የዓለም ከተማ ወረዳ ማዕከል ያሠራውን ጽሕፈት ቤት አስመረቀ።

በተስፋዬ አእምሮ
 የካቲት 29፣2003 ዓ.ም

በሰሜን ሸዋ ሀገረ ስብከት የዓለም ከተማ ወረዳ ማዕከል ያስገነባውን ጽሕፈት ቤት የካቲት 13 ቀን 2003 ዓ.ም  አስመረቀ፡፡ 

የወረዳ ማዕከሉ ሰብሳቢ ወ/ሪት ሰላማዊት ፍስሐ በምረቃ መርሃ ግብሩ ላይ እንደገለጹት ወረዳ ማእከሉ ከተቋቋመበት ከ1992 ዓ.ም ጀምሮ የራሱ የሆነ ጽሐፈት ቤት አልነበረውም። የተለያዩ መረጃዎችም በአባላት እጅ ይቀመጡና ለጥፋት ይጋለጡ እንደነበር አስታውሰው ይኸን ችግር ለመቅረፍ የማእከሉ ጽሕፈት ቤት የሚገነባበት ቦታ ለማግኘት ለቅዱስ አማኑኤል ቤተ ክርስቲያን ሰበካ ጉባኤ ጥያቄ ቀርቦ በሰበካ ጉባኤው መልካም ፈቃድ ከ2001 ዓ.ም ጀምሮ የገንዘብ ማሰባሰብና የግንባታ ሥራው ተጀምሮ አሁን ለምረቃ በቅቷል ብለዋል፡፡

የጽሕፈት ቤቱ መገንባት የማዕከሉን አገልግሎት ለማፋጠን ከፍተኛ ድርሻ የሚኖረው ሲሆን ለጽሕፈት ቤቱ ሥራ የወጣው ወጪ ፣ ዘጠኝ ሺ ስድስት መቶ አርባ ስምንት ብር ከበጎ አድራጊዎች፣ አርባ ሦስት ሺ ሰባት መቶ ሰላሳ ስድስት ብር ከአባላት እንዲሁም ሁለት ሺ ብር ከእድር የተገኘ ሲሆን በድምሩ 55,384.00 ብር /በሃምሳ አምስት ሺህ ሦስት መቶ ሰማንያ አራት ብር/ መሆኑንና በአጠቃላይ 95 ከመቶ ግንባታው በአባላት፣ በምዕመናንና በግቢ ጉባኤያት ተሳትፎ እንደተከናወነ የደብረ ብርሃን ወረዳ ማዕከል ያደረሰን መረጃ ይጠቁማል፡፡

በዕለቱ ጥሪ የተደረገላቸው የገዳማትና አድባራት አስተዳዳሪዎች፣ የወረዳ ማዕከሉ አባላት፣ የደብረ ብርሃን ማዕከልና የዋና ማዕከል ተወካዮች ተገኝተዋል፡፡

የቅድስት አርሴማ ጽላት በቁፋሮ ተገኘ።

 በተስፋዬ አእምሮ
 የካቲት 29፣2003 ዓ.ም
የሰሜን ሸዋ ሀገረ ስብከት አንጎለላና ጠራ ወረዳ በቂጣልኝ ቀበሌ የቅድስት አርሴማ ጽላት በቁፋሮ ተገኘ፡፡
 
ጽላቱ አባ ኃይለ ሥላሴ ለማ በተባሉ አባት አስተባባሪነት ዋሻ ውስጥ የተገኘ ሲሆን፥ ዋሻው በግራኝ ወረራ ዘመን የተዘጋ እንደሆነ ይታመናል፡፡ 
 
ከዚህ በፊት በዋሻው ውስጥ የተለያዩ ቅርሶች የተገኙ ሲሆን ሌሎች ቅርሶችን ለመፈለግ ቁፋሮ ሲካሄድ ይህ ጽላት እንደተገኘ ለቅርሱ እውቅና የሰጡት የአካባቢው ባሕልና ቱሪዝም ቢሮ እና ማኅበራዊ ፍርድ ቤት አረጋግጠዋል፡፡

የወረዳው ቤተ ክህነትና የኩሉ ወይን ቅዱስ ጊዮርጊስ ሰበካ ጉባኤም ለሚመለከታቸው አካላት እንዳሳወቁና በአሁኑ ጊዜም ጽላቱ ወደ ሀገረ ስብከቱ ሊቀ ጳጳስ ተወስዶ እንዲባረክና አገልግሎት መስጠት እንዲጀምር ለማድረግ ምእመናን በዝግጅት ላይ መሆናቸውን የደብረ ብርሃን ማዕከል ያደረሰን መረጃ ያመለክታል፡፡

ቅድስት(የዐቢይ ጾም ሁለተኛ ሳምንት)

የዕለተ ሰንበት መዝሙር (ከጾመ ድጓ)

ግነዩ ለእግዚአብሔር ወጸውዑ ስሞ ወንግርዎሙ ለአሕዛብ ምግባሮ ሀቡ ስብሐተ ለስሙ አክብሩ ሰንበተ ተገበሩ ጽድቀ ዝግቡ ለክሙ መዝገበ ዘበሰማያት ኅበ ፃፄ ኢያማስኖ ወኢይረክቦ ሰራቂ ድልዋኒክሙ ንበሩ ዘበላዕሉ ጸልዩ ኀበ ሀሎ ክርስቶስ
ትርጉም: ለእግዚአብሔር ተገዙ ስሙንም ጥሩ ሥራውንም ለአሕዛብ ንገሯቸው ለስሙም ምስጋናን ስጡ /አቅርቡ/ ሰንበትን አክብሩ እውነትንም አድርጉ ብል የማያበላሸው ሌባም የማያገኘው በሰማያት ያለ መዝገብን ለእናንተ ሰብስቡ፤ ተዘጋጅታችኹም ተቀመጡ ክርስቶስ ወዳለበት ወደላይ አስቡ፡፡

ምንባባት
መልዕክታት
1ኛ ተሰ.41-12 አሁንም ወንድሞቻችን ሆይ በእኛ ዘንድ እንደ ታዘዛችሁ በሚገባ ትሄዱ ዘንድ እግዚአብሔርንም ደስ ታሰኙ ዘንድ ደግሞ እንደ ሄዳችሁ ከፊት ይልቅ በዚሁ ታበዙና ትጨምሩ ዘንድ በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ እንነግራችኋለን፤ እንማልዳችኋለንም፡፡ በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስም ያዘዝናችሁን ትእዛዝ ታውቃላችሁ፡፡(ተጨማሪ ያንብቡ)
1ኛጴጥ.1·13-ፍጻ.ስለዚህ የልቡናችሁን ወገብ ታጥቃችሁና ነቅታችሁ ኑሩ፤ ኢየሱስ ክርስቶስም ሲገለጥ የምታገኙትን ጸጋ ፈጽማችሁ ተስፋ አድርጉ፡፡ (ተጨማሪ ያንብቡ)
ግብረ ሐዋርያት
የሐዋ.10·17-29. ጴጥሮስም ስለ አየው ራእይ ምን እንደሆነ ሲያወጣና ሲያወርድ ከቆርኔሌዎስ ተልከው የመጡ ሰዎች የስምዖንን ቤት እየጠየቁ በደጅ ቁመው ነበር፡፡ (ተጨማሪ ያንብቡ)
ምስባክ
መዝ.95·5 እግዚአብሔርሰ ሰማያተ ገብረ አሚን ወሠናይት ቅድሜሁ ቅድሳት ወዕበየ ስብሐት ውስተ መቅደሱ

ትርጉም፦እግዚአብሔር ግን ሰማያትን ሠራ ምስጋና ውበት በፊቱ ቅዱሰነትና ግርማ በመቅደሱ ውስጥ ናቸው፡፡

ወንጌል
ማቴ.6·16-24 €œበምትጾሙበት ጊዜ እንደ ግብዞች አትጠውልጉ፤ እነርሱ እንደ ጾሙ ለሰው ይታዩ ዘንድ መልካቸውን ይለውጣሉና እውነት እላችኋለሁ ዋጋቸውን ተቀብለዋል፡፡ (ተጨማሪ ያንብቡ)
ቅዳሴ
ዘኤጲፋንዮስ

 

ሰበር ዜና

(ሐሙስ የካቲት 24  2003 ዓ.ም. )
ብፁዕ አቡነ ይስሐቅ አረፉ።
የቀድሞው የጠቅላይ ቤተ ክህነት ሥራ አስኪያጅና የባሌ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ የነበሩት ብፁዕ አቡነ ይስሐቅ አረፉ። abune yishaqe.jpg
 
በድንገተኛ ህመም ሳቢያ ወደ ባልቻ ሆስፒታል ለሕክምና በመሄድ ላይ ሳሉ እንዳረፉ ለማወቅ ተችሏል።
 
አስከሬናቸው ከሚገኝበት ከባልቻ ሆስፒታል ነገ የሚወጣ ሲሆን ቀብራቸውም የፊታችን ቅዳሜ  ይፈጸማል ተብሎ ይጠበቃል።

7ኛው ሀገር አቀፍ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት /ግቢ ጉባኤያት/ ሴሚናር ነገ ይጀመራል፡፡

(ሐሙስ የካቲት 24  2003 ዓ.ም. ) 
በእንዳለ ደጀኔ
በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በሰ/ት/ቤቶች ማደራጃ መምሪያ ማኅበረ ቅዱሳን 7ኛውን የግቢ ጉባኤያት ተወካዮች ሴሚናር ከየካቲት 25-27 ቀን 2003 ዓ.ም አዲስ አበባ ላይ እንደሚያካሄድ አስታወቀ፡፡

የግቢ ጉባኤያት ማደራጃና ማስተባበሪያ ክፍል ሓላፊ ዲ/ን ተ/ብርሃን ገ/ሚካኤል እንደገለጹት በሴሚናሩ 310 የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት /የግቢ ጉባኤያት/  ተወካዮች የ41 ማእከላትና ወረዳ ማእከላት የግቢ ጉባኤያት ማደራጃና ማስተባበሪያ ክፍል ሓላፊዎች ይገኛሉ፡፡

ሴሚናሩም ማኅበሩ በ1984 ዓ.ም በቅዱስ ሲኖዶስ ጸድቆ በተሰጠው መተዳደሪያ ደንብ መሠረት በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት /ግቢ ጉባኤያት/ የሚገኙ የቤተ ክርስቲያን ልጆች በማስተማርና ለቤተ ክርስቲያን ተተኪ ትውልድ እንዲሆኑ ለማብቃት እየሠራ መሆኑን የሚያሳይ ነው፡፡

ሴሚናሩ በሚካሄድባቸው 3 ቀናት በሀገሪቱ ካሉ የከፍተኛ ተቋማት የግቢ ጉባኤያት ተወካዮች ሴሚናር ላይ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የልምድ ተሞክሮ፣ የአገልግሎት ስልትና መንፈሳዊ ሕይወት እንዲሁም በምግባረ ሰናይ ያላቸውን ተሳትፎ አጠናክረው የሚሔዱበትን አቅጣጫ መንደፍ የሚያስችል ውይይት እንዲደረግ ይጠበቃል፡፡

የግቢ ጉባኤያት ሴሚናር፣ ከከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተመርቀው የሚወጡ ተማሪዎች ቤተ ክርስቲያናቸውንና ሀገራቸውን በጥሩ ሥነ-ምግባርና በታማኝነት በተማሩበት ሙያ ለማገልገል የሚያስችል የተለያዩ የአገልግሎት ስልቶችን የሚረዱበት፣ ራዕይ ያላቸው፤ በገንዘባቸው፣ በዕውቀታቸውና በጉልበታቸው አስተዋጽኦ ሊያበረክቱ የሚችሉበትን አቅጣጫ የሚያውቁበት ሲሆን፣ ከተቋማቸው ማኅበረሰብ፣ ከአጥቢያ ሰ/ት/ቤቶችና ሰ/ጉባኤያት ጋር በመሆን የቤተ ክርስቲያንን ሁለንተናዊ አገልግሎት ለመፈፀም የሚዘጋጁበት እንደሚሆን ሓላፊው ገልፀዋል፡፡

ማኅበሩ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ሥር ከተቋቋመበት ከ1984 ዓ.ም ጀምሮ፣ ዓለም አቀፍ መንፈሳዊና ማኅበራዊ አገልግሎት በመስጠት ላይ የሚገኝ ሲሆን በአሁኑ ወቅት በሥሩ የሚገኙ ከ120.000 በላይ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተማሪዎችን የቤተ ክርስቲያንን ትምህርት እያስተማረ ይገኛል፡፡

ለ7ኛ ጊዜ በተዘጋጀው በዚሁ የግቢ ጉባኤ ተወካዮች ሴሚናር ቅዱስ ፓትሪያሪኩን ጨምሮ ሊቃነ ጳጳሳት፣ የጠቅላይ ቤተክህነት የመምሪያ ሓላፊዎች፣ የአዲስ አበባ ሃ/ስብከት የመምሪያ ሓላፊዎችና ጥሪ የተደረገላቸው የክብር እንግዶች ይገኛሉ፡፡

መጋቢት 11 ሲምፖዚየም

2011-1.jpg

ከ400 በላይ የጉምዝ ብሔረሰብ አባላት ተጠመቁ።

በሪሁን ተፈራ ከባህር ዳር ማዕከል
በምዕራብ ጎጃም ሀገረ ስብከት ወንበርማ ወረዳ የሚገኙ ከ400 በላይ የሚሆኑ የጉምዝ ብሔረሰብ አባላት በጎመር ቅድስት ክርስቶስ ሰምራ ቤተክርስቲያን እሑድ  የካቲት 13 ቀን 2003 ዓ.ም በብፁዕ አቡነ በርናባስ የምዕራብ ጎጃም ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ፣ በሀገረ ስብከቱ ቆሞሳትና ካህናት መጠመቃቸውን የማኅበረ ቅዱሳን ባህር ዳር ማዕከል ገለጸ፡፡

 
ብፁዕ አቡነ በርናባስ የካቲት 12ቀን 2003 ዓ.ም ከቀኑ በ10፡40 ሰዓት ጎመር ሲደርሱ  የወረዳው ቤተ ክህነት ሥራ አስኪያጅና ሌሎች ሠራተኞች፣ የማኅበረ ቅዱሳን ባሕር ዳር ማዕከል፣ የሽንዲ ወረዳ ማዕከል አባላት፣ የአካባቢው ሰንበት ትምህርት ቤት ወጣቶች፣ ምእመናን እና የጉምዝ ብሔረሰብ አባላት፣ በመዝሙርና በእልልታ የታጀበ ደማቅ አቀባበል አድርገውላቸዋል፡፡
akebabele.jpg

ከዚህ በተጨማሪም በዕለቱ የማኅበረ ቅዱሳን ሽንዲ ወረዳ ማዕከል አባላት፣ የኮሊ ኢየሱስ ቤተክርስቲያን መዘምራን፣ የሸንዲ ደብረ ብሥራት ቅዱስ ገብርኤል ቤተክርስቲያን መዘምራን፣ ጎመር ቅድስት ክርስቶስ ሰምራ ቤተክርስትያን ሰንበት ትምህርት ቤት ተማሪዎች መዝሙርና ሥነ ጽሑፍ በኦሮምኛ በአማርኛ ቋንቋ ለምእመናን አቅርበዋል፡፡

Abune Bernabas Siatemku.jpgሥርዓተ ጥምቀቱ ከሌሊቱ 10፡00 ሰዓት የተጀመረ ሲሆን የተጠመቁት ምእመናን በሥርዓተ ቅዳሴው ተሳትፈው ሥጋ ወደሙ ከተቀበሉ በኋላ በሊቀ ማዕምራን ሀዲስ ጤናው የሀገረ ስብከቱ ስብከተ ወንጌል ክፍል ኃላፊ እና በመጋቤ ምሥጢር ኃይለማርያም ታዬ ትምህርት ተሰጥቶ ሀገረ ስብከቱ ለተጠማቂያን የብሔረሰቡ አባላት 600 የአንገት መስቀል አበርክቷል፡፡

ተጠማቂ  ምእመናኑ አባይ በረሃን ከሚያዋስኑ ከወንበርማ ወረዳ ሦስት ቀበሌዎች የመጡ ሲሆኑ በአካባቢው ከአፄ ኃ/ሥላሴ ዘመነ መንግሥት በፊት ጀምሮ የተሠሩ አብያተ ክርስቲያናት አልፎ አልፎ ያሉና የተጠመቁ የብሔረሰቡ ምእመናን ቢኖሩም ለዚህ በርካታ  የብሔረሰቡ አባላት መጠመቅ ምክንያት የሆኑት አቶ አያና የተባሉ የቻግኒ ወረዳ ማዕከል አባል ወደ ቦታው ለሥራ በመጡና አሁን የተዛወሩት ግለሰብ እና መምህርት መድኃኒት ሞላ የሽንዴ ወረዳ ማዕከል አባል አማካኝነት እንደሆነ ተገልጿል፡፡

የሽንዲ ወረዳ ማዕከል በ1994 ዓ.ም ሁለት ህፃናትን ከአካባቢው በመውሰድና የአብነት ትምህርት ቤትYewerwda Maekelu Meketel sebsabi Betemeherte laye.jpg ለማስገባት የጀመረው ሙከራ ልጆቹ ሊለምዱ ስላልቻሉ ቢቋረጥም ለዚህ እንቅስቃሴ መጠናከር በምዕራብ ጎጃም ሀገረ ስብከት ወንበርማ ወረዳ ቤተክህነት እና ከአካባቢው ሰንበት ትምህርት ቤት ወጣቶች ጋር በመሆን 2000 ዓ.ም ግንቦት 16 ቀን ወደ የማቤል ቅድስት ኪዳነ ምሕረት ቤተክርስቲያን በወረዳ ማዕከሉ አስተባባሪነት የተደረገ የእግር ጉዞና ከአካባቢው የጎሳ አካላት ጋር የተደረገው ትምህርትና ውይይት ትልቅ በር እንደከፈተና ከዚያም በኋላ በወረዳ ቤተክህነቱ እና ወረዳ ማዕከሉ የሚደረጉ ትምህርተ ወንጌል ይበልጥ ግንኙነታቸውን እንዳጠናከረው ለማወቅ ተችሏል፡፡

የባህርዳር ማዕከል እና ሽንዲ ወረዳ ማዕከል በሽንዲ ከተማ የእራት ግብዣ በማዘጋጀትና ከበጎ አድራጊዎች 4000 ብር አስባስቦ ቆርቆሮ እና እንጨት ገዝቶ በማጓጓዣ፤ ግንቦት 2002 ዓ.ም ጉባኤ በማካሄድና ከ460 በላይ የብሔረሰቡ አባላት ጋር ውይይት አድርጎ በቀበሌው ባሉት በመምህርት መድኃኒት ሞላና አንድ ሌላ መምህር አስተባባሪነት ተጨማሪ እንጨት እንዲያዋጡ በማድረግ ቤተክርስቲያን በጎመር ቀበሌ ሊሠራ ችሏል፡፡

ብፁዕ አቡነ በርናባስ ከአሁን በፊት የተጠመቁትንና አዲስ ተጠማቂያንን እንዲበረቱ መክረው በበዓሉ ለተገኙ ምዕመናን እንዳሉት “የእግዚአብሔር ፈቃድ ስለሆነ ወገኖቻችን ወደዚህች ሃይማኖት ሊመጡ ችለዋል፡፡ ስለዚህ ሁላችንም በደስታ ልንቀበላቸው፣ ልንከባከባቸውና ልንደግፋቸው ይገባል”፡፡ ሲሉ አሳስበዋል፡፡

የብሔረሰቡ አባላት በበኩላቸው ከ 2፡00-4፡00 ሰዓት የሚፈጅ የእግር ጉዞ ተጉዘው  እንደተጠመቁ በመግለጽ ለሰሩት ቤተክርስቲያን ጽላት እንዲገባላቸው፣ በቅርብ ቦታ ተጨማሪ አብያተ ክርስቲያናት እንደሰሩላቸውና ካህናት እንዲመደቡላቸው ጠይቀዋል፡፡ ብፁዕ አቡነ በርናባስም ከወረዳ ቤተክህነት ጋር በመሆን የተቻላቸውን እንደሚፈጽሙና ምዕመናን ከጎናቸው በመሆን ለቤተክርስቲያን ሥራ እንዲተጉ ጠይቀዋል፡፡ በመጨረሻም በብፁዕነታቸው ጸሎትና ቡራኬ ጉባኤው ተጠናቋል፡፡

 ረድኤተ እግዚአብሔር አይለየን።

 

ከተለያዩ ሀገረ ስብከቶች የተውጣጡ ሰልጣኞች ተመረቁ፡፡

 በፈትለወርቅ ደስታ

የማኅበረ ቅዱሳን ትምህርትና ሐዋርያዊ አገልግሎት ክፍል ባዘጋጀው ስልጠና  ከተለያዩት ቦታዎች የመጡ 27 ሰልጣኞች ለሁለት ሳምንት የቆየ መሠረታዊ የሃይማኖት ትምህርት ሲከታተሉ ቆይተው የካቲት 13 ቀን 2003 ዓ.ም. ተመረቁ፡፡

የትምህርትና ሐዋርያዊ አገልግሎት ክፍል አስተባባሪ ቀሲስ ታደሰ ጌታሁን እንደገለፁት ይህ ሥልጠና ለ13ኛ ጊዜ የተሰጠ ሲሆን ከዚህ በፊት በተካሄዱት 12 ዙር ስልጠናዎች 219 ሰልጣኞች ስልጠናውን ተከታትለዋል፡፡ ስልጠናውን ከወሰዱት በጠረፋማ ቦታዎች ከሚኖሩት ብሔረሰቦች ውስጥ ከጋምቤላ፣ ከአፋር፣ ከኦሮሚያ፣ ከቤንሻንጉል፣ ከደቡብ ኦሞ፣ ከጂንካ፣ ከሰመራ፣ ከአላባ፣ ከጠምባሮ፣ ከስልጤና ከጉራጌ ዞኖች የተውጣጡ  እንደነበሩ አስታውሰው በአሁኑ መርሐ ግብር ስልጠናውን የወሰዱት ከሱማሌ፣ ከቦረና፣ ከጉጂና ሊበን ዞኖች የመጡ ናቸው ሲሉ ገልጸዋል፡፡

በዚህ ስልጠና ስለ ስነ ፍጥረት፣ ትምህርተ ሃይማኖት፣ የቤተክርስቲያን ታሪክ፣ ሥርዓተ ቤተክርስቲያን፣ ነገረ ቅዱሳን፣ ክርስትያናዊ ሥነ ምግባር፣ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናትና የስብከት ዘዴ በሚሉ ርእሶች ስልጠናው ተሰጥቷል፡፡ በተጨማሪ ሰልጣኞቹ ታሪካዊ ቦታዎችንና ሙዚየሞችን በቆይታቸው ወቅት ጎብኝተዋል፡፡

የሰልጣኞቹ ተወካዮች እንደገለጹት “በሚኖሩበት ጠረፋማ አካባቢ ያሉ ምእመናን በመናፍቃንና በአሕዛብ የተከበቡ ሲሆን መናፍቃን በገንዘብና በስልጣናቸው በመጠቀም የተለያዩ ስልጠናዎችን እያዘጋጁ አብዛኛውን ምእመን በቋንቋቸው እያስተማሩ ወደ መናፍቅነት እየለወጧቸው እንደነበርና በአንዳንድ ቦታዎች ደግሞ ምንም አይነት ቤተክርስቲያን ባለመኖሩ ሕብረተሰቡ በባእድ አምልኮ ውስጥ እንደሆነ ገልጸው፤ የአካባቢው ምዕመናን መጠመቅ እንደሚፈልጉና ቤተክርስቲያንም ተሠርቶላቸው ቅዳሴ የሚያስቀድሱበት፣ ሥጋ ወደሙ የሚቀበሉበት፣ ጸሎት የሚያደርሱበት፣ ወንጌልን የሚማሩበት በአጠቃላይ አምልኮተ እግዚአብሔር የሚፈጽሙበት ቤተክርስቲያን እንዲሰራላቸው ለቤተክርስቲያን ልጆች ጥሪያቸውን አቅርበዋል፡፡

ሰልጣኞቹ በስልጠናው በቆዩበት ወቅት ለምግብ፣ አልባሳትና ለመጓጓዣ 50.000.00 ብር በላይ ወጪ የተደረገ ሲሆን ይህ ገንዘብ በቅዱሳት መካናት ልማትና ማኅበራዊ አገልግሎት እንዲሁም በስብከተ ወንጌል ማስፋፊያ ክፍልና አውሮፓ ባሉ በጎ አድራጊ ምእመናን የተገኘ መሆኑ ተገልጿል፡፡

ቀሲስ ታደሰ በሰጡት አስተያየት የአሁኑን ጨምሮ በአጠቃላይ 246 ሰልጣኞች እንደተመረቁ ገልጸው ሰልጣኞቹ ወደ ቤተሰቦቻቸው ሲመለሱ መጻሕፍት፣ አልባሳት፣ ትራንስፖርት በተደጋጋሚ ስልጠናና ድጋፍ እንደሚያስፈለጋቸው፣ ወደ ተለያዩ ከፍተኛ መንፈሳዊ ተቋማት እየመጡ የሚሰለጥኑበትና ሃይማኖታቸውን የሚያጸኑበት መንገድ ለመፈለግ የብዙ ምእመናን ድጋፍና ርብርብ አስፈላጊ በመሆኑ እውቀት ያለው በእውቀቱ ገንዘብ ያለው በገንዘቡ እንዲሁም በጸሎት ቤተክርስቲያንን መደገፍና የተሰጠውን ኃላፊነት  እያንዳንዱ ምዕመን መወጣት እንዳለበት አሳስበዋል፡፡

በምረቃ መርሐ ግብሩ ላይ ለሰልጣኞች የምስክር ወረቀትና ለወደፊት እውቀታቸውን ለማዳበርና ለአገልግሎት የሚረዳቸውን መጽሐፍ ቅዱስንና በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ሥርዓት የተዘጋጁ የትምህርተ ሃይማኖት፣ የሥርዓተ ቤተክርስቲያን፣ ትውፊትና የቤተክርስቲያን ታሪክ የሚያስረዱ መጽሐፍትና ሌሎች አጋዥ ጽሑፎች ተሰጥቷቸዋል፡፡

የማኅበሩ ዋና ሰብሳቢ ቀሲስ ዶ/ር ሙሉጌታ ስዩም ለሰልጣኛቹ ባስተላለፉት መልእክት ማኅበሩ ወደ ፊት በእያንዳንዱ ብሔረሰብ ቋንቋ ስልጠና እንደሚሰጥና አሁን ግን ሠልጣኞቹ የሰለጠኑትን ለወገኖቻቸው እንዲያካፍሉ በቋንቋቸው እየተረጎሙ ማስተማር እንዳለባቸውና በጾምና በጸሎት በሕይወት በመተርጎም የተጣለባቸውን ኃላፊነት ሊወጡ እንደሚገባቸውና ማኅበሩም በየጊዜው የማሻሻያ ስልጠና  እንደሚሰጣቸው ገልጸው መርሃ ግብሩን በጸሎት ዘግተው ፍጻሜ ሆኗል፡፡

 

በሐዋሳ ያለው ችግር እንደ ቀጠለ ነው፡፡

ሰኞ፣ የካቲት 14/2003 ዓ.ም                                                                    በተ/ሥላሴ ጸጋ ኪሮስ
 
hawassakidusgebriel.jpgትናንት እሑድ የካቲት 13/2003 ዓ.ም በሐዋሳ ደብረ ምሕረት ቅዱስ ገብርኤል ገዳም ከቅዳሴ በኋላ በብፁዕ አቡነ ገብርኤል ሊሰጥ የነበረው ትምህርተ ወንጌል በተወሰኑ የሰ/ት/ቤት ወጣቶች አመጽ ተስተጓጉሏል፡፡ ከሥፍራው የደረሰንን ሪፖርት እንደሚከተለው አቅርበናል፡፡
 
ብፁዕነታቸው ጸሎተ ቅዳሴውን ከመሩ በኋላ ለማስተማር ዐውደ ምሕረት ላይ ወጥተው ከካህናቱ ጋር ተቀመጡ፡፡ ወጣቶቹም የሰንበት ትምህርት ቤት ዩኒፎርም ለብሰው ዝማሬ ማቅረብ ጀመሩ፡፡ በተለምዶ ሁለት መዝሙር ቀርቦ ስብከተ ወንጌል የሚጀመር ቢሆንም ትናንት ግን “እመቤቴ ማርያም እለምንሻለሁ” እና “የኢቲሳ አንበሳ ተክልዬ ተነሳ” የሚሉ መዝሙሮች ከተዘመሩ በኋላም ዝማሬው አልቆመም፡፡ 
 
ወጣቶቹ ከኪሳቸው ይዘውት የነበረውን ጥቁር ጨርቅ አውጥተው እያውለበለቡ “መዘመራቸውን” ቀጠሉ፡፡ ይህንን የተመለከቱት ብፁዕ አቡነ ገብርኤል ትምህርት መስጠቱን ትተው ወደ ቤተ ክርስቲያን በመግባት ቅድስቱ ላይ በመሆን የማሰናበቻ ጸሎቱን አድርሰዋል፡፡

ከጸሎቱ በኋላ ብፁዕ አቡነ ገብርኤል “ጥቂት ወጣቶች የቤተ ክርስቲያንን ሰላም አያደፈርሱም፣ …. የቤተ ክርስቲያን ዐውደ ምሕረት ተከብሮ ይኖራል፣ … ከአሁን በኋላ እንድንጨክን እያደረጋችሁን ነው…” በማለት ጠንከር ያለ ወቀሳና ተግሣጽ አስተላልፈዋል፡፡ ምእመናን ስለ ቤተ ክርስቲያን ሰላም እንዲጸልዩም በአጽንዖት አሳስበዋል፡፡ ለምነዋል፡፡

ብፁዕነታቸው ይህንን መልእክት ሲያስተላልፉ ወጣቶቹ በከፍተኛ ድምፅ እየዘመሩና ከበሮ እየመቱ እንዳይሰሙ ለማድረግ ጥረት ሲያደርጉ ነበር፡፡

እነዚሁ ወጣቶች እና ሌሎች ከ60 – 100 ያህል የሚሆኑ “ምእመናን” ብፁዕ አቡነ ገብርኤል ከቅዳሴ በኋላ ወደሚወጡበት የቤተ ክርስቲያኑ የምሥራቅ በር ጥቁር ጨርቃቸውን እያውለበለቡና “አንፈራም አንሰጋም…” እያሉ እየዘመሩ በመሄዳቸው በቤተ ክርስቲያኑ ግቢ ውስጥ የነበሩት ምእመናን ግልብጥ ብለው ወደዚያው በመሄድ ብፁዕ አቡነ ገብርኤልን አጅበው እስከ መንበረ ጵጵስናቸው /መኖሪያቸው/ አድርሰዋቸዋል፡፡ ሰዎቹ ለምን ዓላማ ጥቁር ጨርቅ እያውለበለቡና እንደዚያ እያሉ እየዘመሩ ወደ ብፁዕነታቸው እንደሄዱ ግልጽ ባይሆንም በኋላ ተመልሰው ወደ ሰንበት ትምህርት ቤት አዳራሽ ገብተዋል፡፡

ብፁዕ አቡነ ገብርኤልን አጅበው ወደ ቤታቸው ያደረሱት ምእመናን “አይዝዎት አባታችን፣  ሰላማችንን እያጠፋውና እየበጠበጠን ያለው ዲያብሎስ በመሆኑ ልንታገሥ ይገባል፣ እኛም ከጎንዎት ነን…” በማለት ብፁዕነታቸውን አጽናንተዋል፡፡ ብፁዕነታቸውም ለዚህ ሁሉ ዋናው መፍትሔ ጸሎት በመሆኑ ሁሉም ስለቤተ ክርስቲያን ሰላም በመጸለይ እንዲተጋ በድጋሚ በማሳሰብ ሕዝቡን በቡራኬ አሰናብተዋል፡፡

ትናንት ይህንን ሁከት ያደረሱት ወጣቶች በቀድሞው የሀገረ ስብከቱ ሥራ አስኪያጅ አማካኝነት በተፈጸመው ቃለ ዐዋዲውን ያልጠበቀ ምርጫ በተመረጠው የሰንበት ትምህርት ቤት አመራር የሚመሩ ሲሆኑ፣ ይህ ሁኔታ ከመፈጸሙ ከአንድ ቀን በፊትም /ቅዳሜ የካቲት 12/2003 ዓ.ም/  በሰንበት ትምህርት ቤቱ አዳራሽ ተገኝተው እንደተወያዩ ለማወቅ ተችሏል፡፡ ከዚህ በፊት ብፁዕነታቸው ወደ ሀገረ ስብከቱ ለመጀመሪያ ጊዜ ሲሄዱ በተመሳሳይ መልኩ ጥቁር ጨርቅ እያውለበለቡ እንደተቀበሏቸውም ይታወሳል፡፡

ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተባባሰ የመጣውንና የታቀደና የተቀናጀ የሚመስለውን እንቅስቃሴ በማየት፥ እነዚህ አካላት ሆን ብለው የቤተ ክርስቲያንን ገጽታ የማጉደፍና አገልግሎቷን የማደናቀፍ ብሎም ምእመናንን አስመርሮ ከቤተ  ክርስቲያን የማስወጣት ሥውር ተልእኮ ባላቸው የውስጥ አርበኞች የሚነዱ እንዳይሆኑ ስጋት እንዳላቸው የሚገልጹ ምዕመናንንም ቁጥር በርካታ ነው፡፡

የደቡብ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ክቡር አቶ ሽፈራው ሽጉጤ በቤተ ክርስቲያን ምንም ዓይነት ሁከት መፈጠር እንደሌለበትና ተቃውሞም ቢኖር ሰላማዊ በሆነ መንገድ ብቻ መቅረብ እንዳለበት ያሳሰቡ መሆኑ ይታወሳል፡፡

የደቡብ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ከምእመናን ጋር ተወያዩ።

በተ/ሥላሴ ጸጋ ኪሮስ

በሐዋሳ ቅዱስ ገብርኤል ቤተ ክርስቲያን የተነሳው አለመግባባት አሁንም ቀጥሎ ማክሰኞ በ08/06/03 ዓ.ም በቤተ ክርስቲያን ውስጥ በተፈጠረው ግጭት ወጣቶችና ምእመናን ጉዳት ደርሶባቸዋል። እርሱን ተከትሎ ያለመግባባቱን ተዋናዮች ሰብስበው ያናገሩት የደቡብ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ክቡር አቶ ሽፈራው ሽጉጤ ተቃውሞን ሰላማዊ በሆነ መልኩ ብቻ መግለጥ እንደሚቻል አሳስበዋል።
 
በግጭቱ ወቅት በስፍራው እንደተገኙ የተናገሩ የዐይን ምስክር “በቤተ ክርስቲያን ውስጥ በሁለት ጎራ ተለይቶ ጉባኤ ከተጀመረ ቆይቷል።” ብለው፤ ስለ ዕለቱ ክስተት ሲናገሩ “በአንደኛው ወገን የተወሰኑ ሰዎች ለጸሎት ተሰብስበው እያሉ ከቀኑ 9፡30 ሲሆን፥ ከሌላኛው ወገን በትር ይዘው በመምጣት ሁለት ልጆችን በተደጋጋሚ ሲደበድቧቸው፤ ሌላ አንዲት ምእመን ግንባሯ ላይ ተፈንክታ እንደተመለከቱ ገልጸዋል።

ከዚህ አለመግባባትና ግጭት በኋላ ከሁለቱም ወገን የተወከሉ ሃምሳ ሃምሳ ሰዎችና የሀገረ ስብከቱ ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ገብርኤል በተገኙበት ከክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ክቡር አቶ ሽፈራው ሽጉጤ ጋር ውይይት ተካሂዷል። በውይይቱ ወቅት ሁለቱም ያላቸው ሃሳብና ቅሬታ አቅርበዋል።

በአንደኛው ወገን የአለመግባባቶቹ መነሻና ሂደቶቹ የቀረቡ ሲሆን፥ በሌላኛው በኩል በአብዛኛው ሲነገሩ የነበሩት የማኅበረ ቅዱሳንን ጣልቃ ገብነት፥ እንዲሁም ማኅበሩን የመክሰስ ሁኔታዎች እንደነበር ምንጮቻችን ገልጸዋል።

ክቡር ርዕሰ መስተዳድሩ በውይይቱ ወቅት አጽንኦት ሠጥተው የገለጹት ነገር፥ ከእንግዲህ አንዲት ጠጠር በቤተ ክርስቲያን ውስጥ እንደማትወረወርና ማንኛውንም ተቃውሞ ሰላማዊ በሆነ መልኩ መግለጥ እንደሚቻል ነው።

አቶ ሽፈራው አያይዘውም “ሊቀ ጳጳሱ እዚህ ቦታ እስከተቀመጡ ድረስ በሀገረ ስብከታቸው የሊቀ ጳጳሱ ወሳኔ የቤተ ክርስቲያኒቱ የመጨረሻ ውሳኔ ነው፤ እርሱን ተቀብለን እንሄዳለን” በማለት አብራርተዋል።  

መነሻው ከ9 ወር በፊት አካባቢ እንደሆነ የሚነገርለት አለመግባባት፥ ቀኖና ቤተ ክርስቲያን ይጠበቅ፣ የቃለ ዓዋዲው መመሪያ ይከበር፣ የቅዱስ ሲኖዶስ ውሳኔ ተግባራዊ ሊሆን ይገባል፤ በሚሉና ይህንን በሚቃወሙ መካከል እንደሆነ የሲዳማ፣ አማሮና ቡርጅ ልዩ ዞኖችና ወረዳዎች ሀገረ ስብከት ሥራ አስኪያጅ ሊቀ ኅሩያን ዓለም እሸት ገ/ጻድቅ ከማኅበረ ቅዱሳን የአማርኛ መካነ ድር ጋር ባደረጉት ቆይታ መግለጻቸው ይታወሳል።