ዓለመ ሰማይ

በዓለመ ሰማይ እግዚአብሔር አምላክ ፍጥረቱን መፍጠር በጀመረበት በመጀመሪያው ቀን እሑድ አስቀድሞ የተፈጠሩት ሰባቱ ሰማያትና መላእክት ናቸው፡፡ ሰማያቱም እንደ ስያሜያቸው የራሳቸው ትርጓሜ አላቸው፡፡

ተአምራትን ፍለጋ

በዚህ ምድር እንደ ክርስቲያን ሆነን ስንኖር የሚገጥሙን ፈተናዎችና አጣብቂኞች ይኖራሉ፡፡ የሚገጥሙንም አንዳንድ ፈተናዎችም ከማስጨነቃቸው የተነሣ በእግዚአብሔር ተአምር እናመልጣቸው ዘንድ እንመኝ ይሆናል፡፡ ይሁን እንጂ ፈተናዎቹ ጸጋና ክብር ሊያሳጡንም ጭምር ስለሚችሉ ተአምራት ተደርገውልን ከምናመልጣቸው በሃይማኖትና በምግባር ጸንተን፣ በጾም በጸሎት ታግሠናቸው ድል ብንነሣቸው የበለጠ ክብርን ልናገኝባቸው እንችላለን፡፡ ከጻድቁ ኢዮብ፣ ከሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ፣ ከደቀ መዝሙሩ ከቅዱስ ጢሞቴዎስም ተግባራዊ ሕይወት ይህን እንማራለን፡፡

እግዚአብሔርን ለማመን በቤቱ ጸንቶ ለመኖር ለሚገጥሙን የዚህ ዓለም መሰናክሎች ሁል ጊዜ ተአምራትን መሻት እግዚአብሔር የሚወደው መንገድ አይደለም፡፡ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በመዋዕለ ሥጋዌ በሚያስተምርበት ወራት ጻፎችና ፈሪሳውያን ወደ እርሱ ቀርበው ‹‹መምህር ሆይ ከአንተ ምልክት እንድናይ እንወዳለን›› አሉት፡፡ እርሱ ግን መልሶ ‹‹ክፉና አመንዝራ ትውልድ ምልክትን ይሻል፤ ከነቢዩም ከዮናስ ምልክት በቀር ምልክት አይሰጠውም፡፡ ዮናስ በዓሣ አንበሪ ሆድ ሦስት ቀንና ሦስት ሌሊት ይኖራል፤ የነነዌ ሰዎች በፍርድ ቀን ተነሥተው ይፈርዱበታል፤ በዮናስ ስብከት ንስሓ ገብተዋልና፤ እነሆም ከዮናስ የሚበልጥ ከዚህ አለ፡፡ ንግሥተ አዜብ በፍርድ ቀን ከዚህ ትውልድ ጋር ተነሥታ ትፈርድበታለች፤ የሰሎሞንን ጥበብ ለመስማት ከምድር ዳር መጥታለችና፡፡ አነሆም ከሰሎሞን የሚበልጥ ከዚህ አለ›› አላቸው፡፡ (ማቴ.፲፪፥፴፰‐፵፪)

ምልክትን (ተአምርን) የሚፈልግ ትውልድ ለምን ክፉና አመንዝራ ተባለ? ‹ክፉ› የተባለው እምነቱን በተአምራት ላይ ስላስደገፈና ስለሚያስደግፍ ነው፡፡ ‹አመንዝራ› የተባለበትም ምክንያት አመንዝራ ሰው ነገሩ አንድ ሲሆን ዕለት ዕለት ሴት (ወንድ) ሊለወጥለት እንዲወድ አይሁድና የአይሁድን መንገድ የሚከተሉ ሰዎችም ዕለት ዕለት ትምህርትና ተአምራት ሊለወጥላቸው ይወዳሉና ነው፡፡

‹‹የለመንከኝን ሁሉ አደርግልህ ዘንድ ቃል ኪዳንን ሰጥቼሃለሁ››

ለሰማንያ ዓመት በጫካ ውስጥ ከአንበሶችና ከነብሮች እንዲሁም ከአራዊት ጋር መኖርን ሳይፈሩ እስከ ሞት ድረስ የታገሡ እንዲሁም በዝቋላ ተራራ ባለው ባሕር ውስጥ መቶ ዓመት ተዘቅዝቀው ለኢትዮጵያ ሰዎች ምሕረትን የለመኑ አባታችን አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ ቃል ኪዳን የተቀበሉበትን ጥቅምት አምስት ቀን እናከብር ዘንድ ይገባል፡፡ በሀገረ ግብጽ የተወለዱት ጻድቁ አባት የእግዚአብሔር ትእዛዝ ሆኖ ስለ ኢትዮጵያ ይለምኑና ይማልዱ ዘንድ ፈቃዳቸውም ስለነበር ቤተሰቤን ሆነ ሕዝቤን ሳይሉ ወደ ሀገራችን በመምጣት በጭንቅላታቸው ተዘቅዝቀው ደማቸው ፈሶ እስኪያልቅና ሥጋቸውም አልቆ አጥንቶቻው እንደበረዶ እስኪሆን ድረስ የጸለዩ ታላቅ አባታችን ናቸው፡፡

ውኃ የሌለባቸው ምንጮች

ውኃ ከምንጭ ተገኝቶ እየፈሰሰ የፍጥረትን ጥማት ያረካል፡፡ በውኃ ሰው ሕይወቱን ያለመልማል፤ እንስሳትና አራዊትም እንዲሁ፡፡ ዕፅዋትና አዝርዕትም ያለ ውኃ አይለመልሙም፤ አይበቅሉምም፡፡ በቅዱሳት መጻሕፍት እንደ የአገባቡ መምህራን በውኃ ምንጭ ተመስለዋል፡፡ ከምንጭ ንጹሕ ውኃ ተገኝቶ ፍጥረትን እንደሚያረሰርስ ከመምህራንም አንደበት በውኃ የሚመስል ቃለ እግዚአብሔር እየፈሰሰ የሰው ልጆችን በጽድቅ እንዲኖኑ ያደርጋል፡፡ ምእመናን ውኃ ቃለ እግዚአብሔር ከሚገኝባቸው እውነተኞች መምህራን እግር ሥር ተገኝቶ በመማር ከድርቀት ኃጢአት ወደ ልምላሜ ጽድቅ ይመጣሉ፤ የመንፈስ ፍሬንም ያፈራሉ፡፡

ግሽን ማርያም

በሀገራችን ኢትዮጵያ በወሎ ክፍለ ሀገር አምባሰል አውራጃ የሚገኘው ታላቁ የግሸን ማርያም ደብር የግማደ መስቀሉ መገኛ በመሆኑ ለሕዝበ ክርስቲያኑ ትልቅ ተስፋና መመኪያ ነው፡፡ መስቀል የክርስትናችን መገለጫ፣ የብርሃናችን ዐምድ እንዲሁም የሰላማችን መገኛ ነውና፡፡

ጉባኤ ኒቅያ

ጉባኤ ኒቅያ ቤተ ክርስቲያን አንድነቷን የጠበቀችበት፣ አርዮስና አርዮሳውያን የተወገዙበት፣ የጌታችን የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ የባሕርይ አምላክነት፣ አዳኝነት፣ ጌትነት፣ መድኃኒትነት የተመሠከረበት፣ ኦርቶዶክስ የሚለው ስም ትምክህት የሆነበት ነው፡፡ ቤተ ክርስቲያን ይህን ጉባኤ ትቀበላለች፤ ትልቅም ስፍራ አላት፡፡

‹‹ሥዕሏ ሥጋን የለበሰች ትመስል ከሠሌዳዋም ቅባት ይንጠፈጠፈ ነበር››

ሕዝበ ክርስቲያን ከሚያከብሩት ከእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ፴፫ቱ በዓላት አንዱ ጼዴንያ ማርያም በቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን በመስከረም ፲ ቀን ይከበራል፡፡ በተለይም በሀገራችን ኢትዮጵያ በአዲስ አበባ  ቡራዮ አካባቢ ጼዴንያ ማርያም በምትባል ቤተ ክርስቲያን በዕለቱ ታቦተ ክብሩ ከመንበሩ ወጥቶ በደማቁ ተከብሮ ይውላል፡፡ ጼዴንያ በምትባል ሀገር ሥጋ የለበሰች ከምትመስል ሥዕል ከሠሌዳዋ ቅባት እየተንጠፈጠፈ አምላክን የወለደች የእመቤታችን የድንግል ማርያም ተአምር ተገልጧልና፤ ይህችን ድንቅ ሥዕልም ቅዱስ ሉቃስ እንደሣላት ይነገራል።

በዓለ መጥምቀ መለኮት ቅዱስ ዮሐንስ

መጥምቀ መለኮት ቅዱስ ዮሐንስ በሰማዕትነት ያረፈበት ዕለት መስከረም ሁለት የተከበረ ነው፡፡ ይኸውም ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የመጥምቁን ክብር ‹‹እውነት እላችኋለሁ፥ ከሴቶች ከተወለዱት መካከል ከመጥምቁ ዮሐንስ የሚበልጥ ማንም የለም” በማለት መሥክሮለታል፡፡ (ማቴ. ፲፩፥፲፩፣ ሉቃ ፯፥፳፰)

በዓለ ቅዱስ ሩፋኤል

ጳጉሜን ሦስት ቀን የሊቀ መላእክት የቅዱስ ሩፋኤል በዓል በየዓመቱ ይታሰባል፤ ይከበራልም፡፡ መልአኩ የጦቢትን ዓይን ያበራና ወለተ ራጉኤልን ተቆራኝቷት ከነበረው ጋኔን ያላቀቀ ነውና፡፡ ሊቀ መላእክት ቅዱስ ሩፋኤል ከመላእክት አለቆች ሦስተኛ የሆነ ነው፡፡ ደግሞም ከእስክንድርያ ውጭ በደሴት የታነጸች ቤተ ክርስቲያን በከበሩ ሊቀ ጳጳሳት ቴዎፍሎስ ዘመን በውስጧ ተአምር የተገለጸበትና የከበረችበት ዕለት ነው፡፡

ዕረፍተ ዘአበዊነ አብርሃም፣ይስሐቅ ወያዕቆብ

የአባቶቻችን የአብርሃም፣ የይስሐቅና የያዕቆብን መታሰቢያቸውን እናደርግ ዘንድ የቤተ ክርስቲያን መምህራን አባቶቻችን አዘውናል፤ ከእርሳቸው ዘለዓለም የሚኖር ርስትን ተቀብለናልና፡፡ የእነዚህንም አባቶች ገድላቸውን እንዘክር ዘንድ ተገቢ ነው፡፡