ዓለመ ሰማይ

ጥቅምት ፲ ቀን ፳፻፲፭ ዓመተ ምሕረት

በዓለመ ሰማይ እግዚአብሔር አምላክ ፍጥረቱን መፍጠር በጀመረበት በመጀመሪያው ቀን እሑድ አስቀድሞ የተፈጠሩት ሰባቱ ሰማያትና መላእክት ናቸው፡፡ ሰማያቱም እንደ ስያሜያቸው የራሳቸው ትርጓሜ አላቸው፡፡

፩. ጽርሐ አርያም

ከሰባቱ ሰማያት የመጀመሪያ የሆነና ለሰማያት የመጨረሻ ክፍል ሲሆን ከላይ ወደታች ሲቆጠር የመጀመሪያ ደረጃ ያለው ነው። እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም በጽርሐ አርያም እንደምትመሰል ሊቃውንቱ በሌሊት ሰዓታት ላይ እየዘመሩ ያመሰግኗታል፡፡ እርሷ የአምላካችን እግዚአብሔር ማደሪያ (ሀገር) ናትና፡፡

፪. መንበረ መንግሥት 

እግዚአብሔር በወደደው መጠን ለወዳጆቹ የሚገለጥበት፣ የክብሩ ዙፋን የተዘረጋበት፣ ቅዱሳን መላእክት በፊቱ እየሰገዱ ምስጋና የሚያቀርቡበት፣ የሞቱ ሰዎች ነፍሳቸው ሰግዳ ፍርድ የምትቀበልበት ነው። (ኢሳ.፮፥፩፣ ሕዝ.፩፥፳፪-፳፯፣ራእ.፬ ፥፪)

፫. ሰማይ ውዱድ 

በዐራቱ መዐዝን ቁመው ዙፋኑን የተሸከሙ አርባዕቱ እንስሳ (የሰው፣ የላም፣ የንሥር፣ የአንበሳ) ምስል ያላቸውና ዘወትር ዙፋኑን የሚያጥኑ ፳፬ ካህናተ ሰማይ ያሉበት የሰማይ ክፍል ነው። (ሕዝ.፩፥፬-፸፭፣ራእ.፬፥፬)

፬. ኢየሩሳሌም ሰማያዊት (መንግሥተ ሰማያት) 

በመጀመሪያ ሳጥናኤል (ዲያብሎስ) የነበረባት ሰማይ ኢየሩሳሌም ሰማያዊት ናት፤ አምላኩን ሳይክድና ከክብሩ ሳይዋረድ በፊት በዚህች ሰማይ ይኖር እንደነበር ቅዱሳት መጻሕፍት ይጠቅሳሉ፡፡ በምጽአት ቀን ደግሞ ጻድቃን ከጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ፍርድ በኋላ የሚወርሷት ርስታቸው ናት። (ገላ.፬፥፳፮፣ዕብ.፲፪፥ ፳፪፣ዮሐ.፲፬፥፪)

፭. ኢዮር

እግዚአብሔር ቅዱሳን መላእክት ከፈጠራቸው በኋላ በነገድ ፻ በአለቃ ፲ አድርጎ በሦስቱ ሰማያት አስፍሯቸዋል፡፡ ኢዮርን በዐራት፣ ራማን በሦስት፣ ኤረርንም በሦስት ከፍሎ ነው በዐሥሩ ከተማ ያሰፈራቸው፡፡

በዚህም መሠረት ኢዮርን ላይና ታች አድርጎ በዐራት ከተማ ከፍሏታል፡፡ በእርሷ ያሉትን መላእክትን በ፵ ነገድ ዐራት አለቃ አድርጎ ከፈላቸው፡፡ የመጀመሪያው ነገድ ‹‹አጋእዝት›› ይባላሉ፡፡ አለቃቸው ሣጥናኤል ነበር፤ እርሱም የመላእክትን ሁሉ ጸሎት ወደ እግዚአብሔር ያሳርግ ነበር፡፡ ከክብሩ ሲዋረድ ቅዱስ ሚካኤል በምትኩ ተሹሞበታል፡፡

ሁለተኛው ነገድ ‹‹ኪሩቤል›› ይባላሉ፡፡ እነርሱም መንበረ ሥላሴን ይሸከማሉ፡፡ የቀሳውስት አምሳል ናቸው፡፡ አለዎቻቸው ገጸ ሰብና ገጸ አንበስ ናቸው፡፡ በሦስተኛው ከተማ በኢዮር ያሉት ሱራፌል ይባላሉ፡፡ የዲያቆናት አምሳል ናቸው፡፡ በትንቢተ ኢሳያስ በምዕራፍ ስድስት ላይ የተገለጹትና ኢሳያስን ከለምጹ እንዲፈወስ ያደረጉት ናቸው፤ አመቆቻቸው ገጸ ላህምና ገጸ ንስር ናቸው፡፡

በነገራችን ላይ ‹‹ከሩቤል›› ወይም ‹‹ሱራፌል›› የሚባሉ የግለሰብ መጠሪያ ስሞች ስሕተት ናቸው፡፡ አንደኛ እነዚህ ስሞች የብዙ መላእክት መጠሪያን የሚወክሉ ናቸው፡፡ ለአንዱ ሲሆን ‹‹ኪሩብ፣ ሱራፊ› ይባላል፡፡ ‹‹ከሩቤል›› ወይም ‹‹ሱራፌል›› ማለት ግን የብዙ ቁጥራቸው መጠሪያ ነው፡፡ ሁለተኛውም ምክንያት ደግሞ የእግዚአብሔርንም ሆነ የቅዱሳን መላእክትን ስም እንዳለ በቁሙ ወስዶ ለግል መጠሪያ ስም ማዋል ተገቢ አይደለም፡፡ ‹‹ወለተ ሚካኤል፣ ክብፈ ገብርኤል….›› እየተባሉ ይሰየማሉ እንጂ ቀጥታ ሚካኤል ገብርኤል እያሉ ሰዎችን መሰየም ስሕተት ነው፡፡

ዐራኛው ከተማ በኢዮር ያሉት ኃይላት ይባላሉ፡፡ የእሳት ሰይፍ ይዘው በሥሉስ ቅዱስ ፊት የሚቆሙ ናቸው፡፡ በመንፈሳዊ ሕይወት የዛሉና የደከሙ ክርስቲያኖችን የሚያበረታቱ ናቸው፡፡ አለቃቸውም ቅዱስ ሚካኤል ነው፡፡

፮. ራማ

እግዚአብሔር በራማ ያሉትን መላእክት በ፴ ነገድ በሦስት አለቃ አድርጎ ከፈላቸው፡፡ የመጀመሪያዎቹ ‹‹አርባብ›› ይባላሉ፡፡ የሥላሴ እልፍኝ አስከልካዮች ናቸው፡፡ የእግዚአብሔርን መንበር በክንፎቻቸው ይሸፍናሉ፡፡ አለቃቸው ቅዱስ ገብርኤል ነው፡፡ ሁለተኞቹ በራማ ከተማ ያሉት ‹‹መናብርት›› ይባላሉ፡፡ ለእግዚአብሔርን እጅግ ቅርብ የሆኑ ናቸው፡፡ የመብረቅ ጋሻቸውን የእሳት ጦራቸውን ይዘው የሥላሴ ጋሻ ጃግሬዎች ሆነው በተጠንቀቅ ይቆማሉ፡፡ የሰውን ችግር ለእግዚአብሔር ያቀርባሉ፡፡ (መዝ.፹፰፥፮) አለቃቸው ቅዱስ ሩፋኤል ነው፡፡

ሦስተኞቹ በራማ ከተማ ያሉት ‹‹ሥልጣናት›› ይባላሉ፡፡ መላውን ፍጥረት ለመጠበቅ ሥልጣን የተሰጣቸውና የምጽአት ዕለት አዋጅ ነጋሪዎች ናቸው፡፡ (ዳን. ፲፪፥፩) አለቃቸው ቅዱስ ሱርያል ነው፡፡

፯. ኤረር

እግዚአብሔር በኤረር ያሉትን መላእክት በ፴ ነገድ በሦስት አለቃ አድርጎ ከፈላቸው፡፡ የመጀመሪያዎቹ ‹‹መኳንንት›› ይባላሉ፡፡ የስላሴ የእሳት ባለ ቀስት ናቸው፡፡ የሰው ልጅ ልዩ ጠባቂዎች ናቸው፤ በተለይ በአደጋ ጊዜ ሎጥን እንዳዳኑት ፈጥነው ይደርሳሉ፡፡ በዕለተ ምጽዓት የሰውን ሁሉ ዐፅም ሰብስበው ለትንሣኤ ዘጉባኤ ያበቃሉ፡፡ አለቃቸው ቅዱስ ሰዳካኤል ነው፡፡

ሁለተኛዎቹ ‹‹ሊቃናት›› ይላሉ፡፡ የሥላሴ የእሳት ፈረሶች ናቸው፡፡ በእሳት ፈረስ ይመላለሳሉ፡፡ እነዚህም ፳፬ቱ ካህናተ ሰማይ ሲሆኑ አለቃቸው ቅዱስ ሰላታኤል ነው፡፡ በኤረር ከተማ የሰፈሩት ሦስተኛዎቹ ‹‹መላእክት›› ይባላሉ፡፡ ፍጥረትን ሁሉ የሚጠብቁ ናቸው፡፡ አለቃቸው ቅዱስ አናንኤል ነው፡፡ በእነዚህ የማይጠበቅ ፍጥረት የለም፤ ከአዝርእት ጀምሮ ሁሉን ይጠብቃሉ፡፡

ሦስቱም የመላእክት ዓለማት (መኖሪያዎች) ሲሆኑ ከዳግም ምጽአት በኋላ ወዳለመኖር ሲያልፉ ቅዱሳን መላእክት ከጻድቃን ጋር በመንግሥተ ሰማያት ይጠቃለላሉ (ይኖራሉ)። (ማቴ. ፳፪፥፴) ከሰባቱ ሰማያት ቀጥሎ ያለውና ምጽዓት የሚባለው የሰባቱ ሰማያት መሠረት ነው። እነዚህን ሰማያት በሃይማኖት እንጅ ዛሬ በሥጋ ዓይን ልናያቸው አንችልም። በሰማያት ይቅርና በዓለማችን ያሉ በዓይናችን የማናያቸው ብዙ ጥቃቅን ነገሮች መኖራቸው ይታወቃል። ቁሳዊ አስተሳሰብ ላላቸው ሰዎች ይህ ምሥጢር ይከብዳቸል፤ የሃይማኖት ሰዎች ግን ሁሉንም ሳይጠራጠሩ በሃይማኖት እውነት ነው ብለው ይቀበላሉ። ሃይማኖት ለብዙ እንቆቅልሾች መልስ ስለሚሰጥ ለሚያምኑ ሰዎች ታላቅ እፎይታ ነው።

ቅዱስ ዮሐንስ በራእዩ ‹‹በእግዚአብሔር ፊት የሚቆሙ ሰባት መላእክትን አየሁ›› እንዳለ ሊቃነ መላእክት በቁጥር ሰባት ናቸው፡፡ (ራእ.፰፥፪) እነርሱም፡- ፩) ቅዱስ ሚካኤል፣ ፪) ቅዱስ ገብርኤል፣ ፫) ቅዱስ ሩፋኤል፣ ፬) ቅዱስ ራጉኤል፣ ፭) ቅዱስ ዑራኤል፣ ፮) ቅዱስ ፋኑኤል እና ፯) ቅዱስ አፍኒን ናቸው፡፡

ቅዱሳን መላእክት 

መልአክ የሚለው ቃል ተመልአከ፤ አለቃ ሆነ ካለው የግእዝ ግሥ የተገኘ ነው፤ ቅዱሳን መላእክት እግዚአብሔርን እያመሰገኑ ክብሩን ወርሰው ለመኖር የተመረጡና የተሾሙ መሆናችውን በዚህ ቃል እንረዳለን፡፡ በተመሳሳይም ለአከ፤ ላከ ካለው ግሥ የተገኘ ሲሆን ቅዱሳን መላእክት የእግዚአብሔር መልእክተኞች መሆናቸውን ይገልጻል።

እግዚአብሔር አምላክ መላእክትን የፈጠራቸው በመጀመሪያው ቀን እሑድ ከእሳትና ከነፋስ ነው። ረቂቅነታቸውንና ለአገልግሎት ፈጣን መሆናቸውን በዚህ የተገለጠ ሆኗል። መናፍስትም ስለሆኑ በዓይን አይታዩም። (መዝ.፻፫፥፬ እና ዕብ.፩፥፯) መላእክት የሥጋ ባሕርይ ስሌላቸው አይሞቱም፤ ፆታም የላቸውም፤ ሆኖም  በወንድ ፆታ ይጠራሉ። የመላእክት አገልግሎት ያለ ዕረፍት እግዚአብሔርን ማመስገን ነው። (መዝ.፻፵፰፥፪፤ ኢሳ.፮፥፫)  ከእግዚአብሔር ወደ ሰዎች ይላካሉ። (ሉቃ.፩፥፲፩፤ ሐዋ.፲፥፫፤ዘፍ. ፲፱፥፩) የሰዎችን ጸሎት ያሳርጋሉ። (ዘካ.፩ ፥፲፬፤ራእ. ፰፥፫) የእግዚአበሔርን ወዳጆች ይጠብቃሉ። (መዝ.፺፥፲፩፤ ፪ኛነገ.፲፱፥፴፭)

ቅዱሳን መላእክት ከብዛታቸው የተነሣ ቁጥራቸው አይታወቅም፤ አይወሰንም። በመቶ ነገድ የተከፋፈሉ ሲሆኑ ለየነገዱ አለቃ አለው። ሳጥናኤል ከክብሩ ሳይዋረድ ለመጀመሪያው ነገድ አለቃ ነበረ።  የመጀመሪያ የክብር ስሙ ሳጥናኤል ነው። ሲክድ ስሙም ተወሰደበትና ‹‹ዲያብሎስ (ፈታዌ፤ አምላክና አምላክነትን ፈላጊ ፣ ዖፍ ሰራሪ፤ ለማሳት የሚፋጠን በራሪ ወፍ፣ ጋኔን፤ ዕቡይ፣ ትዕቢተኛ፣ ውዱቅ፤ የተጣለ፣ ሰይጣን፤ ባለጋራ፣ ከሳሽ) የሚባሉና ግብሩን የሚገልጹ ስሞች ተሰጡት፡፡››

ፈጣሪያችን እግዚአብሔር መላእክትን ፈጥሮ በተሰወራቸው ጊዜ አእምሯቸው ጠያቂ አገናዛቢ ስለሆነ ‹‹ማን ፈጠረን? ከየት መጣን?›› እያሉ እርስ በእርሳቸው ሲጠያየቁ በቦታና በመዓርግ ታላቅ የነበረው ሳጥናኤል ማንም ሳያሳስተውና ሳይመክረው ሐሰትን ለመጀመሪያ ጊዜ ከልቡ (ከአእምሮው) አንቅቶ ‹‹እኔ ፈጠኋችሁ›› ብሎ በድፍረት ተናገረ። (ዮሐ. ፰፥ ፵፬)። በዚህ ጊዜ ቅዱስ ገብርኤል ‹‹ንቁም በበኅላዌነ እስከንረክቦ ለአምላክነ፤ የፈጠረን አምላካችንን እስክናገኘው (እስኪገለጥልን) ድረስ በያለንበት እንጽና›› በማለት ብሎ ባረጋጋቸው ጊዜ በመላእክት መካከል መለያየት ተፈጠረ፤ ይህም ዲያብሎስ በመላእክት መካከል የዘራው የመጀመሪያ መከፋፈል ነው። (ማቴ.፲፫፥፳፰) በዚህ ጊዜ እግዚአብሔር ‹‹ብርሃን ይሁን›› ብሎ ብርሃንን ፈጠረ። (ዘፍ.፩፥፫)

ብርሃን በተፈጠረ ጊዜ ሳጥናኤል ምንም መፍጠር የማይችል የሐሰተኛ አምላክ መሆኑ ተገለጠበት። በስሕተቱም ተፀፅቶ ሊመለስ ስላልቻለ ቅዱሳን መላእክት በሰልፍ (በጦርነት) ተዋግተው መዓርጉ ተነጥቆ ከነበረበት የክብር ቦታ ከመንግሥተ ሰማያት ከነሠራዊቱ (ከነተከታዮቹ) ወደ ጥልቁ ተጥሏል። (ራእ.፲፪፥፮፤ኢሳ .፲፬ ፥፲፤ይሁ.፩፥፲፫)

ይቆየን!

ምንጭ፡- መጽሐፈ ቀሌምንጦስ በገብረ ዮሐንስ ገብረ ማርያም እና ‹‹መላእክት›› በዲያቆን አቤል ካሣሁን፣ ፳፻፱ ቅዳሴ ሠለስቱ ምዕት ትርጓሜ››