የአዲስ አበባ ማእከል 18ኛ መደበኛ ጠቅላላ ጉባኤ ተካሄደ፡፡

ጥቅምት 22 ቀን 2005 ዓ.ም.

በእንዳለ ደምስስ


የአዲስ አበባ ማእከል 18ኛ ጠቅላላ ጉባኤ ከጥቅምት 17-18 ቀን 2005 ዓ.ም. በጠቅላይ ቤተ ክህነት ስብከተ ወንጌል አዳራሽ ለሁለት ቀናት ተካሄደ፡፡

 

መርሐ ግብሩ በመንበረ ልዑል ቅዱስ ማርቆስ ቤተ ክርስቲያን ልዑካን ጸሎተ ወንጌል በማድረስ በብፁዕ አቡነ ዮሴፍ የባሌ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ቡራኬና ጸሎት ተጀምሯል፡፡

 

በአዲስ አበባ ማእከል ሰብሳቢ በዲያቆን አንዱ ዓለም ኀይሉ የመክፈቻ ንግግር ጉባኤው የቀጠለ ሲሆን በመንበረ ፓትርያርክ ቅድስት ማርያም ገዳም የፈለገ ሕይወት ሰንበት ትምህርት ቤት አባላት ያሬዳዊ ዝማሬ በማቅረብ የወንጌል ትምህርት በቀሲስ ፋሲል ታደሰ ተሰጥቷል፡፡

 

በተያዘለት የጊዜ መርሐ ግብር መሠረት የ2004 ዓ.ም. ዓመታዊ እቅድ ክንውን አፈጻጸምና የ2003 ዓ.ም. ኦዲትና ኢንስፔክሽን ሪፖርት ቀርቧል፡፡

 

በ2004 ዓ.ም. ዓመታዊ እቅድ ክንውን በተመለከተ ማእከሉ የማኅበረ ቅዱሳንን የማስፈጸም አቅም ከማጎልበት አንጻር፣ ግቢ ጉባኤያትን ለቤተ ክርስቲያን አገልግሎት ማብቃት፣ ስብከተ ወንጌልን ማስፋፋት፣ አጽራረ ቤተ ክርስቲያን በቤተ ክርስቲያን ላይ የሚያደርሱትን ጥቃት መግታት፣ የቅዱሳት መካናት፣ የአብነት ትምህርት ቤቶችንና ሰንበት ትምህርት ቤቶችን አቅም ከማጠናከር አንጻር የቤተ ክርስቲያንን እና የምእመናንን ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ተሳትፎ ማሳደግ፣ ጠንካራ የመረጃ ሥርዓት እና ሚዲያ መዘርጋት በሚሉ ርዕሰ ጉዳዮች ላይ የታቀዱትን በማስፈጸም ረገድ የተከናወኑትን በዝርዝር ቀርበዋል፡፡ በተጨማሪም ደጋፊ ተግባራት ተብለው በእቅድ የተያዘለትን የጽ/ቤት፣ የአባላት አገልግሎት ማስተባበሪያ ክፍል፣ ግቢ ጉባኤ አገልግሎት ማስተባበሪያ ክፍል፣ ትምህርትና ሐዋርያዊ አገልግሎት ክፍል፣ የልማት ተቋማት አስተዳደር፣ ማኅበራዊ አገልግሎትና ልማት ክፍል ሂሣብና ንብረት ክፍል፣ የእቅድ ዝግጅትና ክትትል ክፍሎችን የወረዳ ማእከላት አጠቃላይ አፈጸጸም የተከናወኑትን በመቶኛ በማስላት ቀርበዋል፡፡

 

በአገልግሎት ላይ በዓመቱ ውስጥ ያጋጠሙ ችግሮች በሪፓርቱ የተዳሰሱ ሲሆን በተለይም ከሀገረ ስብከት ጋር ከተወሰኑ የአገልግሎት ግንኙነት በዘለለ ጠንካራ ግንኙነት ለመፍጠር ምላሽ ማጣት፣ ልምድ ያላቸው የግቢ ጉባኤያትን በሚገባ ሊመሩ ሊቆጣጠሩ የሚችሉ የግቢ ጉባኤያትን ሙሉ በሙሉ የሚያስተባብሩ አስተባባሪዎች ያለማግኘት ወርኀዊ አስተዋጽኦ በማሰባሰብ ሂደት ውስጥ የክፍሎች ተሳትፎ ማነስ ይጠቀሳሉ፡፡

 

ትኩረት ከሚሹ ጉዳዮች መካከልም ከሰንበት ትምህርት ቤቶች አንድነት ጋር ግንኙነት ማጠናከር፣ የሠራተኛ ጉባኤትን አያያዝና ቀጣይ ሂደት፣ ከቁጥር ይልቅ ጥራት ላይ ትኩረት ማድረግ እንደሚገባ ተገልጿል፡፡

 

በቀረበው ሪፖርት ላይ መነሻ በማድረግ ከተሳታፊዎች ለቀረቡ ጥያቄዎች በሚመለከታቸው የክፍሉ ሓላፊዎች ምላሽ ተሰጥቷቸዋል፡፡

 

ከሰዓት በኋላ በተደረገው መርሐ ግብር ላይ በማኅበረ ቅዱሳን የወረዳ ማእከላት የአገልግሎት እና የወደፊት አቅጣጫ ዳሰሳዊ ጥናት ለጠቅላላ ጉባኤው ቀርቧል፡፡ በጥናቱ ላይ ከተካተቱት ዋና ዋና ጉዳዮች መካከል የአባላት ተሳትፎ የወረዳ ማእከላት እንቅስቃሴ፣ የአጥቢያ ቤተ ክርስቲያናት ከማኅበረ ቅዱሳን ወረዳ ማእከላት ጋር ያለው ክፍተት የወረዳ ማእከላት ከአዲስ አበባ ማእከል ጋር ያላቸው ግንኙነት በጥናቱ የተዳሰሱ ሲሆን ሊወሰዱ የሚገባቸው መፍትሔዎች ከአባላት፣ ከወረዳ ማእከላት፣ ከሰንበት ትምህርት ቤቶች ከስብከተ ወንጌል ከሰንበት ትምህርት ቤቶች ኅብረት የሚጠበቁትን በዝርዝር አቅርበዋል፡፡ በመጨረሻም በቀረበው ጥናት ላይ ውይይት ተደርጓል፡፡

 

በማግስቱ እሑድ ጥቅምት 18 ቀን 2004 ዓ.ም. በተካሄደው የጠቅላላ ጉባኤ ውሎ ሥልታዊ አገልግሎት ለቤተ ክርስቲያን ሁለንተናዊ እድገት ከማእከላት አቅም አንጻር በሚል ርዕስ ጥናት የቀረበ ሲሆን በጥናቱ ላይ ውይይት ተካሂዶበታል፡፡ የወንጌል ትምህርት፣ የ2005 ዓ.ም. የሥራና የበጀት እቅድ፣ በእቅዱ ላይ የተካሄደ ውይይትና በማእከሉ መዘምራን ያሬዳዊ ዝማሬ ቀርበዋል፡፡ በመጨረሻም የዋናው ማእከል መልእክት በማድመጥ መርሐ ግብሩ በጸሎት ተጠናቋል፡፡