡፡

ቁ.19. ፍርዱም ይህ ነው ብርሃን ክርስቶስ ወደ ዓለም መጥቶአልና፡፡ ሰውም ከብርሃን ጨለማን፣ ከዕውቀት ድንቁርናን ከክርስቶስ ሰይጣንን፣ ከወንጌል ኦሪትን ወዷልና እስመ እኩይ ምግባሩ፡፡

ቁ.20. ምግባሩ ክፉ የሆነ ሰው ሁሉ ብርሃንን ይጠላልና ወደ ብርሃን አይመጣም ሥራው እንዳይገለጥበት ሥራው ክፉ ስለሆነ ሥራው በጎ የሆነ ሰው ግን ወደ ብርሃን ይመጣል፡፡ ሥራው ይገለጥ ዘንደ ስለ እግዚአብሔር ብሎ ይሠራዋልና ሥራቸው ክፉ የሆነ ጸሐፍት ፈሪሳውያን፣ አይሁድ፣ አሕዛብ ጌታን ይጠላሉ በጌታ አያምኑም ሥራቸው እንዳይገለጥ ሥራቸው ክፉ ስለሆነ ሥራቸው በጎ የሆነ ሐዋርያት፣ አይሁድ አሕዛብ ግን በጌታ ያምናሉ ሥራቸው ይገለጥ ዘንድ ሥራቸው በጎ ስለሆነ፡፡

ሰማዕቱ የአቡነ ጴጥሮስ ሐውልት

በሰማዕቱ አቡነ ጴጥሮስ ሐውልት ጉዳይ ውይይት ተደረገ

በዳዊት ደስታ

መጋቢት 9 ቀን 2005 ዓ.ም.

ሰማዕቱ የአቡነ  ጴጥሮስ ሐውልት

 

የሰማዕቱ የአቡነ  ጴጥሮስ ሐውልት የቴክኒክ ጥናት ኮሚቴ ሐውልቱ ያለምንም ጉዳት እንዴት መነሣት እዳለበት ከባለ ድርሻ  አካላት ጋር ውይይት አደረገ፡፡

 

የቴከኒክ ጥናት ኮሚቴው የካቲት ፲፫ ቀን ፳፻፭ ዓ.ም በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የስብሰባ አዳራሽ ለግማሽ ቀን ባካሔደው ውይይት ሐውልቱ ተነሥቶ ወደ ሥራ ከመገባቱ በፊት በሚያስፈልጉ ጉዳዮች ላይ በስፋት መክሯል፡፡

 

ሐውልቱ ከቦታው ተነሥቶ የመንገድ ግንባታው ከተጠናቀቀ በኋላ እንዴት ወደ ነበረበት መመለስ እነዳለበት ኮሚቴው ከወዲሁ ዝግጅት እያደረገ መሆኑን የቴክኒክ  ጥናት ኮሚቴው የፕሮጀክቱ ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ በኃይሉ ስንታየሁ አስታውቀዋል፡፡

 

የሰማዕቱ የአቡነ ጴጥሮስ ሐውልት በጊዜያዊነት የሚነሣበት ምክንያት በዐደባባይ ላይ የቀላል ባቡር መስመር ዝርጋታ ስለሚካሔድ ጉዳት እንዳይደርስበት በሚል እንደሆነ በሐውልቱ  አነሣስ የቴክክ ጥናት ኮሚቴ የፕሮጀክቱ ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ በኃይሉ ስንታየሁ ስለ አዲስ አበባ ባቡር ፕሮጀክት አሠራር አጠቃላይ ገለጻ አድርገዋል፡፡

 

በውይይቱ መርሐ ግብሩ ላይም ሁለት ጥናታዊ ጽሑፎች የቀረቡ ሲሆን የመጀመሪያው “የአቡነ ጴጥሮስ ሐውልት ታሪካዊ ዳራና ሐውልቱ የሚገኝበት ሁኔታ” በሚል ርእስ ጥናት ያቀረቡት በቅርስ ጥናትና ጥበቃ ባለሥልጣን የቅርስ ጥበቃና እንክብካቤ ዳይሬክቶሬት ጊዜያዊ አስተባባሪ አቶ ኃይሉ ዘለቀ ናቸው፡፡

 

እንዲሁም የቴክኒክ ጥናት ኮሚቴው ሰብሳቢና ከፍተኛ የማይንቀሳቀስ ቅርስ ጥገና ባለሙያ አቶ በየነ ደሜ “ የአቡነ ጴጥሮስ ሐውልት አነሣሥ” በሚል ርእስ ጥናታዊ ጽሑፍ አቅርበዋል፡፡

 

በቀረቡት ጥናታዊ ጽሑፎች ላይ የተለያዩ ጥያቄዎችና አስተያየቲች ከተሳታፊዎቹ የቀረበ ሲሆን ፤ በተለይ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንን ወክለው የተገኙት መ/ር ዳንኤል ሰይፈ ሚካኤል “ እስካሁን ተነሥቶ ያልተመለሰ ሐውልት ስላለ ማነው የሰማዕቱ አቡነ ጴጥሮስ ሐውልትን በባለቤትነት የሚያስመልሰው ፤ ቤተ ክርስቲያን ለእኒህ ቅዱስ አባት የመጨረሻ ክብር ሰጥታ አክብራለችና ሐውልቱ ሲመለስ እንደቀድሞ ስለመከበሩ ምን ዋስትና አለው ” ሲሉ ስጋታቸውን ገልጠዋል፡፡

 

ሌላው በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የኢትዮጵያ ቋንቋዎችና ጥናት  ምርምር መምህር ዶክተር ሐሰን ሰይድ “ ወደፊት የባቡር ንቅናቄ ስለሚኖር በሐውልቱ ላይ የሚያመጣውን አደጋ ከወዲሁ አብሮ ማጤን ያስፈልጋል” ሲሉ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል፡፡

 

ለተነሡት ጥያቄዎችና አስተያየቶች ከጥናት አቅራቢዎቹ  በቂ ምላሽና ማብራሪያዎች ተሰጥቶባቸዋል፡፡

 

በጊዜያዊነት የሚነሣው የሰማዕቱ የአቡነ ጴጥሮስ ሐውልት የባቡር ሀዲዱ ዝርጋታ ተጠናቆአስኪያልቅ ድረስ በብሔራዊ ሙዚየም እንደሚቀመጥ ተጠቁሟል፡፡ሐውልቱ መቼ እንደሚመለስ ፣ የአወሳሰዱ ሒደትና የሚያስፈልጉ ግብአቶችን እንዲሁም ወጪዎችን በሚመለከት የቅርስ ባለአደራ ባለሥልጣንና የአዲስ አበባ አስተዳደር እንደሚፈራረሙ ለማወቅ ተችሏል፡፡

 

በውይይቱ መርሐ ግብር ላይ የተለያዩ የመንግሥት መሥሪያ ቤት ባለሥልጣናት ፣ የቤተ ክርስቲያንና የጥንታዊት ኢትዮጵያ ጀግኖች አርበኞች ተወካዮች፣ የዩኒቨርስቲ ምሁራንና ተጋባዥ  እንግዶች ተገኝተዋል፡፡

ምንጭ፡-  ስምዐ ጽድቅ  ፳ኛ ዓመት ቁጥር ፲፪  ከመጋቢት ፩ -፲፭ ቀን ፳፻፭ ዓ.ም.

 

የዲላ ዮኒቨርሲቲ ግቢ ጉባኤ የተመሠረተበትን አስራ ስድስተኛ ዓመቱን አከበረ

መጋቢት 6 ቀን 2005 ዓ.ም.


በዲ/ን ቴዎድሮስ ኃይሉ

በማኅበረ ቅዱሳን በዲላ ወረዳ ማእከል ሥር የሚገኘው የዲላ ዮኒቨርሲቲ ግቢ ጉባኤ የተመሠረተበትን ዐሥራ ስድስተኛ ዓመቱን በዋለሜ ደብረ ሰላም ቅዱስ ዑራኤል ቤተ ክርስቲያን በደመቀ ሁኔታ አከበረ፡፡

ግቢ ጉባኤው ከየካቲት 29 ቀን እስከ መጋቢት 1 ቀን 2005 ዓ.ም የተመሠረተበትን በዓል ሲያከብር በማኅበረ ቅዱሳን የአዋሣ ማእከል ለግቢ ጉባኤ ተማሪዎች የእንኳን አደረሳችሁ መልእክት አስተላልፏል፡፡ ማእከሉ በወከለው በአቶ ታደሰ ፈንታ በኩል ባስተላለፈው መልእክት “ዛሬ የምሥረታ በዓላችሁን የምታከብሩ ተማሪዎች ከመደበኛው ትምህርታችሁ ጎን ለጎን መንፈሳዊ ተግባራችሁን አጠናክራችሁ እንድትቀጥሉ ጥሪያችንን በማቅረብ ነው” በማለት የእንኳን አደረሳችሁ መልእክቱን አስተላልፏል፡፡

 

አያይዞውም “የግቢ ጉባኤያት ተማሪዎች በዕድሜ ዘመናችሁ ሁሉ በሥርዓተ አምልኮ መጽናት፣ በግቢ ቆይታችሁ በምታገኙት መንፈሳዊ ዕውቀት በመደገፍ ሀገራችሁንና ቤተ ክርስቲያናችሁን ማገልገል፣ ማኅበራችሁ ማኅበረ ቅዱሳን አሁን በመስጠት ላይ ያለውን አገልግሎት በማጠናከርና ከማኅበሩ ጎን በመሆን ለቤተ ክርስቲያን ያላችሁን ታማኝነት ትወጡ ዘንድ እናሳስባችኋለን” ብሏል፡፡

የዲላ ዮኒቨርሲቲ ዋናው ግቢ ጉባኤ ሰብሳቢ ተማሪ ገብሬ ወርቁ ስለግቢው ምሥረታ በዓል አከባበር ሲናገር “የዘንድሮን ምሥረታ በዓል ግቢ ጉባኤው ሲያከብር ወጣቶች ቤተ ክርስቲያን የምትጠብቅባቸውን መንፈሳዊ አገልግሎት በብቃት እንዲወጡ ለማስቻል በማሰብ ነው” ብሏል፡፡

 

የዲላ ዋለሜ ደብረ ሰላም ቅዱስ ዑራኤል ቤተ ክርስቲያን አስተዳዳሪ መላከ ሰላም አምሳሉ ሣለ በምሥረታ በዓሉ ላይ በመገኘት አባታዊ ምክራቸውን የለገሱ ሲሆን መላከ ሰላም አምሳሉ በምክራቸው “የዲላ ዮኒቨርሲቲ ግቢ ጉባኤ በዚህ ደብር መኖሩ በቤተ ክርስቲያኒቱ የወንጌል አገልግሎት ላይ ከፍተኛ መንፈሳዊ አስተዋጽኦ አድርጓል፤ በመሆኑም የግቢ ጉባኤያት ተማሪዎች የምሥረታ በዓላችሁን ስታከብሩ መንፈሳዊ አገልግሎታችሁን ወደ ፊትም አጠናክራችሁ ለመቀጠል በማሰብ መሆን አለበት” ሲሉ መክረዋል፡፡

በምስረታ በዓሉ ላይ በተጋባዥ መምህራንና መዘምራን፣ በተመራቂ ተማሪዎች እና በግቢ ጉባኤው ተማሪዎች ስብከቶች፣ መዝሙሮችና ልዮ ልዮ መንፈሳዊ መርሐ ግብራት ቀርበዋል፡፡ እንዲሁም ከሠላሳ በላይ የሚሆኑ የግቢው ተመራቂ ተማሪዎች በምስረታ በዓሉ ላይ በመገኘት ለግቢ ጉባኤ ተማሪዎች ልምዳቸውንና ተሞክሯቸውን አካፍለዋል፡፡

አቶ ፍፁም ኩራባቸው የ2001 ዓ.ም የዲላ ዮኒቨርስቲ ተመረቂ ሲሆን በምሥረታ በዓሉ ላይ በመገኘቱ የፈጠረበትን ስሜት ሲናገር “በምሥረታ በዓሉ ላይ በመገኘት ሳከብር ቀድሞ በግቢ ውስጥ የነበረኝን መንፈሳዊ አገልግሎት በማስታወስ ወደ ፊት በበለጠ ለማገልገል የሚያስችለኝን መንፈሳዊ ስንቅ የምንሰንቅበትና ለግቢ ተማሪዎች ከወንድሞቻችን ጋር በመሆን ተሞክሯችንን የምናስተላልፍበት ልዮ ጊዜ በመሆኑ በጣም ደስተኛ ነኝ” ሲል ተናግሯል፡፡

በተያያዘም በምሥረታ በዓሉ ላይ የግቢ ጉባኤው የአዳራሽ አሠሪ ኮሚቴ ግቢ ጉባኤው በ600 ካሬ ሜትር ላይ እየሠራ ያለው አዳራሽ እየተፋጠነ እንደሆነ ገልጸል፡፡ የአዳራሽ አሠሪ ኮሚቴው በተወካያቸው በተማሪ ፍርዴ ጥላሁን በኩል ባቀረበው ሪፖርት “ተማሪዎች ቃለ እግዚአብሔር የሚማሩበትን አዳራሽን ለመሥራት እስከ አሁን አንድ ነጥብ ሁለት ሚሊዮን ብር እንደፈጀና በቀጣይ ሊሠሩ ስላሰቧቸው የበር፣ የመስኮት፣ የኮርኒስ እንዲሁም የማጠቃለያ ሥራ የዕርዳታ ጥሪ” አቅርበዋል፡፡

የዲላ ዮኒቨርስቲ ግቢ ጉባኤ በተማሪዎች ከፍተኛ ትጋትና በአካባቢው ምእመናን ተነሳሽነት የዋለሜ ደብረ ሰላም ቅዱስ ዑራኤል ቤተ ክርስቲያንን አንጾ ቅዳሴ ቤቱን በ1994 ዓ.ም እንዲከበር ማድረጉ የሚታወስ ነው፡፡ 

 

abune mathias1

ቅዱስነታቸው የመጀመሪያ እንኳን አደረሳችሁ መልእክታቸውን አስተላለፉ

የካቲት 28 ቀን 2005ዓ.ም

በእንዳለ ደምስስ

abune mathias1ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት የአብይ ጾምን በማስመልከት የካቲት 29 ቀን 2005 ዓ.ም. የእንኳን አደረሳችሁ መልእክት አስተላለፉ፡፡

 

ቅዱስነታቸው ባስተላለፉት መልእክት “ለእግዚአብሔር ሕግ መገዛት እስከተቻለ ድረስ ክፉውንና በጎውን ለይቶ ማወቅ ስለማያዳግት በተቻለ መጠን ከፊታችን ሰኞ መጋቢት 2 ቀን 2005 ዓ.ም. በሚጀመረው በታላቁ ጾማችን በዓብይ ጾም ወራት ጎጂ ከሆኑ ተግባራት ሁሉ መራቅ አለብን፡፡ ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ዓለምን የማዳን ሥራ ከመጀመሩ በፊት ዐርባ ቀንና ዐርባ ሌሊት በመጾም ድኅነተ ነፍስ እንዳስገኘልን ሁሉ እኛም ፈለጉን ተከትለን ጾም በመጾም ጥንካሬን አግኝተን ረቂቅ የሆነውን የዲያብሎስ ፈተና ማሸነፍ በሚያስችለን ቀጥተኛ መንገድ ለመጓዝ ቅድመ ዝግጅት ማድረግ ይጠበቅብናል” ብለዋል፡፡

የጾም ዋና ዓላማው ለእግዚአብሔር ቃል በሙሉ ኃይል ለመታዘዝ መዘጋጀት እንደሆነ የገለጹት ቅዱስ ፓትርያርኩ በጾም ወራት ሊፈጸሙ ይገባቸዋል ያሏቸውንም ሲጠቅሱ “ተግባራችን ሁሉ በእግዚአብሔር ዘንድ የተወደደ ሊሆን የሚችለው ርኅራኄን፤ ቸርነትን፤ ምጽዋትን፤ ፍቅርን፤ ስምምነትን፤ ትሕትናን፤ መረዳዳትን፤ መተዛዘንን ገንዘብ አድርገን የጾምን እንደሆነ ነው፡፡ በጾም ወራት ልንፈጽማቸው የሚገቡን የትሩፋት ሥራዎች ብዙዎች ቢሆኑም በተለይ መሠረታዊ የሆነ የኑሮ ፍላጎት ላልተሟላላቸው ወገኖቻችን ማለትም ልብስ ለሌላቸው ልብስ በማልበስ፤ የምግብ እጥረት ላጋጠማቸው የሚቻለንን በመለገስ፤ ማረፊያ ለሌላቸው መጠለያዎችን በመቀለስ ወገኖቻችንን መርዳት ያስፈልጋል” በማለት መልእክት አስተላልፈዋል፡፡

ወደ ቤቴል ውጣ በዚያም ኑር ዘፍ.35፥1

የካቲት 27 ቀን 2005 ዓ.ም.

ዲ/ን ሰለሞን መኩሪ

ይህንን የተናገረ አምላካችን እግዚአብሔር ነው፡፡ ይህ የተነገረው እስራኤል ለተባለ ያዕቆብ ነው፡፡ በቅዱስ መጽሐፍ ታሪኩ ተጽፎ እንደምናገኘው ከወንድሙ ከዔሳው ሸሽቶ የአባቱን የይስሐቅን በረከት ተቀብሎ ወደ አጎቱ ወደ ላባ ሲሄድ ሎዛ ከምትባለው ምድር ሲደርስ ጊዜው መሸ፡፡ እርሱም ደክሞት ስለነበር ድንጋይ ተንተርሶ ተኝቶ ሳለ ሌሊት በራእይ እግዚአብሔር ተገለጠለት ራእዩም የወርቅ መሰላል ከምድር እስከ ሰማይ ተተክሎ በመሰላሉ መላእክት ሲወጡ ሲወርዱ ነበር፡፡ እግዚአብሔርም በዙፋኑ ተቀምጦ ነበር፡፡

 

ያዕቆብንም “እኔ የአብርሃም አምላክ የይስሐቅ አምላክ እግዚአብሔር ነኝ፤ አትፍራ፣ ይህችን አንተ የተኛህባትን ምድር ለአንተም ለዘርህም እሰጣለሁ ዘርህም እንደ ባሕር አሸዋ ይሆናል፡፡ በአንተ በዘርህ አሕዛብ ይባረካሉ፡፡ እነሆም እኔ ከአንተ ጋር እሆናለሁ፡፡ የነገርኩህን ሁሉ እስካደርግልህ ድረስ አልተውህም” አለው፡፡ ያዕቆብም ከእንቅልፍ ተነሥቶ በእውነት እግዚአብሔር በዚህ ስፍራ አለ፤ እኔ አላወቅሁም ነበር፡፡

 

ይህ ሥፍራ እንዴት ያስፈራል? ይህ ስፍራ የእግዚአብሔር ቤት ነው እንጂ ሌላ አይደለም፤ ይህችም የሰማይ ደጅ ናት፡፡ ያዕቆብም ማልዶ ተነሣ ተንተርሷት የነበረችውንም ድንጋይ ወስዶ ሐውልት አድርጎ አቆማት፤ በላይዋም ዘይት አፈሰሰባት፡፡ ያዕቆብም ያን ሥፍራ ቤቴል ብሎ ጠራው አስቀድሞ ግን የዚያ ከተማ ስም ሎዛ ነበር፡፡ ያዕቆብም ስዕለትን ተሳለ፡፡ እግዚአብሔር ከእኔ ጋር ቢሆን በምሄድበት መንገድ ቢጠብቀኝ፣ የምበላውን እንጀራ የምለብሰውን ልብስ ቢሰጠኝ ወደ አባቴ አገር በሰላም ቢመልሰኝ እግዚአብሔር አምላኬ ይሆንልኛል፡፡ ለሐውልት ያቆምኳት ይህች ድንጋይ የእግዚአብሔር ቤት ትሆንልኛለች፤ ከሰጠኸኝ ሁሉ ለአንተ ከአስር እጅ አንዱን እሰጥሃለሁ አለ፡፡ እግዚአብሔርም ስእለቱን ሰምቶ ሁሉንም ፈጸመለት ወደ አጎቱ ወደ ላባ ደርሶ ሚስት አግብቶ ብዙ ልጆችን ወልዶ እንዲሁም ብዙ ባሮችን እና ሀብት ንብረት አፍርቶ ወደ አባቱ ሀገር ሲመለስ እግዚአብሔር አምላክ ተገለጠለትና “ወደ ቤቴል ውጣ በዚያም ኑር” ብሎ አዘዘው ዘፍ.28፥10-20፣ ዘፍ.35፥1፡፡

x

 

ለመሆኑ ይህች ቤቴል ማን ናት? እግዚአብሔር አምላክ ለጊዜው ያዕቆብና ቤተሰቡ እንዲኖሩባት ለፍጻሜው ሁላችንም እንድንኖርባት የታዘዝንባት ቤቴል ምስጢራዊ ትርጉሟ ምን ይመስላል? አባቶቻችን እንዲህ ይተረጉሙታል፡፡

 

1.    ቤቴል የተባለች እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ናት፡፡

አባታችን ያዕቆብ በፍኖተ ሎዛ ባየው ራእይ እግዚአብሔር አምላክ የእመቤታችን የቅድስት ድንግል ማርያምን ክብር ገልጾለታል፡፡ ይኸውም የወርቅ መሰላል ከምድር እስከ ሰማይ ድረስ ተተክሎ በመሰላሉ መላእክት ከላይ ወደ ታች ሲወርዱ እና ሲወጡ ተመልክቷል፡፡ በመሰላል የላዩ ወደ ታች እንዲወርድ አምላክ ሰው ለመሆኑ የታቹ ወደ ላይ እንዲወጣ ሰው አምላክ ለመሆኑ ምክንያት እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ናት፡፡ መሰላሉ ደግሞ ወርቅ ነበር፡፡

 

ወርቅ ፅሩይ ነው፡፡ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያምም በማሰብ፣ በመናገር፣ በመተግበር፣ በመዳሰስ፣ በማሽተት ወ.ዘ.ተ. ሰው ሁሉ ኀጢአት በሚሠራበት ህዋስ ሁሉ ያልተዳደፈች፣ ንጽሕት፣ መልዕልተ ፍጡራን /ከፍጡራን በላይ/ መትሕተ ፈጣሪ /ከፈጣሪ በታች/ ናት፡፡ ከነገደ መላእክት ከደቂቀ አዳም በክብር የሚመስላት በጸጋ የሚተካከላት የለም፡፡ ይህንንም ሊቁ ቅዱስ ኤፍሬም በውዳሴ ማርያም ዘረቡዕ ሲገልጽ “የዐቢ ክብራ ለማርያም እምኩሎሙ ቅዱሳን” “የማርያም ክብር ከቅዱሳን ክብር ይበልጣል” ብሏል፡፡

 

በወርቁ መሰላል መላእክት ሲወጡ ሲወርዱ መታየታቸው እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ምዕራገ ጸሎት እንደሆነች በእመቤታችን ምልጃ የሰው ሁሉ ጸሎት ወደ እግዚአብሔር እንደሚቀርብ የእግዚአብሔርም ቸርነት ለሰዎች እንደሚሰጥ ያመለክታል፡፡ ሊቁ አባ ጽጌ ድንግል በማኅሌተ ጽጌ ድርሰቱ “አልቦ ጸሎት ወአልቦ ትንባሌ እንበሌኪ ማርያም ዘየዓርግ ሎዓሌ” ብሎ አጉልቶታል በወርቁ መሰላል ጫፍ ዙፋን ነበር፡፡ በዙፋኑም ላይ እግዚአብሔር ተቀምጦ ለያዕቆብ ተገልጦለታል፡፡ ባርኮታል፤ ዙፋን የእመቤታችን የቅድስት ድንግል የማኅፀኗ ምሳሌ ነው፡፡ በማኅፀኗም ፍጥረቱን ለማዳን እግዚአብሔር ሰው እንደሆነ ማለትም በማኅፀነ ድንግል መፀነሱን ያመለክታል፡፡ ከዚያም በአጭር ቁመት በጠባብ ደርት በሰው መጠን መገለጹን ያስረዳል፡፡ ያዕቆብን እንደባረከው ርስት እንደሰጠው ሁሉ በእመቤታችን ሥጋ ተገልጦ በበደሉ ምክንያት የተረገመውን ሰው እንደባረከው አጥቶት የነበረውን ርስት ገነት መንግሥተ ሰማያትን እንደሰጠው ያመለክታል ዮሐ.14፥2፡፡ “በአባቴ ቤት ብዙ ማደሪያ አለ ቦታ  አዘጋጅላችሁ ዘንድ እሄዳለሁና፡፡ ዳግመኛም እመጣለሁ እናንተም እኔ ባለሁበት ትኖሩ ዘንድ ወደ እኔ እወስዳችኋለሁ” እንዲል፡፡ ፍጥረቱም ሁሉ ፈጣሪው እግዚአብሔር ተመለከተው፡፡

 

ፍጥረት ማለትም መላእክትና ደቂቀ አዳም ፈጣሪያቸው እግዚአብሔርን ለመመልከት የቻሉት በእመቤታችን ሥጋ በመገለጡ ነው፡፡ ያዕቆብ ተንተርሶት የነበረው ድንጋይ እመቤታችን በትንቢተ ነቢያት ጸንታ መኖሯን ያመለክታል፡፡ እንግዲህ ይህችን ነቢያት በትንቢታቸው ደጅ ሲጠኗት የነበረችውን እግዚአብሔር የተገለጠባት የእግዚአብሔር ዙፋን ጸሎትን መሥዋዕትን ሁሉ የምታሳርግ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያምን አማላጅ መጠጊያ ልናደርግ ያስፈልጋል፡፡ ያዕቆብ በቤቴል እንዳደረ እኛም በአማላጅነቷ ከልጇ ዘንድ በተሰጣት የከበረ ቃል ኪዳን ልባችንን እንድናኖር ያስፈልጋል መዝ.47፥12፡፡ “በብርታቷ ላይ ልባችሁን አኑሩ” እንዲል፡፡ የእመቤታችን ምልጃ ለሁላችንም ይደረግልን፡፡

 

2.    ቤቴል የተባለች ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ናት፡፡

አባታችን ያዕቆብ ባየው ራእይ የቅድስት ቤተ ክርስቲያንን ክብር እግዚአብሔር ገልጦለታል፡፡ ያዕቆብ የጳጳሳት የቀሳውስት ምሳሌ ነው፡፡ ቦታው የቅድስት ቤተ ክርስቲያን፣ የተንተራሰውን ድንጋይ ዘይት አፍስሶበታል፡፡ ለጊዜው ቦታው እንዳይጠፋበት ለምልክት ለፍጻሜው ሊቃነ ጳጳሳት ቅድስት ቤተ ክርስቲያንን በቅብዐ ሜሮን እንደሚያከብሯት የመንፈስ ቅዱስ የጸጋው ግምጃ ቤት እንደሚያደርጓት ማሳየቱ ነው፡፡ ሐዋ.20፥28፡፡ የወርቁ መሰላል ምሳሌዋ የሆነ የእመቤታችን የቅድስት ድንግል ማርያም ዘለዓለማዊ ድንግልና ክብር አማላጅነት የሚነገርባት እግዚአብሔር የታየባት ዙፋኑ የተዘረጋባት ይኸውም የታቦቱ ምሳሌ ነው፡፡ መላእክት የእግዚአብሔርን ቸርነት ወደ ሰው ልጆች የሚያመጡባት የሰው ልጆችን ጸሎት ወደ እግዚአብሔር የሚያሳርጉባት ዘወትርም በኪዳን በቅዳሴ በማኅሌት በሰዓታት የማይለያት የምሕረት አደባባይ አማናዊት ቤቴል ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ናት፡፡

 

አምላካችን እግዚአብሔር ለቅዱስ ያዕቆብ “ወደ ቤቴል ውጣ በዚያም ኑር” ሲል አዞታል፡፡ ምክንያቱም ሕይወት የሚገኝባት በሥጋ በነፍስ የምንጠበቅባት ስለሆነ ነው፡፡ አባቶቻችን ቅዱሳን ሐዋርያት በደብረ ታቦር የጌታችንን ብርሃነ መለኮቱን በተመለከቱ ጊዜ ቅዱስ ጴጥሮስ “በዚህ መሆን ለእኛ መልካም ነው” ማቴ.17፥4 እንዳለ በቅድስት ቤተ ክርስቲያን መኖር ለእኛ መልካም ነው፡፡ ቅዱስ ዳዊትም እግዚአብሔርን አንዲት ነገር ለመንኩት እርሷንም እሻለሁ በሕይወቴ ዘመን ሁሉ በእግዚአብሔር ቤት እኖር ዘንድ …. ቤተ መቅደሱንም አገለግል ዘንድ እንዳለ መዝ.26፥4፡፡ ቅዱስ ዳዊት መንግሥቱ እንዲደላደልለት ዙፋኑ እንዲጸናለት ያይደለ በእግዚአብሔር ቤት መኖር እንዲገባ አጥብቆ እግዚአብሔርን የለመነበት ልመና ነው፡፡ ይህም የተወደደ ሆኖለታል፡፡ እንግዲህ በእግዚአብሔር ቤት በአማናዊት ቤቴል ለመኖር እንዴት ሆነው ተዘጋጅተው መውጣት /መሄድ/ እንደሚገባቸው ያዕቆብ ለቤተሰቡ አስገነዘባቸው እንዲህ አላቸው፡፡

 

1.    እንግዶች አማልክትን ከእናንተ አስወግዱ አላቸው፡፡

አባታችን ያዕቆብ ለቤተሰቦቹና ከእርሱ ጋር ላሉት “ከእናንተ ጋር ያሉ እንግዶችን አማልክት ከእናንተ አስወገዱ” አላቸው አምላካችን እግዚአብሔር በአምልኮቱ የሚገባበትን አይወድም በሊቀ ነቢያት በሙሴ አድሮ ሲናገር “ከእኔ በቀር ሌሎች አማልክትን አታምልክ” ዘጸ.20፥3 ብሏል፡፡ ሰማይና ምድርን በውስጧ ያሉትን የሚታየውንና የማይታየውን ፈጥሮ በመግቦቱ በጠብቆቱ የሚያስተዳድር እግዚአብሔር ሆኖ ሳለ ከእግዚአብሔር ሌላ አምላክ አጥንት ጠርቦ ድንጋይ አለዝቦ፣ በጨሌ፣ በዛፍ፣ በተራራ፣ በጠንቋይ ወ.ዘ.ተ. ማምለክ አይገባም፡፡ እንዲህ በሚያደርጉ ሰዎች ላይ የእግዚአብሔር ቁጣው ትነዳለችና ዘጸ.20፥4፡፡ ዛሬም በዘመናችን ከወገብ በላይ ታቦት ከወገብ በታች ጣዖት ሆነው ወደ ቤተ ክርስቲያን የሚመጡ ሰዎች አሉ፡፡ ጠዋት ቤተ ክርስቲያን መጥተው ኪዳን አድርሰው ቅዳሴ አስቀድሰው ለእግዚአብሔር የሚገባውን እጣኑን ጧፉን ዘቢቡን ሌላም ለቤተ ክርስቲያን የሚያስፈልገውን ሰጥተው ሰግደው አምልኮታቸውን ፈጽመው ደግሞ ሲመሽ ሰው አየኝ አላየኝ ብለው ጨለማን ተገን አድርገው ጫት፣ ሰንደል፣ ቡና፣ ቄጤማ ተሸክመው ወደ ቤተ ክርስቲያን በሄዱበት እግራቸው ወደ ጠንቋይ ቤት የሚሄዱ በዚያ የሚሰግዱ በቤታቸውም ጠንቋዩ ያዘዛቸውን ጨሌ የሚያስቀምጡ ቀን እና ወር ለይተው ጥቁር በግ ገብስማ ዶሮ ወ.ዘ.ተ.

 

የሚያርዱ እህል የሚበትኑ እንደዚህ ባለ በሁለት እግር በሚያነክስ ልብ ወይም ሁለት እግር አለኝ ብሎ ሁለት ዛፍ ላይ ሊወጣ የሚመኝ ሰው ከእግዚአብሔር አንዳች ነገር አያገኝም፡፡ ስለዚህ ይህንን ሰይጣናዊ ልምድ አስወግዶ ማለትም ከዚህ የኀጢአት ሥራ ንስሐ ገብቶ ተለይቶ በፍጹም ልብ በፍጹም ነፍስ እግዚአበሔርን ብቻ በማምለክ ወደ ቅድስት ቤተ ክርስቲያን መገስገስ ያስፈልጋል፡፡ የያዕቆብ ቤተሰቦች የአባታቸውን ምክር ሰምተው የጣዖት ምስል ተቀርፆባቸው የነበሩ በእግራቸውና በእጃቸው በጆሮአቸውም የነበሩትን አውልቀው ለያዕቆብ ሰጡት እርሱም እንዳያገኟቸው አድርጎ አርቆ ቀበራቸው፡፡ እስከ ዛሬም አጠፋቸው ዘፍ.35፥4 እንዲል፡፡ ያዕቆብ የቀሳውስት ምሳሌ ነው፡፡ ቤተሰቦቹ የምእመናን ምስሎቹን አምጥቶ ለያዕቆብ እንደመስጠት ኀጢአትን ለካህን መናዘዝ ከአምልኮ ጣዖት እንደመለየት ሲሆን ያዕቆብ ወስዶ እንደ ቀበራቸው በቀኖና ወደ እግዚአብሔር የመቅረብ ምሳሌ ነው፡፡ ከአምልኮ ጣዖት ተለይተን እግዚአብሔርን ብቻ እያመለክን በቤቱ በቅድስት ቤተ ክርስቲያን እንድንኖር የቅዱሳን አምላክ ይርዳን፡፡

 

2.    ንጹሐን ሁኑ ልብሳችሁን እጠቡ አላቸው፡፡

አባታችን ያዕቆብ ለቤተሰቡ እንግዶችን አማልክትን እንዲያስወግዱ ካዘዙ በኋላ እነርሱም ካስወገዱ በኋላ የሰጣቸው መመሪያ “ንጹሐን ሁኑ ልብሳችሁን እጠቡ” አላቸው፡፡ ሰው ወደ ቤተ ክርስቲያን ሲመጣ አፍአዊ /የውጭ/ ንጽሕናውን እንዲሁም ውስጣዊ /የልብ/ ንጽሕናውን መጠበቅ እንደሚገባው አስተማረ ዘሌ.11፥44 እኔ እግዚአብሔር አምላካችሁ ነኝና ሰውነታችሁን ቀድሱ ንጹሐንም ሁኑ እኔ አምላካችሁ እግዚአብሔር ቅዱስ ነኝና፡፡” ይላል ስለዚህ ወደ ቅዱስ እግዚአብሔር ወደ ክብሩ ዙፋን ወደ ጸጋው ግምጃ ቤት ወደ ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ከእግዚአብሔር ለመገናኘት ንጹሕ ልብስ ለብሰን ደግሞ በንስሐ ታጥበን ሕይወታችንን አድሰን ሊሆን ይገባል፡፡ ቅዱስ ዳዊትም በመዝ.50፥7 “በሂሶጵ እርጨኝ እነጻማለሁ እጠበኝ ከበረዶም ይልቅ ነጭ እሆናለሁ፡፡” እንዲል፡፡

 

አንዳንድ ሰዎች ወደ ቤተ ክርስቲያን ለመሄድ የልብስ ንጽሕና መጠበቅ የሚገባ የማይመስላቸው ወደ አንድ ሰርግ ወይም ድግስ በሰው ፊት ለመታየት የሚያደርጉትን ጥንቃቄ እና የአለባበስ ሥርዓት ወደ ቤተ ክርስቲያን ግን ሲመጡ አልባሌ ሆነው መምጣት የሚገባ የሚመስላቸው አሉ አንዳንዶችም ወደ ቤተ ክርስቲያን ሲመጣ ሰውነትን የሚያራቁት /የሚያስገመግም/ ልብስ ለብሰው የሚመጡ አሉ ይህ የሚገባ አይደለም፡፡ ምክንያቱም ለጸሎት የመጣውን ሰው አእምሮ የሚሰርቅና የሚያሰናክል እንዳይሆን መጠንቀቅ ያስፈልጋል፡፡ ምስጢሩ ግን አባታችን ያዕቆብ ለቤተሰቡ ንጹህ ሁኑ ልብሳችሁን እጠቡ ማለቱ በንስሐ ሕይወት ተዘጋጅታችሁ ወደ እግዚአብሔር ቤት ወደ ቅድስት ቤተ ክርስቲያን በእግረ ልቡና ውጡ ለማለት ነው፡፡ ለዚህም የቅድስት ሥላሴ ቸርነት የእመቤታችን የቅድስት ድንግል ማርያም አማላጅነት የቅዱሳን መላእክት ፈጣን ተራዳኢነት የቅዱሳን ጸሎትና ምልጃ አይለየን ይርዳን አሜን፡፡

1-bealesimet

የ6ኛው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ፓትርያርክ ሥርዓተ ሢመት ፈጸሙ

የካቲት 27 ቀን 2005ዓ.ም

በእንዳለ ደምስስ

ሪፖርታዥ

1-bealesimet“የቤተ ክርስቲያንን ትምህርተ ሃይማኖትንና ቀኖና ቤተ ክርስቲያንን አከብራለሁ አስከብራለሁ” ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት

 

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን 6ኛ ፓትርያርክ ሆነው የተመረጡት ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት ሥርዓተ ሢመት በመንበረ ጸባዖት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል የካቲት 24 ቀን 2005 ዓ.ም. እንደተፈጸመላቸው ቤተ ክርስቲያንንና ምእመናንን ለማገልገል ቃለ መሐላ የፈጸሙ ሲሆን ከሰሜን አሜሪካ ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት ጋር የሚካሄደው የእርቀ ሰላም ሂደት እንደሚቀጥልም ተናግረዋል፡፡

 

በሥርዓተ ሢመቱ ላይ የመንግሥት ባለስልጣናት፤ ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት፤ የአኀት ቤተ ክርስቲያናት ልዑካን ምእመናን በተገኙበት በፈጸሙት ቃለ መሐላ “. . . የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ምእመናንና ምእመናት፤ የሁሉም አባት ሆኜ በእኩልነት፤ በግልጽነትና በታማኝነት በፍቅርና በትሕትና አገለግላለሁ፡፡ በምሥጢረ ሥላሴና በምስጢረ ሥጋዌ ትምህርትና ቀኖና ቤተ ክርስቲያን መሠረት የእግዚአብሔርን አንድነትና ሦስትነት አምኜ አስተምራለሁ፡፡ . . . የእግዚአብሔር ቸርነት፤ የድንግል ማርያም አማላጅነት፤ የቅዱሳን መላእክት፤ የቅዱሳን ነብያት፤ የቅዱሳን ሐዋርያት፤ የቅዱሳን ጻድቃን ሰማእታት ተራዳኢነትን በማመን ሁሉንም ለመባረክ፤ ለመቀደስና ለማገልገል ቃል እገባለሁ፡፡ በኒቅያ በ325 ዓ.ም. በ318ቱ ሊቃውንት፤ በቁስጥንጥንያ በ381 ዓ.ም. በ150 ሊቃውንት፤ በኤፌሶን በ431ዓ.ም. በ200 ሊቃውንት የተወሰነውን ትምህርተ ሃይማኖት፤ ቀኖና ቤተ ክርስቲያንን አከብራለሁ፤ አስከብራሉ፡፡ ለዚህም በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም ቃል እገባለሁ” ብለዋል፡፡

 

በዐውደ ምሕረት ላይ በተካሄደው መርሐ ግብር የደብረ አሚን አቡነ ተክለ ሃይማኖት ቤተ ክርስቲያን ሊቃውንት በዓሉን በማስመልከት2-bealesimet ያሬዳዊ ወረብ አቅርበዋል፡፡ በተጨማሪም  በጠቅላይ ቤተ ክህነት አስተባበሪነት ከየቤተ ክርስቲያኑ የተውጣጡ ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን የቆሜ አጫበር ወረብ፤ እንዲሁም የሰንበት ትምህርት ቤቶች ማደራጃ መምሪያ የመዝሙር ክፍል አባላት ለበዓሉ ያዘጋጁትን ያሬዳዊ ወረብ አቅርበዋል፡፡

 

በመርሐ ግብሩ ላይ በብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃማኖት መልካም ፈቃድ ብፁዕ አቡነ ፊልጶስ የጠቅላይ ቤተ ክህነት ዋና ሥራ አስኪያጅና የኢሉባቦር ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጰስ ባስተላለፉት መልእክት “ታሪካዊት፤ ጥንታዊት፤ ብሔራዊትና አለማቀፋዊት የሆነችው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያናችን በየጊዜው ከውስጥም ከውጪም የሚደርስባትን መከራና ፈተና ሁሉ በጸሎቷ፤ በትዕግስቷ ተቋቁማ በደሙ በዋጃትትና በመሠረታት በሚጠብቃትም በዓለም ቤዛ በመድኀኒታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ኀይል አሁን ካለችበት ደረጃ ደርሳለች፡፡ ጥንታዊትና የሁሉም በኩር የሆነችው ቤተ ክርስቲያናችን ኋላ ቀር እንዳትሆንና ቀዳሚነቷንም እንደያዘች ትጓዝ ዘንድ ብዙ መሥራትና ስብከተ ወንጌልን ማስፋፋትና ማጠናከር ይጠበቅባታል” ብለዋል፡፡ በተጨማሪም አምስተኛው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ፓትርያርክ የነበሩት ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ የጀመሯቸውን የልማት ሥራዎችና  ከዓለም አቀፍ አብያተ ክርስቲያናት ጋር ቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን ያላትን ግንኙነት አጠናክራ እንድትቀጥል 6ኛው ፓትርያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ አጠናክረው እንዲቀጥሉ መልእክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡

 

በበዓለ ሲመቱ ላይ ከተገኙት የአኀት ቤተ ክርስቲያናት ልዑካን መካከል ከሕንድ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ባስልዮስ ባርቶማ ጳውሎስ 2ኛ ዘመንበረ ቶማስ የማንካራ ሜትሮ ፖሊታን ባስተላለፉት መልእክትም በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን 6ኛው ፓትርያርክ በዓለ ሢመት ላይ በመገኘታቸው የተሰማቸውን ደስታ በመግለጽ በሁለቱ አኀት ቤተ ክርስቲያናት መካከል ያለውን የቆየ ግንኙነት ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልጸዋል፡፡

 

3-bealesimetየግብፅ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንን በመወከል በበዓለ ሢመቱ ላይ የተገኙት ብፁዕ አቡነ ጳኩሚስ “በአሁኑ ወቅት በዓለማችን ላይ በጣም ብዙ ችግሮችና ፈተናዎች ይታያሉ፡፡ በቤተ ክርስቲያናችን ላይ የሚያጋጥሙን ፈተናዎችን ለመቋቋም እኛ የኦርየንታል ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያናት የጌታችን የአምላካችን ኢየሱስ ክርስቶስን ቃል ለመፈጸም በአንድነት ሆነን መጸለይና መሥራት ይጠበቅብናል፡፡ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንና የአሌክሳንድርያ ቤተ ክርስቲያን ከ4ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ጀምሮ ያለንን የጠበቀ ግንኙነት አጠናክረን መቀጠል ይገባናል” ብለዋል፡፡

 

በበዓለ ሢመቱ ላይ የኢፌዲሪ ፕሬዚዳንት የክቡር አቶ ግርማ ወልደ ጊዮርጊስ መልእክት የቀረበ ሲሆን ከከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣናት መካከል ክቡር አቶ አባ ዱላ ገመዳ የኢፌዲሪ የተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ንግግር አድርገዋል፡፡ ባስተላለፉት መልእክትም “የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን መንፈሳዊ ብቻ ሳትሆን የአገራችን ታሪክ አካል ናት” ብለዋል፡፡ በዚሁ በዓለ ሢመት ላይ ከፍተኛ የመንግሥት ተወካዮች ንግግር ያደረጉ ሲሆን የአርመንና የግሪክ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያናት፤ የዓለም አብያተ ክርስቲያናት ምክር ቤት፤ የመላው አፍሪካ አብያተ ክርስቲያናት ምክር ቤት ተወካዮች መልእክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡

 

ከአኀት ቤተ ክርስቲያናት የተዘጋጁ ስጦታዎችን ለብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም፤ ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃማኖት የተሰጡ ሲሆን የፖርቱጋል አምባሳደር በ1622 እ. ኤ. አ. በፖርቱጋል ቋንቋ ተጽፎ ወደ እንግሊዝኛ የተተረጎመውን “የኢትዮጵያ ታሪክ” የተሰኘውን ባለ ሁለት ቅጽ መጽሐፍ በስጦታ አበርክተዋል፡፡

 

በመጨረሻም ብፁዕ አቡነ ማትያስ በሰጡት ቃለ ምዕዳንና ቡራኬ “ በእግዚአብሔር ቅዱስ መንፈስ የሚመራው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ4-bealesimet ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ በቀኖና ቤተ ክርስቲያን መሠረት ባለው መንፈሳዊ ሥልጣን ምርጫው እንዲፈጸም ባሳለፈው ውሳኔ የእግዚአብሔር ቅዱስ ፈቃድ ተጨምሮበት ምርጫው ተከናውኗል፡፡ እግዚአብሔር ሥራውን የሚሠራው በሰው ላይ አድሮ ነው፡፡ ሓላፊነቱና ሸክሙ ከባድ ቢሆንም እንደ ፈቃድህ ይሁን በማለት የእግዚአብሔርን ጥሪ በትሕትና ተቀብዬዋለሁ፡፡ መታዘዝ ከመሥዋዕት ይበልጣልና፡፡ አቅሜ የፈቀደውን ያህል ለቤተ ክርስቲያኔ እታዘዛለሁ፡፡ አልችልም ማለት እችል ነበር ነገር ግን የቤተ ክርስቲያንን ጥሪ አልቀበልም ማለት መሥዋዕትነትን መሸሽ ሆነ፡፡ ይህ መንፈሳዊ ሥልጣን የክርስቶስ መከራ መስቀልን ተሸክሞ ለመሥዋዕትነት መሰለፍ እንጂ ለክብርና ለልዕልና እንዳልሆነ ይገባኛል፡፡ ሁላችሁም እንደምትረዱኝም ተስፋ አደርጋለሁ፡፡ እግዚአብሔር ይርዳኝ፡፡ ጸሎታችሁና ትብብራችሁ አይለየኝ፡፡ ይህንን ታላቅ ሓላፊነት  ከእግዚአብሔር እርዳታ ጋር ከቅዱስ ሲኖዶስ አባላት ጭምር እንጂ የእኔ ብቻ ሊሆን ስለማይችል በጋራ እንወጣዋለን የሚል ጽኑ እምነት አለኝ” ብለዋል፡፡

 

በተጨማሪም በሰሜን አሜሪካ ከሚገኙት ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት ጋር የሚደረገውን የእርቀ ሰላም ሂደት በማስመልከት “ለረጅም ጊዜ ሲያወዛግብ የከረመው የእርቅና የሰላም ጉዳይ ለጊዜው ባይሳካም በቅዱስ ሲኖዶስ ውሳኔ መሠረት ጥረቱ ይቀጥላል፡፡ ተስፋ አንቆርጥም” ብለዋል፡፡

 

በሰሜን አሜሪካ ከሚገኙ ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት ጋር በሐምሌ 2002 ዓ.ም. በየካቲት 2004 ዓ.ም. እንዲሁም በኅዳር 2005 ዓ.ም. ለሦስት ጊዜያት  እርቀ ሰላም ለማካሔድ ጥረቶች መደረጋቸው ይታወሳል፡፡

1-bealesimet

የ6ኛው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ፓትርያርክ ሥርዓተ ሢመት ፈጸሙ

የካቲት 26 ቀን 2005ዓ.ም

በእንዳለ ደምስስ
ሪፖርታዥ
1-bealesimet

“የቤተ ክርስቲያንን ትምህርተ ሃይማኖትንና ቀኖና ቤተ ክርስቲያንን አከብራለሁ አስከብራለሁ” ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን 6ኛ ፓትርያርክ ሆነው የተመረጡት ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት ሥርዓተ ሢመት በመንበረ ጸባዖት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል የካቲት 24 ቀን 2005 ዓ.ም. እንደተፈጸመላቸው   ቤተ ክርስቲያንንና ምእመናንን ለማገልገል ቃለ መሐላ የፈጸሙ ሲሆን ከሰሜን አሜሪካ ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት ጋር የሚካሔደው የእርቀ ሰላም ሂደት እንደሚቀጥልም ተናግረዋል፡፡
በሥርዓተ ሢመቱ ላይ የመንግስት ባለስልጣናት፤ ብፁዐን ሊቃነ ጳጳሳት፤ የአኀት ቤተ ክርስቲያናት ልዑካን ምእመናን በተገኙበት በፈጸሙት ቃለ መሐላ “. . . የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ምእመናንና ምእመናት ፤ የሁሉም አባት ሆኜ በእኩልነት፤ በግልጽነትና በታማኝነት በፍቅርና በትሕትና አገለግላለሁ፡፡ በምሥጢረ ሥላሴና በምስጢረ ሥጋዌ ትምህርትና ቀኖና ቤተ ክርስቲያን መሠረት የእግዚአብሔርን አንድነትና ሦስትነት አምኜ አስተምራለሁ፡፡ . . . የእግዚአብሔር ቸርነት፤ የድንግል ማርያም አማላጅነት ፤ የቅዱሳን መላእክት ፤ የቅዱሳን ነብያት፤ የቅዱሳን ሐዋርያት ፤ የቅዱሳን ጻድቃን ሰማእታት ተራዳኢነትን በማመን ሁሉንም ለመባረክ፤ ለመቀደስና ለማገልገል ቃል እገባለሁ፡፡ በኒቅያ በ325 ዓ.ም. በ318ቱ ሊቃውንት ፤ በቁስጥንጥንያ በ381 ዓ.ም. በ150 ሊቃውንት ፤ በኤፌሶን በ431ዓ.ም. በ200 ሊቃውንት የተወሰነውን ትምህርተ ሃይማኖት ፤ቀኖና ቤተ ክርስቲያንን አከብራለሁ፤ አስከብራሉ፡፡ ለዚህም በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም ቃል እገባለሁ” ብለዋል፡፡
በአውደ ምሕረት ላይ በተካሔደው መርሐ ግብር የደብረ አሚን አቡነ ተክለ ሃይማኖት ቤተ ክርስቲያን ሊቃውንት በዓሉን በማስመልከት ያሬዳዊ ወረብ አቅርበዋል፡፡ በተጨማሪም  በጠቅላይ ቤተ ክህነት አስተባበሪነት ከየቤተ ክርስቲያኑ የተውጣጡ ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን የቆሜ አጫበር ወረብ፤ እንዲሁም የሰንበት ትምህርት ቤቶች ማደራጃ መምሪያ የመዝሙር ክፍል አባላት ለበዓሉ ያዘጋጁትን ያሬዳዊ ወረብ አቅርበዋል፡፡
በመርሐ ግብሩ ላይ በብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃማኖት መልካም ፈቃድ ብፁዕ አቡነ ፊልጶስ የጠቅላይ ቤተ ክህነት ዋና ሥራ አስኪያጅና የኢሉባቦር ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጰስ ባስተላለፉት መልእክት “ታሪካዊት፤ ጥንታዊት፤ ብሔራዊትና አለማቀፋዊት የሆነችው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያናችን በየጊዜው ከውስጥም ከውጪም የሚደርስባትን መከራና ፈተና ሁሉ በጸሎቷ፤ በትዕግስቷ ተቋቁማ በደሙ በዋጃትትና በመሠረታት በሚጠብቃትም በዓለም ቤዛ በመድኀኒታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ኃይል አሁን ካለችበት ደረጃ ደርሳለች፡፡ ጥንታዊትና የሁሉም በኩር የሆነችው ቤተ ክርስቲያናችን ኋላ ቀር እንዳትሆንና ቀዳሚነቷንም እንደያዘች ትጓዝ ዘንድ ብዙ መሥራትና ስብከተ ወንጌልን ማስፋፋትና ማጠናከር ይጠበቅባታል” ብለዋል፡፡ በተጨማሪም አምስተኛው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ፓትርያርክ የነበሩት ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ የጀመሯቸውን የልማት ስራዎችና  ከዓለም አቀፍ አብያተ ክርስቲያናት ጋር ቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን ያላትን ግንኙነት አጠናክራ እንድትቀጥል 6ኛው ፓትርያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ አጠናክረው እንዲቀጥሉ መልእክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡
በበዓለ ሲመቱ ላይ ከተገኙት የአኀት ቤተ ክርስቲያናት ልዑካን መካከል ከሕንድ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ባስልዮስ ባርቶማ ጳውሎስ 2ኛ ዘመንበረ ቶማስ የማንካራ ሜትሮ ፖሊታን ባስተላለፉት መልእክትም በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን 6ኛው ፓትርያርክ በዓለ ሢመት ላይ በመገኘታቸው የተሰማቸውን ደስታ በመግለጽ በሁለቱ አኀት ቤተ ክርስቲያናት መካከል ያለውን የቆየ ግንኙነት ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልጸዋል፡፡
የግብጽ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንን በመወከል በበዓለ ሢመቱ ላይ የተገኙት ብፁዕ አቡነ ጳኩሚስ “በአሁኑ ወቅት በዓለማችን ላይ በጣም ብዙ ችግሮችና ፈተናዎች ይታያሉ፡፡ በቤተ ክርስቲያናችን ላይ የሚያጋጥሙን ፈተናዎችን ለመቋቋም እኛ የኦርየንታል ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያናት የጌታችን የአምላካችን ኢየሱስ ክርስቶስን ቃል ለመፈጸም በአንድነት ሆነን መጸለይና መሥራት ይጠበቅብናል፡፡ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንና የአሌክሳንድርያ ቤተ ክርስቲያን ከ4ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ጀምሮ ያለንን የጠበቀ ግንኙነት አጠናክረን መቀጠል ይገባናል” ብለዋል፡፡
በበዓለ ሢመቱ ላይ የኢፌዲሪ ፕሬዚዳንት የክቡር አቶ ግርማ ወልደ ጊዮርጊስ መልእክት የቀረበ ሲሆን ከከፍተኛ የመንግስት ባለሥልጣናት መካከል ክቡር አቶ አባ ዱላ ገመዳ የኢፌዲሪ የተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ንግግር አድርገዋል፡፡ ባስተላለፉት መልእክትም “የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን መንፈሳዊ ብቻ ሳትሆን የአገራችን ታሪክ አካል ናት” ብለዋል፡፡ በዚሁ በዓለ ሢመት ላይ ከፍተኛ የመንግሥት ተወካዮች ንግግር ያደረጉ ሲሆን የአርመንና የግሪክ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያናት፤ የአለም አብያተ ክርስቲያናት ምክር ቤት፤ የመላው አፍሪካ አብያተ ክርስቲያናት ምክር ቤት ተወካዮች መልእክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡
ከአኀት ቤተ ክርስቲያናት የተዘጋጁ ስጦታዎችን ለብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም፤ ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃማኖት የተሰጡ ሲሆን የፖርቱጋል አምባሳደር በ1622 እ. ኤ. አ. በፖርቱጋል ቋንቋ ተጽፎ ወደ እንግሊዝኛ የተተረጎመውን “የኢትዮጵያ ታሪክ” የተሰኘውን ባለ ሁለት ቅጽ መጽሐፍ በስጦታ አበርክተዋል፡፡
በመጨረሻም ብፁዕ አቡነ ማትያስ በሰጡት ቃለ ምእዳንና ቡራኬ “ በእግዚአብሔር ቅዱስ መንፈስ የሚመራው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ በቀኖና ቤተ ክርስቲያን መሠረት ባለው መንፈሳዊ ሥልጣን ምርጫው እንዲፈጸም ባሳለፈው ውሳኔ የእግዚአብሔር ቅዱስ ፈቃድ ተጨምሮበት ምርጫው ተከናውኗል፡፡ እግዚአብሔር ሥራውን የሚሠራው በሰው ላይ አድሮ ነው፡፡ ሃላፊነቱና ሸክሙ ከባድ ቢሆንም እንደ ፈቃድህ ይሁን በማለት የእግዚአብሔርን ጥሪ በትህትና ተቀብዬዋለሁ፡፡ መታዘዝ ከመስዋእት ይበልጣልና፡፡ አቅሜ የፈቀደውን ያህል ለቤተ ክርስቲያኔ እታዘዛለሁ፡፡ አልችልም ማለት እችል ነበር ነገር ግን የቤተ ክርስቲያንን ጥሪ አልቀበልም ማለት መሥዋእትነትን መሸሽ ሆነ፡፡ ይህ መንፈሳዊ ስልጣን የክርስቶስ መከራ መስቀልን ተሸክሞ ለመሥዋእትነት መሰለፍ እንጂ ለክብርና ለልዕልና እንዳልሆነ ይገባኛል፡፡ ሁላችሁም እንደምትረዱኝም ተስፋ አደርጋለሁ፡፡ እግዚአብሔር ይርዳኝ፡፡ ጸሎታችሁና ትብብራችሁ አይለየኝ፡፡ ይህንን ታላቅ ኃላፊነት  ከእግዚአብሔር እርዳታ ጋር ከቅዱስ ሲኖዶስ አባላት ጭምር እንጂ የእኔ ብቻ ሊሆን ስለማይችል በጋራ እንወጣዋለን የሚል ጽኑ እምነት አለኝ” ብለዋል፡፡
በተጨማሪም በሰሜን አሜሪካ ከሚገኙት ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት ጋር የሚደረገውን የእርቀ ሰላም ሂደት በማስመልከት “ለረጅም ጊዜ ሲያወዛግብ የከረመው የእርቅና የሰላም ጉዳይ ለጊዜው ባይሳካም በቅዱስ ሲኖዶስ ውሳኔ መሠረት ጥረቱ ይቀጥላል፡፡ ተስፋ አንቆርጥም” ብለዋል፡፡
በሰሜን አሜሪካ ከሚገኙ ብፁዐን ሊቃነ ጳጳሳት ጋር በሐምሌ 2002 ዓ.ም. በየካቲት 2004 ዓ.ም. እንዲሁም በኅዳር 2005 ዓ.ም. ለሦስት ጊዜያት  እርቀ ሰላም ለማካሔድ ጥረቶች መደረጋቸው ይታወሳል፡፡
abune mathias entronment

የ6ኛው ፓትርያርክ ሥርዓተ ሢመት ተፈጸመ

የካቲት 24 ቀን 2005 ዓ.ም.

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን 6ኛ ፓትርያርክ ሆነው የተመረጡት የብጹዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ሥርዓተ ሢመት በመንበረ ጸባዖት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል የካቲት 24 ቀን 2005 ዓ.ም. ተፈጸመ፡፡

ከዋዜማው ጀምሮ ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን የማኅሌት ጸሎት በማድረስ የተጀመረው ሥርዓተ ጸሎት ከሌሊቱ 10፡00 ሰዓት ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ከአቃቤ መንበረ ፓትርያርኩ ብፁዕ አቡነ ናትናኤል፤ እንዲሁም ብፁዐን ሊቃነ ጳጳሳት ጋር በመሆን በመንበረ ጸባዖት ቅድሥት ሥላሴ ካቴድራል በመገኘት ሥርዓተ ጸሎቱ ቀጥሏል፡፡
ከኪዳን ጸሎት በኋላ ሥርዓተ ቅዳሴው ቀጥሎ ፤ ከሥርዓተ ቅዳሴው ጋር በማያያዝ የቅዱስ ፓትርያርኩ ሥርዓተ ሢመት በአቃቤ መንበሩ ብፁዕ አቡነ ናትናኤል እየተመራ በማከናወን ቅዱስ ፓትርያርኩ ቤተ ክርስቲያኒቱን ለማገልገል ቃለ መሐላ ፈጽመዋል፡፡ ከሥርዓተ ሢመቱ በኋላ ከአኀት ቤተ ክርስቲያናት መካከል የሕንድ፤ የግብጽ እንዲሁም የአርመን ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያናት በየተራ ጸሎት አድርሰዋል፡፡
abune mathias entronment
ሥርዓተ ቅዳሴው እንደተጠናቀቀ በአውደ ምሕረት ላይ የተለያዩ መንፈሳዊ መርሐ ግብሮች ተከናውነዋል፡፡ የአኀት ቤተ ክርስቲያናት እንዲሁም ከፍተኛ የመንግስት ባለሥልጣናት ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም፤ ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን 6ኛው ፓትርያርክ ሆነው በመሾማቸው መልካም ምኞታቸውን በመግለጽ  ለቤተ ክርስቲያኒቱና ለአገር እድገት በጋራ እንደሚሰሩ ገልጸዋል፡፡
ዝርዝሩን ይከታተሉን፡፡