በዓለ ደብረ ታቦር
በዲ/ን ደረሰ ተሾመ
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ለሐዋርያዊ ተልእኮዋ ስኬትና ለምእመናን መንፈሳዊ ዕድገት የሚጠቅሙ፣ ከጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የማዳን ሥራ ጋር የተያያዙ ዘጠኝ ዓበይት በዓላትን በከፍተኛ መንፈሳዊ ሥርዓት ታከብራለች። ከነዚህ ዓበይት በዓላት መካከል በየዓመቱ ነሐሴ 13 ቀን የሚከበረው የደብረ ታቦር በዓል አንዱ ነው።
ይህ በዓል አምላካችን ኢየሱስ ክርስቶስ በታቦር ተራራ ላይ ብርሃነ መለኮቱንና ክብረ መንግሥቱን የገለጠበት፣ አምላክ ሰው የመሆኑ (የነገረ ተዋሕዶ) ፍጹምነት በግልጽ የታየበት፣ የነቢያትና የሐዋርያት ምስክርነት የተረጋገጠበት ዕለት ነው። በባሕላዊ ገጽታው «ቡሄ» በመባል የሚታወቀው ይህ በዓል፣ መንፈሳዊ ምሥጢሩን ከኢትዮጵያውያን ማኅበራዊና ባሕላዊ ትውፊት ጋር አስተሳስሮ የያዘ ታላቅ ሃይማኖታዊ ክብረ በዓል ነው።
፩. የደብረ ታቦር ተራራ ታሪካዊና መጽሐፍ ቅዱሳዊ መሠረት
«ደብረ ታቦር» የሚለው ስም «ደብር» (ተራራ) እና «ታቦር» (በገሊላ አውራጃ የሚገኝ የረጅም ተራራ ስም) ከሚሉ ሁለት ቃላት የተዋቀረ ነው። ተራራው ከገሊላ ባሕር በምዕራብ በኩል 10 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የሚገኝ ሲሆን፣ ከባሕር ጠለል በላይ 575 ሜትር (1,886 ጫማ) ያህል ከፍታ አለው።
በብሉይ ኪዳን ታሪክ፦
የትንቢት መፈጸሚያ፦ ልበ አምላክ ክቡር ዳዊት «ታቦርና አርሞንኤም በስምህ ደስ ይላቸዋል» (መዝ. 88፥12) በማለት አስቀድሞ የተናገረው ትንቢት ጌታችን ብርሃነ መለኮቱን ሲገልጥ ተፈጽሟል።
የመዳንና የድል አምባ፦ በዘመነ መሳፍንት ነቢይት ዲቦራ እና ባርቅ የከነዓናውያኑን መሪ ሲሳራን ከነሠራዊቱ ድል ያደረጉበት ስፍራ ነው (መሳ. 4፥6)። በምሥጢሩ ባርቅ የጌታችን፣ ሲሳራ ደግሞ የአጋንንት ምሳሌ ሲሆኑ፤ ጌታችን በደብረ ታቦር ክብሩን በመግለጥ አጋንንትን ድል የማድረጉ ምሳሌ ነበር።
የአበው ድንቅ ቦታ፦ ነቢዩ ሳሙኤል ትንቢት ተናግሮበታል፣ ንጉሥ ሳኦል ከሦስት ሰዎች ጋር ተገኝቶበታል (1ኛ ሳሙ. 10፥3)። አበው አብርሃምና ኖኅ ቀስተ ደመና ተተክሎ ያዩበት ሲሆን፣ አባታችን ኖኅ «መካነ ብርሃን» (የብርሃን ቦታ) ብሎ ጠርቶታል።
በሐዲስ ኪዳንና በትውፊት፦ የወንጌል ጸሐፍያን «ረጅም ተራራ፣ ቅዱስ ተራራ» ብለው የጠሩት ሲሆን፣ ሐዋርያት በሲኖዶሳቸው እንዲሁም ሊቁ ቅዱስ ያሬድ በድጓው የተራራውን ስም «ደብረ ታቦር» በማለት በግልጽ አስፍረውታል።
፪. ነገረ ተዋሕዶ እና «ተስእሎተ ቂሣርያ» (የቂሣርያ ጥያቄ)
የድኅነታችን መሠረት የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ፍጹም አምላክ፣ ፍጹም ሰው መሆን (ነገረ ተዋሕዶ) ነው። ጌታችን ፍጥረታቱን ለክሕደት አሳልፎ የማይሰጥ አምላክ በመሆኑ፣ ደቀ መዛሙርቱ በክርስቶስ ማንነት ላይ እንዳይጠራጠሩ ነገረ ተዋሕዶን በትምህርትም በተአምራትም ገልጦላቸዋል።
የቂሣርያ ጥያቄ (ማቴ. 16፥13-20)፦ ጌታችን በፊሊጶስ ቂሣርያ «ሰዎች የሰውን ልጅ ማን ይሉታል?» ብሎ ሲጠይቅ፣ ቅዱስ ጴጥሮስ «አንተ የሕያው እግዚአብሔር ልጅ ነህ» ብሎ አምላክነቱን መሰከረ።
ከስድስት ቀን በኋላ፦ ቅዱስ ጴጥሮስ የመሰከረውን ምስክርነት ከአብና ከመንፈስ ቅዱስ እንዲሰሙ፣ ከነቢያት አንደበት እንዲረዱ እና በተአምራት ልባቸው እንዲከፈት፣ ጌታችን ከተስእሎተ ቂሣርያ በ6ኛው ቀን (ነሐሴ 13 ቀን) አዕማደ ሐዋርያት የተባሉትን ጴጥሮስን፣ ያዕቆብንና ዮሐንስን ይዞ ወደ ደብረ ታቦር ወጣ።
የተራራው መንፈሳዊ ምሳሌነት፦
የወንጌል ምሳሌ፦ ተራራ ሲወጡት ያስቸግራል፣ ከወጡት በኋላ ግን ደስ ይላል፤ ወንጌልም ሲማሯት ታስቸግራለች፣ ከተማሯት በኋላ ግን ጽድቅንና ኃጢአትን ለይታ ስታሳውቅ ደስ ታሰኛለች።
የመንግሥተ ሰማያት ምሳሌ፦ ተራራን በብዙ ጻዕር እንዲወጡት፣ መንግስተ ሰማያትንም በብዙ መከራ ያገኟታል።
የቤተ ክርስቲያን ምሳሌ፦ መሠረቱ ከመሬት፣ አናቱ ከሰማይ እንደሆነ ሁሉ፤ የቤተ ክርስቲያንም መሠረቷ በምድር፣ ራሷ (ክርስቶስ) በሰማይ ነው።
፫. የብርሃነ መለኮቱ መገለጥና የነቢያቱ ምስክርነት
ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በተወለደ በ32 ዓመት ከ6 ወር ከ13 ቀን (በዘመነ ማቴዎስ፣ ነሐሴ 13 በዕለተ እሑድ) በደብረ ታቦር ሲጸልይ ሳለ በፊታቸው ተለወጠ። ፊቱ እንደ ፀሐይ በራ፣ ልብሱም እንደ ብርሃን ነጭ ሆነ። ይህም ውላጤ/መለወጥ ሳይሆን የመለኮቱን ባሕርያዊ ብርሃን መግለጡ ነው።
የሙሴና የኤልያስ መቅረብ ምሥጢር፦ ከሞተ ብዙ ዘመን የሆነውን ሙሴን ከመቃብር አስነሥቶ፣ ኤልያስን ደግሞ ከብሔረ ሕያዋን አምጥቶ በደብረ ታቦር እንዲቆሙ ያደረገበት ምክንያት እርሱ የሕያዋንና የሙታን አምላክ መሆኑን እንዲመሰክሩ ነው።
የሙሴ ምስክርነት፦ «እኔ ባሕር ብከፍልም፣ መና ባወርድም እስራኤልን ማዳን ያልተቻለኝ ደካማ ነኝ፤ የእኔን ፈጣሪ እንዴት ሙሴ ይሉሃል? የሙሴ ፈጣሪ እግዚአብሔር ይበሉህ እንጂ!» ብሎ አምላክነቱን መሰከረ። በተጨማሪም በዘጸ 33፥13-23 ላይ «ፊቴን ማየት አይቻልህም፣ ጀርባዬን ታያለህ» ተብሎ ለሙሴ የተሰጠው ተስፋ፣ ከ5500 ዘመን በኋላ አምላክ ሰው ሆኖ በደብረ ታቦር በባሕርዩ ሲገለጥለት ተፈጽሟል።
የኤልያስ ምስክርነት፦ «እኔ ሰማይ ብዘጋም እስራኤልን ማዳን የማይቻለኝ ነኝ፤ የኤልያስ ፈጣሪ እግዚአብሔር ይበሉህ እንጂ!» በማለት የባሕርይ አምላክነቱን አረጋገጠ።
የሕግና የደናግል ምሳሌ፦ ከሕጋውያን ሙሴን፣ ከደናግል ኤልያስን በማምጣት፤ በሕግ ያገቡም ሆኑ በንጽሕና የኖሩ መነኮሳት አብረው መንግሥተ ሰማያትን እንደሚወርሱ አመልክቷል።
፬. የሐዋርያት ምስክርነት፣ የደመናው መጋረድና የሥላሴ መገለጥ
በዚያ ሰዓት ሐዋርያው ቅዱስ ጴጥሮስ በታየው ታላቅ የብርሃን ግርማ ተደንቆ «ጌታ ሆይ በዚህ መኖር ለእኛ መልካም ነው፤ አሐደ ለከ፣ ወአሐደ ለሙሴ፣ ወአሐደ ለኤልያስ (አንድ ለአንተ፣ አንድ ለሙሴ፣ አንድ ለኤልያስ ሦስት ዳስ እንሥራ)» አለ።
ይህ ንግግር የቅዱስ ጴጥሮስን ትሕትና (ራሱንና ባልንጀሮቹን አለመጥቀሱ) የሚያሳይ ቢሆንም፣ የክርስቶስን አምላክነት አርቆ አለመረዳቱንም ያመልክታል፤ ፈጣሪ በሰው እጅ በተሠራ ዳስ የሚወሰን አይደለምና። ለዚህም ነው በቅዱስ ወንጌል «የሚለውን አያውቅም ነበር» ያለው።ሉቃስ 9፡33፣ ማር 9፥6
የምሥጢረ ሥላሴ መገለጥ፦ ቅዱስ ጴጥሮስ ይህን ሲናገር ብሩህ ደመና መጥቶ ጋረዳቸው። ከደመናውም «የምወደው፣ ልመለክበት የወደድኩት ልጄ ይህ ነው፤ እርሱን ስሙት» የሚል የአብ ድምፅ መጣ።
አብ በደመና «የምወደው ልጄ ይህ ነው» ሲል ተናገረ።
ወልድ በፍጹም ሰውነቱ ብርሃነ መለኮቱን ገለጠ።
መንፈስ ቅዱስ በብሩህ ደመና ተመስሎ ታየ። በዚህም በደብረ ታቦር የምሥጢረ ሥላሴ አንድነትና ሦስትነት ለዓለም ለሦስተኛ ጊዜ በግልጽ ተገለጠ።
፭. የደብረ ታቦር (ቡሄ) በዓል ባሕላዊና መንፈሳዊ ትውፊቶች በኢትዮጵያ
በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የደብረ ታቦር በዓል ትልቅ መንፈሳዊና ባሕላዊ ቦታ አለው። ከዋዜማው ጀምሮ ማኅሌት ይቆማል፤ ሊቁ ቅዱስ ያሬድ «ሰባሕኩከ በደብር በቅድመ ሙሴ ወኤልያስ» እያለ በደብረ ታቦር የታየውን ምሥጢር ያመሰግናል።ትርጉሙም «በተራራ ላይ ሙሴና ኤልያስ በነበሩበት ፊት አመሰግንሃለሁ/አከብርሃለሁ» ማለት ሲሆን፣ የሚያሳየውም ክርስቶስ በደብረ ታቦር ተራራ ላይ መለኮታዊ ክብሩን መግለጡንና ከሙሴና ኤልያስ ጋር መነጋገሩን ነው።
የባሕላዊ መገለጫዎች መንፈሳዊ ትርጉም፦
ቡሄ (ገላጣ)፦ «ቡሄ» ማለት ገላጣ፣ ብርሃን ማለት ነው። የክረምቱ ጭጋግና ደመና ተወግዶ የብርሃን ወገግታ የሚታይበት፣ የብርሃነ መለኮቱ መገለጫ ወቅት በመሆኑ «ቡሄ» ተባለ።
ሙልሙል ዳቦ፦ ጌታ በደብረ ታቦር ብርሃኑን ሲገልጥ እረኞች በብርሃኑ ተደንቀው ሳይመለሱ ሲቀሩ፣ ወላጆቻቸው ዳቦ ጋግረው ፍለጋ ወጡ። ይህንን በማሰብ እናቶች ለሕፃናት «ሙልሙል» ዳቦ ይሰጣሉ።
ችቦ ማብራት፦ በበዓሉ ዋዜማ የሚበራው ችቦ በደብረ ታቦር የታየውንና ዓለምን ያበራው የብርሃነ መለኮቱ ምሳሌ ነው።
ጅራፍ ማጮህ፦ በደብረ ታቦር የተሰማውን የነጎድጓድ ድምፅ እና የሐዋርያቱን መደንገጥ ለማስታወስ ወጣቶች ጅራፍ ያጮኻሉ።
የአብነት ተማሪዎች፦ እንደ ሐዋርያት ሃይማኖትንና ነገረ መለኮትን የሚማሩ በመሆናቸው በዓሉን በልዩ ሁኔታ ያከብሩታል።
የተከበራችሁ ክርስቲያኖች ምንም እንኳን በሀገራችን በየአካባቢው በዓሉ በተለያየ መንገድ ቢከበርም በዓለ ደብረ ታቦር በዋናነት የባሕል ትዕይንት ማሳያ ሳይሆን የነገረ ተዋሕዶ ምሥጢር ማሳያ/መገለጫ ነው። ሃይማኖታዊ ባሕልና ትውፊቱ የሚያስፈልገው መሠረተ እምነቱን ጠንቅቆ ለሚያውቅ ሃይማኖተኛ ሕዝብ ነው። ስለሆነም ምእመናን በዓሉን ሲያከብሩ ከባሕላዊው ጨዋታ ባሻገር፣ ቅዱስ ጴጥሮስ «በዚህ መኖር ለእኛ መልካም ነው» እንዳለው፣ በደብረ ታቦር የምትመሰለው ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ጸንተው በመኖር፣ ሕገ ተፋቅሮን አስቀድመውና ምግባር ትሩፋት ሠርተው ሊሆን ይገባል።
የነገረ ተዋሕዶውን ምሥጢር ዐውቀንና ተረድተን እንድንኖር መንፈሳዊ ጥበቡንና ጸጋውን ያብዛልን አሜን ።
