ሊቀ ሰማዕታት ቅዱስ ጊዮርጊስ

ሚያዚያ ፳፻፲፭ ዓመተ ምሕረት

ፀሐይና የአጥቢያ ኮከብ የተባለ ታላቅና ክቡር የሆነ የሰማዕቱ የቅዱስ ጊዮርጊስ የምስክርነት ፍጻሜ የሆነበት ቀን ሚያዚያ ፳፫ የከበረ ነው፡፡

የቅዱስ ጊዮርጊስ አባት ቀጰዶቅያ አገር ይኖር የነበረ አንስጣስዮስ የተባለ መስፍን ነው፡፡ እናቱም ቴዎብስታ የተባለች ፍልስጥዔማዊ ነበረች፤ የዚህ ቅዱስ አባትም የሞተው በልጅነቱ ስለዚህም ሌላ ደግ ክርስቲያናዊ መስፍን ወስዶ አሳደገው፡፡ መስፍኑም በጦር ኃይል አሰለጠነው፡፡ ሃያ ዓመትም በሞላው ጊዜ መስፍኑ የ፲፭ ዓመት ልጁን ሊያጋባውና ሀብቱን ሊያወርሰው ድግስ ደገስ፤ ነገር ግን ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ቅዱስ ጊዮርጊስን ለዚህ አልመረጠውምና  የመስፍኑን ነፍስ ወሰደ፡፡ ቅዱስ ጊዮርጊስም ኀዘኑን ከጨርሰ በኋላ ወደ ቤሩት ሀገር ሄደ፡፡ በዚያም ደራጎንን ያመልኩና ሴት ልጆቻቸውን ይገብሩለት ነበር፤ ሰማዕቱም ደራጎኑን በኃይለ መስቀል ድል ነሥቶት ገድሎታል፤ ሕዝቡንም ወደ አምልኮተ እግዚአብሔር መልሷቸዋል፡፡

ዕድሜው ሃያ ዓመት በሞላ ጊዜም ወደ ንጉሥ ዱድያኖስ ዘንድ የአባቱን ሹመት ሊቀበል ሄደ፤ ነገር ግን በዚያን ጊዜ ንጉሡ ሕዝቡ ጣዖትን እንዲአመልኩ ያስገድዳቸው ነበር፡፡ ስለዚህም ቅዱስ ጊዮርጊስ እጅግ በማዘኑ ገንዘቡን በሙሉ ለድኆችና ለምስኪኖች በመስጠት ባሮቹንም ነፃ አወጣቸው፡፡

ከንጉሥ ዘንድ በመሄድ በፊቱ ቆሞ በክብር ባለቤት በጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ታመነ፡፡ ንጉሡ ግን በማባበልና ቃል ኪዳንም በመግባት አምላኩን ክዶ ለጣዖታት እንዲሠዋ ለማድረግ ሞከረ፡፡ ብዙ አስጨናቂ ሥቃይንም አሠቃየው፤ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ግን ያጸናው  ቍስሉንም ያድነው ነበር፤ ለሦስት ጊዜም እንደሚሞት እርሱም እንደሚአስነሣው በአራተኛውም የምስክርን አክሊልን እንደሚቀበል ነገረው፡፡ በዚህም ጊዜ ቃል ኪዳንም ገባለት፤ ለሰባት ዓመትም በጽኑዕ መከራና በሥቃይም እንዲሁም በተጋድሎ እንደሚኖር በዚያም ስሙ በዓለሙ ሁሉ የተገለጠ እንደሚሆን መላእክትም እንደሚያገለግሉትም ነገረው፡፡

ቅዱስ ጊዮርጊስ ትእዛዙን ባለመቀበሉ ንጉሥ ዱድያኖስ እጅግ አዝኖ አትናስዮስ የሚባል ታላቅ ሥራየኛ ካስመጣ በኋለ መርዝን ቀምሞና በጽዋ መልቶ ለቅዱስ ጊዮርጊስ እንዲጠጣው ሰጠው፡፡ መርዙም በፍጥነት የሚገድል ነበርና ወዲያውኑ የሚሞት መስሎት ነበር፡፡ ቅዱሱም ጊዮርጊስ ግን ያንን ጽዋ ቢጠጣውም ምንም ጉዳት ሳይደርስበት ቀረ፡፡

የእግዚአብሔር ድንቅ ሥራ በመሆኑም ይህን ተአምር አይቶ ያ መሠርይ በክብር ባለቤት በጌታ በኢየሱስ አምኖ በሰማዕትነት መሞት ቻለ፡፡ ቁጥራቸውም ሠላሳ ሺህ ሰባት መቶ ነፍስ የሚሆኑ ሌሎች ብዙዎች ሰዎች ከእርሱ ጋር በሰማዕትነት ሞተው የሕይወት አክሊልን ተቀዳጁ፡፡

ከዚህ በኋላ ቅዱስ ጊዮርጊስም በንጉሥ ዱድያኖስና በ፸ ነገሥታት ፊት በቆመ ጊዜ እነርሱ የተቀመጡባቸው የዕንጨት ወንበሮችን ቅዱሱን ‹‹እንዲበቅሉ፣ እንዲአብቡና እንዲአፈሩ ታደርጋቸው ዘንድ ከአንተ እንሻለን›› አሉት፡፡ ቅዱስ ጊዮርጊስም በዚያን ጊዜ ወደ እግዚአብሔር ጸሎት አደረገ፤ ወንበሮቹንም እነርሱም እንዳሉት አደረጋቸው፤ የአምላክን ድንቅ ሥራና ተአምር አይተውም ቍጥር የሌላቸው ብዙ አሕዛብ በጌታችን አመኑ፡፡

ነገሥታቱ ግን ከማመን ይልቅ ቅዱሱን በጐድጓዳ ብረት ምጣድ ውስጥ አበሰሉት፡፡ አቃጥለውና አሳርረውም ሥጋውንና ዐጥንቱን ፈጭተውና አመድ ካደረጉ በኋላ ከረጅም ተራራ ላይ በተኑት፡፡ ሆኖም ጌታችን ኢየሱስ ነፍሱን ወደ ሥጋው መልሷት ደግሞ አስነሣው፡፡ ቅዱስም ጊዮርጊስም ዳግም ተነሥቶ ከነገሥታቱ ፊት በመቆም ተመልሶ በክብር ባለቤት በጌታችን ኢየሱስ ስም ሰበከ፡፡ በዚያም ጊዜ ቍጥር የሌላቸው አሕዛብ አይተው የእግዚአብሔርን ሥራ አደነቁ፤ በጌታችንም አምነው በሰማዕትነት ሞቱ፡፡

ነገሥታቱም ዳግመኛ ማመን አዳግቷቸው እርሱን ሊፈትኑት ‹‹ሙታኖችን ብታሥነሣ አምላክህ ዕውነተኛ አምላክ እንደሆነ እናውቃለን፡፡ በእርሱም እናምናለን›› አሉት፡፡ ቅዱሱም ወደ አምላክ በመጸለይ ከጒድጓድ ውስጥ ወንዶችና ሴቶችን ጐልማሶችንም አስነሣላቸው፤ እነርሱም በሚደንቅ ሥራው በክብር ባለቤት በጌታችን ስም አስተማሩ፤ የገሃነምንም ወሬ ተናገሩ፤ በጥምቀትም ክርስትናን ተቀብለው ዐረፉ፡፡

ከሀድያን ነገሥታት ግን ‹‹ሙታንን ያስነሣህ አይደለም የረቀቁ ሰይጣናትን አሳየህ እንጂ›› ብለው ተከራከሩ፡፡ ከዚያም አንዲት ድኃ ሴት እንድትጠብቀው አደረጉ፤ እርሷም እንጀራ ልትለምንለት በወጣች ጊዜ የእግዚአብሔርም መልአክ ማዕድ አቀረበለት፡፡ በዚህም ጊዜ የድኃዋ ሴት የቤቷ ምሰሶ ላይ ቅርንጫፍን አብቅሎ ታላቅ ዛፍም ሆነ፡፡

እርሷም በተመለሰች ጊዜ ቤቷ የተደረገውን ተአምር አይታ ‹‹የክርስቲያኖች አምላክ ሰው ተመስሎ ወደ እኔ መጣ›› አለች፡፡ ቅዱስ ጊዮርጊስ ግን ‹‹እኔ አምላክ አይደለሁም፡፡ የአምላክ ባሪያ ነኝ እንጂ›› አላት፡፡ እርሷም እንዲህ ብላ ለመነችው፤ ‹‹የአምላክ አገልጋይ ከሆንክ ቸርነትህ እንድትደርሰኝ እለምንሃለሁ፡፡ ዕውር፣ ደንቆሮ፣ ዲዳ፣ ጐባጣ የሆነ ልጅ አለኝና ታድንልኝ ዘንድ እለምንሃለሁ፡፡›› እርሱም ሴቲቱን ስለ ጌታችን እምነትም ካስተማራት በኋላ ልጃ ላይ በመስቀል ምልክት ሲያተብበት አይኑ ማየት ቻለ፡፡ በሌላ ቀንም ቅዱሱም እንዲህ አላት፤ ‹‹እንዲሰማ፣ እንዲናገር፣ እንዲሔድና እንዲአገለግለኝም እኔ እሻለሁ፡፡›› በዚህም ጊዜ ንጉሡ በአገሩ ውስጥ ሲዘዋወር ከመበለቲቱ ቤት ላይ የበቀለውን ዛፍ አይቶ አደነቀ፤ ስለ እርሷም ሲጠይቅ ቅዱስ ጊዮርጊስ የተቀመጠባት የመበለቷ የቤት ምሰሶ ላይ ዛፉ እንደበቀለ ነገሩት፡፡ ንጉሡም ይህን በሰማ ጊዜ ተቆጥቶ ከዚያ ወስዶ አስገረፈው፤ በመንኰራኵርም እንዲያበራዩት ሲያደርግ ቅዱሱ ስለሞተ ከከተማ ውጭ ጣሉት፤ ለሦስተኛ ጊዜም ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከሞት አስነሣው፤ ንጉሡም ከሞት እንደተነሣ ሲመለከት ደነገጠ፤ አደነቀም፡፡

ዳግመኛም ንጉሡ ቅዱስ ጊዮርጊስን በመሸንገል በመንግሥቱ ላይ ምክትል እንደሚያደርገው ዘንድ ቃል ገባለት፤ ቅዱሱ ግን እየዘበተበት ‹‹ነገ በጥዋት ለአማልክቶችህ መሥዋዕትን አቀርባለሁ፤ አንተም ሕዝቡ እንዲሰበሰቡ እዘዝ፤ እኔ ስሠዋ እንዲዩ›› አለው፡፡ ንጉሡም ይህ የተናገረው ነገር ዕውነት መስሎት የሚሠዋ መስሎት ተደስቶ ወደ ቤተ መንግሥቱም እልፍኝ አስገብቶ አሳደረው፡፡

ቅዱስ ጊዮርጊስም ለጸሎት በመነሣት የዳዊትን መዝሙር አነበበ፤ በዚህም ጊዜ የንጉሥ ዱድያኖስ ሚስት ንግሥት እለስክንድርያ ሰምታ ቃሉ ደስ ስላሰኛት የሚያነበውንም እንዲተረጒምላት ለመናቸው፡፡ እርሱም እግዚአብሔር ዓለምን ከፈጠረበት ሰው እስከሆነበት ጊዜ የሆነውን ሁሉ አስተማራት፡፡ ንግሥቷም ትምህርቱም በልቡዋ ስለተቀርጸባት በክብር ባለቤት በጌታችን አመነች፡፡

በማግሥቱም ዐዋጅ ነጋሪ ሀገሩን በመዞር ቅዱስ ጊዮርጊስ ለአማልክት ሲሠዋ ለማየት ሰው ሁሉ እንዲሰበሰብ ለሕዝቡ ነገረ፤ ዐዋጁን የሰማችው ያቺ ድኃ መበለትም ዕውነት መስሏት እጅግ እያዘነች እያለቀሰችም ከልጅዋ ጋር ወጣች፡፡

ቅዱስ ጊዮርጊስም ባያት ጊዜ ፈገግ ብሎ ‹‹ልጅሽን በምድር ላይ አኑሪው›› አላት፡፡ ከዚያም ልጅዋን ጠርቶ ‹‹ወደ አጵሎን ሒድ፤ ወደ እኔም ይመጣ ዘንድ በክብር ባለቤት በጌታዬ ኢየሱስ ስም እዘዘው›› አለው፡፡ በዚያንም ጊዜ ልጁ ድኖ ቅዱስ ጊዮርጊስ እንዳዘዘው ወደ ጣዖቱ ቦታ ሒዶ አዘዘው፡፡ በጣዖቱ ያደረ ያ ርኵስ መንፈስም ከማደሪያው ወጥቶ ቅዱስ ጊዮርጊስ ወደ አለበት መጥቶ ‹‹እኔ ሰውን ሁሉ የማስት እንጂ አምላክ አይደለሁም›› ብሎ በሕዝቡ ሁሉ ፊት አመነ፡፡ ቅዱሱም ትውጠው ዘንድ ምድርን አዘዛትና ወዲያውኑ ዋጠችው፤ ጣዖታቱንም ከአገልጋዮቻቸው ጋራ አጠፋቸው፤ ንጉሡም ከወገኖቹ ጋር ዐፈረ፡፡ (መጽሐፈ ስንክሳር ዘወርኃ ሚያዚያ ፳፫)

ንጉሡም እጅጉን ተበሳጭቶና ተቆጥቶ ንግሥቷ ጋር ገባ፡፡ እርሷም ‹‹አምላካቸው ጽኑዕና ኃያል ነውና ክርስቲያኖችን አትጣላቸው አላልኩህምን›› አለችው፡፡ ንጉሡም ይህንንም ሰምቶ በጣም ተቆጣ፤ ቅዱስ ጊዮርጊስ ሚስቱን ወደ ክርስቲያን እንደቀየራትም አወቀ፡፡ ከዚህም በኋላ ከከተማ ውጭ እንዲጐትቷትና በመጋዝም እንዲሰነጥቋት አዘዘ፡፡ የሰማዕትነት አክሊልንም በመንግሥተ ሰማያት ተቀበለች፡፡

ነገሥታቱም በዚህ ጊዜ አፍረው ደነገጡ፤ ከዚህም የባሳ ኀፍረት እንዳያመጣባቸውም ራሱን በሰይፍ እንዲያቆርጠው ንጉሥ ዱድያኖስን መከሩት፡፡ ንጉሡም ምክራቸውን ሰምቶ የቅዱስ ጊዮርጊስ ራስ እንዲቆረጥ አዘዘ፡፡ በዚህም ጊዜ ቅዱስ እጅግ ደስ አለው፡፡ ጌታችንም እሳትም ከሰማይ አውርዶ ሰባውን ነገሥት እንዲያቃጥላቸው፣ መከራውም ከክርስቲያን ወገን ጸጥ ይል ዘንድ ለመነው፡፡ ወዲያውም እሳት ወርዶ ሰባውን ነገሥታት ከሠራዊታቸው ጋር አቃጠላቸው፡፡

በዚህም ጊዜ የክብር ባለቤት ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለቅዱስ ጊዮርጊስ ተገልጠለትና ብዙ ቃል ኪዳን ሰጠው፡፡ እንዲህ አለው፤ ‹‹በምድር መታሰቢያህን ለሚያደርግ ሁሉ እኔ ኃጢአቱን ሁሉ እደመስሳለሁ፤ በመከራም ውስጥ ሁኖ በባሕርም ሆነ በየብስ ወይም በደዌ በስምህ የሚለምነኝን እኔ ፈጥኜ ከመከራው አድነዋለሁ፡፡›› ከዚህም በኋላ ጌታችን በክብር ወደ ሰማይ ዐረገ፡፡

ቅዱስ ጊዮርጊስም ራሱን ዘንበል አደረገ፤ በሰይፍም ቆረጡት፤ በመንግሥተ ሰማያት አክሊላትን ተቀበለ፡፡ ክርስቲያኖቹም ሥጋውን ወስደው በልብስ ጠቀልለው ወደ ሀገሩ ልዳ ከወሰዱት በኋላ ቤተ ክርስቲያንም ሠርተው በውስጥዋ አኖሩት፤ ከእርሱም ቍጥር የሌላቸው ብዙዎች ድንቆች ተአምራቶች ተገለጡ፡፡

አምላካችን እግዚአብሔር ከቅዱስ ጊዮርጊስም በረከት ያሳትፈን፤ የሰማዕቱም ረድኤት ሁላችን የክርስቲያን ወገኖችን ከሥጋና ከነፍስ መከራ ይጠብቀን፤ ለዘለዓለሙ አሜን!!!

ምንጭ፡- መጽሐፈ ስንክሳር ሚያዚያ ፳፫