ጽኑ ተስፋ

በመዝሙርና ሥነ ጥበባት ክፍል

ነሐሴ ፯ ቀን ፳፻፲፫ ዓ.ም

ተድላ እና ደስታ ከሞላባት ገነት
ሥርዓተ ጾም ነው የተተከለባት
ደግሞም በሌላ መልክ የሞት ሕግ አለባት
የሕጉን ጽንዐት አዳም ጠነቀቀ
ከእባብም ሽንገላ ራሱን ጠበቀ

ሕጉን እንደ ማዕቀብ ሔዋን ስለዐወቀች
ዕውቀትን ፍለጋ በለሷን ቀጠፈች
ቀጥፋውም አልቀረች ከሁለት ከፈለች
ለአዳም አጎረሰች የጾም ሕግ ሻረች

አዳም ተታለለ… ጾም እንደ ገደፈ
ልብሱ ተገፈፈ
ፈራ ደነገጠ
በገነት መካከል ሀፍረት ተገለጠ

በዛፍ ተጠለለ… በቅጠል ሸፈነ
በለስ አገልድሞ ዕርቃኑን ከደነ
አዳም!… አዳም!… አዳም ብሎ እግዚአብሔር ተጣራ
ዕራቁቴን ኾንኩኝ ደግሞም ተሸሸግኩኝ አለ ስለፈራ

ፍርሃት ዕውቀት ነው!
ዕውቀቱ ግን ሞት ነው
ከእግዚአብሔር የለየው

በለመደ እጁ ከዕፀ ሕይወት ቀጥፎ ዳግም እንዳይበላ
ከገነት አስወጣው!… ምድርም አበቀለች እሾህ አሜኬላ
አዳም በሐዘን ውስጥ ደም ዕንባ አነባ
በመቃብሩ ላይ ተስፋውን ገነባ

አበው ነቢያቱ ሳሉ በመከራ
የአሞጽ ልጅ ኢሳይያስ ስለ ዘር አወራ
በአዳም ወገብ ውስጥ ያለች ተሠውራ
በሔዋን ማሕፀን ውስጥ ከዕንቍ የምታበራ

አለች ንጽሕት ዘር መርገም ያላገኛት
ለቃሉ ማደሪያ መርጦ ያዘጋጃት
በሰዶም የሆነው በእኛ እንዳይደርስብን
የሠራዊት ጌታ ዘርን አስቀረልን

አምስት ቀን ተኩል ደጅ እየተጠናች
ይህች ንጽሕት ዘር ዛሬ ተገለጠች
ከኢያቄም አብራክ ከሐና የተገኘች…
ቅድስተ ቅዱሳን ማርያም ተፀነሰች
ሁለተኛዋ ሔዋን የድኅነት ምንጭ ሆነች።