senod 2005

የቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ ተጠናቀቀ

ግንቦት 30 ቀን 2005 ዓ.ም.

በእንዳለ ደምስስ

senod 2005

ከግንቦት 21 ቀን ጀምሮ እስከ ግንቦት 30 2005 ዓ.ም.  ድረስ ሲካሔድ የሰነበተው የቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ ለቤተ ክርስቲያኗ አስፈላጊ ናቸው ያላቸውን ውሳኔዎች በማሳለፍ ተጠናቀቀ፡፡ በዚህም መሠረት የሚከተሉትን ጠቅለል ያሉ ውሣኔዎች ተላልፈዋል፡፡  በቤተ ክርስቲያኒቱ ላይ የሚታዩ ብልሹ የአስተዳደርና የአሰራር ችግሮችን  ማሻሻል፤ ጥራት የጎደለው የፋይናንስ አያያዝን መዋጋት፤ ሙስናንና ለብክነት የተጋለጡ አሰራሮችን ለመቅረፍ እንዲቻል ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት፤ ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን፤ ምሁራንና ምእመናን የሚገኙበት ዓብይ ኮሚቴ ማዋቀሩን ይፋ ማድረግ፡፡ በተጨማሪም የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት በአንድ ሀገረ ስብከት፤ በአንድ የቅዱስ ፓትርያርክ ረዳት ሊቀ ጳጳስ እንዲመራ የተደረገ ሲሆን ፤ የመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ጽ/ቤት ዋና ሥራ አስኪያጅና የቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ጸሓፊ ምርጫም ተከናውኗል፡፡ ከሀገር ውጪ ከሚገኙ የቤተ ክርስቲያን አባቶች ጋር የተጀመረው የሰላም ውይይት ጥረት እንደሚቀጥልም የቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ ውሳኔ አሳልፏል፡፡

ዝርዝር መግለጫውን ከዚህ በታች እንደሚከተለው አቅርበነዋል፡፡

 

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን

    በፍትሕ መንፈሳዊ አንቀጽ 5 ቁጥር 164 ላይ ከበዐለ ትንሣኤ በኋላ በሃያ አምስተኛው ቀን  ቅዱስ ሲኖዶስ ጉባኤ እንዲካሔድ በተደነገገው ቀኖና ቤተ ክርስቲያን መሠረት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ ከግንቦት 21 – 30 ቀን 2005 ዓ.ም. ተካሒዷል፡፡ ይህ ጉባኤ የርክበ ካህናት ጉባኤ ተብሎ የሚታወቅ ሲሆን ከላ በተጠቀሰው ቀኖና ቤተ ክርስቲያን እንደተገለጸው ብፁዐን ሊቃነ ጳጳሳት በቤተ ክርስቲያን ያለውን አጠቃላይ መንፈሳዊ፤ ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ጉዳዮችን በማየት በመንፈስ ቅዱስ መሪነት ታላላቅ ውሳኔዎችን የሚወሰንበት ዓብይ ጉባኤ ነው፡፡

    ቅዱስ ሲኖዶስ በቤተ ክርስቲያናችን ውስጥ ያሉትን ወቅታዊና ነባራዊ ጉዳዮችን ለመመርመርና ለመገምገም ባለው ሐዋርያዊ ኃላፊነት ለቤተ ክርስቲያን መንፈሳዊ ተልእኮ አፈጻጸም እንቅፋት ናቸው ብሎ ያመነባቸውን ጉዳዮች በአጀንዳ ቀርጾ፤ በስፋትና በጥልቀት ተወያይቶ ውሳኔ ሰጥቶባቸዋል፡፡ ቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን በምድር ላይ ያለች የእግዚአብሔር መንግስት ማዕከል፤ በባሕርይዋም ንጽሕትና ቅድስት ብትሆንም ኃጢአትና ስሕተት በነገሰበት ዓለም ያለች በመሆንዋ ከእርስዋ መሠረታዊ ባሕርይ ጋር የማይስማሙ ተግባራት እንዳይጋቡባት የመጀመሪያው ጥበቃ በብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት ላይ ያረፈ ነው፡፡ በተለይም የአሁኑ ዓላማችን ጥበብ ባፈራው የአሠራር ዕውቀት በየቀኑ በለውጥ ጎዳና በሚራመድበት ጊዜ ቤተ ክርስቲያናችንም ከዓለሙ በተሻለና በበለጠ በመንፈሳዊና በአእምሮአዊ ጥበብ ሕዝበ ክርስቲያኑን መምራት፤ ማስተማርና ማገልገል ይጠበቅባታል፡፡ በቤተ ክርስቲያናችን እነዚህን የተቀደሱ ተግባራት በሥራ ለመተርጎም ወቅታዊ እንቅፋት ሊሆኑ የሚችሉ ነገሮች ምን ምን ናቸው? በማለት ቅዱስ ሲኖዶስ በጥልቀት ተመልክቶአል፡፡

    በዚህ መሠረት ጉባኤው ብዙ ውይይት ካደረገ በኋላ የሚከተሉትን ዓበይት ውሳኔዎችን አሳልፎአል፡፡

 

  1. በየሥራ ዘርፉ እየተከሠተ ያለው የመልካም አስተዳደርን ችግር በተለይም ብልሹ አስተዳደርና አሠራር፤ ዘመኑን ያልዋጀና ጥራት የጎደለው የፋይናንስ አያያዝ፤ እንደዚሁም ለሙስናና ለብክነት የተጋለጡ አሠራሮች ሁሉ ወሳኝ በሆነ መልኩ ለመቅረፍና ለማድረቅ፣ ከዚህም ጋር ቤተ ክርስቲያናችን በመሪ እቅድ መሥራት የምትችልበትን አሠራር ለመቀየስ፣ ቅዱስ ሲኖዶስ፡- ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት፣ ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን፣ ምሁራን ምእመናን የሚገኙበት ዓቢይ ኮሚቴ ተቋቁሞ ጉዳዮን የማጣራትና የማጥናት ሥራውን እንዲቀጥል ተስማምቶ በአንድ ድምፅ ወሰኖአል፡፡

  2. የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ለሌሎች አህጉረ ስብከት በመልካም አስተዳደርና በፋይናንስ አያያዝ፣ እንደዚሁም በስብከተ ወንጌልና በአገልግሎት አሰጣጥ ለሌሎች እንደዚሁም በመልካም አስተዳደር፣ በፋይናንስ አያያዝና በሰው ኀይል አመዳደብ የሕግ የበላይነትን አክብሮ እንዲሠራ አስፈላጊውን ክትትል ሁሉ በቋሚ ሲኖዶስና በመንበረ ፓትርያርኩ ጥብቅ ክትትል እንዲደረግ፤

  3. የቤተ ክርስቲያናችን የሕይወት ምንጭ የሆነውን የስብከተ ወንግል ትምህርት በሰው ኀይል፣ በሚድያም ጭምር እየታገዘ በመላው ዓለም ላሉ የቤተ ክርስቲያናችን ተከታዮች ትምህርቱን በጥራትና በጥልቀት ይሰጥ ዘንድ አስፈፋሚው አካል ጠንከር ያለ ሥራ እንዲሠራ ቅዱስ ሲኖዶስ በሙሉ ድምጽ ወስኗል፡፡ የመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ጽ/ቤት ዋና ሥራ አስኪያጅና የቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ጸሐፊ ምርጫ በየሦስት ዓመቱ እንዲካሄድ ሕገ ቤተ ክርስቲያን ባስቀመጠው ድንጋጌ መሠረት ብፁዕ አቡነ ማቴዎስ፤ የወላይታ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ፤ የመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ጽ/ቤት ዋና ሥራ አስኪያጅ፤ ብፁዕ አቡነ ሉቃስ፤ የሰቲት ሑመራ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ የቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ጸሐፊ አድርጎ ቅዱስ ሲኖዶስ መርጧቸዋል፡፡

  4. ብፁዕ አቡነ እስጢፋኖስ የጅማ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት የብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርክ ረዳት ሊቀ ጳጳስ ሆነው እንዲሠሩ፤ እንደዚሁም የምራቅና ሰሜን አዲስ አበባ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ዳንኤል በኢየሩሳሌም የኢትዮጵያ ገዳማት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ዳንኤል በኢየሩሳሌም የኢትዮጵያ ገዳማት ሊቀ ጳጳስ ሆነው እንዲሠሩ ቅዱስ ሲኖዶስ ወስኗል፡፡

  5. በመካከለኛው ምሥራቅና በሌሎች የዓለም ክፍሎች ለሥራ ፍለጋ በሕገ ወጥ መንገድ በሚሄዱ ልጆቻችንና ወገኖቻችን ላይ እየደረሰ ያለውን ዘግናኝ ድርጊት ለማስቆም መንግሥት እያደረገ ያለው ጥረት ቤተ ክርስቲያናችን በሙሉ ልብ እንደምትደግፈውና ለስኬቱም የበኩሏን እንደምትወጣ፣ ለዚህም በየደረጃው ያሉ መምህራን፣ ካህናትና ሰባክያን ሁሉ የዚህን ጎጂነት ደጋግመው በማስረዳትና በማስተማር ሕዝቡ ግንዛቤ እንዲኖረው ጠንክረው እንዲያስተምሩ ቅዱስ ሲኖዶስ መመሪያ ሰጥቷል፡፡

  6. የሀገራችን ሕዝቦች ከድህነትና ከኋላ ቀርነት ተላቀው መካከለኛ ገቢ ካላቸው ሀገሮች ጋር እኩል ለማሰለፍ በሚደረገው ሁለንተናዊ የልማት ተግባር ቤተ ክርስቲያናችን ከሕዝቡና ከመንግሥት ጎን በመሆን የሚጠበቅባትን ሁሉ እንደምታደርግ ቅዱስ ሲኖዶስ አረጋግጧል፡፡

  7. ኢትዮጵያ ሀገራችን በሀገር ውስጥ፣ በምሥራቅ አፍሪካ፣ በመላ አፍሪካ ከዚያም በመላው ዓለም ሰላም እንዲሰፍን፣ የሰው ልጅ እኩልነትና መብት እንዲከበር፣ ፍትሐዊ የሆነ የሀብት አጠቃቀም እንዲኖር፣ የአየር መዛባትን ለመቋቋም የአረንጓዴ ልማት ሀብት እንዲስፋፋ የምታደርገውን ያላሰለሰ ጥረት ቅዱስ ሲኖዶስ በእጅጉ እያደነቀ የሀገሪቱን መልካም ዝናና በጎ ገጽታ ለመጠበቅ የበኩሉን ጠንክሮ እንዲሠራ አረጋግጧል፡፡

  8. በሀገራችን የዕድገት ሂደት ከፍተኛ ሚና ይጫወታል ተብሎ በመገንባት የሚገኘው ታላቁ የሕዳሴ ግድብ ሥራው ተጠናቆ ጥቅም ላይ እስኪውል ድረስ ቤተ ክርስቲያናችን አስፈላጊውን ድጋፍ ሁሉ እንደማታቋርጥ ቅዲስ ሲኖዶስ ያረጋግጣል፡፡

  9. ሀገራችን ኢትዮጵያ በጤናው ዘርፍ የኅብረተ ሰቡን ጤንነት ለመጠበቅ በተለይም በሀገር አቀፍ ደረጃ ለእናቶችና ለሕፅናት እየተደረገ ያለው ልዩ የጤና እንክብካቤ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ቤተ ክርስቲያናችን ኅብረተሰቡን ከማስተማርና የጉዳዩን ጠቃሚነት ከማስረዳት ባሻገር ለመርሐ ግብሩ መሳካት አስፈላጊውን ድጋፍ እንደምታደረግ ቅዲስ ሲኖዶስ ይገልፃል፡፡

  10. ከሀገር ውጭ ከሚገኙ የቤተ ክርስቲያን አባቶች ጋር የተጀመረው የላም ውይይት በተለያዩ ምክንያቶች እስካሁን የሚፈለገውን የአንድነት ውጤት ባያስገኝም የቤተ ክርስቲያናችን አንድነትና ሰላም ለቤተ ክርስቲያናችንም ሆነ ለሀገራችን እንዲሁም ለሕዝባችን ያለው ትርጉም የላቀ መሆኑን ቅዲስ ሲኖዶስ ስለሚገነዘብ ሁኔታዎች ተመቻችተው የሰላም ውይይቱ እንዲቀጥል ቅዱስ ሲኖዶስ ወስኗል፡፡

  11. ቅዱስ ሲኖዶስ የቤተ ክርስቲያኒቱን መንፈሳዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ተልእኮ ዘመኑ በሚጠይቀው ጥበብና ዕውቀት እየቃኘ ለሃይማኖት፣ ለሀገርና ለሕዝበ ክርስቲያኑ ማበርከት የሚገባውን ሁሉ በብቃት ለመሥራት ከምንም ጊዜ በላይ የተዘጋጀ መሆኑን ሕዝበ ክርስቲያኑቀ ተገንዝቦ እርሱም የበኩሉን ሥራ በቅን መንፈስ እንዲወጣ አበክሮ አሳስቧል፡፡

የቤተ ክርስቲያናችን የመጨረሻ ውሳኔ ሰጭ የሆነው ቅዱስ ሲኖዶስ በየጊዜው የሚያስተላልፋቸው ውሳኔዎችና መመሪያዎች ሁሉ ተፈጻሚነት ኖሮአቸው ጥሩ ውጤት ሊያስገኙ የሚችሉት በሁሉም ደረጃና አካባቢ የሚገኙ የቤተ ክርስቲያናችን ካህናትና ምእመናን ለቅዱስ ሲኖዶስ ውሳኔ ተግባራዊነት በሙሉ ልባዠው ሲሰለፉ እንደሆነ የቅዱስ ሲኖዶስ እምነት ነው፡፡ ስለሆነም ለእናት ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ክብርና ሉዓላዊነት መጠበቅ፣ ለሕልውናዋ መቀጠልና ለዕድገትዋ መስፋፋት የሚቆረቆሩ የቤተ ክርስቲያናችን አገልጋዮችና ተከታዮች በሙሉ ቅዱስ ሲኖዶስ የሚያሳልፋቸውን ውሳኔዎችና መመሪያዎች ለመተግበር አስፈላጊውን ትብብር ሁሉ እንዲያደርጉ በአጽንዖት በማሳሰብ ለዐሥር ቀናት ያህል ሲካሄድ የሰነበተውን ጉባኤ ዛሬ ግንቦት 30 ቀን 2005 ዓ.ም. በጸሎት አጠናቅቋል፡፡

እግዚአብሔር ቅድስት ቤተ ክርስቲያናችንንና ሀገራችን ኢትዮጵያን ይባርክ፤ ይቀድስ፤ አሜን!!

 

አባ ማትየስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ
ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት
ግንቦት 30 ቀን 2005 ዓ.ም.