ቅዱስ ወንጌል

የካቲት ፩ ቀን ፳፻፲፫ ዓ.ም

ወንጌል፡- ወንጌል የሚለው ቃል ‹‹ሄዋንጌሊዎን›› ከሚለው የግሪክ ቃል የመጣ እንደሆነና በግእዝ ቋንቋም ብሥራት፣ ምሥራች፣ አዲስ ዜና፣ መልካም ወሬ፣ ደስ የሚያሰኝ፣ ስብከት ማለት እንደሆነ አለቃ ኪዳነ ወልድ ክፍሌ ይገልጻሉ፡፡ (በመጽሐፈ ሰዋስው ወግስ ወመዝገብ ቃላት ሐዲስ ገጽ ፫፻፺፬)

ወንጌል የምሥራች የተባለበት ምክንያት የጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ መወለድ ለእኛ ድኅነት ይሆን ዘንድ ነውና የመወለዱ ዜና አዲስና መልካም በመሆኑ ነው፡፡ በዚህም ጌታችን ኢየሱስ ያስተማረው ትምህርት እንዲሁም የማዳን ሥራ በሙሉ ወንጌል ተብሏል፡፡ ከቅድስት ድንግል ማርያም ሲወለድም መልአኩ ቅዱስ ገብርኤል እንዲህ ብሎ ለሕዝቡ አብሥሯቸዋል፡፡ ‹‹እነሆ፥ ለእናንተና ለሕዝቡ ሁሉ ደስታ የሚሆን ታላቅ የምሥራች እነግራችኋለሁና አትፍሩ፡፡ እነሆ፥ ዛሬ በዳዊት ከተማ መድኅን ተወልዶላችኋል፤ ይኸውም ብሩክ ጌታ ክርስቶስ ነው፡፡›› (ሉቃ. ፪፥፲-፲፩)

ወንጌል በማን ተሰበከ?

ወንጌል በመጀመሪያ የተሰበከው በጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ነው፡፡ ‹‹ከዚያም ጊዜ ጀምሮ ጌታችን ኢየሱስ መንግሥተ ሰማያት ቀርባለችና ንስሓ ግቡ እያለ ይሰብክ ነበር፡፡››‹‹ጌታችን ኢየሱስ በየከተማውና በየመንደሩ ተመላለሰ፤ የእግዚአብሔርን መንግሥት ሰበከላቸው፤ አስተማራቸው፡፡ ዐሥራ ሁለቱ ደቀ መዝሙርትም ከእርሱ ጋር ነበሩ›› እንዲል፤ (ማቴ. ፬፥፲፯ ሉቃ. ፰፥፩)

የቃሉን ትምህርት እየሰሙ የሚሠራውን የማዳን ሥራ እያዩ ያስተማራቸውን ደቀ መዛሙርቱም ለዚህ ምስክሮች ሆኑ፤ ከጌታችንም ኢየሱስም ከትንሣኤው በኋላ ዐሥራ አንዱ ሐዋርያት በማዕድ ተቀምጠው ሳለ ተገለጠላቸው፤ እንዲህ አላቸው፤ ‹‹ወደ ዓለም ሁሉ ሂዱ፤ ለፍጥረትም ሁሉ ወንጌልን ስበኩ፡፡›› ለሐዋርያትም በአንደበታቸው የምሥራቹን ቃል እንዲሰብኩ በሕይወታቸው ሁሉ የሚመሠክሩበትን የዕውቀትና ጥንካሬ መንፈስ አጎናጸፋቸው፡፡ እነርሱም እንዲህ እያሉ መሰከሩ፡፡ ‹‹ስለሕይወት ቃል ከመጀመሪያው የነበረውንና የሰማነውን በዓይኖቻችንም ያየነውን የተመለከትነውንም እጆቻችንም የዳሰሱትን እናወራለን ሕይወትም ተገለጠ አይተንማል እንመሰክርማለን፡፡›› (ሉቃ. ፳፬፥፵፯-፶፫፣ ማር. ፲፮፥፲፭፣ ፩ ዮሐ. ፩፥፩)

የሐዋርያቱ ስብከትም በአንደበት ብቻ አልነበረም፡፡ የሰው ዘር በሙሉ ድኅነት የሆነውን ወንጌል ለዓለም እንዲዳረስ በተለያዩ ቋንቋዎች በየሀገሩ በአካል እየተገኙ ከማስተማራቸውም በተጨማሪ በጽሑፍም ለትውልድ ትውልድ አስተላልፏል፡፡ ጌታችንም ቅዱሳን ሐዋርያትንና ፸፪ አርድዕትን  ወንጌልን እንዲሰብኩ ከመረጣቸው በኋላ ከአርድዕት ሁለት (ቅዱስ ማርቆስን እና ቅዱስ ሉቃስን) እንዲሁም ከሐዋርያት ሁለት (ቅዱስ ማቴዎስን እና ቅዱስ ዮሐንስ) አድርጎም ወንጌልን እንዲጽፉ አዟቸዋል፡፡ የዚህም ምክንያት ሕዝቡ ወንጌልን የሚያውቁ የቃሉን ትምህርት ከሰሙት እና የእጁን ተአምራት ካዩት ሐዋርያት ጋር  ቀርታለች ብሎው የአርድዕትን ነገር እንዳያቃልሉ ነበር፡፡ አርድዕትም አብረውት ስለተማሩ እነርሱ እንዲሰብኩ ጌታ መርጧቸዋልና፡፡

የመጽሐፍ ቅዱስ ሁለተኛ ክፍል በሆነው የሐዲስ ኪዳን ውስጥ የሚገኙት አራቱ ወንጌሎች ማለትም የማቴዎስ ወንጌል፣ የማርቆስ ወንጌል፣ የሉቃስ ወንጌል እና የዮሐንስ ወንጌል ውስጥ የጌታችንነ ኢየሱስ ክርስቶስን መወለድ፣ መጠመቅ፣ መሰደድ፣ ትምህርት፣ ገቢረ ተዓምራት፣ መከራንና ሥቃይ መቀበል፣ መሰቀል፣ መሞት፣ መነሣት እንዲሁም ማረግ እያንዳንዳቸውን በምዕራፍ በመከፋፈል አስፍረውታል፡፡

ወንጌል በዐራት ክፍል ሆኖ የተጻፈበት ምክንያት በዐራቱ ማዕዘን ፀንቶ በዐራቱ ክፍላተ ዘመን ስለሚመሰል እና በዐራቱ መገብተ አውራኀ ከዋክብት ተመርታ እንደምትኖር ያስረዳል፡፡ አራቱ ወንጌላዊያን ደግሞ በሰማይ አራት ፀወርተ መንበር በሚሸኩት በዐርባዕቱ እንስሳ ኪሩቤል ይመሰላሉ፡፡ እነዚህም የሰው፣ የአንበሳ፣ የላምና የንሥር መልክ አላቸው። ‹‹በዙፋኑም ፊት ብርሌ የሚመስል የብርጭቆ ባሕር ነበር፤ በዙፋኑም መካከል፥ በዙፋኑም ዙሪያ አራቱ እንስሶች አሉ፤ እነርሱም በፊትም፥ በኋላም ዐይኖችን የተመሉ ናቸው፡፡ ፊተኛውን እንስሳ አንበሳን ይመስላል፤ ሁለተኛውም እንስሳ ጥጃን ይመስላል፤ አራተኛውም እንስሳ የሚበር ንስርን ይመስላል›› እንዲል፤ (ራእ. ፬፥፮-፯)

አራቱ ወንጌላውያን በእነዚህ በአራቱ ኪሩቤል ይመሰላሉ፤ በእርሱም መመሰላቸው የሰው ምስል ያለው ስለ ሰው ልጅ ሁሉ የሚጸልይ፣ የንሥር መልክ ያለው ስለአዕዋፍት የሚጸልይ፣ የአንበሳ መልክ ያለው ስለአራዊት የሚጸልይ፣ የላም መልክ ያለው ስለጋማና ለቀንድ ከብቶች የሚጸልይ መሆናቸውን ለመግለጽ ነው።

ቅዱስ ማቴዎስ (ገጸ ሰብእ)

ሐዋርያው ቅዱስ ማቴዎስ የጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የዘር ሐረግ እስከ ልደቱ የጻፈ በመሆኑ በገጸ ሰብእ ይመሰላል፡፡ በፍልስጥኤም፣ በፋርስ፣ በባቢሎን፣ በኢትዮጵያና በዐረቢያ የሰበከው ሐዋርያው በፍልስጥኤምም በሚያስተምርበት ወቅትም የአይሁድና የአረማውያንንም ትምህርት በመቃወሙ እንዲሁም ድውያንን በመፈወሱ እና በአጋንንት ሲሠቃዩ የነበሩት ሰዎችን ማዳኑን የሰሙ የሀገሩ ሰዎች ለእስር ዳርገውት ነበር፤ ሆኖም ግን በዚያም ሆኖ ወንጌልን በመስበኩ ከእነርሱ ውስጥም ክርስትናን አምነው የተቀበሉ ነበሩ፡፡ የዚያን ዘመን ሀገር ገዢም ይህን በሰማ ጊዜ ግን በቅዱስ ማቴዎስ ላይ ሞት ፈረደበት፤ ጥቅምት ፲፪ ቀንም ዐረፈ፡፡ (የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት፣ ቁ. ፩፣ ገጽ ፺፭-፺፱)

ቅዱስ ማርቆስ (ገጸ አንበሳ)

ሐዋርያው ቅዱስ ማርቆስ በአንበሳ  ይመሰላል። የአንበሳ መኖሪያው ጫካ በምድረ በዳ እንደሆነ ሁሉ ካለበት ሆኖ ድምጹን ባሰማ ጊዜ አራዊት በሙሉ ይደነግጣሉ። ቅዱስ ማርቆስም ከአምላካቸው ርቀው እና አምልኮተ እግዚአብሔር የማይፈጽሙት ግብፃውያንን ለመገሠጽና ለማስተማር ተጉዞ በምደረ ግብፅ ‹‹የእግዚአብሔር ልጅ ኢየሱስ ክርስቶስ ወንጌል መጀመሪያ›› ብሎ አስተማራቸው፤ በዚያን ጊዜም በሰዎች ላይ ያደሩ አጋንንትና መናፍቃን ደንግጠዋል።

ሐዋርያው ቅዱስ ማርቆስም በግብፅ ይመለኩ የነበሩ አምልኮተ ላህምን (የላም ጣዖት) በትምህርተ ወንጌል አጥፍቷል። ሊቀ ነቢያት ሙሴም ሆነ ነቢዩ ኤርምያስ አስቀድሞ ወንጌልን ቢሰብኩም ግብፃውያን ግን አምልኮተ እግዚአብሔርን ሊፈጽሙ አልቻሉም ነበር፡፡ በሐዋርያው ማርቆስ ስብከት ግን ክርስቶስን ፍጹም አምነው ተቀብለዋል። ቅዱስ ማርቆስም በግብፅም ብቻ ሳይሆን በእስያ፣ በሮም፣ ሰሜን አፍሪካ እንደሁም በእስክንድርያ ሰብኳል፡፡ (የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት፣ ቁ. ፩፣ ገጽ ፻፫-፻፬)

ቅዱስ ሉቃስ (ገጸ ላሕም)

በላም መልክ የሚመሰለው ቅዱስ ሉቃስ ከሌሎች ለየት ባለ ሁኔታ ክርስቶስ በከብቶች በረት እንደተወለደና እንስሶች ትንፋሻቸውን እንደገበሩለት ጽፏልና። በአንጾኪያ፣ በሮም እና ድልማጥያ ወንጌልንም ሰብኳል፡፡ የቅዱስ ሉቃስ ወንጌል ‹‹የአሕዛብ ወንጌል፣ ሰባኬ መንፈስ ቅዱስ፣ ሰባኬ ጸሎት፣ ወንጌለ አንስት›› ተብሎ ይጠራል፡፡ የዚህም ምክንያት በመጀመሪያ  ወንጌሉ የተጻፈው ለአሕዛብ  በመሆኑ ነው፡፡ የሁለተኛውም ስያሜ የእርሱ ወንጌል ከሌሎቹ ወንጌላት ይልቅ  የጌታችንን የመድኃታችን የኢየሱስ ክርስቶስን እና የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያምንን ጸሎት ደጋግሞ  በመጻፉ ነበር፡፡  በሦስተኛ ደረጃም ስለ እመቤታችን ድንግል ማርያም፣ ስለ ቅድስት ኤልሳቤጥ፣ ስለ ማርያም እንተ እፍረት፣ ስለ ናይን ሴት እንዲሁም ስለ ሌሎች አንስት በሰፊው ስለሚናገር ‹‹ወንጌለ አንስት›› ተብሏል፡፡ (የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት፣ ቁ. ፩፣ ገጽ ፻፱-፻፲፩)

ቅዱስ ዮሐንስ (ገጸ ንሥር)

ቅዱስ ዮሐንስ በንሥር መልክ ይመሰላል። ይህም ንሥር በእግር እንደሚሽከረከራና በክንፍ መጥቆ እንደሚበር ሁሉ ይህ ሐዋርያም እንደሌሎቹ ወንጌላውያን የአብን ልጅ ከሰማየ ሰማያት መውረድ፣ ከድንግል ማርያም መወለድ መከራ መቀበል፣ መሰቀል፣ መሞት፣ ትንሣኤውን እንዲሁም ዕርገቱን ጽፏልና። ንሥር በክንፉ መጥቆ እንዲበር ዮሐንስ ከሌሎቹ ወንጌላውያን ለየት ብሎ አካል ከህልውና ተገልጾለት የቃልን በቅድምና መኖር፣ እንዲሁም የሥላሴን አንድነትና ሦስትነት ጽፏል። ቅዱስ ዮሐንስ  በኢየሩሳሌም፣ በአንጾኪያ፣ በሎዶቅያ፣ በእስያ ከተሞች በተለይም በኤፌሶን ወንጌልን አስተምሯል፡፡ (የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት፣ ቁ. ፩፣ ገጽ ፻፲፪-፻፲፬)

በተለያዩ ዘመናትም የተነሡ የእግዚአብሔር ምርጥ ልጆች፣ ቅዱሳን፣ ጻድቃን፣ ሰማዕታት ሁሉም የሰው ልጆች የመዳን ብሥራት የሆነውን ወንጌል ለዓለም ሰብከው፣ ብዙዎችን ወደ ክርስትና መልሰው፣ ለበርካቶችም የመዳን ምክንያት በመሆን ለእምነታቸው መሥዋዕት ከፍለው እንዲሁም ለሃይማኖታቸው ተሠውተው አልፈዋል፡፡

ወንጌል የሰው ልጅ ሞተ ነፍስ በእርሱ እንደጠፋ፣ ሕይወተ ሥጋ ሕይወተ ነፍስ ያገኘንበት እንደሆነና ዲያብሎስም በእርሱ እንደታሰረ፤ አዳም ከነልጆች የዳነበት መሆኑን ልናምን ይገባል፡፡  በማርቆስ ወንጌልም እንዲህ ተብሎ ተጽፏል፤ ‹‹ጊዜው ደረሰ፤ የእግዚአብሔር መንግሥት ቀርባለችና ንስሓ ግቡ፤ በወንጌልም እመኑ፤›› (ማር. ፩፥፲፭)

ወንጌል የጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ታሪክ በመሆኑ የእርሱ በሥጋ መገለጥ፣ ከንጽሕተ ንጹሐን፣ ቅድስተ ቅዱሳን ድንግል ማርያም መወለዱን፣ መሰደዱን፣ ለእኛ ሲል በቀራንዮ አደባባይ መከራ መቀበሉን እንዲሁም በመልዕልተ መስቀል ላይ መሰቀሉን፣ መሞቱን፣ በትንሣኤው ሙስና መቃብርን ድል አድርጎ መነሣቱን እና ማረጉን ሁሉ የሚዘክር መሆኑን ማወቅና መረዳት አለብን፡፡ ወንጌል የድኅነችን መንገድ ይሆን ዘንድ ተመሥርቶልናልና፡፡ እርሱ ባይወለድ፤ ወንጌልን ባይሰብክና ባይሞትልን ኖሮ እኛ የኃጢአት ሥርየትንም አናገኝም፤ ንስሓችን፣ ጸሎታችን እንዲሁም ምግባራችንም ሁሉ ተቀባይነት አያገኝም ነበር፡፡ ነገር ግን ጌታችን ኢየሱስ በተቀበለው መከራና ሥቃይ ለእኛም የድኅነት መንገድ ሆነልን፤ ከሞት ሞትም አዳነን፤ እርሱ ሞቶ የእርሱን ሕይወት ለእኛ ሰጠን፡፡ ስለዚህም ይህን ተረድተን፤ በክርስቶስ ክርስቲያን ተብለን እንድን ዘንድ ወንጌልን ልንማር ይገባል፡፡