ቅድስት አመተ ክርስቶስ

ዲያቆን ተስፋዬ ቻይ

ግንቦት ፳፮ ቀን ፳፻፲፬ ዓ.ም

ውድ የእግዚአብሔር ልጆች! እንዴት አላችሁ? የዓመቱ የትምህርት ወቅት አልቆ የፈተና ጊዜ በመድረሱ ለመፈተን ዝግጅት ላይ የሆናችሁም ሆነ የተፈትናችሁ በጥሩ ውጤት ወደ ቀጣዩ ክፍል እንደምትዘዋወሩ መልካም ምኞታችን ነው!

ውድ የእግዚአብሔር ልጆች! በርትቶ የተማረና ያጠና በመጨረሻ በጥሩ ውጤት ከክፍል ወደ ክፍል ይዘዋወራል፤ ውጤቱ ጥሩ ከሆነ ደግሞ ይደሰታል! እናንተስ ይህን ለማግኘት ዝግጁ ናችሁ? ከሆነ መልካም!

አያችሁ ልጆች! ንጉሥ ዳዊት በመዝሙሩ እንዲህ ብሏል፤ ‹‹..በለቅሶ የሚዘሩ በደስታ ይለቅማሉ…›› (መዝ.፻፳፭፥፭) እንግዲህ በትምህርት ወቅት መምህራን ሲዘሩት የነበረውን ዕውቀት፣ በአግባቡ የቀሰመ፣ ያጠና፣ ያልገባውን ጠይቆ የተረዳ፣ ጨዋታ ዋዛ ፈዛዛ ሳያበዛ የእንቅልፉን ጊዜ ለጥናት ያዋለ፣ ጠዋት በርትቶ ለትምህርት የተጋ ተማሪ የሥራውን ውጤት የሚያይበት ወቅት የዓመቱ መጨረሻ ነውና እናንተም በርትታችሁ ተማሩ፤ አጥኑ፤ መልካም!

ውድ የእግዚአብሔር ልጆች! ቅዱስ ጳውሎስ ለዕብራውያን ምእመናን በላከው መልእክቱ   ‹‹…ዓለም አልተገባቸውምና በምድረ በዳና በተራራ በዋሻና በምድር ጉድጓድ ተቅበዘበዙ..››  በማለት እንደገለጸው ዓለምን ንቀው በበረሃ በተጋድሎ ሕይወት የኖሩ ብዙ አባቶችና እናቶች አሉ፡፡ (ዕብ.፲፫፥፴፰)  ለዛሬ የኑሯቸውን ፍሬ ተመልክተን፣በእምነት እንመስላቸው፣በምግባር እንከተላቸው ዘንድ ምሳሌ ከሚሆኑን ከቅዱሳን እናቶቻችን መካከል አንዷ ስለሆነችው ስለ ቅድስት  አመተ ክርስቶስ ታሪክ በጥቂቱ ልንነግራችሁ ወደድን። መልካም ንባብ!

ውድ የእግዚአብሔር ልጆች! ቅድስት አመተ ክርስቶስ በበረሃ በተጋድሎ ሕይወት ከኖሩ እናቶቻችን አንዷ ናት! እናታችን ሀገሯ ኢየሩሳሌም ሲሆን ከወላጆቿ ጋር ስትኖር ሥነ ምግባር የነበራት፣ በድንግልና ያለች ጨዋ ልጅ ነበረች፤ ቤታቸው እየመጣም መንፈሳዊ ትምህርት የሚያስተምራት አባት (መነኩሴ) ነበረ፤ ታዲያ ያስተምራት የነበረው አባት በአንድ ወቅት ቤታቸው መምጣት አቆመ፤ በዚህ ጊዜም ቅድስት አመተ ክርስቶስ ካለበት በዓት (ገዳም) ሄዳ ከቤቱ በራፍ ቆመችና በሩን ስታንኳኳ መነኩሴውም ተጸጽቶ ልቅሶን አበዛ፤ በሩን እንዲከፍትላትና የሆነውን ለማወቅ ደጋግማ አንኳኳች፤ መነኩሴው ግን ከመጸለይና ከማልቀስ በቀር ምንም አልመለሰላትም፤ ከዚያም እዚያው እንደ ቆመች ‹‹እኔስ ለምን ስለ ጉስቁልናዬ አላዝንም፤ አልጸጸትም›› አለች፤ ወደ ቤትም ከገባች በኋላ በዘንቢል ሽንብራ በጽዋ ውኃ ይዛ ወደ ጌታችን መቃብር ጎልጎታ ሄዳ እንዲህ ጸለየች፤ ‹‹ጽኑ ኃያል ለዘለዓለም ድንቅ፣ የሆንክ የጠፉትን የምታድን፣ የወደቁትንም የምታነሣ፣ ወደ አንተ የሚጮኹትንም የምትሰማቸው የታመነችብህን ባርያህን ታድናት ዘንድ ይቅርታህንና ምሕረትህን ላክ፤ ከምግባር ደኃ የሆንኩ ባርያህን ጎብኝ፤ ንስሓዬንም ተቀበል፤ ለረጅም ዘመን ስንቅ ይሆነኝ ዘንድ ይህን ሽምብራና ይህን ጽዋ ባርከው…›› ብላ ጸሎቷን ጨረሰች፡፡

ከዚያም ውድ የእግዚአብሔር ልጆች! እናታችን ቅድስት ዓመተ ክርስቶስ ማንም ከሌለበት በርሃ ሄደች፤ የተሰነጠቀ ዓለትም (ዋሻ) አገኘችና ከዚያ ገብታ በጾም በጸሎት ኖረች፤ ይዛ ከነበረው ሽንብራና የጽዋ ውኃ እየተመገበች ፴፰ (ሠላሳ ስምንት) ዓመት በተጋድሎ ኖረች፤ ከቤቷ ስትወጣ ይዛው የነበረውን ሽንብራና ውኃም ምንም ሳይጎድል መልሶ ይሞላ ስለነበር እርሱን እየተመገበች ኖረች።

ከዚያም በአንድ ወቅት በእግዚአብሔር ፈቃድ አባ ዳንኤል የተባሉ አባት በሌሊት ተነሥተው ካሉበት ገዳም አቅራቢያ ወደ ሚገኝ ተራራ ሄዱ፤  በዚያ ተራራ ላይም መላ አካሏ ልክ እንደ አባታችን አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ በፀጉር የተሸፈነ ሰው ተመለከቱ፤ ቀስ ብለው ጠጋ ሲሉ ወደ ተሰነጠቀው ዓለት (ዋሻ) ውስጥ ገባችባቸው፤ አባ ዳንኤልም ‹‹የእግዚአብሔር ሰው ሆይ ከአንተ በረከትን እንድቀበል ወደ እኔ ትመጣ ዘንድ በእግዚአብሔር ስም እለምንሃለሁ›› ብለው ተጣሩ፤ ቅድስት ዓመተ ክርስቶስም ‹‹አባት ሆይ ሴት ነኝ፤ ልብስም አለበስኩም፤ ስለዚህ አልመጣም›› አለቻቸው፤ አባ ዳንኤልም ካባቸውን ወደ ዋሻ ውስጥ ወረወሩላት፤ ከዚያም ካባውን ደርባ ወጣች፤ አብረውም ጸሎት አደረጉ፤ ከዘንቢሉም ሽንብራ ሰጠቻቸው በሉ፤  ውኃም ከጽዋ ጠጡ፤ ምንም ሳይጎድል መልሶ ሞላ፤ ከዚያም ታሪኳን ለአባ ዳንኤል ነገረቻቸው፡፡

ውድ የእግዚአብሔር ልጆች! አባ ዳንኤል ይህን ድንቅ ተአምር ካዩ በኋላ ወደ ገዳማቸው በመሄድ ለወንድሞቻቸው መነኰሳት ነገሩ፤ ልብስም ሰብስበው ሊሰጧት ተመልሰው እናታችን ቅድስት አመተ ክርስቶስ ካለችበት ገዳም መጡ፤ ግን አላገኟትም፤ ፈልገው ባጧት ጊዜ አዝነው ሳሉ ሁለት አረጋውያን መጥተው አመተ ክርስቶስ ዐርፋ እንደቀበሯት ነገሯቸው፡፡

ውድ እግዚአብሔር ልጆች! እናታችን ቅድስት አመተ ክርስቶስ በጾም በጸሎት በገድል በትሩፋት በበረሃ ውስጥ ተወስና ለ፴፰ (ሠላሳ ስምንት) ዓመት ከተጋደለች በኋላ ግንቦት ፳፰ (ሃያ ስምንት ቀን) በክብር ዐረፈች፤ መነኰሳቱም በክብር ቀብረዋት ዋሻውን በድንጋይ ዘግተው በረከትን ተቀብለው እግዚአብሔርን እያመሰገኑ ተመለሱ፤ እኛ ግን ስለ ቅድስት አመተ ክርስቶስ በጥቂቱ ብቻ ገለጽንላችሁ፤ ከቅድስት አመተ ክርስቶስ  እናታችን ሕይወት ብዙ እንማራለን! እስኪ እናንተ  ምን ምን ተማራችሁ!!! ጨዋነትን፣ ጥሩ ሥነ ምግባር ይዞ ማደግን፣ጎበዝ አስተዋይ መሆን እንደሚገባ፣ የአባቶችን ፈለግ መከተል፣ የእግዚአብሔርን ድንቅ ሥራ፣ በእምነት መጸለይን፣ ቅዱሳት መጻሕፍትን ማንበብ፣… መልካም!

ፈጣሪችን እግዚአብሔር ከቅድስ አመተ ክርስቶስ ረድኤት በረከቱን ይክፈለን፤ አሜን! ቸር ይግጠመን!!!

ስብሐት ለእግዚአብሔር

ወወላዲቱ ድንግል

ወለመስቀሉ ክቡር አሜን!!!