ጽድቅ

ጥር ፳፮ ቀን ፳፻፲፫ ዓ.ም.

ጽድቅ ማለት እውነት፣ ርግጥ፣ ቅንነት እንደሆነ አለቃ ኪዳነ ወልድ ክፍሌ በመጽሐፈ ሰዋስው ወግስ ወመዝገበ ቃላት ሐዲስ መጽሐፋቸው ውስጥ ገልጸዋል፡፡ በመጽሕፍ ቅዱስ ላይ እንደተጻፈው ደግሞ ሰው በእግዚአብሔር ታምኖ በፊቱም ክብርና ሞገስ የሚያስገኝለት በጎ ሥራ ጽድቅ ይባላል፡፡ ‹‹መጽሐፍ፥ አብርሃም በእግዚአብሔር አመነ፤ ጽድቅ ሆኖም ተቈጠረለት የሚለው ተፈጸመ፤ የእግዚአብሔርም ወዳጅ ተባለ፤ ሰው በሥራ እንደሚጸድቅ በእምነት ብቻም እንዳይደለ ታያለህን? እንዲሁ ዘማይቱ ረአብ ደግሞ ጕበኞችን ተቀብላ፥ በሌላ መንገድ ባወጣቻቸው ጊዜ በሥራ አልጸደቀችምን? ከነፍስ የተለየ ሥጋ የሞተ እንደ ሆነ፥ እንዲሁ ደግሞ ከሥራ የተለየ እምነት የሞተ ነው›› እንዲል፤ (ገጽ ፯፻፵፮፣ ያዕ. ፪-፳፬-፳፮)

የጽድቅ ሥራን ለመሥራት በመጀመሪያ የእግዚአብሔርን ሕልውና በመረዳት እና በማመን፤ እርሱን ደስ የሚያሰኝ ሥራን መተግበር ያስፈልጋል፡፡ አብርሃም ፈጣሪውን ለማወቅ ሽቶ በሰማይና በምድር ያሉትን ፍጥረታት እንደመረመረ፤ አምላኩ እግዚአብሔርን በማወቅ በእርሱ ታምኖ በጽድቅ እንደኖረ እንዲሁም እርሱን እስከማናገር የደረሰ ጻድቅ ሰው እንደነበር በመጽሐፍ ቅዱስ ተጽፎ እናገኘዋለን፡፡ ጻድቃን በሕይወት ዘመናቸው በሙሉ ለእግዚአብሔር ታምነው በጽድቅ ሥራ ይኖራሉ፤ በመጽሐፈ ሄኖክ እንደተገለጸው በጎ ሥራን የሚፈጽሙ ሰዎች በመሆናቸው እስከ ሕልፈተ ሕይወታቸው ድረስ ፈጣሪያቸውን ደስ የሚያሰኙ ናቸው፡፡ (ዘፍ. ፲፪-፳፭)

እንደ አብርሃም ያሉ ጻድቃን ሰዎች የእግዚብሔር ምርጥ ልጆቹ በመሆናቸው ክብራቸው ታላቅ ነው፡፡ ‹‹እናንተ ጻድቃንና የተመረጣችሁ፥ ብፁዓን ናችሁ፤ ዕድላችሁ ክቡር ነውና፡፡ ጻድቃን በፀሐይ ብርሃን፥ የተመረጡትም በዘለዓለማዊ የሕይወት ብርሃን ይሆናሉ፡፡ ለሕይወታቸው ዘመንም ፍጻሜ የለውም፥ ለቅዱሳንም የዘመን ቊጥር የላቸውም፡፡›› (ሄኖ. ፲፭፥፳፱-፴፰)
የጽድቅን መሥራት በደስታም ሆነ መከራም ጊዜ መሆን አለበት፤ በየትኛውም የበጎም ሆነ የመከራ ዘመን ውስጥ ሆነን በእምነትና በሃይማኖታችን በመጽናት በጎ ሥራን ከመፈጸም ወደኋላ ማለት የለብንም፡፡ ጻድቃን በችግርም ሆነ በመከራ ጊዜ ስለ ጽድቅ ይተጋሉ፤ ይራባሉ፤ ይጠማሉም፡፡ ‹‹ስለጽድቅ የሚራቡና የሚጠሙ ብፁዓን ናቸው ይጠግባሉና›› እንዲል፤ በዚህ ዓለም ብዙ የተፈተኑ፣ ሥቃይን የተቀበሉና ለሃይማኖታቸው መሥዋዕትን የሚከፈሉ ጻድቃን መንግሥተ ሰማያትን ይወርሳሉ፡፡ (ማቴ.፭፥ ፮)

ኃጥአን ግን በምድር እና ጊዜያዊ በሆነው ሕይወት ተታለውና ለሥጋቸው ተገዝተው የሚኖሩ በመሆናቸውና መብልና መጠጥ በማብዛታቸው ለጥፋት ይዳረጋሉ፤ ክፋትን እንጂ የጽድቅን ሥራ መተግበር ይሳናቸዋል፡፡ በጾም በጸሎት ከመትጋት ይልቅ ሆዳቸውን ለመሙላት መብልን በማዘውተር እና ቤተ ክርስቲያን ከመሄድ ይልቅ መዝናኛ ቦታዎችን በማጫናነቅ ያለልክ አልኮልን ጭምር መጠጣትን ያዘወትራሉ፡፡ ምድራዊ የሆነው መብል ግን ከእግዚአብሔር ያርቀናል፤ ምክንያቱም ሰማያዊው አባታችን የሚያኖረን በሰማይ ቤቱ ነውና ሰማያዊ ሕብስት ለመመገብ መብቃት አለብን፡፡ ይህንን ማግኘት የምንችለው በጽድቅ ሥራ ነው፤ ሁል ጊዜም ቢሆንም በጎ ማሰብና መሥራት ያስፈልጋል፡፡

ጻድቁ አባት አቡነ ተክለ ሃይማኖት የሕይወታቸውን ሩቡን ዘመናቸውን እንደተራቡ እና እንደተጠሙ ገድላቸው ይገልጻል፡፡ ‹‹ጽድቅን የሚራቡና የሚጠሙ…›› ያላቸውም ስለ ጽድቅ ብለው ከመብል እና መጠጥ ራሳቸውን ገተው እና ፈጣሪያቸውን ለማግኘት የተራቡትንና የተጠሙትን እንደ አቡነ ተክለ ሃይማኖት አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ አቡነ አረጋዊ እንዲሁም ከቅዱሳት አንስት ደግሞ ቅድስት ክርስቶስ ሰምራ ያሉ ጻድቃንን ነው፡፡

ጽድቅን የሚፈጽማት የእግዚአብሔርን መንግሥት ይወርሳል፤ የእግዚአብሔርን መንግሥት የምታሰጥ ወንጌል በመንፈስ ቅዱስ የሆነ እምነትን ተስፋንና ፍቅርን እንጂ መብል መጠጥን አትሰብክም፡፡ አንድም ልብላ ልጠጣ በምትል ሰውነት ወንጌል አይዋሐድም፤ ‹‹አሁንም ወንድማችን ይታነጽ ዘንድ ሰላምን እንከተላት፡፡ በመብል ምክንያት የእግዚአብሔርን ፍጥረት አናፍርስ፤ ለንጹሓን ሁሉ ንጹሕ ነው፤ ለወንድም ዕንቅፋት ከመሆን ሥጋን አለመብላት ወይንንም አለመጠጣት ይሻላል፡፡ እምነት ካለህ እግዚአብሔር ፊት ባመንኸው እምነት ራስህን አጽና፤ ባገኘው አእምሮ ራሱን የሚዘልፍ ብፁዕ ነው፡፡ የሚጠራጠር ግን ቢበላ ይፈረድበታል፤ በማመን አልሆነምና፤ ያለ እምነትም የሚደረግ ሁሉ ኃጢአትና በደል ነው፡፡›› (ሮሜ.፲፬፥፲፱-፳፫)

ጻድቃን ከመራባቸውና መጠማታቸውም ባሻገር ምድራዊ ሕይወትን በመናቅ ይሰደዳሉ፤‹‹ስለ ጽድቅ የሚሰደዱ ብፁዓን ናቸው፤ መንግሥተ ሰማያት የእነርሱ ናትና›› እንደተባለው ለምናኔ እንዲሁም ለሃይማኖት መሥዋዕት በመክፈል ይሰደዳሉ፡፡ ቅዱስ ጳውሎስም ስለ ጽድቅ ብለው ስለተሰደዱት ጻድቃን ሲናገር እንዲህ ብሏል፡፡ ‹‹በመጋዝ የሰነጠቁአቸው፥ በድንጋይ የወገሩአቸው፥ በሰይፍም ስለት የገደሉአቸው አሉ፤ ማቅ፥ ምንጣፍና የፍየል ሌጦ ለብሰው ዞሩ፤ ተጨነቁ፤ ተቸገሩ፤ መከራ ተቀበሉ፤ ተራቡ፥ ተጠሙም፡፡ ዓለም የማይገባቸው እነዚህ ናቸው፤ ዱር ለዱርና ተራራ ለተራራ፥ዋሻ ለዋሻና ፍርኩታ ለፍርኩታም ዞሩ፡፡›› (ማቴ .፭፥ ፲፣ዕብ.፲፩፥፴፯)

ቅዱስ ጳውሎስ ‹‹ኢየሱስ ክርስቶስን በማምለክ ሊኖሩ የሚወዱ ሁሉ ይሰደዳሉ›› እንዳለ ስደት የክርስቲያኖች መገለጫ ነው፡፡ ጌታችንም ‹‹በዓለም ሳላችሁ መከራ አለባቸው፤ ነገር ግን አይዞአችሁ እኔ ዓለምን አሸንፌዋለሁ›› ብሎ አስተማረን፡፡ ምንም እንኳን ክርስቲያኖች በተለያየ መንገድ ቢሰደዱም ምክንያታቸው ግን የሁሉም አንድ ነው። ያም ስለ ጽድቅ ይሰደዳሉ፤ አንዳንዶች በአካል ሲሰደዱ ሌሎቹ በኅሊና ይሰደዳሉ። ስለዚህ ስደት የክርስቲያኖች ሕይወት መሆኑን በማሰብ ለእግዚአብሔር ታምኖ በጽድቅ ሥራ መኖር ይገባል፡፡ (ዮሐ. ፮፥፴፫፣ ፪ ጢሞ. ፫፥፲፪)

ጻድቃን ለሃይማኖታቸው እስከ መሠዋትም ይደርሳሉ፤ ቅዱሳት መጻሕፍት ላይ ተመዝግቦ እንደምናገኘው በዘመናት የነበሩ ጣዖት አምላኪ ነገሥታት ክርስቲያኖችን በማደንና በመያዝ ሃይማኖታቸውን እንዲቀይሩ ሊያስማሙአቸው በሚጥሩበት ጊዜ ባለመቀበላቸው በግፍ እንዳሰቃዩአቸው እንረዳለን፡፡ በተለይም መጽሐፈ ስንክሳር ላይ ሰማዕታት የሆኑትን የጻድቃን ታሪክ ተመዝግቦ እናገኘዋለን፡፡ ሕይወታቸውን በሙሉም እነርሱ ተርበው የተራበ ሲያበሉ፤ ተጠምተው የተጠማ ሲያጠጡ፣ በመከራ ውስጥ ሆነው የተቸገሩትን ሲያጽናኑና በተሰጣቸውም ጸጋ የታመሙትን ሲፈውሱ ኖረው በመጨረሻም በዕለተ ዕረፍታቸው ለሃይማኖታቸው በመሠዋት የሰማዕትነት አክሊልን እንደተቀዳጁ በገድላቸው ተጽፎ እናገኛዋለን፡፡ እንደ ሰማዕቱ ቅዱስ ጊዩርጊስ፣ ቅዱስ እስጢፋኖስ፣ ሰማዕቱ ቂርቆስ እና እናቱ ቅድስት ኢየሉጣ፣ ቅድስት አርሴማ እና ሌሎች በርካታ የእግዚአብሔር ምርጥ ልጆች ፈጣሪያቸውን የሚያስደስት ሥራ ሠርተው የክብርን ሞት የሞቱ እንዲሁም ከእራሳቸው አልፈው ለሌሎች ድኅነት የሆኑ ብፁዓን ናቸው፡፡
በየትኛውም ዘመን የምንኖር የሰው ዘር በሙሉ በክርስቶስ ክርስቲያን እንባል ዘንድ የጽድቅ ሥራን መተገብር ይጠበቅብናል፤ ይህም በእውነት መንገድ በመጓዝ በሕገ እግዚአብሔር መገዛትና ሥርዓቱን በመጠበቅ በሃይማኖት መኖርን ጭምር ያመለክታል፡፡
በጽድቅ ሥራ ለመኖር በትዕግሥት የችግርና መከራን ጊዜ ማሳለፍ ያስፈልጋል፤ አሁንም ካለንበትም መከራና ስቃይ ለመውጣትና ፈተናችን ለመወጣት በሥጋት የሚሆነውን ከመጠበቅ ይልቅ እያንዳንዳችን በቀሪው የሕይወት ዘመናችን በጎ ሥራን አብዝተን መተግበር የተሻለ ነው፡፡ ዓለማችን እንዲህ በጦርነት፣ በመከራና በቸነፈር በተጨነቀችበት ዘመን ወደ እግዚአብሔር የበለየ በመጠጋት በጽድቅ ልንኖር ይገባል፡፡ ምክንያቱም ምድር ለጻድቃንንም ሆነ ለኃጥአንም ዕድላችን አንድ ጊዜ በመሆኑ ሁላቻንም እንደሥራችን ፍርድን እስክናገኝ ድረስ የጽድቅ ሥራን መሥራት ያስፈልገናል፡፡

በአሁኑ ጊዜ ቤተ ክርስቲያን ፈተና ላይ በመሆኗ እንዲሁም ልጆቿ በስደትና መከራ ውስጥ ናቸው፤ ብዙዎችም ሃይማኖታቸውን ላለመቀየር አንገታቸውን ለሰይፍ ሰጥተዋል፤ ሰውነታቸው እና ቤት ንብረተቻውም በእሳት ተቃጥሎባቸዋል፡፡ ሌሎች ደግሞ በስደት፣ በስቃይና በእንግልት ከርመው ለሕልፈተ ሕይወት ተዳርገዋል፡፡ አንዳንዶች ግን ይህን ሁሉ መከራ አልፈው አሁንም በሕይወት ይገኛሉ፡፡ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስም እንደተናገረው ‹‹ስለ ጽድቅ የሚሰደዱ ብፁዓን ናቸው፤ መንግሥተ ሰማያት የእነርሱ ናትና» ወደ ፊትም ለሃይማኖታቸው ይሰደዳሉ፤ ይራባሉ፤ ያጠማሉ፡፡ ይህ የክርስቲያናዊነት መገለጫ በመሆኑ ዛሬም ነገም እስከ ዕለተ ሞታችን ድረስ የሚቀጥል በመሆኑ ሳንሰለች እና ሳናማርር የጽድቅ ሥራችንንም መቼም ቢሆን ማቆም የለብንም፤ ችግር፣ መከራ እንዲሁም ስቃይን ተቋቁመን ልንኖር ይገባል፡፡