ዓለመ ምድር

ጥቅምት ፳፫ ቀን ፳፻፲፭ ዓመተ ምሕረት

የአምላካችን ክብርና ድንቅ ሥራ የተገለጠበት ዓለም በውስጡ የያዛቸውም ፍጥረታት የእርሱን ግብር ይገልጻሉ፡፡ ፈጣሪያችን እግዚአብሔር ሰማይ ዙፋኑ ምድር መረገጫው እንደመሆኑም በአርያም ዘወትር እየተመሰገነ ይኖራል፡፡ ለክብሩ መገለጫ የፈጠራቸው እልፍ አእላፍ መላእክት ያለማቋረጥ እርሱን ያመሰግናሉ፡፡ (ኢሳ.፷፮፥፩)

ምንም እንኳን ቃሉን ጠብቀው ለአምላካቸው የሚታዘዙት ረቂቃን ፍጥረታት የሚገኙት በሰማይ ቢሆንም በዚህ ‹‹አሜከላና እሾህ ይብቀልብሽ›› ተብላ በተፈረደባት ምድርም ቅዱስ ቃሉን ዐውቀውና ጠብቀው ለሕጉ በመገዛት የኖሩ ቅዱሳን፣ ጻድቃንና ሰማዕታት ሁሉ በሰማይዊት እየሩሳሌም ለመኖር ሲበቁ እርሱን ለማየት፣ ለማመስገንና አብረውት ለመኖር ችለዋል፡፡ (ዘፍ.፫፥፲፰)

አምላካችን እግዚአብሔር ፍጥሩትን በሙሉ የፈጠረው ለመልካምና ለክብር ነው፡፡ (ዘፍ.፩፥፩-፴፩) ስለዚህም የተቀደሰውና የተከበረው ሁሉ በሰማይ ቢገኝ እንኳን ምድርንም የፈጠረው የሰው ልጆች በሙሉ በሃይማኖት፣ በጽድቅና በመንፈሳዊ ጸጋ ከእርሱ ጋር እንድንኖር ነው፡፡ በመጀመሪያ መሬት (ምድር) በውስጧ ለሚገኙት ሁሉ መኖሪያ እንድትሆን የተፈጠረችው ከምንም ነው። መሬት ብትን (አፈር) ነበረች፤ ምድር የተባለችውና ዛሬ እንደምናየው የጸና የሆነችው ከውኃ ጋር ተዋሕዶ በመጠንከሯ ነው፤ በምድር በውስጥ ሦስት ባሕርያት ሲኖሩ እነርሱም ደረቅነት (የብስነት)፣ ክብደት (ግዙፍነት)፣ ጥቁርነት (ጽሉምነት) ናቸው።

አዳም ዕፀ በለስን በልቶ ከገነት በመባረሩ በእርሱም ጥፋት ምድር ተረግማለችና እሾህና አሜከላ አብቅላለች፡፡ በሊቃውንቱ አተረጓጎም ምድር በችግርና በመከራ የተከበበች መሆኗን እንረዳለን፡፡ የሰው ልጅ የሞት ፍርድ ተፈርዶበት ወደ መሬትነቱ እስኪለወጥ ድረስ በምድራዊ ሕይወቱ ብዙ ሊፈተን፣ መከራና ሥቃይ ሊቀበል እንደሚገባ አመላካች ነው፡፡ ይህም ጠላታችን ዲያብሎስ ያመጣብን ጥፋት በመሆኑ በዚህ ምድር በፈተና እንድንኖር የታዘዝን መሆኑን ማገናዘብ ያስፈልጋል፡፡

ጥንተ ጠላት ዲያብሎስ የእግዚአብሔር አምላካችን ትእዛዝ ባለመቀበል ለማመስገን ባለመፍቀዱ  ከክብሩ ተዋርዶ ወደ ምድር ከተጣለበት ጊዜ ጀምሮ በሰዎች ላይ ብዙ መከራና ሥቃይ አምጥቶብናል፡፡ በአዳም ላይ በቅንዓት ተነሣሥቶ በማሳት ከገነት ማስባረር ብቻም ሳይሆን በምድር ሲኖር በኀዘንና በሥቃይ ሰላምና ደስታ አጥቶ እንዲኖር መከራ አብዝቶበታል፡፡ ዘወትር አምላኩን መበደሉን በማስብ በለቅሶ ይማጸን የነበረው የመጀመሪያው ሰው አዳም ግን ፈጣሪው አዝኖለትና በቅዱሳን መልአክት በኩል ረድቶት በዚህች ምድር ላይ እንዴት መኖር እንደሚችል ስላመለከተውና ስላስረዳው ምድርን ሁለተኛ (ጊዜያዊ) ቤቱ አድርጓት ነበር፡፡ በእርሷም ለ፱፻፴ (ዘጠኝ መቶ ሠላሳ) ዓመት ኖሯል፡፡ ‹‹ብዙ ተባዙ፤ ምድርን ሙሏት›› ብሉም አምላክ እንዳዘዛቸው አዳም ከሚስቱ ከሔዋን ዘር ተክቷል፡፡ (ዘፍ.፱፥፩) እነርሱም በተመሳሳይ መልኩ ልጆች በመውለዳቸው የሰው ዘር ሐረግ በምድር መላ፡፡

በሰው ሰውኛ ልኬት ምድር እጅግ ሰፊ እንደመሆና መጠን በውስጧ ከያዘቻቸው ግዑዛን ነገሮችና እንስሳት ይልቅ በረቀቀ አእምሮ አስቦና አገናዝቦ መልካሙን ከክፉ፣ መጥፎውን ከጥሩ ለይቶ ማወቅና በጎውን ማድረግ የሚችለው ክብሩ ፍጥረት ሰው አምላኩን የሚበድል መሆኑ ግን እጅግ አሳዛኝና አስከፊ ነው፡፡ ሰዎች በአንድም ይሁን በሌላ በስሕተት ብቻም ሳይሆን በድፍረት ፈጣሪያቸውን ያስከፋሉ፤ ያሳዝናሉ፡፡ ጥፋት ማጥፋታቸውን እንዲሁም ኃጢአት መሥራታቸውን ባወቁ ጊዜ እንኳን ተጸጽተው ይቅርታና ምሕረት ከመለመን ይልቅ ምንም ጥፋት እንዳልሠራ ሰው እራስን በማሰብ ያለ ንስሓ ምድራዊ ሕይወታቸውን ይኖራሉ፡፡

በተለይም በአሁኑ ጊዜ ሰዎች ክፋትና ኃጢአት አብዝተው በመሥራቸው የተነሣ በጎውንና ክፉን አንድ አድርጎ ማሰብ ደረጃ ደርሰዋል፡፡ ከወጣቱ እስከ አዛውንቱ የዕድሜ ክልል ያሉት ፈጣሪን በመርሳትም ይሁን በመዳፈር የፈለጉትን ምድራዊ ነገር ለማግኘት ክፋትና በደል በሰዎች ላይ ይፈጽማሉ፡፡ ለዚህም በዚህ ወቅት በግልጽ የተመለከትነው ነባራዊ የሀገራችን የማኅበረሰባዊ ቀውስና ጥቃት ምስክር ነው፡፡ በዘርና በሃይማኖት ከፋፍለው ሊያጠፋን የሚዳክሩ ጠላታችን ሁሉ በእኛ ጥፋት ሊያመጡብን እንደሆነ ልንገዘነብ ይገባናል፡፡ ያለበለዚያ ግን የሰይጣን ቁራኛ መሆናችን አይቀርም፡፡

ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን ምድር በገነት ወይም በሲኦል ልትመሰል እንደምትችል ያስረዳሉ፡፡ በቤተ ክርስቲያን ወርቃማ ዘመናት ተብሎ የሚጠሩትንም በመጥቀስ የተመረጡ ቅዱሳን ነገሥታት የነገሡበት፣ ደጋግ አባቶች የኖሩበት፣ ሊቀ ጳጳሳትና ጳጳሳት እንዲሁም ቀሳውስትና ካህናት በበጎና በመልካም መንገድ ምእመናንን መርተው በቅድስና ሕይወት ለርስተ መንግሥተ ሰማያት ባበቁበት ጊዜ ምድር በገነት ትመሰል እንደነበር ያስረዳሉ፡፡ በዚህም ወቅት እግዚአብሔር አምላክ ከሕዝቡ ጋር ይኖር እንደነበር ቅዱሳት መጻሕፈት ምስክሮች ናቸው፡፡ በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ ሕዝበ እስራኤል በነቢያቱ ሙሴና ኢያሱ አማካኝነት ከጠላት (ከግብጽ) ባርነት ወጥተው ወደ ምድረ ርስት እንደደረሱ ተመዝግቦ ይገኛል፡፡ (ዘፀ.፲፪፥፵፩‐፵፪፣ኢያ.፲፪፥፲፫፥፲፬-፳፩)

በተመሳሳይ መልኩም በሌሎች ዘመናት ጣዖት አምላኪ ነገሥታት በነገሡበት ጊዜም ፈጣሪያቸው ከጠላቶቻቸው ታድጎ በሰላምና በአንድነት ወደ ሀገራቸው መርቶ በማስገባት በጎ ጊዜን አምጥቶላቸዋል፡፡

በሐዲስ ኪዳን ደግሞ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለዓለም ድኅነት ሲል ከንጽሕት ቅድስት ድንግል ማርያም ተወልዶ፣ ሥጋ ለብሶ፣ እንደ ሕፃን በጨርቅ ተጠቅልሎና በጥቂቱ አድጎ ከሰዎች ጋር ኖሯል፡፡ በዮርዳኖስ ወንዝም በመጥምቀ መለኮት ቅዱስ ዮሐንስ እጅ ተጠምቆ፣ በመዋዕለ ስብከቱ ብዙዎችን አስተምሮ እንዲሁም በገቢረ ተአምራቱ ብዙዎችን አድኗል፡፡ የመረጣቸው ዐሥራ ሁለቱ ቅዱሳን ሐዋርያትን ቃሉን በማስተማር በመንፈስ ቅዱሳ ጸንተው እንዲኖሩ ተአምራትን እያደረገ አሳይታቸዋል፡፡ ይህም በተሰመሳሳይ መልኩ እነርሱም ለሌሎች እንዲያስተማሩና እንዲፈውሱ ነበር፡፡ ጌታችን ለሐዋርያቱ ትሕትናን ለማስተማር ጎንበስ ብሎ እግራቸውን አጥቧል፤ አብራቸው ማዕድ ቆርሷል፡፡ ከዚህም ባሻገር ፍቅሩን በመስቀሉ ላይ ተሰቅሎ ገልጾልናል፡፡     እኛ ሰዎች ይህን ተምሳሌት አድረገን እንኖር ዘንድ ተገቢ ነው፤ ስለ ሰዎች ፍቅርና ድኀነት ሲል የተሰቀለው የዓለም ቤዛ መድኃኒዓለም የከፈለልንን መሥዋዕትና ያደረግልንን ሁሉ በመረዳት ዘወትር ልናመሰግነውና ልንታዘዘው ይገባል፡፡ በሕይወት ዘመናችን ሁሉም መስቀሉን ተሸክመን መኖር ያስፈልጋል፡፡ አምላካችን ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በምድር ያደረገው ሁሉ ሰዎችን ለማዳን በመሆኑ ይህን እውነት ልንጠራጠርና ልንክድ አይገባም፡፡ ምክንያቱም ከኃጢአት ባርነትና ከሰይጣን አረንቋ የሚያወጣን የእውነት መንገድ እርሱ ነውና፡፡ (ዮሐ.፲፬፥፮)  ስለዚህም ሰዎች ኃጢአት ቢሠሩ እንኳን በንስሓ ወደ አምላክ መመለስ እንደሚችል በማመን ከሥጋዊ ወይም ምድራዊ ሕይወት ይልቅ መንፈሳዊውን በማስበለጥና ለነፍሳችን ድኅነት በማሰብ ለሕጉ መገዛትና ትእዛዙን ጠብቀን መኖር ከእኛ ይጠበቃል፡፡

ይቆየን!