ቃና ዘገሊላ

ጥር ፰፤፳፻፲፭ ዓመተ ምሕረት

ቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን በጥር ፲፪ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በቃና ዘገሊላ በተደረገ ሠርግ ቤት ያደረገውን ተአምር በማሰብ በዓልን ታደርጋለች፡፡ ጌታችን ከጥምቀቱ በኋላ በዶኪማስ ሠርግ ቤተ ከእናቱ ቅድስት ድንግል ማርያም እንዲሁም ከደቀ መዛሙርቱ ጋር ታጋብዞ በነበረበት ጊዜ ለእንግዶች ወይን ጠጅ አለቀባቸው፡፡

በዚህም ጊዜ “እናቱ ጌታችን ኢየሱስን የወይን ጠጅ እኮ የላቸውም” አለችው፡፡ ጌታችን ኢየሱም “ አንቺ ሆይ ካንቺ ጋር ምን አለኝ? ጊዜዬ ገና አልደረሰም” አላት፡፡ እናቱም ለአሳላፊዎቹ “የሚላችሁን ሁሉ አድርጉ” አለቻቸው፡፡ በዚይም እንደ አይሁድ ልማድ የሚያነጹባቸው ስድስት የድንጋይ ጋኖች ነበሩ፡፡ ከእነርሱም እያንዳንዱ ሁለት ወይም ሦስት እንስራ ይይዙ ነበር፡፡ ጌታችን ኢየሱስም “ጋኖቹን ውኃ ሙሉአቸው” አላቸው፤ እስከ አፋቸውም እስከ ላይ ሞሉአቸው፡፡ አሁንም ቅዱና ወስደውም ሰጡት፡፡ አሳዳሪውም ያን የወይን ጠጅ የሆነውን ውኃ ቀምሶ አደነቀ፤ ከወዴት እንደመጣም አላወቀም፤ የቀዱት አሳላፊዎች ግን የወይን ጠጅ የሆነውን ያን ውኃ ያውቁ ነበር፡፡ ውኃውን የሞሉ እነርሴ ነበሩና፡፡ አሳዳሪውም ሙሽራውን ጠርቶ “ሰው ሁሉ መልካሙን የወይን ጠጅ አስቀድሞ ያጠጣል፤ ከጠገቡ በኋላም ተርታውንም ያመጣል፤ አንተ ግን መልካሙን የወይን ጠጅ እስከአሁን አቆየህ” አለው፡፡ ጌታችን ኢየሱስም በቃና ዘገሊላ ያደረገው የተአምራት መጀመሪያ ይህ ነው፤ ክብሩንም ገለጠ፤ ደቀ መዛሙርትም አመኑበት፡፡ (ዮሐ.፪፥፩-፲፩)

ከበዓሉ በረከት ያሳትፈን፤ አሜን፡፡