መልእክተ ቅዱስ ፓትርያርክ
“ያለምንም ደመወዝ በራሳቸው ዓቅም በግብርና እየተዳደሩ ቤተ ክርስቲያንን በጥሩ ሰብእና በንጽሕና እና በቅድስና ጠብቀው ያስረከቡ እልፍ አእላፍ አበው እንዳልነበሯት ዛሬ የተሻለ ኑሮና ደመወዝ እያገኘን እግዚአብሔርን እንደቀኖናው በጥንቃቄ ማገልገል አቅቶናል” ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ፓትርያርክ
ጥቅምት ፬/፳፻፲፰ ዓ.ም
በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!!!
ብፁዕ አቡነ ሳዊሮስ
የመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት ዋና ሥራ አስኪያጅ
የደቡብ ምዕራብ ሸዋና የሸገር ከተማ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ፣
ብፁዕ አቡነ ዲዮስቆሮስ
የቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ጸሐፊ እና የራያ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ፣
ብፁዕ አቡነ ሕርያቆስ
የአዲስ አበባና ሐድያ ስልጤ አህጉረ ስብከት ሊቀጳጳስ
ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት የቅዱስ ሲኖዶስ አባላት፣
የመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ጽ/ቤት የየመምሪያውና የየድርጅቱ ኃላፊዎች ፣
ከሀገር ውስጥና ከውጭ ሀገር የመጣችሁ የየሀገረ ስብከቱ ሥራ አስኪያጆችና የየክፍሉ ተወካዮች፣
የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ኃላፊዎች፣
የገዳማትና አድባራት አስተዳዳሪዎችና ተወካዮች
የምእመናንና የሰንበት ትምህርት ቤት ተወካዮች፣
በአጠቃላይ በዚህ ዓመታዊ ጉባኤ የተገኛችሁ ክቡራና ክቡራት
እግዚአብሔር አምላካችን ዓመቱን ጠብቆ በከፍተኛ ጉጉት ለምንጠብቀው አርባ አራተኛው የሰበካ ጉባኤ አጠቃላይ መንፈሳዊ ዓለም ዓቀፍ ጉባኤ ስላደረሰን ክብርና ምስጋና ለእርሱ እናቀርባለን፡፡ እናንተንም እንኳን በደኅና መጣችሁ እንላለን፡፡
“ዑቁ እንከ ዘከመ ተሓውሩ ከመ ጠቢባን በንጽሕ ወአኮ ከመ ዓብዳን፤ ጥበብ እንደሌላቸው ሳይሆን እንደ ጥበበኞች እንዴት በንጽሕና እንደምትመላለሱ ዕወቁ” (ኤፌ.፭፥፲፭)፤ ሁሉንም መስጠትና መንሣት የሚችለው እግዚአብሔር አምላክ ጥበብን ለሰው ልጆች ሰጥቶአል፤ የሚሰጠው የጥበቡ ደረጃ የተለያየ ቢሆንም እግዚአብሔር ከጥበብ ባዶ አድርጎ የፈጠረው ግን የለም፤ የእግዚአብሔር ስጦታዎች ለፍጡራን ሲሰጡ ሊጠቀሙባቸው እንጂ እንዲሁ በከንቱ ሊያባክኑዋቸው አይደለም፡፡
ቅዱስ መጽሐፍ ስለ ጥበብ አስፈላጊነት በብዙ ቦታ ያስተምራል፤ በተለይም ጠቢቡ ሰሎሞን “ጥበብ ትኄይስ እምኲሉ መዛግብት ወኲሉ ክብር ኢመጠና ላቲ፤ ከሀብት ሁሉ ጥበብ ትበልጣለች፤ ክብርም ሁሉ አይመጣጠናትም” በማለት የጥበብ ብልጫ ተወዳዳሪ የሌላት እንደሆነች ያስገነዝበናል፤ እግዚአብሔርም ሥራውን ሁሉ በጥበብ እንደሚሠራ “ወኲሎ በጥበብ ገበርከ፤ ሁሉንም በጥበብ አደረግህ” በሚል ተጽፎ ይገኛል፤ እግዚአብሔር ሥራውን በጥበብ እንደሚሠራ፣ እኛንም በጥበብ መሥራት እንዳለብን ሲያስተምረን፣ ‹‹ኩኑ ጠቢባነ ከመ አርዌ ምድር እንደ እባብ ብልሆች ሁኑ›› ብሎናል፡፡
ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት!
ክቡራን የጉባኤው ተሳታፊዎች!
ዘመንና ቦታ ሳይገድበን ምንጊዜም ሥራችንን በጥበብ መሥራት እንዳለብን ቢታወቅም ዛሬ ላይ ከምን ጊዜውም በበለጠ በጥበብ መመላለስ የሚያስፈልግበት ጊዜ ላይ እንገኛለን፤ የዛሬዎቹ ችግሮች በአንድ አካባቢ ብቻ ያሉ ሳይሆኑ ዓለም ዓለፍ ቅርጽ ያላቸው እንደሆኑ ታላላቅ መሪዎች ሳይቀሩ በዓለም መድረክ ላይ ስሞታ ሲያቀርቡ በዓይናችን አይተናል፤ በጆሮአችንም ሰምተናል፤ በሁኔታውም የክርስትና ሃይማኖት በአጠቃላይ በተለይም ደግሞ የኦርቶዶክሱ ወገን የችግሩ ገፈት ቀማሽ እንደሆነ እየተስተዋለ ነው፡፡
እኛም የዚሁ ወገን አካል በመሆናችን የችግሩ ቀማሽ መሆናችን አልቀረም፤ በየቀኑ ካህናትና ምእመናን ይገደሉብናል፤ አብያ ክርስቲያናት ይቃጠሉብናል፤ የእምነትና የኅሊና ነጻነት በእጅጉ የሳሳ ሆኖብናል፤ አላስፈላጊ ጫናዎችም በዝተውብናል፤ ከውጭና ከውስጥ በተቀነባበረ ስሌት የቤተክርስቲያናችንን ስም ማጥፋት የዕለት ተግባራቸው ያደረጉ አካላት ተበራክተዋል፡፡
ቤተ ክርስቲያናችን ከነባሩና ረጅም ዘመን ካስቈጠረው ሰፊ ማእዷ እያበላቻቸው ያለች መሆኗን ዘንግተው እንብላሽ፣ እንዋጥሽ የሚሉዋት ወገኖች በዝተዋል፣ በእነዚህና በሌሎች ምክንያቶች አባቶች እንደልብ ተንቀሳቅሰው መሥራት የማይችሉባቸው አጋጣሚዎች እየተፈጠሩ ነው፤ የወለጋው ችግር ለዚህ በዋናነት ተጠቃሽ ነው፡፡
ታድያ እነዚህን ፈተናዎች ለማለፍ ጥበብ ያስፈልጋል፤ ነገር ግን ጥበብ መከተል ማለት ዝም ብሎ ማለፍ ወይም አይተው እንዳላዩ ሆኖ መኖር ማለት አይደለም፤ በጥበብ መመላለስ ማለት ከሁሉ በፊት ችግሮችንና የችግሮችን መንሥኤዎች በአግባቡ መረዳትና መለየት መቻል ነው፤ ከዚያም ራስን ለከፋ አደጋ በማያጋልጥ መልኩ የተለያዩ ስልቶችን በመጠቀም መሸጋገር መቻል ነው፤ በዚህ ዘመን እንዲህ ያለ ጥበብ መጠቀም የግድ ያስፈልጋል፡፡
ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት!
ክቡራን የጉባኤው ተሳታፊዎች! ቤተ ክርስቲያናችን እየተፈተነች ያለችው ከውጭ ብቻ ሳይሆን ከውስጥም ጭምር እንደሆነ መካድ የለብንም፤ ንጽሕትና ቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን ሥር የሰደደ የቅድስና ሕይወትና በፈሪሀ እግዚአብሔር የተቃኘ ሥነ ምግባር ያላት ቤተ ክርስቲያን ናት፤
በአሁኑ ጊዜ ግን እነዚህ ሁሉ ቦታቸውን እየለቀቁ ያሉ መስለዋል፤ ቤተ ክርስቲያን በረጅሙ ታሪኳ ሲያስተምሩም ሆነ ሲማሩ፣ ሲመንኑም ሆነ ሲመነኲሱ፣ ሲቀድሱም ሆነ ሲያስቀድሱ ያለምንም ደመወዝ በራሳቸው ዓቅም በግብርና እየተዳደሩ ቤተ ክርስቲያንን በጥሩ ሰብእና በንጽሕና እና በቅድስና ጠብቀው ያስረከቡ እልፍ አእላፍ አበው እንዳልነበሯት ዛሬ የተሻለ ኑሮና ደመወዝ እያገኘን እግዚአብሔርን እንደቀኖናው በጥንቃቄ ማገልገል አቅቶናል፤ ምእመናንም በዚህ ምክንያት እየተሰናከሉ እንደሆነ እየተስተዋለ ነው፡፡ ሚድያውም ስሕተቶችን ወደ ውጭ በማውጣት ሰድቦ ለሰዳቢ እየዳረገን ነው፤ ይህ ሊሆን የቻለው የቤተ ክርስቲያን ሀብትና ንብረት በአግባቡ በመያዝ ለታለመለት ዓላማ ማዋል አለመቻላችን ነው፤ ይህ ችግር ባለበት ከቀጠለ ሌላ ጦስ ይዞብን እንዳይመጣ ሁነኛ ለከት ማኖር የግድ ይሆናል፡፡
የሰበካ ጉባኤ አደረጃጀት የቤተ ክርስቲያናችንን ሀብተ ጸጋ በማሳደግ ረገድ አስተማማኝ ስልት እንደሆነ በተግባር የተረጋገጠ ነው፤ ሆኖም ሲጀመር ሳለ የነበረ መነቃቃት በአሁኑ ጊዜ የቀነሰ መስሎ ይታያል፤ አሁን በቤተ ክርስቲያን ሰፊ ሽፋን ይዞ የሚገኘው የሙዳየ ምጽዋት ገቢ እንጂ የሰበካ ጉባኤ አስተዋፅኦ እንደአይደለ ሁላችንም እናውቃለን፤ በተለይም በከተሞች ውስጥ ነገሩ ጎልቶ ይታያል፡፡
ይህ የሆነበት ምክንያት ምናልባትም በየደረጃው በኃላፊነት ያለን ሰዎች ሻል ያለ ደመወዝ ስለምናገኝ የሰበካ ጉባኤው ተልእኮ ከሚፈለገው ደረጃ ላይ የደረሰ መስሎን ይሆናል፤ ነገር ግን ከሰማንያ ከመቶ ያላነሰ የገጠሪቱ ቤተ ክርስቲያን አገልጋይ መምህርና ካህን አሁንም ያለ ደመወዝ የሚኖር ነው፤ ሕዝበ ክርስቲያኑም ከቤተ ክርስቲያኑ ሊያገኘው የሚገባ የበጎ አድራጎት የጤና የትምህርትና የማኅበራዊ ዋስትና አገልግሎት በሚጠበቀው ደረጃ ሊያገኝ አልቻለም፤ የገዳማትና የአብነት ት/ቤቶች ችግሮችም በነበሩበት የልመና ኑሮ እየቀጠሉ ነው፤ በውጤቱም በችግር የሚኖሩ ገዳማት የተዘጉ የአብነት ት/ቤቶችና አብያተ ክርስቲያናት ከተበራከቱ ሰነባብቶአል፡፡
ታድያ ይህንን ሁሉ መልክ ማስያዝና ቤተ ክርስቲያንን ለቀጣዩ ትውልድ ማሸጋገር የሚቻለው በጥበብና በጥበብ ብቻ መሥራት ሲቻል ነው፤ ይህንን ችግር መፍታት የሚያስችል ጥበብ ደግሞ በዘመናችን አለ፤ የጠፋው ቅንነቱና ፈቃደኝነቱ ነው፡፡
በየዓመቱ የምናካሄደው አጠቃላይ የሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ እንደነዚህ ያሉትን ችግሮች መቅረፍ የሚያስችል ካልሆነ ተሰብስበናል ማለቱ ብቻ ትርጉም ሊኖረው አይችልም፤ ስለሆነም ከዚህ በላይ የተጠቃቀሱና ሌሎችም የቤተ ክርስቲያናችን ተግዳሮቶች ካሉ በዚህ ጉባኤ በማንሣት በማየትና በመገምገም ለቤተ ክርስቲያን አሻጋሪና ጥበባዊ ውሳኔ እንዲያሳልፍ አባታዊ ጥሪያችንን እናስተላልፋለን፡፡
በመጨረሻም
ዓመታዊው ዓለም ዓቀፍ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን አጠቃላይ ሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ በዛሬው ዕለት በጸሎተ ወንጌል የተከፈተ መሆኑን በእግዚአብሔር ስም እናበሥራለን፡፡
መልካም ጉባኤ ያድርግልን!
እግዚአብሔር አምላክ ኢትዮጵያንና ሕዝቦችዋን ይባርክ !!!
ወስብሐት ለእግዚአብሔር !!!
አሜን!!!
አባ ማትያስ ቀዳማዊ
ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ
ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት
ጥቅምት ፬ ቀን ፳፻፲፰ ዓመተ ምሕረት
አዲስ አበባ – ኢትዮጵያ