ዘወረደ

መጋቢት 12 ቀን 2005 ዓ.ም.

በአባ አሥራተ ማርያም ደስታ

የዮሐ.3፥10-21  ምንባብ በአንድምታ ትርጓሜ

ቁ.11. ራሱን ከዮሐንስ አግብቶ፡፡ ያየነውን፣ የሰማነውን እናስተምራለን ብዬ እንድናስተምር በእውነት እነግርሃለሁ፡፡ ምስክርነታችንን ግን አትቀበሉም፡፡

ቁ.12. ምድራዊ ልደታችሁን ስነግራችሁ ብነግራችሁ ያልተቀበላችሁኝ ሰማያዊ ልደታችሁን ብነግራችሁ እንደምን ትቀበሉኛላችሁ፡፡ ለዚህ ምክንያት አለው በጥምቀት፣ በንፍሐት ይሰጣል፡፡ ለዚያ ግን ንቃሕ ዘትነውም ባለው ነው፡፡ ምክንያት የለውምና፡፡  

ቁ.13. ወደ ሰማይ የወጣ የለም፣ ወደ ሰማይ የወጣው ከሰማይ የወረደው ክርስቶስ ነው እንጂ፡፡ ይህንስ ለምን ይሻዋል ቢሉ የወጣውም የወረደውም አንድ አካል አንድ ባሕርይ ነው ለማለት ሰማያዊ ሀብትን ሰማያዊ ዕውቀትን ገንዘብ ያደረገ የለም፣ ሰማያዊ ሀብትን ሰማያዊ እውቀት ገንዘብ ያደረገ ከሰማይ የወረደው ክርስቶስ ነው እንጂ፡፡

ቁ.14. ሙሴ እባብ በምድረ በዳ እንደ ሰቀለ እንዲሁ የሰው ልጅ ክርስቶስ ይሰቀል ዘንድ አለው፡፡ ጌታ መሰቀሉ ስለምን ነው ቢሉ ትንቢቱ ምሳሌው ሊደርስ ሊፈጸም፡፡ ጌታ እስራኤልን መና ከደመና አውርዶ ውኃ ከጭንጫ አፍልቆ ቢመግባቸው ከዚህ ምድሩ ብቅ ሰማዩ ዝቅ ቢልለት፣ ከደጋ ላይ ቢሆንለት የወርጭ ሰደቃ እያበጀ ውኃውን እያረጋ መና መገብኳችሁ ይላል እንጂ ይክልኑ እግዚአብሔር ሠርዓ ማዕድ በገዳም ቆላ ቢሆንማ ባልተቻለውም ነበር ብለዋል፡፡ ጌታም የርሱን ከሃሊነት የነርሳቸውን ሐሰት ለመግለጥ ሙሴን አውርዶሙ ቆላተ ሐራሴቦን አለው፡፡ ነቅዐ ማይ የሌለበት በረሐ ነው፡፡ ይዟቸው ወርዷል መናም ዘንሞላቸዋል፣ ውኃውም ፈልቆላቸዋል፡፡ ነገር ግን ነዘር የሚባል እባብ እየነከሰ ይፈጃቸው ጀመር፡፡ ሙሴን ከኛ ስሕተት ኃጢአት አይታጣምና ወደ እግዚአብሔር አመልክትልን አማልደን አሉት፡፡ ወደ እግዚአብሔር ቢያመለክትላቸው ድሩቶን ብርት /ነሐስ/ አርዌ /እባብ/ አስመስለህ ሠርተህ ከሚገናኙበት አደባባይ ከእንጨት ላይ ስቀልላቸው ያልጸናባቸው መልኩን አይተው የጸናባቸው ድምጹን ብቻ ሰምተው ይዳኑ አለው እንዳዘዘው አደረገው፡፡ ያልጸናባቸው መልኩን አይተው የጸናባቸው ድምጹን ብቻ ሰምተው ድነዋል፡፡ አርዌ ምድር የዲያብሎስ፤ አርዌ ብርት የጌታ ምሳሌ፤ በአርዌ ምድር መርዝ እንዳለበት በዲያብሎስም ፍዳ ኃጢአት አለበት፡፡ በአርዌ ብርት መርዝ እንደሌለበት በጌታም ፍዳ ኀጢአት የለበትም፡፡ ጽሩይ እንደሆነ ጌታም ጽሩየ ባሕርይ/ በባሕርዩ ንጹሕ/ ነው፡፡ አርዌ ብርት በአርዌ ምድር አምሳል መስቀሉ፣ ጌታም በአርአያ እኩያን ለመስቀሉ ምሳሌ፡፡ ተቅለቈ ምስለ ጊጉያን ከክፉዎች ተቆጠርኩ እንዲል፡፡ ይህንም ሊቁ ከመ ይደምረነ ምስለ ነፍስ ጻድቃን ከጻድቃን ነፍስ ይደምረን ዘንድ ብሎ ተርጉሞታል፡፡ መልኩን አይተው ድምጹን ሰምተው የዳኑ በአካል ያዩ ከቃሉ ሰምተው ያመኑ የዳኑ ድምጹን ብቻ ሰምተው የዳኑ ከርሱ በኋላ በተነሡ መምህራን ሰምተው ያመኑ የዳኑ የምእመናን ምሳሌ፡፡

ቁ.15. በእርሱ ያመነ ሁሉ እንዳይጎዳ ለዘለዓለም ይድን ዘንድ እንጂ፡፡ አይጎዳም ይድናል እንጂ፡፡

ቁ.16. አንድ ልጁን ለሁሉ ቤዛ አድርጎ እስከ መስጠት ደርሶ እግዚአብሔር ዓለሙን ወዶታልና፡፡ በእርሱ ያመነ ሁሉ እንዳይጎዳ የዘላለም ደኅንነት ያገኝ ዘንድ ነው እንጂ፡፡ በርሱ ያመነ ሁሉ አይጎዳም የዘላለም ደኅንነት ያገኛል እንጂ፡፡

ቁ.17. እግዚአብሔር በዓለሙ ሊፈርድበት ልጁን ወደዚህ ዓለም አልሰደደውም፡፡ እርሱ ስለካሠለት ያድነው ዘንድ እንጂ አስቀድሞ ያልተፈረደበት ሆኖ ሊፈርድበት አልሰደደውም፡፡ ተፈርዶበታልና ከተፈረደበት ፍርድ ሊያድነው ነው እንጂ፡፡ በሥጋው ሊፈርድበት አልላከውምና ተኀደገ ለከ ኀጢአትከ ተኀደገ ለኪ ኀጢአተኪ እያለ ሥርየተ ኀጢአትን ሊሰጥ ነው እንጂ፡፡

ቁ.18. በእርሱ ያመነ አይፈረድበትም፡፡ በእርሱ ባላመነ ግን ፈጽሞ ይፈረድበታል፡፡ በአንድ በእግዚአብሔር ልጅ አላመነምና፡፡

ቁ.19. ፍርዱም ይህ ነው ብርሃን ክርስቶስ ወደ ዓለም መጥቶአልና፡፡ ሰውም ከብርሃን ጨለማን፣ ከዕውቀት ድንቁርናን ከክርስቶስ ሰይጣንን፣ ከወንጌል ኦሪትን ወዷልና እስመ እኩይ ምግባሩ፡፡

ቁ.20. ምግባሩ ክፉ የሆነ ሰው ሁሉ ብርሃንን ይጠላልና ወደ ብርሃን አይመጣም ሥራው እንዳይገለጥበት ሥራው ክፉ ስለሆነ ሥራው በጎ የሆነ ሰው ግን ወደ ብርሃን ይመጣል፡፡ ሥራው ይገለጥ ዘንደ ስለ እግዚአብሔር ብሎ ይሠራዋልና ሥራቸው ክፉ የሆነ ጸሐፍት ፈሪሳውያን፣ አይሁድ፣ አሕዛብ ጌታን ይጠላሉ በጌታ አያምኑም ሥራቸው እንዳይገለጥ ሥራቸው ክፉ ስለሆነ ሥራቸው በጎ የሆነ ሐዋርያት፣ አይሁድ አሕዛብ ግን በጌታ ያምናሉ ሥራቸው ይገለጥ ዘንድ ሥራቸው በጎ ስለሆነ፡፡