ደቂቅ አገባብ

መምህር በትረማርያም አበባው

ግንቦት  ፳፮ ቀን ፳፻፲፬ ዓ.ም

የተወደዳችሁ አንባብያን! እንደምን ሰነበታችሁ? የእግዚአብሔር አምላካችን ስም የተመሰገነ ይሁን! ባለፈው የትምህርታችን ክፍለ ጊዜ ‹‹ዐቢይ አገባብ›› በሚል ርእስ አስተምረናችሁ ነበር፡፡ በዚህ ሳምንት ደግሞ ለሰጠናችሁ መልመጃ ምላሽና ስለ ‹‹ደቂቅ አገባብ›› እንመለከታለን፤ በጥሞና ተከታተሉን!

የመልመጃ ጥያቄዎች

የሚከተሉትን የግእዝ ዓረፍተ ነገሮች ወደ አማርኛ ተርጉሙ!

፩) ጻመወ በእንተ ዘገብረ

[ጻመወ-ደከመ፥ ገብረ-ሠራ]

፪) ሞተ እስመ ወድቀ

[ሞተ-ሞተ፥ ወድቀ-ወደቀ)

፫) ኢተረክበ ኤልያስ በይነ ዘዐርገ

[ ዐርገ-ዐረገ፥ ኢተረክበ-አልተገኘም]

የሚከተሉትን የአማርኛ ዓረፍተ ነገሮች ወደ ግእዝ ተርጉሙ!

፩) ስላነገሠው ተጸጸተ

[ነስሐ-ተጸጸተ፥ ነግሠ-ነገሠ]

፪) ከእርሷ ስለተወለደ ይወዳታል።

[እምኔሃ-ከእርሷ፥ ተወልደ-ተወለደ፥ አፍቀረ-ወደደ]

የሚከተሉትን የግእዝ ዓረፍተ ነገሮች ወደ አማርኛ ተርጉሙ!

፩) ኀበ አፍቀረነ ናፍቅሮ

፪) መንገለ ጸለየ ተባረከ

፫) ወእደ ተናገረ ተሰምዐ

፬) እስመ ወለድኪ ለነ ንጉሠ

፭) አኮኑ አጽባዕት እምነ አጽባዕት የዐቢ

የጥያቄዎች መልሶች

፩) ስለሠራ ደከመ

፪) ስለወደቀ ሞተ

፫) ኤልያስ ስላረገ አልተገኘም

፬) ነስሐ በይነ ዘአንገሦ

ነስሐ እስመ አንገሦ

፭) ያፈቅራ በእንተ ዘተወልደ እምኔሃ

የጥያቄዎች መልሶች

፩) ከወደደን ዘንድ እንውደደው

፪) ከጸለየ ዘንድ ተባረከ

፫) ከተናገረ ዘንድ ተሰማ

፬) ንጉሥን ወልደሽልናልና

፭) ከጣት ጣት ይበልጣልና

ደቂቅ አገባብ

ደቂቅ የተባለው እንደ ዐቢይ አገባብ በዐበይት አናቅጽ ላይ እየወደቀ ማሰሪያነትን ስለማያስለቅቅ ነው። አገባብ መባሉ ግን በሰዋስው ላይ እየወደቀ ማድረጊያ መነሻ አቀባይ ተሳቢ ስለሆነ ነው።

፩) ዲበ፣ላ ዕል፣መልዕልት…..ላይ ይሆናሉ። የሹመት የቦታ ናቸው።

ምሳሌ ተሠይመ ጴጥሮስ ላዕለ ሐዋርያት ስንል በሐዋርያት ላይ ተሾመ ማለት ነው። ነበረ ላዕለ ጴጥሮስ ሲም ከጴጥሮስ በላይ ተቀመጠ ማለት ነው። ተሰቅለ ክርስቶስ ዲበ ዕፀ መስቀል። ክርስቶስ በእንጨት መስቀል ላይ ተሰቀለ ማለት ነው። ላዕል በደጊመ ቃል ይነገራል። ሲነገርም የሚከተሉት ግሦች ይስማሙታል። እሊህም ርእየ፣ነጸረ፣ ሮጸ፣ሖረ፣ አንፈርዐፀ፣አንቃዕደወ ናቸው። ላዕለ ላዕለ ርእየ ቢል ወደላይ ወደላይ አየ ወይም ላይ ላዩን አየ ተብሎ ይታረጎማል። በዚህ ጊዜ አንደኛው ላዕለ አማርኛ ጨራሽ ይባላል።

፪) ታሕት፣መትሕት…….ታች ይሆናሉ። ሲገቡ ታች ባለው ባለው ነገር ነው። ድንግል ማርያምን መልዕልተ ፍጡራን መትሕተ ፈጣሪ ሲላት ከፍጡራን በላይ ከፈጣሪ በታች ናት ማለቱ ነው።

፫) ውስተ፣ውሳጤ……ውስጥ ይሆናሉ። ነበረ ውሳጤ ቤት ስንል ቤት ውስጥ ተቀመጠ ማለት ነው። ውስተ ማሕፀነ ድንግል ኀደረ ይላል።

፬) ድኅረ፣ከዋላ……ኋላ ይሆናሉ። ሖረ ድኅረ ሲል ወደኋላ ሄደ ማለት ነው። ከዋላ ይመጽእ ቢል ኋላ ይመጣል ማለት ነው።

፭) ማእከል…….መካከል ይሆናል። ተሰቅለ ክርስቶስ ማእከለ ፈያት ቢል ትርጉሙ ክርስቶስ በሽፍቶች መካከል ተሰቀለ ማለት ነው።

፮) ቅድመ፣መቅድመ…….ፊት ይሆናሉ። በቅድመ መላእክቲከ እዜምር ለከ ስንል በመላእክት ፊት እዘምርልሃለሁ ማለት ነው።

፯) ለ……ብዙ ትርጉም አለው። በቁሙ ተብሎ ይተረጎማል። ለምሳሌ ለማርያም ንዜምር ብንል ትርጉሙ ለማርያም እንዘምራለን ማለት ነው። ለ አቀብሎ ሸሽ ሲሆን ለይኩን ብርሃን ይላል። ትርጉሙ ብርሃን ይሁን ማለት ነው። ተጠቃሽና ጠቃሽ ሲሆን ተብሎ ይተረጎማል። አፈቅሮ ለክርስቶስ ብል ትርጉሙ ክርስቶስን እወደዋለሁ ማለት ነው። ለ ጊዜ ተብሎ ይተረጎማል ሀበነ ረድኤተ ለምንዳቤነ ሲንል በችግራችን ጊዜ ረድኤትን ስጠን ማለት ነው።

፰) እንበለ……..በቀር ይሆናል። ሲገባም አልቦ ባዕድ አምላክ እንበለ እግዚአብሔር ይላል። ትርጉሙ ከእግዚአብሔር በቀር ሌላ አምላክ የለም ማለት ነው።

፱) በ……….ብዙ ትርጉም አለው። በ በቁሙ ተብሎ ይተረጎማል። ለምሳሌ ንዑ ንትፈሣሕ በእግዚአብሔር ሲል ትርጉሙ ኑ በእግዚአብሔር ደስ ይበለን ማለት ነው። በ ተብሎም ይተረጎማል። ለምሳሌ ይትራወጽ ኖላዊ ሀገረ በሀገር ሲል ትርጉሙ እረኛ ሀገር ለሀገር ይሮጣል ማለት ነው። በ ተብሎ ይተረጎማል። ቀስተ ዮናታን ኢተቀብዐት በቅብዕ የሚለው ትርጉሙ የዮናታን ቀስት ቅብዕን አልተቀባችም ማለት ነው።

፲) ምስለ…….ጋራ፣ አብሮ ይሆናል። ንዒ ማርያም ምስለ ሚካኤል ይላል ትርጉሙ ማርያም ከሚካኤል ጋር ነይ ማለት ነው። ተሰደት ማርያም ምስለ ዮሴፍ ሲል ትርጉም ማርያም ከዮሴፍ ጋር ተሰደደች ተብሎ ይተረጎማል።

፲፩)በይነ፣እንበይነ፣በእንተ፣ህየንተ፣ፍዳ፣ተውላጠ፣አስበ፣እሴተ፣ቤዛ፣ ዓይነ፣ተክለ፣አቅመ፣አያተ…….. ስለ ይሆናሉ ። በእንተ/በይነ/እንበይነ ማርያም ቢል ትርጉሙ ስለማርያም ማለት ነው። ቤዛ ስለ የሚሆን ቤዛነቱን ሳይለቅ ነው። ቤዛ ይስሐቅ ወረደ በግዕ ሲል ስለ ይስሐቅ በግ ወረደ ማለት ነው። እሴተ እና አስበ ስለ የሚሆኑ ዋጋነታቸውን ሳይለቁ ነው። መስፍን ረከበ ስፉሐ ሐገረ አስበ ዕርገቱ እሴተ ዕርገቱ ይላል። ተክለ ስለ የሚሆነው ምትክነቱን ሳይለቅ ነው። ተክለሃይማኖት አውጽአ ስድስተ አክናፈ ተክለ እግሩ ይላል ትርጉሙ ተክለሃይማኖት ስለ እግሩ ስድስት ክንፎችን አወጣ ማለት ነው። ዐይነ ስለ ሲሆን  በራሱ ይገባል። ዐይነ ዐይን ይጥፋዕ ዐይን ይላል ትርጉሙ ስለ ዐይን ዐይን ይጥፋ ማለት ነው።

፲፪) ኀበ፣መንገለ፣እንተ፣ውስተ፣ለ፣በ ወደ ይሆናሉ።ንሑር ኀበ/መንገለ ግዮን ቢል ትርጉሙ ወደ ግዮን እንሂድ ማለት ነው። ውስተ ጽባሕ ነጽሩ ሲል ወደ ምሥራቅ ተመልከቱ ማለት ነው። ወመንፈስከ ቅዱስ ይምርሐኒ በምድረ ጽድቅ ሲል ቅዱስ መንፈስህ ወደ ጽድቅ ምድር ይምራኝ ማለት ነው።

፲፫) ከመ፣ሕገ፣አርአያ፣ህየንተ፣አያተ፣ ጽላሎተ፣ምስለ፣አምሳለ…. እንደ ይሆናሉ። ተክዕወ ደመ ኢየሱስ ምስለ ማይ ሲል ትርጉሙ የኢየሱስ ደም እንደ ውሃ ፈሰሰ ተብሎ ይተረጎማል። ከመ ሐሊብ ዘዕጎልት ስምከ ይጥዕም ጊዮርጊስ ሰማዕት ቢንል ትርጉሙ እንደጊደር ወተት ስምህ ይጣፍጣል ጊዮርጊስ ሰማዕት ማለት ነው። መሀረ ጳውሎስ ህየንተ ጴጥሮስ ሲል ጳውሎስ እንደ ጴጥሮስ አስተማረ ማለት ነው። አያተ መዓር ይጥዕም ሲል እንደ ማር ይጥማል ማለት ነው።

፲፬) እም፣እምነ….ከ ይሆናል። እምተናግሮ ይኄይስ አርምሞ ስንል ከመናገር ዝም ማለት ይሻላል ማለት ነው። እምን ያዳምቀዋል። ለኪ ይደሉ ዘእምኵሎሙ ቅዱሳን ይላል። እምነ መንግሥት የዐቢ ክህነት ይላል ትርጉሙ ከመንግሥት ክህነት ይበልጣል ማለት ነው።

፲፭) እስከ……እስከ ተብሎ ይተረጎማል። ምሳሌ ነግሠ ሞት እምነ አዳም እስከ ሙሴ ሲል ትርጉሙ ከአዳም እስከ ሙሴ ሞት ነገሠ ማለት ነው።

፲፮) በበ፣ለለ፣ዘዘ….እየ፣በየ ይሆናሉ። ለምሳሌ በበዘመኑ ሲል በየዘመኑ ማለት ነው። ለለዕለቱ ሲል በየዕለቱ ማለት ነው። ዘዘ ሲገባ በራሱ ይነገራል። ዘዘዚኣሁ ስንል እየራሱ ተብሎ ይተረጎማል።

የመልመጃ ጥያቄዎች

የሚከተሉትን ዓረፍተ ነገሮች ወደ ግእዝ ቋንቋ ተርጉሙ!

፩) አባቴም እስከዛሬ ይሠራል

፪) ከረኀብ ጦር ይሻላል

፫) ጅብ ከሄደ ውሻ ጮኸ

፬) እናምናለን በአብ

፭) ፊቷ እንደ ኮከብ ያበራል።

የሚከተሉትን ዓረፍተ ነገሮች ወደ አማርኛ ቋንቋ ተርጉሙ!

፩) ተንሥኡ ለጸሎት

፪) ንሑር ኀበ ደብረ ከርቤ

ረድኤተ እግዚአብሔር አይለየን!