ሐዲስ ሐዋርያ አቡነ ተክለ ሃይማኖት ዘኢትዮጵያ

ቅዱሳን ጻድቃን በመንፈሳዊ አርአያነታቸው፣ በጸሎታቸውና በትምህርታቸው ከከበቡን የነፍስ ጠላቶች፤ ከርኲሳን መናፍስትና ከጨለማው ልጆች፣ ከክፉ ሰዎች ሽንገላና ተንኰል ለመሰወርና ለመጠበቅ ከእግዚአብሔር የተቀበሉት ሥልጣን ምንጊዜም ይሠራል፡፡ በጻድቃን መኖር ሀገር ከጥፋት ትድናለች፡፡ የጻድቃንን ስም ጠርቶ እግዚአብሔርን በመለመን በረከትና ረድኤት ይገኛል፡፡ ስለ ጻድቃን ብሎ እግዚአብሔርም ምሕረቱን ያድላል፡፡ ጻድቃንን ማሰብ ሥራቸውን መዘከር ክርስቲያናዊ ሕይወታችንን ያጐለምሳል፤ በነፍስ በሥጋ ይታደገናል፤ ይጠቅመናል፡፡

ስለዚህም ቤተ ክርስቲያናችን ጻድቃንን እንድናስባቸው፣ በስማቸውም ለድሆች እንድንመጸውት፣ መታሰቢያቸውን እንድናደርግ የምትመክረን፤ የምታስተምረን (ማቴ.፲፥፵፩-፵፪)፡፡ ቅዱሳን ጻድቃን በሕይወተ ሥጋ ሳሉም ሆነ ከሞቱ በኋላ በዐጸደ ነፍስ ሆነው በጸሎታቸው ለሚታመኑ፣ በቃል ኪዳናቸው ለሚማጸኑ ምእመናን በመጸለይና ወደ እግዚአብሔር በማማለድ ድኅነተ ሥጋ፣ የድኅነት ነፍስን የሚያስገኙልን የችግር ጊዜ አማላጆቻችንና አስታራቂዎቻን ናቸው፤ ከእነዚህ ቅዱሳን መካከል ኢትዮጵያዊው ጻድቅ አቡነ ተክለ ሃይማኖት አንደኛው ናቸው፡፡

ተክል ማለት ፍሬያማ ዕንጨት፣ ዛፍ፣ ቅመም፣ ቅጠላ ቅጠል፣ የሚበላ፣ የሚሸተት፣ ገነታዊ ዕፅ፣ እንዲሁም ሕግ፤ ሥርዓት ማለት ነው (ማቴ.፲፭፥፲፫)፡፡ ሃይማኖትማለት ደግሞ በሀልዎተ እግዚአብሔር፣ እግዚአብሔር የሁሉ አስገኚ መሆኑን፣ በሥላሴ አንድነትና ሦስትነት፣ በቅዱሳን ተራዳኢነት ማመን አምኖም መመስከር ማለት ሲሆን ተክለ ሃይማኖት የሚለው ሐረግም የሃይማኖት ተክል፣ ይኸውም የጽድቅ ፍሬን ያፈራ፣ ከኃጢአት ሐሩር ማምለጫ ዛፍ፣ ምእመናንን በቃለ ወንጌል ያጣፈጠ ቅመም፣ መዓዛ ሕይወቱ የሚማርክ፣ ቢመገቡት ረኃበ ነፍስን የሚያስወግድ ቅጠል፣ የጻድቃን መጠለያ ዕፅ የሚል ትርጕም አለው፡፡‹‹ተክለ ሃይማኖት ማለት የአብ የወልድ የመንፈስ ቅዱስ ተክል ማለት ነው›› ሲል የጻድቁን ስም ይተረጕመዋል፡፡

ጻድቁ አባታችን ሕይወታቸዉን ሙሉ ለእግዚአብሔር በመስጠት፣ እንደ በሬ ተጠምደው፣ እንደ ገበሬ ታጥቀው፣ ይህንን ዓለም ንቀው፣ በጾም በጸሎት ተወስነው በብሕትውና በመኖራቸው፤ እርሳቸው በአሚነ ሥላሴ ጸንተው ሌሎችንም እንዲጸኑና እንዲያምኑ በማድረጋቸው፤ እንደዚሁም እንደ ቅዱሳን ሐዋርያት ወንጌልን በመላው ኢትዮጵያ እየተዘዋወሩ በመስበክ በጌታችን በመድኃኒታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ስም ድውያነ ሥጋን በተአምራት፣ ድውያነ ነፍስን በትምህርት የፈወሱ ሰባኬ ወንጌል በመሆናቸው ‹‹ተክለ ሃይማኖት›› ተብለው ይጠራሉ፡፡

አቡነ ተክለ ሃይማኖት በእግዚአብሔር ድንቅ ጥበብ፣ በሊቀ መላእክት ቅዱስ ሚካኤል ብሥራት፤ በኢትዮጵያ ምድር በሰሜን ሸዋ ሀገረ ስብከት ልዩ ስሙ ኢቲሳ በሚባል ቦታ ከአባታቸው ከካህኑ ጸጋ ዘአብና ከእናታቸው ከቅድስት እግዚእ ኀረያ መጋቢት ፳፬ ቀን ተፀንሰው ታኅሣሥ ፳፬ ቀን ፲፪፻፲፪ ዓ.ም ተወለዱ፡፡ በተወለዱ በሦስተኛው ቀን እሑድ ከጠዋቱ ሦስት ሰዓት ከእናታቸው ዕቅፍ ወርደው ‹‹አሐዱ አብ ቅዱስ፤ አሐዱ ወልድ ቅዱስ፤ አሐዱ ውእቱ መንፈስ ቅዱስ፤ አንዱ አብ ቅዱስ ነው፤ አንዱ ወልድ ቅዱስ ነው፤ አንዱ መንፈስ ቅዱስ ነው፤›› በማለት ሥላሴን አመስግነዋል፡፡ ወላጆቻቸው ያወጡላቸው ስም ፍሥሐ ጽዮን የሚል ሲሆን ተክለ ሃይማኖት›› ደግሞ የእግዚአብሔር መልአክ ቅዱስ ሚካኤል ያወጣላቸው ስም ነው፡፡ በተወለዱ በ፲፭ ዓመታቸው ዲቊናን፤ በ፳፪ ዓመታቸው ደግሞ ቅስናን ከግብፃዊው ጳጳስ ከአባ ጌርሎስ (ቄርሎስ) ተቀብለዋል፡፡

አንድ ቀን ወደ ጫካ ለአደንበሔዱበት ዕለት ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ተገልጦላቸው ጸጋ መንፈስ ቅዱን አሰደረባቸው፤ እንደዚሁም ሐዲስ ሐዋርያ ብሎ ወንጌል ወዳልተዳረሰበት ቦታ እንደሚልካቸው ነገራቸው፡፡ ቅዱስ ሚካኤልም ከአውሬ አዳኝነት ሰውን ወደ እግዚአብሔር መንግሥት ለመመለስ እንደ ተመረጡና አጋንንትን የማውጣት፣ ተአምራትን የማድረግ ሥልጣን እንደ ተሰጣቸው፤ ስማቸውም ተክለ ሃይማኖት እንደሚባልና ትርጓሜውም ተክለ አብ፣ ተክለ ወልድ፣ ተክለ መንፈስ ቅዱስ ማለት እንደ ሆነ አስረዳቸው፡፡ ከዚህ በኋላም ወደ ቤታቸው ተመልሰው ያላቸውን ንብረት ሁሉ ለቤተ ክርስቲያንና ለነዳያን ሰጥተው አቤቱ ጌታዬ ኢየሱስ ክርስቶስ ሆይ! የመንግሥተ ሰማያትን በር ትከፍትልኝ ዘንድ እነሆ ቤቴን እንደተከፈተ ተውኩልህ›› በማለት ቤታቸውን ትተው ወንጌልን ለማስተማር ፈጥነው ወጡ፡፡ ከዚያ ጊዜ ጀምረው በመላው ኢትዮጵያ እየተዘዋወሩ ወንጌልን በመስበክና ተአምራትን በማድረግ ብዙ አሕዛብን ከአምልኮተ ጣዖት ወደ አምልኮተ እግዚአብሔር፤ ከገቢረ ኀጢአት ወደ ገቢረ ጽድቅ መልሰዋል፡፡ ቤተ ክርስቲያንንም አንጸዋል፡፡ ሐዲስ ሐዋርያየተባሉትም በዚህ ተልእኳቸው ሲሆን፣ ትርጕሙም ሐዲስ ኪዳንን ወይም ሕገ ወንጌልን እየተዘዋወረ የሚያስተምር ሰባኬ ወንጌል፤ በክርስቶስ ስም ድንቅ ድንቅ ተአምራትን የሚደርግ የክርስቶስ ተከታይ (ሐዋርያ) ማለት ነው፡፡

አባታችን ተክለ ሃይማኖት ሕይወታቸዉን ሙሉ ለእግዚአብሔር በመስጠት፣ እንደ በሬ ተጠምደው፣ እንደገበሬ ታጥቀው፣ ይህንን ዓለም ንቀው፣ በጾም በጸሎት ተወስነው፣ በብሕትውና ኖረዋል፡፡ በተጨማሪም እንደቅዱሳን ሐዋርያት ወንጌልን በመላው ኢትዮጵያ እየተዘዋወሩ የሰበኩ፣ በጌታችን በመድኃኒታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ስም ድውያነ ሥጋን በተአምራት፣ ድውያነ ነፍስን በትምህርት የፈወሱ ሐዋርያ ናቸው፡፡ አቡነ ተክለ ሃይማኖት ከሚታወሱባቸው በዓላት መካከልም ታኅሣሥ ፳፬ ቀን የሚከብረው በዓለ ልደታቸው አንደኛው ነው፡፡ መጽሐፈ ስንክሳር ዜና ልደታቸውን ሲናገር ‹‹ሐዲስ ሐዋርያ›› በማለት በክብር ጠርቷቸዋል፡፡

ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለደቀ መዛሙርቱ ‹‹እናንተን የሚቀበል እኔን ይቀበላል፤ እኔንም የሚቀበል የላከኝን ይቀበላል፡፡ ነቢይን በነቢይ ስም የሚቀበል የነቢይን ዋጋ ያገኛል፡፡ ጻድቅንም በጻድቅ ስም የሚቀበል የጻድቁን ዋጋ ያገኛል፡፡ማንም ከእነዚህ ከታናናሾቹ ለአንዱ ቀዝቃዛ ጽዋ ብቻ በደቀ መዝሙር ስም የሚያጠጣ እውነት እላችኃለሁ፤ ዋጋ አይጠፋበተም፤››(ማቴ. ፲፥፵-፵፪) በማለት የተናገረውን መለኮታዊ ቃል ኪዳን ቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን መሠረት አድርጋ መጋቢት ፳፬ ቀን ፅንሰታቸውን፣ ታኅሣሥ ፳፬ ቀን ልደታቸውን፣ ጥር ፳፬ ቀን ስባረ ዐፅማቸውን፣ ግንቦት ፲፪ ቀን ፍልሰተ ዐፅማቸውን፣ ነሐሴ ፳፬ ቀን ደግሞ ዕለተ ዕረፍታቸውን በመንፈሳዊ ሥርዓት በደስታ ታከብራለች፡፡ የአቡነ ተክለ ሃይማኖትና የሁሉም ጻድቃን ጸሎት፣ በረከት፣ ረድኤትና ምልጃ በመላው ሕዝበ ክርስቲያን ላይ ለዘለዓለሙ ጸንቶ ይኑር፡፡

ስብሐት ለእግዚአብሔር

ምንጭ፡ ገድለ አቡነ ተክለ ሃይማኖት፤ መጽሐፈ ስንክሳር (ታኅሣሥ ፳፬፣ ጥር ፳፬፣ መጋቢት ፳፬፣ ግንቦት ፲፪ እና ነሐሴ ፳፬ ቀን)፤ መለከት መጽሔት ፲፰ኛ ዓመት፣ ቍጥር ፱፡፡