06Begena

ትልቁ በገና

ጥር 11 ቀን 2006 ዓ.ም.                                                                                                                                                        

እንዳለ ደምስስ

የማኅበረ ቅዱሳን የመዝሙር ክፍል አባላትና የአቡነ ጎርጎርዮስ የትምህርትና ሥልጠና ማእከል በበገና ድርደራ የሠለጠኑ 250 ወጣቶችን የከተራ በዓልን ለማክበር የመንበረ ፓትርያርክ ቅድስተ ቅዱሳን ማርያም ገዳምን በዝማሬ አጅበው ወደ ጃንሜዳ 06Begenaሰልፋቸውን ይዘው በገናቸውን እየደረደሩ ይጓዛሉ፡፡ አሰላለፋቸውና ብዛታቸው እንዲሁም ጸዓዳ አለባበሳቸው ለዓይን ይማርካሉ፤ እንደ ምንጭ ውኃ ኮለል እያለ የሚፈሰው ዝማሬ ነፍስን ያለመልማል፡፡ ምእመናን በትኩትና በተመስጦ፤ ጎብኚዎች ባዩት ነገር በመገረም የፎቶ ግራፍና የቪዲዮ ካሜራቸውን አነጣጥረው የቻሉትን ያህል ያነሳሉ፡፡

 

በመካከላቸው አንድ በገና ከሁሉም ቁመት በላይ ረዝሞ ይታያል፡፡ ሰልፉ ቆም ሲል ጠጋ ብዬ ተመለከትኩት፡፡ ከዚህ በፊት እንዲህ አይነት ትልቅ በገና አይቼ እንደማላውቅ እርግጠኛ ነኝ፡፡ በገናውን የያዙት ልጆች መገረሜን አስተውለው “ይህ በገና በዓለማችን ከሚገኙ በገናዎች ትልቁ ነው፡፡ በገና እግዚአብሔርን ለማመስገን የምትጠቀመው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርሰቲያን ብቻ ናት፡፡ እስከ ዛሬ ኢትዮጵያ ውስጥም ይህንን በገና በትልቅነቱ የሚስተካከለው የለም” አሉኝ፡፡ በገናውን እንደ ሕፃን ልጅ በፍቅር እንደሚያሻሽ አባት ዳሰስኩት፡፡

 

በገናው ሁለት ሜትር ከሃያ ሳንቲ ሜትር ይረዝማል፡፡ አሥር አውታሮች ሲኖሩት እያንዳንዱ አውታር በስምንት በጎች አንጀት የተሠራ ነው፡፡ አሥሩ አውታሮች በአጠቃላይ በ80 በጎች አንጀት ተዘጋጅተዋል፡፡ ከላይ ያለው ብርኩማ ስልሳ ሳንቲ ሜትር ይረዝማል፡፡ በተጨማሪም በገናውን ለማዘጋጀት የአንድ ትልቅ በሬ ቆዳ ፈጅቷል፡፡

 

ማኅበረ ቅዱሳን በየዓመቱ በጥምቀት በዓል ላይ ለታቦታት ክብር ሲባል፤ እንዲሁም ሊጠፋ ተቀርቦ የነበረውን የቤተ ክርስቲያናችን ቅርስ ቀድሞ ወደነበረበት ለመመለስና ለትውልድ ለማስተላለፍ በአቡነ ጎርጎርዮስ ሥልጠና ማእከል ወጣቶችን በማሰልጠን ላይ ይገኛል፡፡