‹‹ደስ ይበልሽ÷ ጸጋን የተመላሽ ሆይ÷ እግዚአብሔር ከአንቺ ጋር ነው፤ ከሴቶች መካከል አንቺ የተባረክሽ ነሽ›› (ሉቃ. ፩፥፳፰-፳፱)

ናዝሬት ገሊላ ከምትባል ከተማ ከዳዊት ወገን ከሆነው ዮሴፍ ለሚባል ሰው የታጨች አንዲት ድንግል ነበረች፤ ስሟም ማርያም ነው፡፡ ከዕለታት አንድ ቀን መንገድ ላይ በመሄድ ሳለች ‹‹ትፀንሲ›› የሚል ድምጽ ሰማች፤  መለስ ብላ ብታይ ማንንም ማየት አልቻለችም፤ ‹‹አዳም አባቴን እና ሔዋን እናቴን ያሳተ ይሆናል እንጂ ሌላ አይደለም›› ብላም አሰበች፡፡ ዳግመኛም ‹‹ትፀንሲ›› የሚል ድምጽ ሰማች፡፡ ‹‹ይህ ነገር ደጋገመኝ፤ እንዲህ ያለውን ነገር ከቤተ መቅደስ ሆነው ሊረዱት ይገባል›› ብላ ከቤተ መቅደስ ገብታ ወርቅና ሐር እያስማማች መፍተል ጀመረች፡፡

ብሥራታዊው መልአክ ቅዱስ ገብርኤልም በአምሳለ አረጋዊ እንዲህ አላት ‹‹ደስ ይበልሽ÷ ጸጋን የተመላሽ ሆይ÷ እግዚአብሔር ከአንቺ ጋር ነው፤ ከሴቶች መካከል አንቺ የተባረክሽ ነሽ፡፡›› (ሉቃ. ፩፥፳፰-፳፱) ድንግል ማርያምም ‹‹እንዲህ ያለ የምስጋና እጅ መንሻ እንዴት ይደረግልኛል?›› ብላ ጠየቀችው፡፡ መልአኩም መልሶ ‹‹ማርያምሆይ አትፍሪ፤ ከእግዚአብሔር ዘንድ ባለሟልነትን አግኝተሻልና፤ እነሆ ትፀንሺያለሽ፤ ትወልጃለሽ፤ ስሙንም ኢየሱስ ትይዋለሽ፤ ይህ የሚወለደው ከሦስቱ ቅዱስ አንዱ ቅዱስ ነው፤ እርሱም  የእግዚአብሔር ልጅ ይባላል›› አላት፡፡  እርሷም ‹‹ይህነገር እንደምን ይሆንልኛል፤ ወንድ ሳለውቅ?›› አለችው፡፡ መልአኩ ገብርኤልም ‹‹መንፈስ ቅዱስ ይጠብቅሻል፤ የልዑል ኃይልም ያድርብሻል›› አላት፡፡ እርሷም የመልአኩን ቃል ተቀብላ ‹‹እንደ ቃልህ ይደረግልኝ›› አለችው፡፡ በዚህ ጊዜ አካላዊ ቃል በግብረ መንፈስ ቅዱስ ተፀነሰ፡፡ ቅድስት ማርያም እምነቷን በእግዚአብሔር ላይ አድርጋለችና በትንቢተ ነቢያት መሠረት በድንግልና ፀነሰችው፡፡ (ኢሳ. ፯÷፲፬)

ሊቁ አባ ሕርያቆስ በቅዳሴው ስለ ቅዱስ ገብርኤል ብሥራትና ስለ አምላክ ሰው መሆን ሲመሰክር ‹‹እርሱ እግዚአብሔር አብ ንጽሕናሽን ባየ ጊዜ ስሙ ቅዱስ ገብርኤል የሚባል መልአክ ወደ አንቺ ላከ፤ መንፈስ ቅዱስ በላይሽ ያድራል፡፡ የልዑል ኃይልም ይጋርድሻል አለሽ፤ ከአባቱ ሳይለይ ቃል ወደ አንቺ መጣ ሳይወሰን ፀነስሽው፤ በላይ ሳይጎድል በታችም ሳይጨመር በማሕፀንሽ ተወሰነ፤ መጠንና መመርመር የሌለበት እሳተ መላኮት በማሕፀንሽ አደረ›› (ቅዳሴ ማርያም ቁ. ፵፭) ብሏል፡፡ ቤተ ክርስቲያናችንም ይህን የብሥራት ቀን በማሰብ ታከብረዋለች፡፡

ምንጭ፡- ነገረ ማርያም፤ ቅዳሴ ማርያም