የቅዱስ ፓትርያርኩ መልእክት ቤተ ክርስቲያኒቱ በአንገብጋቢነት የምትሻውን ወቅታዊ ጥያቄ የሚመልስ አሳብ የያዘ ነው

 በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ

 
ከአራት ዓመት በፊት 2001 ዓ.ም የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ ቤተ ክርስቲያኒቱን ወደ ተሻለ የአገልግሎት ደረጃ ለማድረስ በመከረበት ጉባኤው ቤተ ክርስቲያኒቱ ያሉባትን ለአገልግሎቱ እንቅፋት የሆኑ ተገቢ ያልሆኑ ድርጊቶችን ለማስወገድ ያሳለፋቸው ውሳኔዎች፣ የተያዙ አቋሞች ነበሩ፡፡ ቅዱስ ሲኖዶስ በጊዜው በቤተ ክርስቲያኒቱ “የአስተዳደር ችግሮች፣ የሙስናና የቤተሰብ አስተዳደር” በቤተ ክርስቲያኒቱ የአገልግሎት መስመሮች ውስጥ ሁሉ መንሰራፋቱን አምኖ ያንን ለማጥራት፣ ዘመኑን የዋጀ በተጠና ዕቅድና አፈጻጸም የሚከናወን፣ ሓላፊነትና ተጠያቂነት የሰፈነበት ዘመናዊ የአስተዳደር ሥርዓት ለመዘርጋት ውሳኔ ማስተላለፉ የሚታወስ ነው፡፡ 

ይሁን እንጂ ወደ ተግባር ለመግባት የተደረገው እንቅስቃሴ ግን ወዲያውኑ ፈተና ገጥሞት ነበር፡፡ ውዥንብር ለመፍጠር፣ አለመግባባትን ለማስፈን የአባቶችን ስም በማጥፋት ለማሸማቀቅ በተለያዩ መንገዶች ጥረት የሚያደርጉ፣ በተናጠልና በቡድን የሚን ቀሳቀሱ የተለያዩ አካላት ስለነበሩ ርምጃው ሳይሳካ ቀርቷል፡፡ በመሠረተ አሳቡ ግን የቤተ ክርስቲያኒቱን የአገልግሎት አካሄድ የማሳደግና የሚያስወቅሱ ነገሮችን የማስወገድ ብርቱ ፍላጎት እንደነበረው ቅዱስ ሲኖዶስ በአቋሙ አሳይቶ አልፏል፡፡

ይህ የነበረ የቅዱስ ሲኖዶስ ሐሳብ ዛሬ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ በግልጽ የተግባራቸው መጀመሪያ፣ የትኩረት አቅጣጫዎቻቸው ሁሉ ራስ እንደሆነ በቅርቡ ለበዓለ ትንሣኤ ባስተላለፉት ይፋዊ መልእክትና ለእንኳን አደረሰዎ በተዘጋጀው መርሐ ግብር ላይ  ባንጸባረቁት አቋም ከላይ አስቀድመን ያነሣናቸውን የቅዱስ ሲኖዶስ አቋሞች አስተጋብተዋል፡፡ ሃይማኖት በምግባር መገለጽ እንዳለበትና ከሃይማኖቱ አሳብ ጋር ስምሙ የሆነ አካሄድ እንዲኖረን የመከሩት ቅዱስነታቸው “ያረጀው ነገር ሁሉ በክርስቶስ ደም ተቀድሶና ነጽቶ ሐዲስ ሆኗል፡፡ አምላካችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሠርቶ የሚያሠራ የመልካም ነገር ሁሉ አርአያ መሪ እንደመሆኑ መጠን አዲሱን መንገድ ከፍቶ እንድንጓዝበት ሲያደርግ እኛም በአዲስ መንፈስ በአዲስ ሕይወት ልንመላለስበት እንጂ እንደገና ወደ አረጀውና ወደ አፈጀው ሕይወት ተመልሰን ልንዘፈቅ አይደለም” ብለዋል፡፡

መልእክታቸው የቤተ ክርስቲያን ልጆችና አገልጋዮች ሁሉ በየደረጃው ያሉ ፍጹም ክርስቲያናዊ ምግባር እንዲላበሱ ያላቸውን አባታዊ ፍላጎት አንጸባርቀዋል፡፡ ይህ የቅዱስነታቸው ምክር በቤተ ክርስቲያን አስተዳደር አካላትም ዘንድ ሊተኮርበት የሚገባ ነው፡፡ ለመልካም ምግባር እንድንሰለፍ በሥራችንም ሁሉ እንድንበረታ ባስተላለፉት በዚሁ ምክራቸው መሠረት የትኞቹም አገልጋዮች መመላለስ ቢችሉ ቤተ ክርስቲያን አሉባት ከሚባሉ ችግሮች ሁሉ መላቀቅ የሚያስችላት አቅም ይሆናል፡፡

ቅዱስነታቸው በተለይም በዕለተ ማዕዶት ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት፣ የቤተ ክህነቱ ከፍተኛ የሥራ ሓላፊዎች፣ የአድባራትና ገዳማት አስተዳዳሪዎች በተገኙበት ባስተላለፉት መልእክት በዓሉ ከዲያብሎስ ቁራኛነት ከሞት አገዛዝ ከአሮጌው እርሾ የተላቀቅንበት መሆኑን ካወሱ በኋላ በዚያው አንጻር የቤተ ክርስቲያን አገልጋዮች ከብልሹ አስተሳሰብ፣ ከብልሹ ምግባር ከሙስና፣ ከብልሹ አሠራር መጽዳት እንደሚገባቸው አሳስበዋል፡፡ ቤተ ክርስቲያን ያላትን ቅድስና ጠብቃ እንድትኖር ልጆቿ በተለይም አርአያ ሊሆኑ የሚገባቸው ካህናት በጎ ካልሆኑና ቤተ ክርስቲያንን ከሚያስተቹ አስተሳሰብና ተግባር እንዲላቀቁ መክረዋል፡፡ ይህም ቀድሞም የነበረው የቅዱስ ሲኖዶስ ቀርጥ አሳብ ተግባራዊ ምላሽ ሊያገኝ የሚችልበት ዕድል እንዳለ ተስፋ ሰጪ ሆኗል፡፡

ማኅበረ ቅዱሳን የቅዱስነታቸው መልእክት ተገቢና ወቅታዊ መሆኑን የሚያምን ሲሆን ለቤተ ክርስቲያኒቱ አገልግሎት ዕድገት በቀና መንፈስ ለሚያስቡ የቅዱስነታቸው የአገልግሎት ጅማሬ ተስፋ ሰጪ እንደሆነ ያስባል፡፡ ይህ የቅዱስነታቸው አቋም በዚሁ ወቅት በሚካሄደው የቅዱስ ሲኖዶስ ጉባኤ ብርቱ ድጋፍ እንደሚያገኝና ጠንከር ያሉ መመሪያዎችን በየደረጃው ላሉ የቤተ ክህነቱ አገልጋዮች ያስተላልፋል ተብሎ ይታመናል፡፡

ከሁሉም በላይ ግን የቅዱስነታቸው መልእክትም ሆነ የቅዱስ ሲኖዶስ አቋም በየደረጃው ባሉ አካላት ተግባራዊ ምላሽ ይፈልጋሉ፡፡ እንደ ከዚህ ቀደሙ ተወስነው የማይተገበሩ ውሳኔዎች፣ ሊራመዱ የማይችሉ አቋሞች ሊሆኑ አይገባም፡፡ ለተግባራዊነቱ ደግሞ ከብፁዓን አባቶች ጀምሮ በርካታ የቤተ ክህነቱ አካላት ድጋፍ እንዳላቸው ቅዱስነታቸው አቋማቸውን በንግግራቸው ባንጸባረቁበት ወቅት በሰጡት ሞቅ ያለ የድጋፍ ምላሽ መረዳት ይቻላል፡፡ ከጥቂት ራስ ወዳዶች በስተቀር የቤተ ክርስቲያኒቱ አገልግሎት ማሻሻያን በብርቱ የማይፈልግ የለም፡፡ በአስቸኳይና በጥብቅ ይፈልገዋል፡፡ የቤተ ክርስቲያኒቱ ገጽታ እንዲጎድፍ የሚሻ የለም፡፡ የጎደፈም ነገር ካለ በፍጥነት ማስተካከያ ለማድረግ መረባረብ ይገባል፡፡ የእርምጃው ቁልፍ ያለው ግን በቅዱስ ሲኖዶስ ጥብቅ አቋም ላይና በቅዱስ ፓትርያርኩ የአስተውሎት ርምጃ ውስጥ ነው፡፡

ለውጥን ምእመናንን በመላው፣ ማኅበረ ካህናቱ በየደረጃው፣ ሰንበት ትምህርት ቤቶችና ማኅበራት፣ አድባራትና ገዳማቱ፣ ተማሪዎችና መምህራኑ፣ ደቀመዛሙርቱና መዘምራኑ ሁሉ በብርቱ ይፈልጋሉ፡፡ ቤተ ክርስቲያን የዕረፍት ወደብ መሆን አለባት፡፡ እንደ ቅዱስነታቸው ንግግርም ለቤተ ክርስቲያን ብቻ ሳይሆን ለሀገርም አርአያ መሆን፣ ለዓለሙ ጨው መሆን አለባት፡፡ አሮጌው ነገር ሁሉ ማለፍ አለበት፤ አዲሱ መልካሙ ነገር ሁሉ ሊመጣ ይገባል፡፡ በዚያን ጊዜ ሁሉም አንድ ሆኖ ያስባል፡፡ መንፈሳዊው ሥራ ይሠለጥናል፤ የሥጋው ሥራ ወደ ቤቱ ይመለሳል፡፡

ዛሬ በየአህጉራቱ ያሉ የኦርቶዶክስ አብያተ ክርስቲያናት በብርቱ ተነቃቅተው የዓለምን ብልሹ ነገር ሁሉ እየተዋጉ ነው፡፡ ጠንካራ አደረጃጀትና የአግልግሎት አድማስ ፈጥረው እየተንቀሳቀሱ ይገኛሉ፡፡ የታሪክ፣ የሞራል፣ የዕውቀት፣ የሥነ ምግባርም መሠረት ያላት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ይሔንን አቅም ፈጥሮ ለመንቀሳቀስ የሚያግዳት አንዳችም ነገር የለባትም፡፡ ዋናውና ወሳኙ ነገር የእግዚአብሔርን ቡራኬ ማስገኘት የሚችል በጎ ምግባር፣ ቀና ሐሳብ ቤተ ክህነቱ ይዞ የመገኘቱ ነገር ነው፡፡ ከዚያ በኋላ ጥቂቱ ብዙ፣ ጥቁሩ ነጭ፣ ክፉው ሁሉ ለመልካም የማይሆንበት ምክንያት እንደማይኖር ማኅበረ ቅዱሳን የጸና አቋም አለው፡፡

በአጠቃላይ ቅዱስነታቸው ያመላከቱንን በጎ መንገድ መከተል ቤተክርስቲያን ያለ አማራጭ ይዛው ልትገኝ የሚገባት አካሄድ ነው፡፡ ለዚህ ጥሪ ምላሽ መስጠት ደግሞ የሁሉም የቤተ ክርስቲያን ቤተሰብ ሓላፊነት ነው፡፡ የማኅበረ ቅዱሳን አባላትም ለዚሁ ጥሪ በጎ ምላሽ ለመስጠት መዘጋጀታቸውን በዚሁ አጋጣሚ ለመግለጽ እንወዳለን፡፡

 

ምንጭ፡- ሐመር መጽሔት 21ኛ ዓመት ቁጥር 1 ግንቦት 2005 ዓ.ም.

ወስብሐት ለእግዚአብሔር           

te 30

በባሕረ ጥበባት /Encyclopedia of EOTC/ ዝግጅት ዙሪያ የምክክር ጉባኤ ተካሔደ

ግንቦት 30 ቀን 2005 ዓ.ም.

በእንዳለ ደምስስ

በማኅበረ ቅዱሳን የጥናትና ምርምር ማእከል አስተባባሪነት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የባሕረ ጥበባት /Encyclopedia of EOTC/ ዝግጅት ዙሪያ ከባለ ድርሻ አካላት ጋር የምክክር ጉባኤ ተካሔደ፡፡

ግንቦት 29 ቀን 2005 ዓ.ም. ከቀኑ አስር ሰዓት ጀምሮ በሰሜን ሆቴል በተካሔደው የምክክር ጉባኤ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ባሕረ ጥበባት /Encyclopedia of EOTC/ ማዘጋጀትte 30 ያስፈለገበት ዋነኛ ምክንያትን አስመልክቶ በማኅበሩ ሰብሳቢ በቀሲስ ዶክተር ሰሙ ምትኩ ተገልጿል፡፡ በንግግራቸውም በተለያዩ ጊዜያት የቤተ ክርስቲያኒቱን ታሪክና ቅርሶች አጥኚዎች፤ ጎብኚዎችና ምእመናን መረጃዎችን ማእከላዊና ሕጋዊ ከሆነ ቦታ ማግኘት አስቸጋሪ መሆኑን አውስተው አለም አቀፍ ተቀባይነት ያለው፤ ሊቃውንቱ የሚያውቁት የቤተ ክርስቲያንን ማንንት የሚገልጽ መረጃ ማዘጋጀት፤ በተለያዩ ጊዜያት በዘርፉ የተሞከረው እውቀት በአንድ ላይ በማሰባሰብ የታሪክ ቅሰጣ ለማስቀረትና ለመከላከል እንዲቻል ይህንን ባሕረ ጥበባት ማዘጋጀት እንዳስፈለገ አብራርተዋል፡፡  

በተካሔደው ውይይትም የሚዘጋጀው ባሕረ ጥበባት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ትውፊት፤ ታሪክና ሥርዓት እንዲይዝ እንዴት ተደርጎ ይዘጋጃል፤ ማነው የሚያዘጋጀው፤ አቅም / የሰው ሃይል፤ten 30 ገንዘብ . . ./ ፤ ተጀምሮ እንዳይቋረጥ ምን መደረግ አለበት፤ የባለሙያዎች ድጋፍ፤ የባለ ድርሻ አካላት ትብብር፤ የአሰራር ሥልቶች ዝግጅት፤ በስንት ጊዜ ይጠናቀቃል? በሚሉና ተያያዥ ጉዳዮች ላይ ሰፋ ያለ ውይይት ተካሒዷል፡፡

በመጨረሻም በአማርኛና በእንግሊዝኛ የሚዘጋጀው የዚህ ባሕረ ጥበባት ባለቤት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ስትሆን ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት፤ ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያንና ባለድርሻ አካላትን በማስተባበር በገንዘብ በጊዜ በሰው ኃይል የተቀናጀ አደረጃጀት ያለው ሆኖ ሥራውን ግን ማኅበረ ቅዱሳን  በበላይነት ቢመራው የተሻለ እንደሚሆን አስተያየት ቀርቧል፡፡ ለሥራው ግብአት የሚሆኑ አሳቦችንም ለማሰሳሰብ የምክክር ጉባኤው በተደጋጋሚ እንደሚደረግ ተጠቅሷል፡፡

tena
በምክክር ጉባኤው ላይ ከሊቃውንት ጉባኤ፣ ከአዲስ አበባ ዮኒቨርሲቲ፣ ከቤተ ክርስቲያኒቱ መንፈሳዊ ኮሌጆች፤ ከቅርስ ጥናትና ጥበቃ ባለሥልጣን፤ ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ቤተ መዛግብትና መጻሕፍት ኤጀንሲ፣ ከአዲስ አበባ ባሕልና ቱሪዝም ቢሮ፣ እንዲሁም የማኅበረ ቅዱሳን ሥራ አመራርና ሥራ አሰፈጻሚ አባላት ተገኝተዋል፡፡

senod 2005

የቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ ተጠናቀቀ

ግንቦት 30 ቀን 2005 ዓ.ም.

በእንዳለ ደምስስ

senod 2005

ከግንቦት 21 ቀን ጀምሮ እስከ ግንቦት 30 2005 ዓ.ም.  ድረስ ሲካሔድ የሰነበተው የቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ ለቤተ ክርስቲያኗ አስፈላጊ ናቸው ያላቸውን ውሳኔዎች በማሳለፍ ተጠናቀቀ፡፡ በዚህም መሠረት የሚከተሉትን ጠቅለል ያሉ ውሣኔዎች ተላልፈዋል፡፡  በቤተ ክርስቲያኒቱ ላይ የሚታዩ ብልሹ የአስተዳደርና የአሰራር ችግሮችን  ማሻሻል፤ ጥራት የጎደለው የፋይናንስ አያያዝን መዋጋት፤ ሙስናንና ለብክነት የተጋለጡ አሰራሮችን ለመቅረፍ እንዲቻል ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት፤ ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን፤ ምሁራንና ምእመናን የሚገኙበት ዓብይ ኮሚቴ ማዋቀሩን ይፋ ማድረግ፡፡ በተጨማሪም የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት በአንድ ሀገረ ስብከት፤ በአንድ የቅዱስ ፓትርያርክ ረዳት ሊቀ ጳጳስ እንዲመራ የተደረገ ሲሆን ፤ የመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ጽ/ቤት ዋና ሥራ አስኪያጅና የቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ጸሓፊ ምርጫም ተከናውኗል፡፡ ከሀገር ውጪ ከሚገኙ የቤተ ክርስቲያን አባቶች ጋር የተጀመረው የሰላም ውይይት ጥረት እንደሚቀጥልም የቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ ውሳኔ አሳልፏል፡፡

ዝርዝር መግለጫውን ከዚህ በታች እንደሚከተለው አቅርበነዋል፡፡

 

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን

    በፍትሕ መንፈሳዊ አንቀጽ 5 ቁጥር 164 ላይ ከበዐለ ትንሣኤ በኋላ በሃያ አምስተኛው ቀን  ቅዱስ ሲኖዶስ ጉባኤ እንዲካሔድ በተደነገገው ቀኖና ቤተ ክርስቲያን መሠረት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ ከግንቦት 21 – 30 ቀን 2005 ዓ.ም. ተካሒዷል፡፡ ይህ ጉባኤ የርክበ ካህናት ጉባኤ ተብሎ የሚታወቅ ሲሆን ከላ በተጠቀሰው ቀኖና ቤተ ክርስቲያን እንደተገለጸው ብፁዐን ሊቃነ ጳጳሳት በቤተ ክርስቲያን ያለውን አጠቃላይ መንፈሳዊ፤ ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ጉዳዮችን በማየት በመንፈስ ቅዱስ መሪነት ታላላቅ ውሳኔዎችን የሚወሰንበት ዓብይ ጉባኤ ነው፡፡

    ቅዱስ ሲኖዶስ በቤተ ክርስቲያናችን ውስጥ ያሉትን ወቅታዊና ነባራዊ ጉዳዮችን ለመመርመርና ለመገምገም ባለው ሐዋርያዊ ኃላፊነት ለቤተ ክርስቲያን መንፈሳዊ ተልእኮ አፈጻጸም እንቅፋት ናቸው ብሎ ያመነባቸውን ጉዳዮች በአጀንዳ ቀርጾ፤ በስፋትና በጥልቀት ተወያይቶ ውሳኔ ሰጥቶባቸዋል፡፡ ቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን በምድር ላይ ያለች የእግዚአብሔር መንግስት ማዕከል፤ በባሕርይዋም ንጽሕትና ቅድስት ብትሆንም ኃጢአትና ስሕተት በነገሰበት ዓለም ያለች በመሆንዋ ከእርስዋ መሠረታዊ ባሕርይ ጋር የማይስማሙ ተግባራት እንዳይጋቡባት የመጀመሪያው ጥበቃ በብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት ላይ ያረፈ ነው፡፡ በተለይም የአሁኑ ዓላማችን ጥበብ ባፈራው የአሠራር ዕውቀት በየቀኑ በለውጥ ጎዳና በሚራመድበት ጊዜ ቤተ ክርስቲያናችንም ከዓለሙ በተሻለና በበለጠ በመንፈሳዊና በአእምሮአዊ ጥበብ ሕዝበ ክርስቲያኑን መምራት፤ ማስተማርና ማገልገል ይጠበቅባታል፡፡ በቤተ ክርስቲያናችን እነዚህን የተቀደሱ ተግባራት በሥራ ለመተርጎም ወቅታዊ እንቅፋት ሊሆኑ የሚችሉ ነገሮች ምን ምን ናቸው? በማለት ቅዱስ ሲኖዶስ በጥልቀት ተመልክቶአል፡፡

    በዚህ መሠረት ጉባኤው ብዙ ውይይት ካደረገ በኋላ የሚከተሉትን ዓበይት ውሳኔዎችን አሳልፎአል፡፡

 

  1. በየሥራ ዘርፉ እየተከሠተ ያለው የመልካም አስተዳደርን ችግር በተለይም ብልሹ አስተዳደርና አሠራር፤ ዘመኑን ያልዋጀና ጥራት የጎደለው የፋይናንስ አያያዝ፤ እንደዚሁም ለሙስናና ለብክነት የተጋለጡ አሠራሮች ሁሉ ወሳኝ በሆነ መልኩ ለመቅረፍና ለማድረቅ፣ ከዚህም ጋር ቤተ ክርስቲያናችን በመሪ እቅድ መሥራት የምትችልበትን አሠራር ለመቀየስ፣ ቅዱስ ሲኖዶስ፡- ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት፣ ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን፣ ምሁራን ምእመናን የሚገኙበት ዓቢይ ኮሚቴ ተቋቁሞ ጉዳዮን የማጣራትና የማጥናት ሥራውን እንዲቀጥል ተስማምቶ በአንድ ድምፅ ወሰኖአል፡፡

  2. የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ለሌሎች አህጉረ ስብከት በመልካም አስተዳደርና በፋይናንስ አያያዝ፣ እንደዚሁም በስብከተ ወንጌልና በአገልግሎት አሰጣጥ ለሌሎች እንደዚሁም በመልካም አስተዳደር፣ በፋይናንስ አያያዝና በሰው ኀይል አመዳደብ የሕግ የበላይነትን አክብሮ እንዲሠራ አስፈላጊውን ክትትል ሁሉ በቋሚ ሲኖዶስና በመንበረ ፓትርያርኩ ጥብቅ ክትትል እንዲደረግ፤

  3. የቤተ ክርስቲያናችን የሕይወት ምንጭ የሆነውን የስብከተ ወንግል ትምህርት በሰው ኀይል፣ በሚድያም ጭምር እየታገዘ በመላው ዓለም ላሉ የቤተ ክርስቲያናችን ተከታዮች ትምህርቱን በጥራትና በጥልቀት ይሰጥ ዘንድ አስፈፋሚው አካል ጠንከር ያለ ሥራ እንዲሠራ ቅዱስ ሲኖዶስ በሙሉ ድምጽ ወስኗል፡፡ የመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ጽ/ቤት ዋና ሥራ አስኪያጅና የቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ጸሐፊ ምርጫ በየሦስት ዓመቱ እንዲካሄድ ሕገ ቤተ ክርስቲያን ባስቀመጠው ድንጋጌ መሠረት ብፁዕ አቡነ ማቴዎስ፤ የወላይታ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ፤ የመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ጽ/ቤት ዋና ሥራ አስኪያጅ፤ ብፁዕ አቡነ ሉቃስ፤ የሰቲት ሑመራ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ የቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ጸሐፊ አድርጎ ቅዱስ ሲኖዶስ መርጧቸዋል፡፡

  4. ብፁዕ አቡነ እስጢፋኖስ የጅማ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት የብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርክ ረዳት ሊቀ ጳጳስ ሆነው እንዲሠሩ፤ እንደዚሁም የምራቅና ሰሜን አዲስ አበባ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ዳንኤል በኢየሩሳሌም የኢትዮጵያ ገዳማት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ዳንኤል በኢየሩሳሌም የኢትዮጵያ ገዳማት ሊቀ ጳጳስ ሆነው እንዲሠሩ ቅዱስ ሲኖዶስ ወስኗል፡፡

  5. በመካከለኛው ምሥራቅና በሌሎች የዓለም ክፍሎች ለሥራ ፍለጋ በሕገ ወጥ መንገድ በሚሄዱ ልጆቻችንና ወገኖቻችን ላይ እየደረሰ ያለውን ዘግናኝ ድርጊት ለማስቆም መንግሥት እያደረገ ያለው ጥረት ቤተ ክርስቲያናችን በሙሉ ልብ እንደምትደግፈውና ለስኬቱም የበኩሏን እንደምትወጣ፣ ለዚህም በየደረጃው ያሉ መምህራን፣ ካህናትና ሰባክያን ሁሉ የዚህን ጎጂነት ደጋግመው በማስረዳትና በማስተማር ሕዝቡ ግንዛቤ እንዲኖረው ጠንክረው እንዲያስተምሩ ቅዱስ ሲኖዶስ መመሪያ ሰጥቷል፡፡

  6. የሀገራችን ሕዝቦች ከድህነትና ከኋላ ቀርነት ተላቀው መካከለኛ ገቢ ካላቸው ሀገሮች ጋር እኩል ለማሰለፍ በሚደረገው ሁለንተናዊ የልማት ተግባር ቤተ ክርስቲያናችን ከሕዝቡና ከመንግሥት ጎን በመሆን የሚጠበቅባትን ሁሉ እንደምታደርግ ቅዱስ ሲኖዶስ አረጋግጧል፡፡

  7. ኢትዮጵያ ሀገራችን በሀገር ውስጥ፣ በምሥራቅ አፍሪካ፣ በመላ አፍሪካ ከዚያም በመላው ዓለም ሰላም እንዲሰፍን፣ የሰው ልጅ እኩልነትና መብት እንዲከበር፣ ፍትሐዊ የሆነ የሀብት አጠቃቀም እንዲኖር፣ የአየር መዛባትን ለመቋቋም የአረንጓዴ ልማት ሀብት እንዲስፋፋ የምታደርገውን ያላሰለሰ ጥረት ቅዱስ ሲኖዶስ በእጅጉ እያደነቀ የሀገሪቱን መልካም ዝናና በጎ ገጽታ ለመጠበቅ የበኩሉን ጠንክሮ እንዲሠራ አረጋግጧል፡፡

  8. በሀገራችን የዕድገት ሂደት ከፍተኛ ሚና ይጫወታል ተብሎ በመገንባት የሚገኘው ታላቁ የሕዳሴ ግድብ ሥራው ተጠናቆ ጥቅም ላይ እስኪውል ድረስ ቤተ ክርስቲያናችን አስፈላጊውን ድጋፍ ሁሉ እንደማታቋርጥ ቅዲስ ሲኖዶስ ያረጋግጣል፡፡

  9. ሀገራችን ኢትዮጵያ በጤናው ዘርፍ የኅብረተ ሰቡን ጤንነት ለመጠበቅ በተለይም በሀገር አቀፍ ደረጃ ለእናቶችና ለሕፅናት እየተደረገ ያለው ልዩ የጤና እንክብካቤ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ቤተ ክርስቲያናችን ኅብረተሰቡን ከማስተማርና የጉዳዩን ጠቃሚነት ከማስረዳት ባሻገር ለመርሐ ግብሩ መሳካት አስፈላጊውን ድጋፍ እንደምታደረግ ቅዲስ ሲኖዶስ ይገልፃል፡፡

  10. ከሀገር ውጭ ከሚገኙ የቤተ ክርስቲያን አባቶች ጋር የተጀመረው የላም ውይይት በተለያዩ ምክንያቶች እስካሁን የሚፈለገውን የአንድነት ውጤት ባያስገኝም የቤተ ክርስቲያናችን አንድነትና ሰላም ለቤተ ክርስቲያናችንም ሆነ ለሀገራችን እንዲሁም ለሕዝባችን ያለው ትርጉም የላቀ መሆኑን ቅዲስ ሲኖዶስ ስለሚገነዘብ ሁኔታዎች ተመቻችተው የሰላም ውይይቱ እንዲቀጥል ቅዱስ ሲኖዶስ ወስኗል፡፡

  11. ቅዱስ ሲኖዶስ የቤተ ክርስቲያኒቱን መንፈሳዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ተልእኮ ዘመኑ በሚጠይቀው ጥበብና ዕውቀት እየቃኘ ለሃይማኖት፣ ለሀገርና ለሕዝበ ክርስቲያኑ ማበርከት የሚገባውን ሁሉ በብቃት ለመሥራት ከምንም ጊዜ በላይ የተዘጋጀ መሆኑን ሕዝበ ክርስቲያኑቀ ተገንዝቦ እርሱም የበኩሉን ሥራ በቅን መንፈስ እንዲወጣ አበክሮ አሳስቧል፡፡

የቤተ ክርስቲያናችን የመጨረሻ ውሳኔ ሰጭ የሆነው ቅዱስ ሲኖዶስ በየጊዜው የሚያስተላልፋቸው ውሳኔዎችና መመሪያዎች ሁሉ ተፈጻሚነት ኖሮአቸው ጥሩ ውጤት ሊያስገኙ የሚችሉት በሁሉም ደረጃና አካባቢ የሚገኙ የቤተ ክርስቲያናችን ካህናትና ምእመናን ለቅዱስ ሲኖዶስ ውሳኔ ተግባራዊነት በሙሉ ልባዠው ሲሰለፉ እንደሆነ የቅዱስ ሲኖዶስ እምነት ነው፡፡ ስለሆነም ለእናት ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ክብርና ሉዓላዊነት መጠበቅ፣ ለሕልውናዋ መቀጠልና ለዕድገትዋ መስፋፋት የሚቆረቆሩ የቤተ ክርስቲያናችን አገልጋዮችና ተከታዮች በሙሉ ቅዱስ ሲኖዶስ የሚያሳልፋቸውን ውሳኔዎችና መመሪያዎች ለመተግበር አስፈላጊውን ትብብር ሁሉ እንዲያደርጉ በአጽንዖት በማሳሰብ ለዐሥር ቀናት ያህል ሲካሄድ የሰነበተውን ጉባኤ ዛሬ ግንቦት 30 ቀን 2005 ዓ.ም. በጸሎት አጠናቅቋል፡፡

እግዚአብሔር ቅድስት ቤተ ክርስቲያናችንንና ሀገራችን ኢትዮጵያን ይባርክ፤ ይቀድስ፤ አሜን!!

 

አባ ማትየስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ
ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት
ግንቦት 30 ቀን 2005 ዓ.ም.

hamela 5

የጀበራ ማርያም ገዳምን እንደገና ለማቋቋም ጥረት በመደረግ ላይ ነው

ግንቦት 3ዐ ቀን 2ዐዐ5 ዓ.ም.

በእንዳለ ደምስስ

በበሰሜን ጎንደር ዞን ደንቢያ ወረዳ በጣና ሐይቅ ደሴቶች ውስጥ ከሚገኙት ገዳማት አንዱ የሆነውና ለረጅም ዘመናት ጠፍ ሆኖ፤ ፈርሶ የቆየው የጀበራ ማርያም ገዳምን መልሶ ለማቋቋም ጥረት በመደረግ ላይ ነው፡፡

hamela 5የጀበራ ማርያም ገዳም በአፄ አምደ ጽዮን ዘመነ መንግሥት በ13ኛው መቶ ክፍለ ዘመን የተገደመ ሲሆን በደርቡሽ ወረራ ወቅት ከፍተኛ ጉዳት ደርሶበት ሙሉ ለሙሉ ፈርሷል፡፡ ነገር ግን አባቶች መልሰው ገዳሙን በመመሥረት አጽንተውት የነበረ ቢሆንም የኢጣሊያ ጦር ኢትዮጵያን ሲወርር በ1956 ዓ.ም. መምህር ካሳ ፈንታ በሚባሉ አባት ቤተ ክርስቲያኑን በማነጽ፤ ገዳሙን መልሶ በመገደም ጥንት ወደነበረበት ለመመለስ ጥረት አድርገው ነበር፡፡ ነገር ግን እሳቸው ካረፉ በኋላ ከእግራቸው ተተክቶ ገዳሙን አጠናክሮ ለመያዝ የሚችል  አባት በመጥፋቱ ገዳሙ ተፈታ፡፡ የቤተ ክርስቲያኑም እንጨት በምስጥ ተበልቶ በንፋስ ኃይል ስለፈረሰ ታቦቱ ከሐይቁ ማዶ በምትገኘው ቅድስት ሃና ማርያም ቤተ ክርስቲያን ውስጥ እንዲገባ ተደርጓል፡፡

ገዳሙን መልሶ በማቅናት ላይ የሚገኙት አባ ዘወንጌል በገዳሙ ውስጥ ከዚህ ቀደም ለሦስት ዓመታት ቆይተው፤ በችግር ምክንያት በመውጣት ወደ ዝቋላ አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ ገዳም ከሔዱ 20 ዓመት ሆኗቸዋል፡፡ “የገዳሙ መፈታት በመስማቴና ህሊናዬ ሊያርፍ ባለመቻሉ አባቶቻችን ያቆዩልንን ገዳም ዳግም ለመመሥረት ወደዚህ መጣሁ፡፡ ከመጣሁም ገና 3 ወራት ብቻ ናቸው የተቆጠሩት” ይላሉ፡፡

በሦስት ወራት ውስጥ ቤተልሔምና ቤተ እግዚአብሔር /ምግብ ማብሰያ/ ተሰርተው ተጠናቀዋል፡፡ በቀጣይነትም ለመናንያን በዓት፤ የእንግዳ ማረፊያ ቤት፤ ከደሴቱ ማዶ በሚገኘውና የገዳሙ ይዞታ በሆነው አንደhamela 4 ሄክታር መሬት ላይ የሞፈር ቤት ለመሥራት በእንቅስቃሴ ላይ ይገኛሉ፡፡ እነዚህ ሥራዎች እንደተጠናቀቁም በጅምር ላይ የሚገኘውን ቤተ ክርስቲያን ለማነጽ ጥረት እንደሚያደርጉ አባ ዘወንጌል ይገልጻሉ፡፡

ጀበራ ማርያም ገዳም ውስጥ በጾም በጸሎት ተወስነው የሚገኙ አባቶች በጸሎታቸው ወቅት  እጆቻቸው እንደ ከዋክብት ያበሩ ስለነበር በአካባቢው የሚገኙ ምእመናን “እጀበራዎች” እያሉ ይጠሯቸው  ስለነበር የገዳሙ ስያሜ ሆኗል፡፡ በአሁኑ ወቅት በገዳሙ ውስጥ ስድስት መናንያን ብቻ ,ይገኛሉ፡፡

hamela 3

የቅዱስ ሚካኤል ታቦት “ካህኑን” አቃጠለ

ግንቦት 30 ቀን 2005 ዓ.ም.

በዲ/ን ቴዎድሮስ ኃይሉ

 

  • የአብያተ ክርስቲያናት ዝርፊያ ተባብሷል

hamela 3የሐምሌ ቅዱስ ሚካኤል ታቦት ግንቦት 2 ቀን 2005 ዓ.ም. ሌሊት በሌቦች ተዘርፎ ሲወሰድ መንገድ ላይ የዘራፊውን “ካህን” አእምሮውን አስቶ፤ መንገዱን አስትቶ፤ በሰው ማሳ ውስጥ እንዳስገባውና ታቦቱም ወደ ሰማይ እየዘለለ ዘራፊውን እንዳቃጠለ የሀባቦ ጉዱሩ ወረዳ ቤተ ክህነት ሥራ አስኪያጅ ሊቀ ትጉኀን ብዙዓለም ግንባር ተናገሩ፡፡

“እንዲሁም ተጠርጣሪው ‘ወየው ለእኔ፤ ወየው ለእኔ’ እያለ ሲጮህ በአካባቢው አትክልት ሲጠብቁ ያደሩ ሰዎች እንደሰሙ እና ተጠርጣሪው እስር ቤት ከገባ በኋላም ‘እባቦች እየመጡብኝ ነው’ እያለ ለፖሊስ እንደሚያመለክት፤ ፖሊሶችም ወደ ታሰረበት ክፍል ሲገቡ ምንም እባብ እንዳላገኙ” ሊቀ ትጉኀን ብዙዓለም የቅዱስ ሚካኤልን ድንቅ ተአምር መስክረዋል፡፡

በመጽሐፍ ቅዱስ ታቦት ድንቅ የሆነ ገቢረ ተአምራትን እንደሚያደርግ የተጠቀሰ ነው፤ ያሉት ደግሞ በጉዱሩና በሀባቦ ጉዱሩ ወረዳዎች በሰባኬ ወንጌልነት የሚያገለግሉት ቆሞስ አባ ወልደ ገብርኤል አበበ ሲሆኑ፤ የሐምሌ ቅዱስ ሚካኤል ታቦትም ገቢረ ተአምሩን ሊሰርቅ በሞከረው “ካህን” ላይ አሳይቷል ብለዋል፡፡

የሐምሌ ቅዱስ ሚካኤል ቤተ ክርስቲያን አገልጋይ ቄስ ዋለ ዓለሙ ስለ ሐምሌ ቅዱስ ሚካኤል ቤተ ክርስቲያን የዘረፋ ሙከራ እንዳመለከቱት “በዕድሜ ዘመኔ እንዲህ ያለ ነገር ተመልክቼ አላውቅም፡፡ በዚህ ዓመት ብቻ የሐምሌ ቅዱስ ሚካኤል ቤተ ክርስቲያን ሁለት ጊዜ (ኅዳር 10 እና ግንቦት 2 ቀን 2005 ዓ.ም) ተዘርፏል፡፡ የግንቦት ሁለት ቀን ግን ለየት ያለ ነበር፡፡ በዕለቱ ታቦት፣ ሙዳየ ምጽዋት፣ መስቀልና መጽሐፍ ባልታወቁ “ካህናት” ተዘርፈው ታቦቱ ከአንድ ኪሎ ሜትር ርቀት በላይ ተወሰዶ በአንድ ሕፃን ልጅና በሦስት ሴቶች ተገኝቷል”  በማለት አስረድተዋል፡፡

የተዘረፈውን ታቦት የእርሻ ማሳ ውስጥ ተቀምጦ ከተመለከቱት ልጆች መካከል ብዙነሽ ዓለማየሁ ስለሁኔታው ስትናገር “አራት ሆነን በአህያዎቻችን ዕቃ ጭነን ወደ ገበያ ስንሄድ ከሐምሌ ቅዱስ ሚካኤል ቤተ ክርስቲያን አካባቢ ካሉ የእርሻ ማሳ ደረስን፡፡ በዚህን ጊዜ አብሮን የነበረው ሕፃን የቤተ ክርስቲያን መጽሐፍ የሚመስል ነገር አየና ለእኛም አሳየን፡፡ እኛም ወንጌል መስሎን ለመሳለም አንሥተን ለመሳለም ስንሞከር አቃተን፤ አንቀጠቀጠን፡፡ ፈርተን አህዮችን ነድተን ልንሄድ ስንል አህዮች ቀድመው ስለወደቁ መነሣት አልቻሉም፡፡ አህዩችን ለማስነሣት ብንሞክርም አልተቻለም፡፡ በመጨረሻ ነገሩ ተአምር መሆኑን ስለተረዳን ለዲያቆናት ስልክ ደወልን” በማለት ምስክርነቷን ሰጥታለች፡፡

ወንጌል መስሏት ለመሣለም የፈለገችው እንሰኔ ዓለማየሁ ስለተመለከተችው ተአምር ስትገልጽ “ጠጋ ብዬ ላነሣው ስሞክር ቀኝ እጄን አሸማቀቀኝ፣ ለዲያቆን ታደለ ደወልን፤ እርሱ መጥቶ ታቦቱ ላይ ፎጣውን አልብሶ ካህናት ሊጠራ ሔደ፤ ከፎጣው ብርሃን ሲወጣ ስንመለከት፤ ታቦቱ የተቃጠለ መሰሎን አለቀስን፤ ታቦቱ ግን ምንም አልሆነም” ብላለች፡፡ አያይዛም ታቦቱን አስቀድሞ የተመለከተው ሕፃን ሌሊቱን ሙሉ ሲባንን ማደሩን አውስታለች፡፡

የሬፍ ቶኮ ታኔ ቀበሌ ገበሬ ማኅበር ሊቀ መንበር ኮንስታብል ደረጀ ጉቱ ስለሁኔታው  ሲያስረዱ “የቤተ ክርስቲያኑን መሰበር የሰማነው ከጠዋቱ ሁለት ሰዓት ላይ ሲሆን፤ ታቦቱንም ሚግሮ ዳሞት አካባቢ ወድቆ፤ በአካባቢውም መዝሙረ ዳዊትና የተሰበሩ ሦስት ባንኮኒዎችን አገኘን፡፡ በመዝሙረ ዳዊቱ ላይ ባገኘነው ማስታወሻ መሠረት ተጠርጣሪውን ልንይዝ ችለናል” ብለዋል፡፡

“ታቦቱን ካለበት ቦታ ማን ያነሰዋል እያልን ስንመካከር ከመካከላችን የነበረ አንድ የሌላ እምነት ተከታይ ‘እኔ አነሣለሁ’ ብሎ ቀረበ፤ ነገር ግን ታቦቱን ሲቀርብ ፈራ፤ ‘ሰውነቴን አቃጠለኝ ራሴን አቃጠለኝ እንደ አንድ ነገር አደረገኝ’ ብሎ በመደንግጥ ሄደ” በማለት ኮንስታብል ደረጀ ተናግሯል፡፡

hamela 2
ታቦታቱን ለማክበር ከመጡት አባቶች መካከል ቆሞስ አባ ወልደ ገብርኤል ስለሁኔታው ሲናገሩ “ታቦቱን ዘራፊው አስቀምጦት የሄደበት ቦታ ዙሪያ ገባው ጭቃ ነበር፡፡ ይህ ጭቃ ታቦቱን ሳይነካ በታቦቱ ዙሪያ መሆኑ የሚያመለክተው ታቦቱ ሌባውን አስሮት ማቆየቱና ሌባው ታቦቱን በዙሪያው ሲዞር ማደሩን የሚያመለክት ነው” ሲሉ አስገንዝበዋል፡፡

ታቦቱ የተገኘው በእኛ የእርሻ ማሳ ላይ ነው፤ የሚሉት የፕሮቴስታንት እምነት ተከታይ የሆኑት ግለሰቦች በበኩላቸው “ታቦቱ እኛ ማሳ ጋር ሲደርስ አልሄድም ማለቱ እግዚአብሔር ስለወደደን ነው፡፡ ይህ ታቦቱ ያረፈበት መሬት የበረከት መሬት ነው” ሲሉ ታቦቱ የተገኘበትን ቦታ ከልለው ለቤተ ክርስቲያን መስጠታቸውን ተናግረዋል፡፡

ታቦተ ሚካኤል ድንቅ የሆነ ሥራውን በዐደባባይ ሠርቶ በሆታና በዝማሬ ግንቦት 3 ቀን 2005 ዓ.ም ወደ መንበረ ክብሩ መመለሱን ቄስ ጋሸነው እንዳላማው አስታውቀዋል፡፡

በተያያዘም ሊቀ ትጉኀን ቀሲስ ብዙዓለም በወረዳቸው ስለተፈጸሙ የአብያተ ክርስቲያናት ዘረፋ እንዳስታወቁት “ከሰኔ 2004 ዓ.ም እስከ ግንቦት 2005 ዓ.ም በወረዳው ካሉ ዐሥራ አንድ አብያተ ክርስቲያናት ውስጥ በፎቃ መድኀኔዓለም ቤተ ክርስቲያን፣ በእንባቦ ቅዱስ ተክለ ሃይማኖት ቤተ ክርስቲያን፣ ሎያ ቅድስት ማርያም ቤተ ክርስቲያን እና በሐምሌ ቅዱስ ሚካኤል ቤተ ክርስቲያን ላይ ሁለት ጊዜና ከዚያ በላይ ዘረፋና የዘረፋ ሙከራ ተካሂዶባቸዋል፡፡ እንዲሁም ብራና መጽሐፍት፤ መስቀሎች፤ መጋረጃዎችና መጎናጸፍያ እንዲሁም ሙዳየ ምጽዋቶች መወሰዳቸውን ተናግረዋል፡፡

የፎቃ መድኀኔዓለም ቤተ ክርስቲያን አስተዳዳሪ የሆኑት ቄስ ዘላለም ጌትነት በበኩላቸው በፎቃ መድኀኔዓለም ቤተ ክርስቲያን ላይ ከፍተኛ የሆነ የዘረፋ ሙከራ እየተደረገ በመሆኑ ለአገልግሎት መቸገራቸውን ተናግረዋል፡፡

የፎቃ መድኀኔዓለም ቤተ ክርስቲያን ዘበኛ አቶ አሰፋ ትእዛዙ ከዘራፊዎቹ ስለገጠማቸው ጥቃት ሲናገሩ “ዓምና በግንቦት ወር ላይ ከምሽቱ አምስት ሰዓት አካባቢ ሦስት ሌቦች መጥተው የቤተ ክርስቲያኑን በር ነኩ፡፡ በራፉ ላይ ያስቀመጥኩት ቆርቆሮ መሳይ ነገር ወደ መሬት በመውደቅ ድምፅ አሰማኝ፡፡ እኔም በፍጥነት በመነሣት ባትሪ ሳበራ ሌቦቹ ጨለማውን ተገን አድርገው ወደ እኔ መጡ፡፡ በገጀራ ሊመቱኝም ሞከሩ፤ ነገር ግን በእግዚአብሔር ጥበቃ በትራቸውን ዛፉ ከለከለው፡፡ በመጨረሻም እግሬን በአንካሴ ወጉኝ፡፡” ብለው ዘራፊዎቹ የተደራጁ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡

በተመሳሳይም በወረዳው ካሉ አብያተ ክርስቲያናት የዘረፋ ጥቃት ከደረሰባቸው አብያተ ክርስቲያናት መካከል አንዱ የእንባቦ ተክለሃይማኖት ቤተ ክርስቲያን አንዱ ነው ያሉት ደግሞ አቶ ዘላለም ኩምሳ ናቸው፡፡

አቶ ዘላለም የእንባቦ ተክለሃይማኖት ቤተ ክርስቲያን በንጉሥ ተክለ ሃይማኖት የታነጸና ረዥም ዕድሜ ያለው በመሆኑ ዘራፊዎችም ከፍተኛ ትኩረት ያደርጉበታል፡፡ ለዚህም ለሦስት ጊዜያት ያህል ሌቦች የዘረፋ ሙከራ እንዳካሄዱበትና የቤተ ክርስቲያኑን ቁልፍና ካዝና በመስበር መጋረጃዎች እንደተወሰዱ ተናግረዋል፡፡

በጥርጣሬ የተያዙ አካላትና መዝረፋቸውን ያመኑ ሰዎች አሉ የሚሉት ደግሞ የወረዳው የፖሊስ ናቸው፡፡ ቢሮው ማንኛውንም ችግሮች ለማስወገድ ቀን ከሌሊት እንደሚሠራና በየቀበሌው ፖሊስ በማስቀመጥ፣ ለሕዝቡ ስለ ሌብነት በማስተማር፣ ለጥበቃ አካላት ሥልጠና በመሥጠት እንደ ሀገር ይሠራል፡፡” ብለዋል፡፡

አያይዘውም “በጥርጣሬ የተያዙ ሌቦችንም ማስረጃ አቅርበን ተገቢውን ፍርድ እንደሚያገኙ እናምናለን  ሕዝቡም ሊተባበር ይገባል” ሲሉ አሳስበዋል፡፡

የሀባቦ ጉዱሩ ወረዳ ቤተ ክህነት የሚገኘው ከአዲስ አበባ በስተ ምዕራብ በቀድሞው ወለጋ ሀገረ ስብከት በአሁኑ ደግሞ ሆሮ ጉዱሩ ወለጋ ሀገረ ስብከት ተብሎ በሚጠራው ሥር ሲሆን በወረዳ ቤተ ክህነቱ ሥር አሥራ አንድ አብያተ ክርስቲያናት መኖራቸውን ለማወቅ ተችሏል፡፡