ወንጌላዊው ቅዱስ ሉቃስ

ጥቅምት ፳፪ ቀን ፳፻፲፭ ዓመተ ምሕረት

በሀገረ አንጾኪያ ከአሕዛብ ወገን የተለወደው አይሁዳዊው ሉቃስ ከሰባ ሁለቱ አርድእት የተቆጠረ ባለ መድኃኒትና ወንጌልን የጻፈ ቅዱስ ሐዋርያ ነው፡፡ ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን በወንጌል ትርጓሜያቸው ስሙ ‹ዓቃቤ ሥራይ› ወይም ‹ባለ መድኃኒት› የሚል ትርጉም በውስጡ የያዘ መሆኑን ያስረዳሉ፡፡ በላቲን ቋንቋ ‹ሉካስ› ማለት ‹ብርሃናማ፣ ብርሃን የያዘ› ማለት ነው፡፡ መጽሐፈ ስንክሳር ደግሞ ብልህና ጥበበኛ በማለት ይገልጸዋል፡፡

ቅዱስ ሉቃስ የሚመሰለው በገጸ ላህም ነው፡፡ ‹‹ፍሪዳ አምጡና እረዱ፤ ከእርሱ ጋር እየበላን ደስ ይበለን›› እያለ ምሳሌውን ይጽፋልና፡፡ (ሉቃ.፲፭፥፳፫) በጤግሮስም ይመሰላል፤ ጤግሮስ ፈለገ መዓር ወይም የመዓር ወንዝ ነው፤ ርስትነቱም ጸዊረ ነገር (ምሥጢር መሸከም) የሚቻላቸው ሰዎች ርስት ነው፡፡

ቅዱስ ሉቃስ በአቴና ሀገር በእስክንድሪያ ሕክምናን አጥንቷል፤ የሥነ ሥዕልም ችሎታ ነበረው፤ ይህን የሥዕል ችሎታውንም በወንጌሉና በሐዋርያት ሥራ መጻሕፍቱ ላይ በሥዕላዊ መልክ ገልጾታል፡፡ የቤተ ክርስቲያን ትውፊት እንደሚናገረው እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ልጇን አቅፋ (ምስለ ፍቁር ወልዳ) ለመጀመርያ ጊዜ የሣለው እርሱ ነው፡፡ ሥዕሎቹም በኢትዮጵያ በተድባባ ማርያም፣ በደብረ ዘመዶ፣ በዋሸራና በጀብላ ይገኛሉ፡፡ ተመሳሳዩም በስፔን ቅድስት ማርያም ካቴድራል እንደሚገኝ ይነገራል፡፡ አባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫ በሰዓታት ምስጋናው ‹‹ከወንጌላውያን አንዱ የሆነው ጠቢቡ ሉቃስ ለሣላት ሥዕልሽ ሰላምታ ይገባል›› በማለት አመስግኗል፡፡

ቅዱስ ሉቃስ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከመረጠው በኋላ የቅዱስ ጳውሎስ ደቀ መዝሙር በመሆን አገልግሏል፡፡ ቀድሞ ዓቃቤ ሥራይ ዘሥጋ (ሥጋዊ ሐኪም) ቢሆንም በኋላ ግን ዓቃቤ ሥራይ ዘነፍስ (መንፈሳዊ ሐኪም) እንደሆነ ሊቃውንቱ ይናገራሉ፡፡ ቅዱስ ጳውሎስ ስለ እርሱ ሲመሰክር ‹‹የተወደደው ባለ መድኃኒቱ ሉቃስ ዴማስም ሰላምታ ያቀርቡላችኋል›› በማለት ገልጦታል፡፡ (ቆላ.፬፥፲፬) ቅዱስ ሉቃስ ተንሣኢ (ፈጣን) እየተባለም የሚጠራው ለስብከተ ወንጌል ስለሚፋጠን ነበር፤ በወንጌሉም አጻጻፍ ላይ ስለ ሕመማቸውና ድኅነት ስለሚያገኙበት ሁኔታ ገልጦ ጽፏል፤ ለዚህም ምሳሌ የሚሆኑት ታሪኮች የደጉ ሳሚራዊና ደም ይፈሳት ስለነበረችው ሴት ናቸው፡፡ (ሉቃ.፲፥፴‐፴፭፤፰፥፵፫) ሐዋርያው መበሥር ወይም ብሥራት ነጋሪ እየተባለም ይጠራል፤ ይህም ብሥራተ መልአክን ጽፏልና ነው፡፡ (ሉቃ.፩፥፩)
የቅዱስ ሉቃስ ወንጌል የተጻፈው በሀገር አኪይያ (ሮም) በጽርዕ (ግሪክ) ቋንቋ ነው፤ የሉቃስ ወንጌል ‹የአሕዛብ ወንጌል›፣ ‹ሰባኬ መንፈስ ቅዱስ›፣ ‹ሰባኬ ጸሎት›፣ ወንጌለ አንስት ተብሎም ይጠራል፡፡

፩. ‹የአሕዛብ ወንጌል› እየተባለ የሚጠራው ወንጌሉ የተጻፈው ለአሕዛብ በመሆኑ ነው፡፡

፪. ሰባኬ መንፈስ ቅዱስ የሚባለው ስለ መንፈስ ቅዱስ ደጋግሞ ስለሚናገር ነው፡፡

፫. ሰባኬ ጸሎት የተባለው ከሌሎች ወንጌላት የበለጠ ደጋግሞ የጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስን እና እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያምን ጸሎት ጽፏልና ነው፡፡

፬. ወንጌለ አንስት የሚባለው ስለ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም፣ ስለ ቅድስት ኤልሳቤጥ፣ ስለ ማርያም እንተ እፍረት፣ ስለ ናይን እና ወዘተ በስፋት ስለሚናገር ነው፡፡

ወንጌሉን ከመጻፉ አስቀድሞም ቅዱስ ሉቃስ የቅዱስ ጳውሎስ ደቀ መዝሙር ከመሆኑ በፊት የቅዱስ ዮሐንስ ደቀ መዝሙር እንደነበረ ትርጓሜ ወንጌል ላይ ተጽፎ ይገኛል፡፡ በአንጾኪያ ሀገር ቅዱስ ጳውሎስን ካገኘው በኋላም ሊቀ ሐዋርያው ሰማዕት እስከሆነበት ድረስ አገልግሎታል፡፡ ከሐዋርያው ቅዱስ ዮሐንስ ጋርም በነበረበት ጊዜም መቄዶንያ የምትባል ሀገር ከፍሎ እንዲስተምር እንደሰጠው በወንጌል ትርጓሜ ተገልዿል፡፡ ቅዱስ ሉቃስም በዚያ ሀገር ከጌታችን ኢየሱስ መፀነስ ጀምሮ፣ መዋዕለ ስብከቱን፣ የሠራውን ትሩፋትና ገቢረ ተአምሩን በሙሉ ለአሕዛቡ በነገራቸው ጊዜ ከኃጢያት ወደ ጽድቅ፣ ከአምልኮ ጣዖት ወደ አምልኮ እግዚአብሔር ተመለሰው በማመን የክርስትና ጥምቀት ተጠምቀዋል፡፡ ለስብከት በሚጓዝበትም ወቅት ትምህርት ባልተዳረሰባቸው ስፍራ ሲያስተምር አንድ ታዖፊላ የተባለ የእስክንድርያ መኮንን ስብከቱን አድምጦ በማመን ‹ዜና ሐዋርያትን› (ገድለ ሐዋርያትን) እንዲጽፍለት በጠየቀው መሠረት ጽፎለታል፡፡ በዚህም ቅዱስ ሉቃስ የጻፋቸው መጻሕፍት ከወንጌሉና ከሐዋርያት ሥራ ጋር ሦስት ናቸው፡፡

ቅዱስ ሉቃስ የሕይወት ታሪኩ እንደሚገለጸው በድንግልና የኖረ ሐዋርያ ነው፤ ሐዋርያዊ አገልግሎቱንም የፈጸመው በአብዛኛው በግሪክ ነበር፡፡ ሐዋርያቱ ቅዱስ ጴጥሮስና ቅዱስ ጳውሎስ ካረፉ በኋላም በሮም ሀገር ማስተምር ቀጠለ፤ በቀናች ሃይማኖትም ይጸኑ ዘንድ ለምእመናን መልእክትን ይጽፍ ነበር፤ ስለዚህም ጣዖት አምላኪዎች ከአይሁድ ጋር በመስማማት በአንድ ምክር ሆነው በንጉሥ ኔሮን ፊት በመቆም ስለ ሐዋርያው ሉቃስ እንዲህ ብለው ተናገሩ፤ ‹‹ይህ ሉቃስ በሥራይ ብዙ ሰዎችን ወደ ትምህርቱ አስገባቸው፡፡›› ንጉሥ ኔሮንም ወደ ፍርድ ዐደባባይ ሉቃስን እንዲያቀርቡት ባዘዘ ጊዜ ሐዋርያው ሉቃስ ዕረፍቱ እንደ ደረሰ በመንፈስ ቅዱስ ዐውቆ ወደ ባሕር ዳርቻ ሄደ፡፡ በዚያም ዓሣ የሚያጠምድ አንድ ሽማግሌ ሰው አግኝቶ መጻሕፍቱንና ደብዳቤዎችን እንደሰጠውና ‹‹ወደ እግዚአብሔር መንገድ መርተው ያደርሱሀልና እነዚህን መጻሕፍት ጠብቃቸው›› በማለት እንደገነገረው መጽሐፈ ስንክሳር ይጠቅሳል፡፡

ከዚህም በኋላ በንጉሥ ኔሮን ፊትም ቀርቦ በቆመ ጊዜ ንጉሡ ‹‹በሥራይህ ሕዝቡን የምታስት እስከ መቼ ነው?›› ብሎ ጠየቀው፤ ቅዱስ ሉቃስም ‹‹እኔ ለሕያው እግዚአብሔር ልጅ ለጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሐዋርያ ነኝ እንጂ ሥራየኛ አይደለሁም›› ብሎ መለሰለት፡፡ ንጉሥ ኔሮንም ሁለተኛ እንዲህ አለው፤ ‹‹እየጻፈች ሰዎችን የምታስት ይህች እጅህን እኔ እቆርጣታለሁ፤›› ይህንንም ብሎ የቀኝ እጁን እንዲቆርጡት አዘዘ፡፡ በቆረጡትም ጊዜ ‹‹ንጉሥ ሆይ እኛ የዚህን ዓለም ሞት እንደማንፈራ ዕወቅ፤ ነገር ግን የጌታዬና የፈጣሪዬን ኃይሉን ታውቅ ዘንድ አሳይሃለሁ፤›› ይህንንም ብሎ የተቆረጠች የቀኝ እጁን በግራ እጁ አንሥቶ ከተቆረጠችበት ቦታዋ ላይ አገናኝቶ እንደ ቀድሞዋ ደኅነኛ አደረጋት፤ ከዚህም በኋላ ለያት፤ በዚያም የነበሩ አደነቁ፤ የሠራዊቱም አለቃና ሚስቱ ብዙዎችም ሰዎች ክብር ይግባውና በጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ አመኑ፤ ቁጥራቸውም ዐራት መቶ ሰባ ሰባት ነፍስ ሆነ፡፡ ንጉሡም ከቅዱስ ሉቃስ ጋር ራሶቻቸውን እንዲቆርጡ በማዘዙ ቆረጡአቸው፤ የምስክርነት አክሊልም በመንግሥተ ሰማያት ተቀበሉ፡፡ ቅዱስ ሉቃስ ያረፈው በ፹፬ ዓመቱ ነው፡፡

ከዚህም በኋላ ሥጋውን በማቅ አይበት ውስጥ አድርገው ወደ ባሕር ጣሉት፡፡ በእግዚአብሔር ፈቃድ ወደ አንድ ደሴት ደረሰ ምእመናንም አግኝተው ወስደው ገነዙት፤ በአማረ ቦታም አኖሩት፡፡

የወንጌላዊው ቅዱስ ሉቃስ አማላጅነት፣ ተረዳኢነትና በረከት አይለየን፤ አሜን!