ነሐሴ 12 ቀን 2004 ዓ.ም.
እንዳለ ደምስስ
መካነ ድራችን በግልጥ ባልታወቀ ምክንያት የሲስተም ችግር ገጥሞት ስለነበር መረጃዎችን በወቅቱ ማድረስ ባለመቻላችን ይቅርታ እንጠይቃለን፡፡
የብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ ፖትርያርክ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት የዓለም አብያተ ክርስቲያናት ምክር ቤት ፕሬዚዳንት፣ የዓለም ሃይማኖቶች ለሰላም የክብር ፕሬዚዳንት ሥርዓተ ቀብር በማስመልከት ቅዱስ ሲኖዶስ መግለጫ ሰጠ፡፡
መግለጫውን የሰጡት ብፁዕ አቡነ ሕዝቅኤል የቅዱስ ሲኖዶስ ጽ/ቤት ዋና ጸሓፊ፣ የከፋ ቤንችና ማጂ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ሲሆኑ
በመግለጫቸውም “ቅዱስነታቸው ሐሙስ ነሐሴ 10 ቀን 2004 ዓ.ም. ከንጋቱ 11፡00 ሰዓት ከዚህ ዓለም በሞተ ሥጋ መለየታቸውን በዕለቱ መግለጻችን ይታወቃል፡፡ በቀጣይነትም የቅዱስነታቸውን የቀብር ሥነ ሥርዓት አፈጻጸም ጊዜና ቦታ በተከታታይ የሚገለጽ መሆኑን በሰጠነው ማሳሰቢያ መሠረት የቀብር ሥነሥርዓቱ ሐሙስ ነሐሴ 17 ቀን 2004 ዓ.ም. በመንበረ ጸባዖት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል እንደሚፈጸም የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ ወስኗል፡፡ እስከዚያው ድረስ ምእመናንና ምእመናት በመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት ጽ/ቤት ስብከተ ወንጌል አዳራሽ በመገኘት ሃዘናቸውን መግለጽ የሚችሉ መሆኑን እንገልጻለን” ብለዋል፡፡
ስለ አሟሟታቸው ማብራሪያ እንዲሰጡ ከጋዜጠኞች ለቀረበላቸው ጥያቄም ቅዱስነታቸው ሱባኤውን ሳያቋርጡ እሑድ ቀድሰው ሰኞና ማክሰኞም ቅዳሴውን እየመሩ መገኘታቸውንና ከሰዓት በኋላ ህመም ስለተሰማቸወ ወደ ሕክምና መሔዳቸውን የገለጹ ሲሆን እረፍት እንዲያደርጉ በሐኪም ከተነገራቸው በኋላ በዚያው የእግዚአብሔር ጥሪ ሆኖ ሌሊት 11፡00 ሰዓት ላይ ማረፋቸውን ገልጸዋል፡፡ በተጨማሪም ስለ ቅዱስነታቸው ሕመም ሲያብራሩ “ብዙ ታመው ቤት አልዋሉም፡፡ ሥራም አላቋረጡም፣ ያልታሰበ ነገር ስለነበር በሞታቸው በጣም ተደናግጠናል፡፡ ሕመማቸው የስኳር ሕመም ጠንቅ ነው፡፡ ቀዶ ጥገናም አልተደገላቸውም በትናንትናው ዕለት እኔ ነኝ አጥቤ የገነዝኳቸው፡፡” በማለት ምላሽ ሰጥተዋል፡፡