«የአሮጊቷ ሣራ» ወለደች ዐዋጅ ተሐድሶ ዘመቻ የጥፋት ፈትል እንደማጠንጠኛ

በመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት በብሉያትና በሐዲሳቱም የምትነሣው ሣራ አበ ብዙኃን ሥርወ ሃይማኖት የምንለው የአብርሃም ሚስት ነች፡፡ እግዚአብሔር ለአብርሃም የብዙዎች አባት እንዲሆን ቃል ኪዳን ሳይገባለት በፊት፣ በመካንነት ታዝን፣ ተስፋም አጥታ ትተክዝ በነበረችበት ጊዜ ሦራ ትባል ነበር፡፡

ሦራ ሙቀት ልምላሜ ከተለያት በኋላ ልጅ እንደምትወልድ ከአብርሃም በኩል እግዚአብሔር ቃል ኪዳን ከገባላት፣ ተስፋም ከተሰጣት በኋላ ሣራ ተብላለች፡፡ እግዚአብሔርም ስለእርሷ ለአብርሃም «የሚስትህን የሦራን ስም ሦራ ብለህ አትጥራ፤ ስምዋ ሣራ ይሆናል እንጂ፤ እባርካታለሁ፤ ደግሞም ከእርሷ ልጅ እሰጥሃለሁ፤ እባርካትማለሁ፤ የአሕዛብ እናት ትሆናለች፤ የአሕዛብ ነገሥታት ከእርሷ ይወጣሉ» በማለት ተናገረው /ዘፍ. 17፥15/፡፡

ሣራ ሦራ ተብላ ትጠራ በነበረበት፣ ያለተስፋ በኖረችበት የቀደመው ዘመኗ ለአብርሃም ልጅ አልወለደችለትም ነበር፡፡ ሦራ ዘር ማጣት ታላቅ ሐዘን በሆነበት በዚያ ዘመን፣ መካንነት ያስንቅ በነበረበት በዚያን ጊዜ አብራም ከሌላ ይወልድ ዘንድ አዘነችለት፡፡ አብራም አጋር ወደ ተባለችው ግብጻዊት ባሪያዋ ይደርስ ዘንድ «እነሆ እንዳልወልድ እግዚአብሔር ዘጋኝ ምናልባት ከእርሷ በልጅ እታነጽ እንደ ሆነ ወደ እርሷ ግባ» አለችው፡፡ /ዘፍ.16፥2/ በትሑቷ ሦራ ምክር አጋር ከአብርሃም በፀነሰችበት ወራት ሦራን አሳዘነቻት፤ አጋርም ተመካች፤ እመቤት የነበረችውን ሦራ ስለመካንነቷ በዓይኗ አቃለለቻት፡፡ ይህ ለሦራ በእግዚአብሔር እና በባሏ በአብራም ፊት ያዘነችበት ሰቆቃዋ ነው፡፡ ሦራም ከሐዘኗ ጽናት የተነሣ አብራምን እንዲህ አለችው «መገፋቴ በአንተ ላይ ይሁን እኔ ባሪያዬን በብብትህ ሰጠሁህ፤ እንዳረገዘችም ባየች ጊዜ እኔን በዓይኗ አቃለለችኝ፤ እግዚአብሔር በእኔና በአንተ መካከል ይፍረድ» አለችው፡፡ በአብራም ፍርድም ሦራ ባሪያዋን አጋርን በመቅጣቷ አጋር ኮበለለች፡፡

እንግዲህ ከላይ አስቀድመን የጠቀስነው ለአብርሃም የተገባው ቃል ኪዳን የተሰጠው ሦራና አብራም በዚህ ሐዘን ውስጥ በነበሩበት ጊዜ ነው፡፡ ያዘነችው ሦራ ከቃል ኪዳኑ በኋላ የብዙኃን እናት ልትሆን ሣራ ተብላ እርሱም የብዙዎች አባት ሊሆን አብርሃም ተብሎ የተስፋው ቃል ተነገረው «በእውነት ሚስትህ ሣራ ወንድ ልጅን ትወልድልሃለች ስሙንም ይስሐቅ ብለህ ትጠራዋለህ ከእርሱ በኋላ ለዘሩ የዘላለም ቃልኪዳን እንዲሆን ቃል ኪዳኔን ከእርሱ ጋር አቆማለሁ» /ዘፍ.17፥19/፡፡

እግዚአብሔር ለአብርሃም ሣራ እንደምትወልድ የነገርውን የተስፋ ቃል በቤቱ በእንግድነት ተገኝቶ አጸና፡፡ «የዛሬ ዓመት እንደ ዛሬው ጊዜ ወደ አንተ በእውነት እመለሳለሁ ሚስትህ ሣራም ልጅን ታገኛለች፡፡»/ዘፍ.18፥10/ አለው፡፡ ሁል ጊዜም ቃሉ የሚታመን እግዚአብሔር ይመስገንና እንደተባለው ሆነ «እግዚአብሔርም እንደተናገረው ሣራን አሰበ እግዚአብሔርም እንደተናገረው ለሣራ አደረገላት ሣራም ፀነሰች እግዚአብሔርም በተናገረው ወራት ለአብርሃም በእርጅናው ወንድ ልጅን ወለደችለት አብርሃም ሣራ የወለደችለትን የልጁን ስም ይስሐቅ ብሎ ጠራው» /ዘፍ.21፥1/ «ሣራም እግዚአብሔር ሳቅ /ደስታ አድርጎልኛል ይህንንም የሚሰማ ሁሉ በእኔ ምክንያት ይስቃል አለች ደግሞም ሣራ ልጆችን እንድታጠባ ለአብርሃም ማን በነገረው በእርጅናው ልጅን ወልጄለታለሁና /ዘፍ. 21፥7/፡፡

እንግዲህ መካኒቱ ሣራ ሙቀት ልምላሜ ከተለያት በኋላ በጨዋነት ወልዳ ለአብርሃም ለዘላለም የገባው ቃል ኪዳን የሚፈጸምበትን ዘር ይስሐቅን አሳድጋለች፡፡ በቃል ኪዳን፣ በተስፋ የተወለደው ይስሐቅ ታላቅ ነውና «የዚህች ባሪያ /የአጋር/ ልጅ ከልጄ ከይስሐቅ ጋር አይወርስም» አለች፡፡ እግዚአብሔርም ቃሏን ተቀብሎ ለአብርሃም «ሣራም የምትነግርህን ቃል ሁሉ ስማ በይስሐቅ ዘር ይጠራልሃልና…» አለው /ዘፍ.21፥1-12/፡፡

እንዲህ በእግዚአብሔር የተስፋ ቃል የከበረችው ሣራ በብሉያት ብቻ ሳይሆን በሐዲሳትም ለተለያዩ ጉዳዮች እንደ አርአያና ምሳሌ ስትጠቀስ እናነባለን፡፡ ሊቀ ሐዋርያት ቅዱስ ጴጥሮስ ሚስቶችን ሲመክር በመልካም ትሑት ሰብእናዋ አርአያ የምትሆን አድርጎ የጠቀሳት ሣራን ነው «ጠጉርን በመሸረብ፣ ወርቅን በማንጠልጠል፣ ወይም ልብስን በመጎናጸፍ በውጪ በሆነ ሽልማት» ሳይሆን «በእግዚአብሔር ፊት ዋጋው እጅግ የከበረ የዋህና ዝግተኛ መንፈስ ያለውን የማይጠፋውን ልብስ» ተጎናጽፋ ውስጧን ያስጌጠች ብፅዕት ሚስት መሆኗን መስክሯል፡፡ «ሣራ ለአብርሃም ጌታዬ ብላ እየጠራችው ታዘዘችለት፤ እናንተም ከሚያስደነግጥ ነገር አንዳች እንኳ ሳትፈሩ መልካም ብታደርጉ ልጆችዋ ናችሁ፡፡» /1ጴጥ. 3፥3-6/ ብሏል፡፡

ቅዱስ ጳውሎስ ደግሞ የክርስቶስ የማዳኑ የምስራች ከታወጀላቸው በኋላ ሕገ ኦሪትን ካልጠበቅን አንድንም የሚሉ ቢጽሐሳውያንን ቃል ሰምተው ያመኑ የገላትያን ሰዎች በገሰጸበት መልእክቱ ሣራን የሕገ ወንጌል ምሳሌ አድርጎ አቅርቧታል፡፡ በአንጻሩ ባሪያዋን አጋርን የሕገ ኦሪት ምሳሌ አድርጎ አቅርቧል /ገላ.4፥21/፡፡

የሣራን ሕይወት በዚህ ጽሑፍ ያነሣንበትንም መሠረታዊ ምክንያትም ይህንን የቅዱስ ጳውሎስን ምሳሌያዊ መልእክት ተንተርሰው ያለአገባቡ እየጠቀሱ የቤተ ክርስቲያናን ልጆች ምእመናንን ግራ ስለሚያጋቡ የተሐድሶ መናፍቃንና ተሐድሶአዊ ትምህርት ስለሚያስተምሩ ሰዎች ሐሳብ ለማንሣት ነው፡፡ በቅድሚያ የቅዱስ ጳውሎስ የመልእክቱን ሐሳብ በአጭሩ እናብራራና፤ ተሐድሶ የዘመቻ ማወራረጃ አድርጎ ስለሚጠቀምበት ጥራዝ ነጠቅ ቃልና አስተሳሰብ ደግሞ ቀጥሎ እናመጣለን፡፡ ሐዋርያው ስለዚህ ነገር ሲናገር የሚከተለውን ብሏል፡፡

«እናንተ ከሕግ በታች ልትኖሩ የምትወዱ ሕጉን አትሰሙምን ? እስኪ ንገሩኝ፤ አንዱ ከባሪያዪቱ አንዱ       ከጨዋዪቱ የሆኑ ሁለት ልጆች ለአብርሃም እንደነበሩት ተጽፏልና፤ ነገር ግን የባሪያዪቱ ልጅ እንደ ሥጋ ተወልዷል፤ የጨዋዪቱ ግን በተስፋው ቃል ተወልዷል፤ ይህም ነገር ምሳሌ ነው እነዚህ ሴቶች እንደ ሁለቱ ኪዳናት ናቸውና፤ ከደብረ ሲና የሆነችው አንዲቱ ለባርነት ልጆችን ትወልዳለች፤ እርሷም አጋር ናት፤ ይህቺም አጋር በዓረብ ምድር ያለችው ደብረ ሲና ናት፤ አሁንም ያለችውን ኢየሩሳሌምን ትመስላለች፤ ከልጆቿ ጋር በባርነት ናትና፤ ላይኛዪቱ ኢየሩሳሌም ግን በነጻነት የምትኖር ናት፤ እርሷም እናታችን ናት… ስለዚህ ወንድሞች ሆይ የጨዋዪቱ ልጆች ነን እንጂ የባሪያዪቱ አይደለንም» /ገላ.4፥21-31/፡፡
በገላትያ መልእክቱ ቅዱስ ጳውሎስ ትኩረት የሰጠው ጉዳይ «የክርስቶስን ሐዋርያት እንዲመስሉ ራሳቸውን እየለወጡ ውሸተኞች ሐዋርያትና ተንኮለኞች ሠራተኞች» ስለነበሩት ከአይሁድ ወገን የሆኑ ካልተገረዛችሁ፣ ሕገ ኦሪትንም ካልፈጸማችሁ አትድኑም እያሉ የሚያስተምሩ ሰዎች ጉዳይ ነው፡፡ እነዚህ ኦሪታዊ ሁኑ የሚሉ ሰዎችን ትምህርት እየሰሙ የወንጌልን ቃል ቸል ያሉት የገላትያን ሰዎች በግልጽ «እግዚአብሔርን ስታውቁ፣ ይልቅስ በእግዚአብሔር ስትታወቁ እንደገና ወደ ደካማ ወደሚናቅም ወደ መጀመሪያ ትምህርት እንዴት ትመለሳላችሁ? እንደገና ባሪያዎች ሆናችሁ ዳግመኛ ለዚያ ልትገዙ ትወዳላችሁን ? ቀንና ወርን ዘመንንም ዓመትንም በጥንቃቄ ትጠብቃላችሁ…» ይላቸዋል፡፡ /ገላ.4፥9-11/
የሐዋርያው ዋነኛ ጉዳይ ሕገ ኦሪት ይጠበቅ አይጠበቅ በመሆኑም ነው «እናንተ ከሕግ በታች ልትኖሩ የምትወዱ ሕጉን አትሰሙምን ?» ያላቸው /ገላ. 1፥21/፡፡ ምክንያቱም ያመኑትን ሁሉ በደሙ የዋጀ የኢየሱስ ክርስቶስ የምስራች ወንጌል ከተነገረች በኋላ ዳግመኛ ወደ ኋላ ተመልሶ ቀንና ወርን ዘመንንም እየቆጠሩ መሥዋዕተ ኦሪትን ለማቅረብ፣ ግዝረትን አበክሮ ለመጠበቅ፣ ያንንም ካልፈጸማችሁ አትድኑም ወደሚል ትምህርት መመለስ ያሳፍራልና፡፡
ስለዚህ እናንተ በኦሪት እንኑር የምትሉ ሆይ! በኦሪት የተነገረውን ምሳሌ አንብቡ ብሎ የሣራን እና የአጋርን ምሳሌነት ያነሣል፡፡ በኦሪት አብርሃም አስቀድመን እንዳየነው ጨዋይቱ ከተባለችው ከእመቤቲቱ ሣራ ይስሐቅን፣ ከባሪያይቱ ከአጋር ደግሞ እስማኤልን ወልዷል፡፡ የሁለቱ ልደት ግን ለየቅል መሆኑን ይነግራቸዋል፡፡ ከባሪያዪቱ የተወለደው አጋር ሙቀት ልምላሜ እያላት ተወልዷልና፤ ከእመቤቲቱ የተወለደው ግን ሙቀት ልምላሜ ከተለያት በዘጠና ዓመቷ/ ከእግዚአብሔር ብቻ በተሰጠው ተስፋ ተአምራትም ተወልዷልና፡፡ እነዚህ ሁለቱ ሴቶች የሕገ ኦሪትና የሕገ ወንጌል ምሳሌ ናቸው፡፡ ቅዱስ ጳውሎስም በቃሉ «ይህም ነገር ምሳሌ ነው» እንዳለ /ገላ. 4፥24/፡፡ አጋር ኦሪትን ደብረ ሲናን አንድ ወገን ያደርጋል፤ ሣራን፣ ወንጌልን ሰማያዊቱ ኢየሩሳሌምን ደግሞ አንድ ወገን እያደረገ እያነጻጸረ ተናግሯል፡፡
አንዲቱ /ኦሪት/ አምሳል መርገፍ ሆና በደብረ ሲና ተሠርታለችና፤ ደብረ ሲናም ከኢየሩሳሌም ስትነጻጸር በምዕራብ ያለች ተራራ ናትና፤ ስለዚህ ይህች ምድራዊት የምትሆን አምሳል መርገፍ አማናዊት ከምትሆን ሰማያዊት ኢየሩሳሌም ጋር ስትነጻጸር ዝቅ ያለች ናትና «ወትትቀነይ ምስለ ደቂቃ» አምሳል መርገፍ በመሆን ከልጆቿ ጋር ትገዛለች፡፡ ላዕላዊት የምትሆን ኢየሩሳሌም ግን ከመገዛት ነጻ ናት ብሎ «ወይእቲ እምነ፤ እርስዋም እናታችን ናት» ይላል፡፡ ይቺም እናታችን ሣራ ምሳሌዋ የምትሆን ወንጌል ናት፡፡
ስለዚህ ከሣራ የተወለደው ተስፋውን ወራሽ እንደሆነ ሁሉ እኛም ከወንጌል የተወለድን ክርስቶሳውያን በይስሐቅ አምሳል እንደይስሐቅ ተስፋውን መውረስ የሚገባን የነጻነት ልጆች ነን ማለቱ እንደሆነ ሊቃውንቱ ያስተምራሉ፡፡ የባሪያዪቱ ልጅ ከእመቤት ልጅ ጋር ተካክሎ ርስት አይወርስምና በበግና በፍየሎች ደም ምሳሌያዊ ወይም ጥላ   አገልግሎት በምትሰጥ ገረድ /ሞግዚት/ የተባለች የኦሪት ልጆች አይደለንም፡፡ ክርስቲያኖች በእግዚአብሔር ልጅ ሥጋና ደም ነጻ በምታወጣ አዲስ ኪዳን የወንጌል ልጆች ነንና፡፡
ሐዋርያው ይህንን ሁሉ ያለው ካልተገረዛችሁ አትድኑም የሚለውን የቢጽ ሐሳውያንን ትምህርት በመኮነን ሲሆን ይህንንም በግልጽ «በክርስቶስ ኢየሱስ ሆኖ በፍቅር የሚሠራ እምነት እንጂ መገረዝ ቢሆን ወይም አለመገረዝ አይጠቅምምና /ገላ. 5፥6/ ይላል፡፡ በክርስቶስ ኢየሱስ ሆኖ በፍቅር የሚሠራ ያለው ሕይወትም ፍትወተ ሥጋን አሸንፎ በመንፈሳዊ ተጋድሎ የበቁ ሆኖ በመንፈስ መራመድን ነው፡፡ ይህ ሣራ በተመሰለችባት ሕገ ወንገል ውስጥ የተጠራንበት የመታዘዝ ሕይወት ነው፡፡ ሐዋርያውም ለገላትያ ሰዎች ይህንኑ ተርጉሞ ሲናገር «የክርስቶስ ኢየሱስም የሆኑት ሥጋን ከክፉ መሻቱና ከምኞቱ ጋር ሰቀሉ» /ገላ. 5፥24/ አለን፡፡ ስለዚህ የቤተክርስቲያን ወገኖች ሁሉ ሥጋን ከክፉ መሻቱና ከምኞት ጋር የሰቀሉ መንፈሳውያን፣ በፍቅር የእግዚብሔርን ትዕዛዝ የሚፈጽመው የጨዋይቱ /የእመቤቲቱ/ የሣራ ልጆች ናቸው፤ እንጂ ሥጋዊ ሥርዓት፣ መርገፍ፣ ጥላ በሆነው ብሉይ ኪዳን ውስጥ የመገረዝ አለመገረዝ ጣጣን የሚሰብኩ፣ የሚሰበኩ በሥጋ ልማድ የወለደችው የባሪያዪቱ የአጋር ልጆች አይደሉም፡፡
እንግዲህ በነጻነት የምትመራውን ላይኛይቱን ኢየሩሳሌምን የመረጡ ክርስቶሳውያን ለ2ሺሕ ዘመናት ያህል ክርስቶስን በመስበክ በስሙም ክርስቲያን ተብለን ስንጠራ ኖረናል፡፡ ኢትዮጵያውያን ክርስቲያኖች ገና አስቀድሞ በ34 ዓ.ም «ኢየሱስ ክርስቶስ የእግዚአብሔር ልጅ እንደሆነ አምናለሁ፡፡ ካለው ጃንደረባው ጀምረው ሠልጥና ከነበረችው ባሪያይቱ አጋር ይልቅ በተስፋው ሥርዓት የወለደችውን እመቤቲቱን ሣራ መርጠው እስከዚህ ዘመን ድረስ ኖረዋል፡፡
ከየካቲት ወር 1990 ዓ.ም ጀምሮ ግን «ተሐድሶ» በኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ላይ በይፋ በጀመረው ዘመቻ ውስጥ የዘመቻው አዋጅ ማጠንጠኛ «አሮጊቷ ሣራ እኔ /እኛን/ ወለደች» የሚለው ቃል ነው፡፡ «የተሐድሶ መነኮሳት ኅብረት» የተባለው ቡድን በቤተ ክርስቲያናችን ውስጥ ሆኖ ከቤተ ክርስቲያን ማዕድ እየተቋደሰ ነገር ግን በመሠሪነት ለመናፍቃን ተላላኪ ሆኖ የቆየ ሲሆን በየካቲት ወር 1990 ግን በአዲስ አበባ ከተማ በኢግዚብሽን ማዕከል በፕሮቴስታንቶች ተደራጅቶ በተዘጋጀው «ጉባኤ» በይፋ ራሱን ለይቶ የ«ተሐድሶ» ጥሪ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ላይ እንዲደረግ ሲያውጅ ተገኝቷል፡፡ /ይህንን ለማጋለጥ የወጣወን ቪዲዮ ፊልም ወይም ቪሲዲ ይመልከቱ/ በዚህ አዋጅ በጉልህ የሚስማው ድምፅ ከላይ የተጠቀሰው «አሮጊቷ ሣራ እኔን ወለደች» የሚለው ንግግር ነበር፡፡ ይህንን ቃል ደጋግሞ ሲያስተጋባ የነበረው አባ ዮናስ /በለጠ/ የተባለው «መነኩሴ» «ወንጌልን ለመስበክ ተሾምኩ፤… አሮጊቷ ሣራ ወለደች፤ አሮጊቷ ሣራ እኔን ወለደች፣ ዘውዱን ወለደች፣ ፍስሐን ወለደች፣ ገብረ ክርስቶስን ወለደች… ይህ ትውልድ የኢያሪኮን ግንብ ያፈርሳል…» ወዘተ እያለ አብረውት ለጥፋት የተሰለፉ ከሃዲ መነኮሳትን እየጠቀሰ ፎክሯል፡፡
በእነ አባ ዮናስ አዋጅ ውስጥ ያለው ግልጽ መልእክት ግን በሁለት መልኩ የሚታይ ወይም ሊተረጎም የሚችል ነው፡፡
1.    ቤተክርስቲያንን በእርጅና ዘመኗ ከወለደችው ከቅድስት ሣራ ጋር በማነጻጸር ራሳቸውን የዚህችው ኦርቶዶክሳዊት ቤተክርስቲያን አድርገው በማቅረብ ከዚህች ቤተክርስቲያንም አካል የተገኙ መሆናቸውን በመግለጥ የቤተክርስቲያን አስተምህሮ እነርሱ የሚሉት እንደሆነ አድርገው ለማደናበር ነው፡፡
2.    ሌላው የድፍረት መልእክት ደግሞ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያንን በባሪያይቱ በአጋር ምሳሌ ልትጠቀስ የምትችል ኦሪታዊት፤ የጨዋይቱ የተባለች የሣራ የተስፋው ዘር ቅሪት የሌለባት፣ የወንጌል ብርሃን ያልበራባት፤ ክርስቶስን የማታውቅ፣ ጌትነቱንም የማታምን አድርገው አቅርበዋታል፡፡ ራሳቸውንም ለኢትዮጵያ ሕዝብ ወንጌልን ለማድረስ የተሾሙ በኩራት አድርገው አቅርበዋል፡፡
የመጀመሪያውን ትርጉም ወይም መልእክት በማጉላትም የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስም የዚህን የ«ተሐድሶ» መሠሪ አካሔድ በውል በመረዳት አውግዞ በመለየትና ውግዘት በማስተላለፍ ለ2ሺሕ ዘመናት ወንጌልን ስትሰብክ የነበረች ቤተ ክርስቲያንን ልዕልናና ክብር አጉድፎ በወንጌል ሰባኪነት ስም በማጭበርበር ፕሮቴስታንታዊ ኑፋቄ ለመዝራት ተሐድሶ እያደባ መሆኑን አጋልጧል፡፡ ጠቅላይ ቤተክህነት ከሰጠው ሰፊ መግለጫ ውስጥ ይህን የተመለከተውን በአጭሩ እንደሚከተለው እናስታውስ፡፡

 

«አሮጊቷ ሣራ ወለደች» የሚል ኃይለ ቃል መናገራቸው ተዘግቧል፤ መናፍቃኑ ይህን የተናገሩት የእነሱን ከጥንታዊቷ ቤተ ክርስቲያናችን አፈንግጦ መውጣት የዘጠና ዓመት እድሜ ከነበራት እና ከቅድስት ሣራ ከተወለደው ከይስሐቅ ልደት ጋር ለማነጻጸር በመፈለግ መሆኑ ግልጽ ነው፡፡


የይስሐቅ እናት ቅድስት ሣራ በመሠረቱ እናትና አባቱን የሚያከብርና የሚያስከብር እንጂ የሚያዋርድ፣ እናትና አባቱን የሚያስመሰግን እንጂ ሰድቦ የሚያሰድብ፣ በእናትና አባቱ እግር የሚተካ እንጂ እናትና አባቱን የሚክድ፣ በወላጆቹ የተመረቀ እንጂ የተረገመ ልጅ እናት አይደለችም፡፡


በቅድስት ሣራ አምሳል የተጠቀሰችው ጥንታዊቷ ቅድስት ቤተ ክርስቲያናችንም እንዲሁ እናቱን ለመሸጥና ለመለወጥ የሚያስማማ፣ እናቱን ሲሰድብና ሲነቅፍ ሐፍረት የማይሰማው ርጉም ልጅ እናት አይደለችም፤ ቤተ ክርስቲያናችን እንዲህ ያለ ልጅ አልወለደችም፣ አትወልድምም፡፡


ጠላትና አረም ሳይዘሩት ይበቅላል እንደሚባለው፣ በአንድ የስንዴ ማሳ ላይ የበቀለ አረም ቢኖር ያ አረም ሳይዘራ የበቀለ መሆኑን ማረጋገጥ አስቸጋሪ እንደማይሆን ሁሉ እነዚህ መናፍቃንም በቤተ ክርስቲያናችን የስንዴ ማሳ ላይ ሳይዘሩ የበቀሉ ጠላቶች እንደሆኑ መገንዘብ አስቸጋሪ አይሆንም፡፡ በምሳሌ ዘር እንደተጠቀሰው /ማቴ.13፥24-30/ በንጹሕ ስንዴ ማሳ ላይ ጠላት የዘራው ክርዳድ ሊበቅል እንደሚችልም ታውቋል፡፡ እነዚህ መናፍቃንም የጠላት እንጂ የቤተ ክርስቲያናችን አበው ተክል ባለመሆናቸው ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን እንደ ተወለዱ አድርገው ራሳቸውን ከማስተዋወቅ ይልቅ የማን ልጆች እንደሆኑ ቢጠይቁ ዕውነቱን ለማወቅ በቻሉ ነበር፡፡


አሁንም ቢሆን ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ለጢሞቴዎስ በጻፈው ሁለተኛ መልእክቱ «በኋላ ዘመን አንዳንድ ሰዎች ገንዘብን የሚወድዱ፣ ራሳቸውን የማይገዙ፣ ሐሜተኞች፣ መልካም የሆነውን ነገር ሁሉ የማይወዱ ከዳተኞች ይሆናሉ፤ የአምልኮት መልክ አላቸው፤ ኃይሉን ግን ይክዱታል፤ ከእነዚህ ደግሞ ራቅ ወደ ቤቶች ሾልከው እየገቡ ኃጢአታቸው የተከመረባቸውን በልዩ ልዩ ምኞትም የሚወሰዱትን፣ ሁልጊዜም እየተማሩ እውነትን ወደ ማወቅ ከቶ ሊደርሱ የማይችሉትን… የሚማርኩ ከእነዚህ ዘንድ ናቸውና» /1ጢሞ. 3.1-7/ ሲል እንደተናገረው እነዚህ መናፍቃን ከዚህ የትንቢት ዘመን የተወለዱ እንጂ የቤተ ክርስቲያናችን ልጆች አለመሆናቸውን በግልጽ መንገር ግዴታ ይሆናል፡፡ /መጋቢት 26 ቀን 1990 ዓ.ም/

ጠቅላይ ቤተክህነት የተነተነበት መንገድ እንዳለ ሆኖ የ«ተሐድሶ» ቡድን «አሮጊቷ» የሚለውን ቃል የመረጠበትን መሠረታዊ ምክንያት በውል ማጤን ይገባል፡፡ ቅዱስ ጳውሎስ ወንጌልን የምትሰብክን ቤተ ክርስቲያን ከቅድስት ሣራ ጋር አነጻጽሮ ባቀረበበት መንገድ አስበው ተናግረውት ቢሆንማ ከኦርቶዶክሳዊት ቤተ ክርስቲያን አፈንግጠው የፕሮቴስታንት ፓስተሮች ባዘጋጁት በዚያ የስድብ ጉባኤ ላይ የቤተ ክርስቲያኒቱን የሃይማኖት ትምህርትና ሥርዓት የምእመ ናንን ሕይወት ባላዋረዱ ባላናናቁ ነበር፡፡ ነገር ግን «አሮጊት /አሮጌ» የሚለውን ቃል የመረጡት ቤተ ክርስቲያን አርጅታለችና ማደስ አለብን ለሚለው አስተሳሰብ መንደርደሪያ ነው፡፡ እነዚህ የተሐድሶ መናፍቃን ተወግዘው ቢለዩም በውጪም በውስጥም ሆነው ቤተ ክርስቲያንን ለመገዝገዝና አስተምህሮአቸውን አንዳንድ የቤተ ክርስቲያኒቱ «መምህራን» አውቀውም ሳያውቁም በየዓውደ ምህረቱ እንዲያስተጋቡ ተፅዕኖ መፍጠራቸውን ቀጥለዋል፡፡

እነ አባ ዮናስ የ«አሮጊቷ ሣራ ወለደች» ቃላቸውን ከአዋጁ ከ12 ዓመታት በኋላ አሁን በይፋ ደግሞ «ቤተ ክርስቲያንን አሪታዊት፣ ጨለማ ውስጥ ናት ሲሉ አሮጊቷ ሣራ ዛሬ እኔን ወለደች፣ እገሌን ወለደች፣ እገሌን ወለደች…» የሚል ከእነ አባ ዮናስ ጋር የቃልና የስሜት ዝምድና ያለው የአዋጅ ቃል በአንዳንድ ሰባኪያን ነን ባዮች ተሰምቷል፡፡ በአባ ዮናስና በእነዚህ ሰባኪያን መካከል ያለው የአቀራረብ ልዩነት የአባ ዮናስ በኤግዚቢሽን ማዕከል፣ እነዚህ ደግሞ በራሷ በቤተ ክርስቲያኒቱ ዓውደ ምህረት ላይ ማወጃቸው ነው፡፡

ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ያስተማረው ትምህርት ቃሉም ትርጓሜውም የታወቀ ሆኖ ሳለ ቤተ ክርስቲያናችንም ከጨዋይቱ የተወለድን ክርስቲያኖች አንድነት መሆኗ ለ2ሺሕ ዘመን የተመሰከረ ሆኖ ሳለ የአሁኖቹ «ሰባክያን» ራሳቸውንና ጓደኞቻቸውን ነጥለው «የተስፋው ወራሾች የአሮጊቷ የሣራ ልጆች» እያሉ የሚያቀርቡበት ገለጻ ትርጓሜ ይፋ መሆን አለበት፡፡

በመሠረቱ በሐዋርያው በቅዱስ ጳውሎስ የተሰበከውን ምሳሌያዊ ትምህርት ይዞ ተንትኖ ማስተማር ተገቢ ነው፡፡ ነገር ግን ከአርባ ሚሊዮን በላይ ምእመናን ባሉበት ጥንታዊት እና ሐዋርያዊት ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ራሳቸውንና እነርሱ የመረጧቸውን የቡድን አባላት አባ ዮናስ ባቀረቡበት መንገድ «የአሮጊቷ ሣራ» ብሎ የጠሩበት ቤተ ክርስቲያን እነርሱን ከመውለዷ በፊት ምን ጎድሎባት፣ ምንስ አጥታ ነበር ? ቅዱስ ጳውሎስ መካኒቱ፣ ጨዋይቱ፣ እመቤቲቱ እያለ የጠራበት ቅጽል እያለ «አሮጊቷ» የሚለውን በማስጮኽ ማቅረብስ ለምን ተፈለገ ? ቀጥተኛ ምንጩስ ማነው ? ምንድነው ? እነዚህ ሁሉ ጥያቄዎች መመለስ ያለባቸው ናቸው፡፡ እነ አባ ዮናስ «አሮጊቷ ሣራ» ያሏትን ቤተ ክርስቲያንን ድንግል ማርያምን፣ ተክለሃይማኖትን፣ ጊዮርጊስን በልብሽ አኑረሻልና አውጪ እያሉ በአደባባይ ድፍረት ተናግረዋል፡፡ በእነዚህ «ሰባክያን» የ«አሮጊቱ ሣራ» አስተምህሮ ውስጥ ያለው አንድምታስ ምንድነው ? እነ አባ ዮናስ በ«አሮጊቷ ሣራ» አስተምህሮአቸው «ቤተክርስቲያኒቱ በ4ኛው ክፍለ ዘመን አባ ሰላማ ከሳቴ ብርሃን ከሰበኩበት ጊዜ በኋላ ወንጌል አልተሰበከችም የወላድ መካን ሆና የኖረች ናት» በማለት አሁን እነርሱ ያንን ለመፈጸም የተወለዱ አድርገው አቅርበዋል፡፡ የእነዚህ ሰባክያን የ«አሮጊቷ ሣራ» አስተምህሮስ ከዚህ አንጻር ምን ይላል ?

ይህ ብቻ ሳይሆን አባ ዮናስ «ይህ ትውልድ የኢያሪኮን ግንብ ያፈርሳል» ያለው ቤተ ክርስቲያኒቱን ዒላማ ያደረገ ፉከራው በእነዚህ ሰባክያን የመዝሙር መንደርደሪያዎች ውስጥ ከሚነገረውና «መዶሻ ያልያዘ ሠራዊት ኢያሪኮን ያፈርሳል…» ከሚሉት አዝማች ቃል ጋር ያለውንም የትርጉም ዝምድና መጤን እንዳለበት         እንድናስብ ያስገድዳል፡፡ በተመሳሳይ ይህንኑ መንገድ ተከትሎ በየደረጃው ምእመናን እነ አባ ዮናስ በግልጽ ያወጁት የ«ተሐድሶ» ፕሮቴስታንታዊ አስተምህሮ ዓውደ ምህረቶቻችን ላይ አሁንም ወደቆሙ «መምህራን» መሻገር አለመሻገሩን ቃሎቻቸውን እያጠኑ ለመመርመር ተገደዋል፡፡ የቤተ ክርስቲያናችን የሚመለከታቸው አካላትም የእነዚህን «ሰባኪያን» ትምህርት መርምረው ካለማወቅ በስሕተት የቀረበ ትምህርት መሆኑን ወይም በድፍረት የቀረበ ለ«ተሐድሶ» ዘመቻ የጥፋት ፈትል ማጠንጠኛ መሆን አለመሆኑን ለይተው እንደሚያቀርቡ ተስፋ እናደርጋለን፡፡

ምንጭ፦ ሐመር 19ኛ ዓመት ቁጥር 2

ወስብሐት ለእግዚአብሔር