ወደ ቤቴል ውጣ በዚያም ኑር ዘፍ.35፥1

የካቲት 27 ቀን 2005 ዓ.ም.

ዲ/ን ሰለሞን መኩሪ

ይህንን የተናገረ አምላካችን እግዚአብሔር ነው፡፡ ይህ የተነገረው እስራኤል ለተባለ ያዕቆብ ነው፡፡ በቅዱስ መጽሐፍ ታሪኩ ተጽፎ እንደምናገኘው ከወንድሙ ከዔሳው ሸሽቶ የአባቱን የይስሐቅን በረከት ተቀብሎ ወደ አጎቱ ወደ ላባ ሲሄድ ሎዛ ከምትባለው ምድር ሲደርስ ጊዜው መሸ፡፡ እርሱም ደክሞት ስለነበር ድንጋይ ተንተርሶ ተኝቶ ሳለ ሌሊት በራእይ እግዚአብሔር ተገለጠለት ራእዩም የወርቅ መሰላል ከምድር እስከ ሰማይ ተተክሎ በመሰላሉ መላእክት ሲወጡ ሲወርዱ ነበር፡፡ እግዚአብሔርም በዙፋኑ ተቀምጦ ነበር፡፡

 

ያዕቆብንም “እኔ የአብርሃም አምላክ የይስሐቅ አምላክ እግዚአብሔር ነኝ፤ አትፍራ፣ ይህችን አንተ የተኛህባትን ምድር ለአንተም ለዘርህም እሰጣለሁ ዘርህም እንደ ባሕር አሸዋ ይሆናል፡፡ በአንተ በዘርህ አሕዛብ ይባረካሉ፡፡ እነሆም እኔ ከአንተ ጋር እሆናለሁ፡፡ የነገርኩህን ሁሉ እስካደርግልህ ድረስ አልተውህም” አለው፡፡ ያዕቆብም ከእንቅልፍ ተነሥቶ በእውነት እግዚአብሔር በዚህ ስፍራ አለ፤ እኔ አላወቅሁም ነበር፡፡

 

ይህ ሥፍራ እንዴት ያስፈራል? ይህ ስፍራ የእግዚአብሔር ቤት ነው እንጂ ሌላ አይደለም፤ ይህችም የሰማይ ደጅ ናት፡፡ ያዕቆብም ማልዶ ተነሣ ተንተርሷት የነበረችውንም ድንጋይ ወስዶ ሐውልት አድርጎ አቆማት፤ በላይዋም ዘይት አፈሰሰባት፡፡ ያዕቆብም ያን ሥፍራ ቤቴል ብሎ ጠራው አስቀድሞ ግን የዚያ ከተማ ስም ሎዛ ነበር፡፡ ያዕቆብም ስዕለትን ተሳለ፡፡ እግዚአብሔር ከእኔ ጋር ቢሆን በምሄድበት መንገድ ቢጠብቀኝ፣ የምበላውን እንጀራ የምለብሰውን ልብስ ቢሰጠኝ ወደ አባቴ አገር በሰላም ቢመልሰኝ እግዚአብሔር አምላኬ ይሆንልኛል፡፡ ለሐውልት ያቆምኳት ይህች ድንጋይ የእግዚአብሔር ቤት ትሆንልኛለች፤ ከሰጠኸኝ ሁሉ ለአንተ ከአስር እጅ አንዱን እሰጥሃለሁ አለ፡፡ እግዚአብሔርም ስእለቱን ሰምቶ ሁሉንም ፈጸመለት ወደ አጎቱ ወደ ላባ ደርሶ ሚስት አግብቶ ብዙ ልጆችን ወልዶ እንዲሁም ብዙ ባሮችን እና ሀብት ንብረት አፍርቶ ወደ አባቱ ሀገር ሲመለስ እግዚአብሔር አምላክ ተገለጠለትና “ወደ ቤቴል ውጣ በዚያም ኑር” ብሎ አዘዘው ዘፍ.28፥10-20፣ ዘፍ.35፥1፡፡

x

 

ለመሆኑ ይህች ቤቴል ማን ናት? እግዚአብሔር አምላክ ለጊዜው ያዕቆብና ቤተሰቡ እንዲኖሩባት ለፍጻሜው ሁላችንም እንድንኖርባት የታዘዝንባት ቤቴል ምስጢራዊ ትርጉሟ ምን ይመስላል? አባቶቻችን እንዲህ ይተረጉሙታል፡፡

 

1.    ቤቴል የተባለች እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ናት፡፡

አባታችን ያዕቆብ በፍኖተ ሎዛ ባየው ራእይ እግዚአብሔር አምላክ የእመቤታችን የቅድስት ድንግል ማርያምን ክብር ገልጾለታል፡፡ ይኸውም የወርቅ መሰላል ከምድር እስከ ሰማይ ድረስ ተተክሎ በመሰላሉ መላእክት ከላይ ወደ ታች ሲወርዱ እና ሲወጡ ተመልክቷል፡፡ በመሰላል የላዩ ወደ ታች እንዲወርድ አምላክ ሰው ለመሆኑ የታቹ ወደ ላይ እንዲወጣ ሰው አምላክ ለመሆኑ ምክንያት እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ናት፡፡ መሰላሉ ደግሞ ወርቅ ነበር፡፡

 

ወርቅ ፅሩይ ነው፡፡ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያምም በማሰብ፣ በመናገር፣ በመተግበር፣ በመዳሰስ፣ በማሽተት ወ.ዘ.ተ. ሰው ሁሉ ኀጢአት በሚሠራበት ህዋስ ሁሉ ያልተዳደፈች፣ ንጽሕት፣ መልዕልተ ፍጡራን /ከፍጡራን በላይ/ መትሕተ ፈጣሪ /ከፈጣሪ በታች/ ናት፡፡ ከነገደ መላእክት ከደቂቀ አዳም በክብር የሚመስላት በጸጋ የሚተካከላት የለም፡፡ ይህንንም ሊቁ ቅዱስ ኤፍሬም በውዳሴ ማርያም ዘረቡዕ ሲገልጽ “የዐቢ ክብራ ለማርያም እምኩሎሙ ቅዱሳን” “የማርያም ክብር ከቅዱሳን ክብር ይበልጣል” ብሏል፡፡

 

በወርቁ መሰላል መላእክት ሲወጡ ሲወርዱ መታየታቸው እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ምዕራገ ጸሎት እንደሆነች በእመቤታችን ምልጃ የሰው ሁሉ ጸሎት ወደ እግዚአብሔር እንደሚቀርብ የእግዚአብሔርም ቸርነት ለሰዎች እንደሚሰጥ ያመለክታል፡፡ ሊቁ አባ ጽጌ ድንግል በማኅሌተ ጽጌ ድርሰቱ “አልቦ ጸሎት ወአልቦ ትንባሌ እንበሌኪ ማርያም ዘየዓርግ ሎዓሌ” ብሎ አጉልቶታል በወርቁ መሰላል ጫፍ ዙፋን ነበር፡፡ በዙፋኑም ላይ እግዚአብሔር ተቀምጦ ለያዕቆብ ተገልጦለታል፡፡ ባርኮታል፤ ዙፋን የእመቤታችን የቅድስት ድንግል የማኅፀኗ ምሳሌ ነው፡፡ በማኅፀኗም ፍጥረቱን ለማዳን እግዚአብሔር ሰው እንደሆነ ማለትም በማኅፀነ ድንግል መፀነሱን ያመለክታል፡፡ ከዚያም በአጭር ቁመት በጠባብ ደርት በሰው መጠን መገለጹን ያስረዳል፡፡ ያዕቆብን እንደባረከው ርስት እንደሰጠው ሁሉ በእመቤታችን ሥጋ ተገልጦ በበደሉ ምክንያት የተረገመውን ሰው እንደባረከው አጥቶት የነበረውን ርስት ገነት መንግሥተ ሰማያትን እንደሰጠው ያመለክታል ዮሐ.14፥2፡፡ “በአባቴ ቤት ብዙ ማደሪያ አለ ቦታ  አዘጋጅላችሁ ዘንድ እሄዳለሁና፡፡ ዳግመኛም እመጣለሁ እናንተም እኔ ባለሁበት ትኖሩ ዘንድ ወደ እኔ እወስዳችኋለሁ” እንዲል፡፡ ፍጥረቱም ሁሉ ፈጣሪው እግዚአብሔር ተመለከተው፡፡

 

ፍጥረት ማለትም መላእክትና ደቂቀ አዳም ፈጣሪያቸው እግዚአብሔርን ለመመልከት የቻሉት በእመቤታችን ሥጋ በመገለጡ ነው፡፡ ያዕቆብ ተንተርሶት የነበረው ድንጋይ እመቤታችን በትንቢተ ነቢያት ጸንታ መኖሯን ያመለክታል፡፡ እንግዲህ ይህችን ነቢያት በትንቢታቸው ደጅ ሲጠኗት የነበረችውን እግዚአብሔር የተገለጠባት የእግዚአብሔር ዙፋን ጸሎትን መሥዋዕትን ሁሉ የምታሳርግ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያምን አማላጅ መጠጊያ ልናደርግ ያስፈልጋል፡፡ ያዕቆብ በቤቴል እንዳደረ እኛም በአማላጅነቷ ከልጇ ዘንድ በተሰጣት የከበረ ቃል ኪዳን ልባችንን እንድናኖር ያስፈልጋል መዝ.47፥12፡፡ “በብርታቷ ላይ ልባችሁን አኑሩ” እንዲል፡፡ የእመቤታችን ምልጃ ለሁላችንም ይደረግልን፡፡

 

2.    ቤቴል የተባለች ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ናት፡፡

አባታችን ያዕቆብ ባየው ራእይ የቅድስት ቤተ ክርስቲያንን ክብር እግዚአብሔር ገልጦለታል፡፡ ያዕቆብ የጳጳሳት የቀሳውስት ምሳሌ ነው፡፡ ቦታው የቅድስት ቤተ ክርስቲያን፣ የተንተራሰውን ድንጋይ ዘይት አፍስሶበታል፡፡ ለጊዜው ቦታው እንዳይጠፋበት ለምልክት ለፍጻሜው ሊቃነ ጳጳሳት ቅድስት ቤተ ክርስቲያንን በቅብዐ ሜሮን እንደሚያከብሯት የመንፈስ ቅዱስ የጸጋው ግምጃ ቤት እንደሚያደርጓት ማሳየቱ ነው፡፡ ሐዋ.20፥28፡፡ የወርቁ መሰላል ምሳሌዋ የሆነ የእመቤታችን የቅድስት ድንግል ማርያም ዘለዓለማዊ ድንግልና ክብር አማላጅነት የሚነገርባት እግዚአብሔር የታየባት ዙፋኑ የተዘረጋባት ይኸውም የታቦቱ ምሳሌ ነው፡፡ መላእክት የእግዚአብሔርን ቸርነት ወደ ሰው ልጆች የሚያመጡባት የሰው ልጆችን ጸሎት ወደ እግዚአብሔር የሚያሳርጉባት ዘወትርም በኪዳን በቅዳሴ በማኅሌት በሰዓታት የማይለያት የምሕረት አደባባይ አማናዊት ቤቴል ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ናት፡፡

 

አምላካችን እግዚአብሔር ለቅዱስ ያዕቆብ “ወደ ቤቴል ውጣ በዚያም ኑር” ሲል አዞታል፡፡ ምክንያቱም ሕይወት የሚገኝባት በሥጋ በነፍስ የምንጠበቅባት ስለሆነ ነው፡፡ አባቶቻችን ቅዱሳን ሐዋርያት በደብረ ታቦር የጌታችንን ብርሃነ መለኮቱን በተመለከቱ ጊዜ ቅዱስ ጴጥሮስ “በዚህ መሆን ለእኛ መልካም ነው” ማቴ.17፥4 እንዳለ በቅድስት ቤተ ክርስቲያን መኖር ለእኛ መልካም ነው፡፡ ቅዱስ ዳዊትም እግዚአብሔርን አንዲት ነገር ለመንኩት እርሷንም እሻለሁ በሕይወቴ ዘመን ሁሉ በእግዚአብሔር ቤት እኖር ዘንድ …. ቤተ መቅደሱንም አገለግል ዘንድ እንዳለ መዝ.26፥4፡፡ ቅዱስ ዳዊት መንግሥቱ እንዲደላደልለት ዙፋኑ እንዲጸናለት ያይደለ በእግዚአብሔር ቤት መኖር እንዲገባ አጥብቆ እግዚአብሔርን የለመነበት ልመና ነው፡፡ ይህም የተወደደ ሆኖለታል፡፡ እንግዲህ በእግዚአብሔር ቤት በአማናዊት ቤቴል ለመኖር እንዴት ሆነው ተዘጋጅተው መውጣት /መሄድ/ እንደሚገባቸው ያዕቆብ ለቤተሰቡ አስገነዘባቸው እንዲህ አላቸው፡፡

 

1.    እንግዶች አማልክትን ከእናንተ አስወግዱ አላቸው፡፡

አባታችን ያዕቆብ ለቤተሰቦቹና ከእርሱ ጋር ላሉት “ከእናንተ ጋር ያሉ እንግዶችን አማልክት ከእናንተ አስወገዱ” አላቸው አምላካችን እግዚአብሔር በአምልኮቱ የሚገባበትን አይወድም በሊቀ ነቢያት በሙሴ አድሮ ሲናገር “ከእኔ በቀር ሌሎች አማልክትን አታምልክ” ዘጸ.20፥3 ብሏል፡፡ ሰማይና ምድርን በውስጧ ያሉትን የሚታየውንና የማይታየውን ፈጥሮ በመግቦቱ በጠብቆቱ የሚያስተዳድር እግዚአብሔር ሆኖ ሳለ ከእግዚአብሔር ሌላ አምላክ አጥንት ጠርቦ ድንጋይ አለዝቦ፣ በጨሌ፣ በዛፍ፣ በተራራ፣ በጠንቋይ ወ.ዘ.ተ. ማምለክ አይገባም፡፡ እንዲህ በሚያደርጉ ሰዎች ላይ የእግዚአብሔር ቁጣው ትነዳለችና ዘጸ.20፥4፡፡ ዛሬም በዘመናችን ከወገብ በላይ ታቦት ከወገብ በታች ጣዖት ሆነው ወደ ቤተ ክርስቲያን የሚመጡ ሰዎች አሉ፡፡ ጠዋት ቤተ ክርስቲያን መጥተው ኪዳን አድርሰው ቅዳሴ አስቀድሰው ለእግዚአብሔር የሚገባውን እጣኑን ጧፉን ዘቢቡን ሌላም ለቤተ ክርስቲያን የሚያስፈልገውን ሰጥተው ሰግደው አምልኮታቸውን ፈጽመው ደግሞ ሲመሽ ሰው አየኝ አላየኝ ብለው ጨለማን ተገን አድርገው ጫት፣ ሰንደል፣ ቡና፣ ቄጤማ ተሸክመው ወደ ቤተ ክርስቲያን በሄዱበት እግራቸው ወደ ጠንቋይ ቤት የሚሄዱ በዚያ የሚሰግዱ በቤታቸውም ጠንቋዩ ያዘዛቸውን ጨሌ የሚያስቀምጡ ቀን እና ወር ለይተው ጥቁር በግ ገብስማ ዶሮ ወ.ዘ.ተ.

 

የሚያርዱ እህል የሚበትኑ እንደዚህ ባለ በሁለት እግር በሚያነክስ ልብ ወይም ሁለት እግር አለኝ ብሎ ሁለት ዛፍ ላይ ሊወጣ የሚመኝ ሰው ከእግዚአብሔር አንዳች ነገር አያገኝም፡፡ ስለዚህ ይህንን ሰይጣናዊ ልምድ አስወግዶ ማለትም ከዚህ የኀጢአት ሥራ ንስሐ ገብቶ ተለይቶ በፍጹም ልብ በፍጹም ነፍስ እግዚአበሔርን ብቻ በማምለክ ወደ ቅድስት ቤተ ክርስቲያን መገስገስ ያስፈልጋል፡፡ የያዕቆብ ቤተሰቦች የአባታቸውን ምክር ሰምተው የጣዖት ምስል ተቀርፆባቸው የነበሩ በእግራቸውና በእጃቸው በጆሮአቸውም የነበሩትን አውልቀው ለያዕቆብ ሰጡት እርሱም እንዳያገኟቸው አድርጎ አርቆ ቀበራቸው፡፡ እስከ ዛሬም አጠፋቸው ዘፍ.35፥4 እንዲል፡፡ ያዕቆብ የቀሳውስት ምሳሌ ነው፡፡ ቤተሰቦቹ የምእመናን ምስሎቹን አምጥቶ ለያዕቆብ እንደመስጠት ኀጢአትን ለካህን መናዘዝ ከአምልኮ ጣዖት እንደመለየት ሲሆን ያዕቆብ ወስዶ እንደ ቀበራቸው በቀኖና ወደ እግዚአብሔር የመቅረብ ምሳሌ ነው፡፡ ከአምልኮ ጣዖት ተለይተን እግዚአብሔርን ብቻ እያመለክን በቤቱ በቅድስት ቤተ ክርስቲያን እንድንኖር የቅዱሳን አምላክ ይርዳን፡፡

 

2.    ንጹሐን ሁኑ ልብሳችሁን እጠቡ አላቸው፡፡

አባታችን ያዕቆብ ለቤተሰቡ እንግዶችን አማልክትን እንዲያስወግዱ ካዘዙ በኋላ እነርሱም ካስወገዱ በኋላ የሰጣቸው መመሪያ “ንጹሐን ሁኑ ልብሳችሁን እጠቡ” አላቸው፡፡ ሰው ወደ ቤተ ክርስቲያን ሲመጣ አፍአዊ /የውጭ/ ንጽሕናውን እንዲሁም ውስጣዊ /የልብ/ ንጽሕናውን መጠበቅ እንደሚገባው አስተማረ ዘሌ.11፥44 እኔ እግዚአብሔር አምላካችሁ ነኝና ሰውነታችሁን ቀድሱ ንጹሐንም ሁኑ እኔ አምላካችሁ እግዚአብሔር ቅዱስ ነኝና፡፡” ይላል ስለዚህ ወደ ቅዱስ እግዚአብሔር ወደ ክብሩ ዙፋን ወደ ጸጋው ግምጃ ቤት ወደ ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ከእግዚአብሔር ለመገናኘት ንጹሕ ልብስ ለብሰን ደግሞ በንስሐ ታጥበን ሕይወታችንን አድሰን ሊሆን ይገባል፡፡ ቅዱስ ዳዊትም በመዝ.50፥7 “በሂሶጵ እርጨኝ እነጻማለሁ እጠበኝ ከበረዶም ይልቅ ነጭ እሆናለሁ፡፡” እንዲል፡፡

 

አንዳንድ ሰዎች ወደ ቤተ ክርስቲያን ለመሄድ የልብስ ንጽሕና መጠበቅ የሚገባ የማይመስላቸው ወደ አንድ ሰርግ ወይም ድግስ በሰው ፊት ለመታየት የሚያደርጉትን ጥንቃቄ እና የአለባበስ ሥርዓት ወደ ቤተ ክርስቲያን ግን ሲመጡ አልባሌ ሆነው መምጣት የሚገባ የሚመስላቸው አሉ አንዳንዶችም ወደ ቤተ ክርስቲያን ሲመጣ ሰውነትን የሚያራቁት /የሚያስገመግም/ ልብስ ለብሰው የሚመጡ አሉ ይህ የሚገባ አይደለም፡፡ ምክንያቱም ለጸሎት የመጣውን ሰው አእምሮ የሚሰርቅና የሚያሰናክል እንዳይሆን መጠንቀቅ ያስፈልጋል፡፡ ምስጢሩ ግን አባታችን ያዕቆብ ለቤተሰቡ ንጹህ ሁኑ ልብሳችሁን እጠቡ ማለቱ በንስሐ ሕይወት ተዘጋጅታችሁ ወደ እግዚአብሔር ቤት ወደ ቅድስት ቤተ ክርስቲያን በእግረ ልቡና ውጡ ለማለት ነው፡፡ ለዚህም የቅድስት ሥላሴ ቸርነት የእመቤታችን የቅድስት ድንግል ማርያም አማላጅነት የቅዱሳን መላእክት ፈጣን ተራዳኢነት የቅዱሳን ጸሎትና ምልጃ አይለየን ይርዳን አሜን፡፡