የኒቂያ ጉባኤ

በቢታንያ አውራጃ ጥቁር ባሕር ወደብ አካባቢ የምትገኘው ኒቂያ በባሕርም ሆነ በየብስ ለሚጓዙ ሰዎች እጅግ ተስማሚ ከተማ እንደነበረች ቅዱሳት መጽሐፍት ይጠቅሳሉ፡፡ የእስክንድርያ ንጉሠ ነገሥታት መናገሻቸውን ወደ ቁስጥንኒያ እስከዛወሩበት ዘመነ መንግሥት ድረስ ከኒቂያ በ፴፪ ኪሎ ሜትር ላይ ያለችው ኒቆሚዲያ ላይ በመስፈራቸው በ፫፻፳፭ ዓ.ም ለተካሄደው ጉባኤ ምቹ ስፍራም ነበረች፡፡

በሦስተኛው መቶ ክፍለ ዘመን ቤተ ክርስቲያን በተለያዩ አቅጣጫዎች በደረሰባት አያሌ ችግሮች እጅግ በመታወኳና በመበጥበጧ መፍትሔ ለመፈለግ ውይይት የተደረገበትና ውሳኔ የተሰጠበት የሊቃውንቶች ስብሰባ የኒቂያ ጉባኤ ነው፡፡ ከችግሮቹ ውስጥ አንዱም ስለ ምሥጢረ ሥላሴ የዶግማ ትምህርት ልዩነት መፈጠሩ ነበር፡፡ በነዚህ ጊዜያት ውስጥ እንደነ ጳውሎስ ሳምሳጢ፣ ሰባልዮ እና አርጌኒስ የመሳሰሉት የተነሱበት ዘመን ነበር፡፡ በተለይም አርዮስ ‹‹ወልድ ፍጡር ነው›› ብሎ በመነሣቱ ቤተክርስቲያን ለብዙ ዓመታት ስትታወክ ቆይታለች፡፡
አርዮስ መሠረታዊ ትምህርቱን በሊብያ፣ ከፍተኛ ትምህርቱን በእስክንድርያ እና መንፈሳዊ ትምህርት፣ የትርጓሜ መጻሕፍትና የነገረ መለኮት ትምህርት ጨምሮ በአንጾኪያ የተማረ ግሪካዊ ነበር፡፡ በዚያን ወቅትም የአንጾኪያ ትምህርት ቤት የክህደት ትምህርት ቅርበት ስለነበረው አርዮስ አብዛኛውን የኑፋቄ ትምህርት ያገኘው ከሉቅያኖስና ከአንጾኪያ ትምህርት ቤቶች ነው፡፡

አርዮስ ብልህና ዐዋቂ፤ አንደበተ ርቱዕና እምቅ የሆነ የግጥም ችሎታ እንደነበረው ይነገራል፡፡ በጊዜው የእስክንድርያ ፓትርያክ ከነበሩት ተፈጻሜተ ሰማዕት ቅዱስ ጴጥሮስ ዲቁና ተቀብሎ አገልግሎት ከጀመረ በኋላ ግን ቤተክርስቲያን ‹‹ወልድ ፍጡር›› እያለ በማስተማርና ‹‹ታሊያ (ማዕድ)›› የተሰኘውን የግጥም መጽሐፉን ተጠቅሞ ትምህርቱን ማሰራጨት ጀመረ፡፡ በዚህ ጊዜ ተፈጻሜተ ሰማዕት ቅዱስ ጴጥሮስ አስጠርተው ትምህርት ሁሉ የተሳሳተ መሆኑንና ከስሕተቱ ተመልሶና ተጸጽቶ ከቅዱሳን አበው ሲተላለፍ በመጣው በኦርቶዶክስ እምነት እንዲጸና መከሩት፡፡ እርሱ ግን ምክራቸውን ወደ ጎን ትቶ የክሕደት ትምርቱን በሰፊው ማስተማር ቀጠለ፤ የዚህ ጊዜ አርዮስን አውግዘው ከዲቁና ማዕረጉ ሻሩት፡፡ የግብጽ ቤተክርስቲያን ትውፊት እንደሚለው ተፈጻሜተ ሰማዕት ቅዱስ ጴጥሮስ ያወገዙት ጌታችን ኢየሱስ በራዕይ ተገልጦ በሰጠው ትእዛዝ መሠረት ነው፡፡ ‹‹አንድ ሌሊት በራዕይ ጌታ ኢየሱስ በሕፃን ልጅ አምሳል እንደ ፀሐይ የሚያበራ ረጅም ልብስ (ቀሚስ) ለብሶ ነበር፡፡ ልብሱ ግን ለሁለት የተቀደደ ሆኖ ያዩታል ሰማዕት ቅዱስ ጴጥሮስም ልብስህን ማን ቀደደብህ (መኑ ሰጠጣ ለልብስከ?) ብለው ሲጠይቁ ጌታ ኢየሱስም ‹‹አርዮስ ልብሴን ቀደደብኝ›› ይላቸዋል፡፡ በዚያኑ ቀን ሁለቱን ተማሪዎቻቸውን አኪላስንና እለእስክንድሮስን አስጠርተው የተገለጠላቸውን ራዕይ በመግለጥ አርዮስን እንዳይቀበሉት ከእርሱም ጋር ኅብረት እንዳይኖራቸው አዘው፤ በዲዮቅልጥያኖስ ሰማዕት ሆነው ዐረፉ፡፡

ከተፈጻሜተ ሰማዕት ቅዱስ ጴጥሮስ ሞት በኋላ አኪላስ በ፫፻፫ ዓ.ም ሊቀ ጳጳስ ሆኖ ተሾመ፡፡ አርዮስም ወደ አኪላስ ቀርቦ ከውግዘቱ እንዲፈታው በከንቱ ውዳሴ አባበለው፡፡ አኪላስም አደራውን በመዘንጋት ከውግዘቱ ፈታው፤ ይባስ ብሎም የቅስና ማዕረግ ሰጥቶ ሾመው፡፡ ሆኖም አኪላስ በሕይወት ብዙ ጊዜ አልቆየም አንድ ዓመት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ በሞት ተለየ፡፡ በቀጠል እለእስክንድሮስ ፓትርያክ ሆኖ ተተካ፡፡ በዚህ ጊዜ አርዮስ ክህደቱን ከማሰራጨት አልታቀበም ነበር፡፡ እንደውም ሕዝቡ ትምህርቱን በቀላሉ እንዲቀበሉ የክሕደት ትምህርቱን በግጥምና ንባብ እያዘጋጀ ማሰራጨት ቀጠለ፡፡ ያም የግጥም መጣጥፍ ‹‹ታሊያ›› ይባል ነበር፤ ትርጉሙም ማዕድ ማለት ነው፡፡ ሕዝቡ ግጥም ስለሚወድ ትምህርቱን ወደ መቀበል ደርሶ ነበር፡፡ በዚያን ጊዜ እለእስክንድሮስ እየተዘዋወረ ከአርዮስ ኑፋቄ እንዲጠበቁ በትጋት ያስተምር ነበር፡፡ በ፫፻፳ ዓ.ም አንድ መቶ ሚያህሉ የሊቢያና የእስክንድርያ ኤጲስ ቆጶሳትን እለእስክንድሮስ አሰባስቦ የአርዮስን አስተሳስቦ ገልጾላቸው ጉባኤውም አልመለስ ያለውን አርዮስን በአንድ ልብ አውግዘው ከቤተክርስቲያን አንድነት ለዩት፡፡

አርዮስ ከጓደኞቹ አንዱ ወደ ነበረው ወደ የኒቆሜዲያ ኤጲስ ቆጶስ አውሳብዮስ በመገስገስ አንድ በአንድ ዘርዝሮ ነገረው፡፡ አውሳቢዮስም አይዞህ ብሎ ተቀብሎ በሀገረ ስብከቱ የሚገኙትን ኤጲስ ቆጶሳትን ሰብስቦ በአርዮስ ጉዳይ ሲኖዶስ አደረገ፡፡ ሲኖዶሱም በግፍ መባረሩን አምኖ ከውግዘቱ ፈቱት፡፡ አርዮስም በ፫፻፳፪ ዓ.ም ወደ እስክንድርያ ተመልሶ እለእስክንድሮስ ቢያወግዘኝ ተፈትቼ መጣሁ እያለ የበፊት ትምህርቱን በስፋት ማስተማር ቀጠለ፡፡ የዚህ ጊዜ ቤተክርስቲያን ታመሰች፡፡ በዚህ ምክኒያት ጉዳዩ ንጉሥ ቆስጠንጢኖስ ደረሰ የዚህ ጊዜ የእስፓኝ ጳጳስ ሆስዮስን ወደ እስክንድርያ ላከው፡፡ ሲመለስ ጉዳዩ የሃይማኖት ችግር እንጂ አስተዳደራዊ ስላልሆነ በጉባኤ መታየት አለበት ብሎ ለንጉሡ አማከረው፡፡ ንጉሥ ቆስጠንጢኖስም በነገሠ በሃያ ዓመቱ በ፫፻፳፭ ዓ.ም ጉባኤ እንዲደረግ አዘዘ፡፡ በዚህም በኒቅያ ፫፻፲፰ አባቶች ተሰበሰቡ፡፡
በጉባኤውም የአርዮስ ክሕደቶች ተመረመሩ፡፡ የእርሱ የኑፋቄ ትምህርትም ‹‹ክርስቶስ ዓለም ሳይፈጠር አልነበረም (ሎቱ ስብሐት)፣ ባሕርዩ ከአብ ያነሰ ነው (ሎቱ ስብሐት)፣ የተፈጠረ እንጂ ከአብ የተወለደ አይደለም (ሎቱ ስብሐት) እንዲሁም በመጀመሪያ ዓለሙን ይፈጥርበት ዘንድ እግዚአብሔር እርሱን ፈጠረው፤ እርሱም ዓለምን ፈጠረ፡፡ በአጠቃላይ ወልድ ፍጡር በመለኮቱ የሚል ነበር (ሎቱ ስብሐት)፡፡›› ሊቃውንቱም ወልድ በባሕርይ ፍጡር ከተባለ በመዳን ላይ ስለሚደርሰው አደጋ ወዘተ በስፋት ተነጋገሩበት፡፡ በተለይም ወጣቱ አትናቴዎስ ኢየሱስ ክርስቶስ መድኃኒት ነው፤ አዳኝ ነው፤ ማዳኑን ካመንክ የባሕርይ አምላክነቱን ማመን አለብህ፤ የሚያድን እግዚአብሔር ብቻ መሆኑን መጽሐፍ ቅዱስ እንደተቀመጠና በተለይም ደግሞ በማቴዎስ ወንጌል የጠፋው በግ ምሳሌ የተቀመጠውን ምስክርነት የወልድ አምላክነት ከመዳናችን በማያያዝ እርሱ አምላክ ካልሆነ እኛም አልዳንም ማለት ነው፡፡ ያዳነን እርሱ አምላክ መሆኑን ማወቅና ማመን አለብን፡፡ ፍጡር ፍጡርን ማዳን አይችልም በማለት አርዮስን በጉባኤው ረቶታል፡፡ በመጨረሻም ጉባኤው ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ አምላክነትና በባሕርይም ከአብ ጋር አንድ ስለመሆኑ የቀረበውን መጽሐፍ ቅዱሳዊ መረጃ ከመረመሩ በኋላ በፍልስፍና ገመድ ተጠላልፎ ወልድ ፍጡር በመለኮቱ ያለውን አርዮስን አውግዘው ከቤተክርስቲያን አንድነት ለዩት፡፡

የኒቅያ ጉባኤ ቤተክርስቲያን አንድነቷን የጠበቀችበት፣ አርዮስና አርዮሳውያን የተወገዙበት፣ የጌታችን የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ የባሕርይ አምላክነት፣ አዳኝነት፣ ጌትነት፣ መድኃኒትነት የተመሠከረበት፣ ኦርቶዶክስ የሚለው ስም ትምክህት የሆነበትነ ጉባኤ ነው፡፡ እንደ ኢትዮጵያ ኦርቶዶደክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ሥርዓት መሠረት መስከረም ፳፩ እስከ ኅዳር ፱ ከመስቀል በዓል ቀጥሎ ጉባኤ ኒቅያ በሰፊው ይታሰባል፡፡

ምንጭ፤ የቤተ ክርሲቲያን ታሪክ በዓለም መድረክ በሊቀ ጳጳስ አቡነ ጎርጎርዮስ፣ የእግዚአብሔር መንግሥት በምድር ላይ በቀሲስ ምክረ ሥላሌ እና የቤተ ክርሲቲያን ታሪክ በሉሌ መልአኩ