ዕንባ በንስሓ ሕይወት

ከምንባባት ዐውድ

ነሐሴ ፫ ቀን ፳፻፲፫ ዓ.ም

በመንፈሳዊ ሕይወታችን ውስጥ ዕንባ በብዙ ምክንያት ይፈጠራል፤ በየዋህነትና በልብ መነካት፣ የዓለምን ከንቱነት በመረዳት፣ ኃጢአትን በማሰብ፣ በፈተናና በችግር፣ ሞትን በማሰብ፣ በደስታና በስሜት፣ በጸሎት፣ በአቅመ ቢስነት፣ በብቸኝነት ስሜት፣ በሌላ ሥቃይ እና በሚታይ ፈንጠዚያ የተነሣ ሰዎች ያነባሉ፡፡ በወንጌል በተጻፈው የጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ትንሣኤ ታሪክ ውስጥ ለመግደላዊት ማርያም የቀረበላት ‹‹ስለምን ታለቅሻለሽ?›› የሚለውን የመላእክት ጥያቄም ሁላችን ልንመልስ ይገባል፤ ዕንባ ሁሉ ዋጋ የሚያስገኝ አይደለምና፡፡ (ዮሐ.፳፥፲፫)

በዚህ ዝግጅታችንም ኃጢአትን በማሰብ ለንስሓ የሚያበቃንን የዕንባ ዓይነት የፀፀትና የንስሓ ዕንባን እንመለከታለን፤ መልካም ንባብ!

የሰው ልጅ በዘመኑ በተለያዩ ምክንያቶች ኃጢአትን ይሠራል፤ ይብዛም ይነሥም የኃጢአት መጨረሻው ቅጣት በመሆኑ ግን በንስሓ ሥርየትን ማግኘት አለበት፤ ለዚህም በዋነኛነት የሚረዳው ከልብ ተፀፅቶ በዕንባ መታጠብ መቻል ነው፡፡

ሰዎች በሠሩት ኃጢአት ተፀፅተው ወደ አምላካቸው እግዚአብሔር ለመመለስ ጉልበት የሚሆናቸው ዕንባ ነው፡፡ ለመፀፀትም የሠራነውን ኃጢአት ማሰብ አለብን፡፡ ሐዋርያው ቅዱስ ጴጥሮስ በጭንቀቱ ጊዜ ጌታችን ክርስቶስን ሲክድ ያደርግ ስለነበረው ነገር እውነታ አልተረዳም ነበር፡፡ ይሁን እንጂ ዶሮ ከጮኸ በኋላ የኃጢአቱ ጥልቀት ስለተሰማው  ‹‹ወደ ውጭም ወጥቶ መራራ ለቅሶን አለቀሰ፡፡›› (ማቴ.፳፮፥፴፰)

የጌታችን የኢየሱስን እግር በዕንባዋ ያጠበችው በፀጉሯም ያበሰችው ሴትም ያደረገችው ተመሳሳይ ነገር ነው፡፡ ጌታችንም ስለ እርሷ የኃጢአት ሥርየት እንዲህ ብሏል፤ ‹‹በዕንባዋ እግሬን አራሰች›› በብዙ ፍቅርም ተመልሳ ጌታ እንዳለው በታላቅ ርኅራኄ ኃጢአቷ ተሠርዮላታል፡፡ ጌታም ጻድቅ እንደሆነ ስለራሱ ከሚያስበው ፈሪሳዊ ስምዖን ይልቅ የእርሷን የዕንባ መሥዋዕት አከበረ፡፡ እርሷም ምንም ቃል አልነበራትም፤ ለመናገርም አልደፈረችም፡፡ ነገር ግን በንስሓ ዕንባዋ ተናገረች፡፡ (ሉቃ.፮፥፵፬፣፯፥፴፰)

ኃጢአቱን የሚያውቅ፣ የሚያምን፣ የሚጸጸትበትም፣ ደፍሮ ለመናገር ያፍራል፡፡ ነገር ግን ለተነሣሂው ይህ የጸና የፀፀትና የሐዘን ስሜቱ በዓይኖቹ ያሉ የዕንባ ቋቶችን ይንዳል፤ ስለዚህም በምሬት ያለቅሳል፡፡ ዕንባውም ከቃላት ሁሉ በላይ የሆነ ትሑት ስብእናን መግለጫ ነው፡፡ አንድ ሰው ያለምንም ስሜት ጥቂት ቃላትን ሊናገር ይችላል፤ ዕንባ ግን ያለ ቃላት የሚገለጽ ነው፡፡ ዕንባ በእርግጥም ገላጭና የእውነተና ትሕትና ስሜት ነው፡፡

ልበ አምላክ የተባለውም ነቢዩ ዳዊት በሠራው ኃጢአት በጊዜ ወደ እግዚአብሔር የተመለሰበት ዕንባ እርሱን ለመሰሉ ሁሉ የሚያስተምር ተጠቃሽ ታሪክ ነው፡፡ ነቢዩም በጥልቅ የፀፀት ስሜት ውስጥ ሆኖ እንዲህ አለ፤ ‹‹በጭንቀቴ ደክሜያለሁ፤ ሌሊቱን ሁሉ አልጋዬን አጥባለሁ፤ በዕንባዬ መኝታዬን አርሳለሁ፡፡›› እንዲሁም ከዕንባው ጋር ሌላም የሚያስፈልግ የምሕረት ምክንያቶችን ሁሉ ማድረጉንም ነግሮናል፤ ‹‹ነፍሴን በጾም አስመረርኳት… ምሳሌንም ሆንሁላችሁ›› እንዲል፤  በፀፀት ዕንባ የደረሰበትን የንስሓ ደረጃ ‹‹ከጩኸት ድምጽ የተነሣ አጥንቶች ከሥጋዬ ጋር ተጣበቁ፤ አመድን እንደ እህል ቅሜያለሁና፤ መጠጤንም ከዕንባዬ ጋር ቀላቅያለሁና›› በማለት ሊያስረዳን ችሏል፡፡ (መዝ. ፮፥፮፣፲፱፥፲፣፲፪፥፭)

በኃጢአት ምክንያት ማልቀስ ልብን ማጠብ ነው፤ ነፍስንም ማንጻትና ኅሊናንም ማንቃት ነው፡፡ ይህም ሰው በሌላ ጊዜ ወደ ኃጢአቱ እንዳይመለስ እንዲሁም ጥንቃቄና መቆጠብን ትክክለኛነትን እንዲማር ያደርገዋል፡፡ አባቶችም መልካምን የምክር ቃል ለሚሻ ‹‹በበኣትህ ጽና፤ ስለ ኃጢአትም አልቅስ›› ይላሉ፡፡

የእግዚአብሔር የኃጢአት ይቅርታ ኃጢአተኛውን ስለ ኃጢአቱ እንዲያለቅስ አያግደውም፡፡ ቅጣትንም በመፍራት አያለቅስም፤ የእግዚአብሔርን ልብ በኃጢአት ሥራው በማሳዘኑ፣ ያለቅሳል እንጂ፤ ኃጢአትን የሚሠራ በዙሪያው የሠፈሩ የእግዚአብሔርን መላእክት ያርቃል፡፡ በተለይም በቅዱሳን መላእክት ፊት እንደ ክፉ ራሱን ይገልጣልና ያለቅሳል፡፡ እንዲሁም ደግሞ በኃጢአቱ የእግዚአብሔር አርአያና አምሳልነቱን አጥቷል፤ ወድቋልም፤ የረከሰም ሆኗልና ያለቅሳል፡፡ መንፈሱ መድከሙ እንዲዚህም መሆኑ እየተሰማው ሳለ ላለማልቀስ ፈቃዱ እንዴት ሊደክም ይችላል? በእውነቱ በጽኑ ያለቅሳል፡፡ በራሱ ፊት የማፈርና የመጨነቅም ስሜት ያድራበታል፡፡ ስለዚህም ነገር ነቢዩ ዳዊትም በመዝሙሩ ‹‹… የፊቴም እፍረት ሸፈነኝ›› ብላል፡፡ ነቢዩ ዳንኤልም የሕዝቡን ኃጢአት ባመነ ጊዜ ‹‹ጌታ ሆይ ባንተ ላይ ኃጢአት ስለሠራን ለእኛና ለነገሥታቶቻችን ለአለቆቻችን ለአባቶቻችን የፊት ዕረፍት ነው›› ብሏል፡፡ (መዝ.፬፥፲፭፣ዳን.፱፥፯‐፰)

ስለዚህም በሰው ዘር ዘንድ በሙሉ የንስሓና የዕንባ አዋጅ ታወጀ፤ ነቢዩ ኢዮኤልም እንዲህ በማለት አስተምሯል፤ ‹‹አሁንስ ይላል እግዚአብሔር በፍጹም ልባችሁን በጾሙም፣ በልቅሶና በዋይታ ወደ እኔ ተመለሱ፤ ልባችሁን እንጂ ልብሳችሁን አትቅደዱ… ወደ እርሱ ተመለሱ፡፡…›› (ኢዩ.፪፥፲፪)

በዘመነ ሐዲስ ሐዋርያት ኃጢአትን የሠሩ ሁሉ በንስሓ ዕንባ እንዲመለሱ ያስተምሩ ነበር፡፡ ቅዱስ ጳውሎስ ለቆሮንቶስ ሰዎች በታላቅ ተግሣጽ እንዲህ ብላቸዋል፡፡ ‹‹እናንተም ታብያችኋል፤ ይልቅስ እንድታዝኑ አይገባችሁምን? ይህን ሥራ የሠራው ከመካከላችሁ ይወገድ።››  ሐዋርያው ቅዱስ ያዕቆብ በበኩሉ ‹‹እናንተ ኃጢአተኞች፥ እጆቻችሁን አንጹ፤ ሁለት ሐሳብም ያላችሁ እናንተ፥ ልባችሁን አጥሩ›› በማለት በመልእክቱ ኃጢአቱን ላደረጉ ሁሉ ያስገነዝባሉ፡፡ (፩ቆሮ. ፭፥፪፣ያዕ. ፬፥፰)

ምንም እንኳን የንስሓ ዕንባ ተብሎ ባይጠቀስም በጌችን ክርስቶስ ዳግም ምጽአት የወጉት ሁሉ የሚያፈሱት ዕንባ የጅምላ እንደሆነ መጽሐፍ ቅዱስ ይመሠክራል፤ የሐዋርያው የቅዱስ ዮሐንስ ራእይ ይህን ሲያስረዳ  ‹‹እነሆ ከደመና ጋር ይመጣል፤ ዐይንም ሁሉ የወጉትም ያዩታል፤ የምድርም ወገኖች ሁሉ ስለ እርሱ ዋይ ዋይ ይላሉ›› በማለት ሲሆን ይህ ሐዘንና ልቅሶ ግን ተስፋ የሌለውና ያለ ዋጋ የሚፈስ ከንቱ ዕንባ ነው፡፡ (ራእ.፩፥፯)

በመሆኑም የፍርድ ቀን ከመምጣ በፊት ነፍሳችን ከኃጢአት የጠራች እንድትሆን ሥርየትን በመሻት ዘወትር ልናለቅስ ይገባል፤  አሁን ካለንበት ችግር መከራ እንዲሁም ጦርነት ይታደገን ዘንድም ከልብ ተፀፅተን በለቅሶ እንማፀን፡፡ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ‹‹ለራሳችሁና ለልጆቻችሁ አልቅሱ›› ብሎ እንደተናገረው ስለ ኃጢአታችን ባለቀስን ጊዜ በእኛ ውስጥ ሆኖ የሚጠብቀንን የእግዚአብሔርን ፍቅር እናስታውሳለን፡፡ የኃጢአት ሥራችንን ለረጅም ጊዜ በቀጠልንም ቊጥር እግዚአብሔርም በእኛ ላይ ያለውን ትዕግሥትና ቻይነት እንዲሁም ፍቅርኑን ባሰብን ጊዜ በርኅራኄ እንደያዘን ስናስተውል ለቅሶአችን ለንስሓችን መነሻ ይሆነናል፡፡ (ሉቃ.፳፫፦፳፩)

በዚህ በያዝነው በጾመ ፍልሰታም ቸርነትና ምሕረትን ታሰጠን ዘንድ እናታችን ቅድስት ድንግል ማርያምን በለቅሶ እንማጸናት፤ ‹‹ሰአሊለነ ቅድስት፤ ድንግል ሆይ ለምኝልን›› እያልንም እንለምናት፡፡ እርሷ የጭንቅ አማላጅ ናትና ከተወደደ ልጇ ታማልደናለች፡፡ በንስሓም ወደ አምላካችን እንድመለስ ትረዳናለች፡፡

የአምላካችን እግዚአብሔር ቸርነት፣ የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም እንዲሁም የቅዱሳን መላእክት፣ የጻድቃን ሰማዕታት አማላጅነትና ተራዳኢነት አይለየን፤ አሜን፡፡

ይቆየን

ምንጭ፡ ‹‹ዕንባ በመንፈሳዊ ሕይወት›› በብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ሺኖዳ ሣልሳዊ፣፳፻፻፰ ዓ.ም፣ በመጽሐፍ ቅዱስ- ብሉይና ሐዲስ ኪዳን