የነነዌ ጾም

ዲያቆን ፍቅረሚካኤል ዘየደ

የካቲት ፲፩ ቀን ፳፻፲፫ ዓ.ም

እግዚአብሔር አምላካችን ወዶ እና ፈቅዶ ከሰባቱ አጽዋማት አንዱ ለሆነው የነነዌ ጾም አድርሶናል፡፡ ሦስት ቀናት የሚጾመው ይህ ጾም የነነዌን ሕዝብ ከጥፋት መመለስ፣ የእግዚአብሔርን ምሕረት እንዲሁም የነቢዩ ዮናስን የዋህነት ያስረዳናል፡፡

በዚያን ዘመን የነነዌ ሰዎች በእግዚአብሔር ፊት የተወገዙ ተግባራትን ይፈጽሙ ነበር፤ ለጣዖታት መስገድና መሠዋት፣ ጥንቆላን ማስፋፋት፣ ሥር እየማሱ ቅጠል እየበጠሱ የሰዎችን አኗኗር ማጎሳቆልና ማዘበራረቅ፣ በዘፈን፣ ስካር፣ በዝሙትና ሌሎች የሥጋ ፈቃዳትን በራስና በሌሎች ላይ መፈጸምም የተለመደ ምግባራቸውም ነበር፡፡ (ገላ ፭÷፲፯-፲፱)

በዚህም ጊዜ እግዚአብሔር አምላክ በእነርሱ ተቆጥቶ የነነዌን ከተማ ሊያጠፋት ቀረበ፤ ሆኖም ግን የፈጣሪ ቸርነትና ምሕረት አያልቅምና በንስሓ ይመለሱ ዘንድ ነቢዩ ዮናስን ወደ እነርሱ ላከው፡፡ ‹‹ተነስተህ ወደ ታላቂቱ ከተማ ወደ ነነዌ ሂድ፤ የክፋታቸውም ጩኸት ወደ ፊቴ ወጥቶአልና ለእነርሱ ስበክ›› አለው፡፡ ነቢዩ ዮናስ ግን ይህን አምላካዊ ትእዛዝ ሳያከብር ከአምላኩ ይሸሽ ዘንድ ወደ ተርሴስ ተነሣ፤ ወደ ኢዮጴም ወረደ፡፡ እንደ ስሙ ርግብ የዋህ የሆነው ዮናስ በሦስት ቀን ውስጥ ነነዌ ትገለበጣለች ብሎ ካስተማረ በኋላ አምላክ መሐሪ ነውና ቢምራቸው ሐሰተኛ እንዳይባል ፈርቶ ከአምላክ መሸሽን መረጠ፡፡ እዚህ ጋር ልናስተውለው የሚገባው ነቢዩ ዮናስ ለመሸሽ የመረጠበትን ምክንያት ነው፡፡ የእርሱ ጭንቀት ‹‹ዛሬ ነነዌ ትጠፋለች ብዬ ሳትጠፋ ብትቀር ወደፊት ማን ለቃሉ እና ለትንቢት ይገዛል፤ ነቢያተ እግዚአብሔርንስ ማን ያደምጣል፤ ማንስ ያከብራቸዋል›› የሚል ነው፡፡ ለአምላኩም ያለው ቀናኢነት እና ጭንቀት እስከ አለመታዘዝ እና መኮብለል አደረሰው፡፡ (ዮና. ፩፥፪)

ወደ ተርሴስም የምታልፍ መርከብ አግኝቶ ተሳፈረ፤ በመርከቡ ላይ እያለም እግዚአብሔር መርከቧን በማዕበል እንድትመታ አደረገ፡፡ ከዮናስ ጋር ተሳፍረው የነበሩ ነጋድያንም ያላቸውን ሀብት ወደ ባሕሩ መጣል ጀመሩ፤ በዚህ ጊዜ ዮናስ በእርሱ ጥፋት ምክንያት ማዕበሉን መነሣቱን በመረዳት ‹‹ማዕበሉ በእኔ ምክንያት የመጣ ስለሆነ ንብረታችሁን ሳይሆን እኔን ወደ ባሕር ጣሉኝ›› አላቸው፡፡ እነርሱም ‹‹ስለዚህ ሰው ነፍስ እንዳንጠፋ፣ ንጹሕም ደም በእኛ ላይ እንዳይደረግብን አይሆንም›› አሉ፡፡ ወደ ባሕሩ ለመጣል ዕጣ በተጣጣሉ ጊዜም ዕጣው በዮናስ ላይ ስለ ወጣ ነጋድያኑ ዮናስን ወደ ባሕሩ ጣሉት፡፡ ከመቅጽበትም ከእግዚአብሔር ዘንድ የታዘዘ ታላቅ ዓሣ አንበሪ ዮናስን ዋጠው፤ ሦስት ቀንና ሦስት ሌሊትም በእርሱ ውስጥ ተቀመጠ፤ በዓሣ አንባሪው ሆድ ውስጥም ሆነም ወደ እግዚአብሔር ይጸልይ ነበር፡፡ በሦስተኛውም ቀን ዓሣ አንባሪው ዮናስን ከባሕሩ ዳርቻ ወስዶ ተፋው፡፡ ዮናስም ነነዌ መድረሱን ባወቀ ጊዜ ከእግዚአብሔር መሸሽ አለመቻሉን ተረድቶ ወደ ከተማው በመሄድ የነነዌ ሰዎችን ንስሓ እንዲገቡ ይሰብክ ጀመር፡፡ ‹‹ዮናስም ተነሥቶ እንደ እግዚአብሔር ቃል ወደ ነነዌ ሄደ፤ ነነዌም ታላቅ ከተማ ነበረች፤ የቅጥርዋም ዙሪያ በእግር የሦስት ቀን መንገድ ያህል ነበር፡፡ ዮናስም የአንድ ቀን መንገድ ያህል ወደ ከተማዪቱ ውስጥ ሊገባ ጀመረ፤ ጮኾም፥ በሦስት ቀን ውስጥ ነነዌ ትገለበጣለች›› እንዲል፡፡ (ዮና. ፩፥፲፪፣ ፫፥፫)

የነነዌ ሰዎችም ቃሉን ሰሙ፤ ‹‹የነነዌ ሰዎችም እግዚአብሔርን አመኑ፤ ለጾም አዋጅ ነገሩ፤ ከታላቁ ጀምሮ እስከ ታናሹ ድረስ ማቅ ለበሱ፤ንጉሡም ከዙፋኑ ተነሥቶ መጎናጸፊያውን አውልቆ ማቅም ለበሰ፤ በአመድም ላይ ተቀመጠ›› ተብሎ እንደተነገረም ንስሓ ገቡ፤ እግዚአብሔር አምላክም ይቀር ብሎ ከጥፋት አዳናቸው፡፡ (ዮና. ፫÷፭-፮)

ነገር ግን ዮናስ በዚህ አልተደሰተም፡፡ የነነዌን መዳን አልተቀበለም፡፡ ሕዝቡም አስመሳይ እና ሐሰተኛ ነቢይ ነው ብለው እንዳይገምቱ ፈርቶ ነበር፡፡ ስለዚህም ወደ እግዚአብሔር ጸለየ ‹‹አቤቱ፥ በሀገሬ ሳለሁ የተናገርሁት ይህ አልነበረምን? አንተ ቸርና ይቅር ባይ፥ ታጋሽም፥ ምሕረትህ የበዛ፥ ከክፉው ነገርም የምትመለስ አምላክ እንደ ሆንህ ዐውቄ ነበርና ስለዚህ ወደ ተረሴስ ለመኰብለል ፈጥኜ ነበር፡፡ አሁንም አቤቱ! ከሕይወት ሞት ይሻለኛልና እባክህ! ነፍሴ ከእኔ ውሰድ፡፡ እግዚአብሔርም ዮናስን ፈጽመህ ታዝናለህን?›› አለው፡፡ (ዮና.፬፥፪-፬)

ከዚህ በኋላም ነቢዩ ዮናስ ከከተማ ወጣ፤ በምሥራቅ በኩል ትንሽ ዳስ ሠራ እና ከጥላዋ በታች ተቀመጠ፡፡ እግዚአብሔር ለከተማይቱ እንደሚራራ ወይም ለእርሱ ብሎ ያጠፋው እንደሆነ ለማየት ፈለገ፡፡ እግዚአብሔር ግን አንድ ቅል እንዲያድግ እና ዮናስን ከፀሐይ እንዲያስጠልለው አደረገ፡፡ ዮናስም ስለ ቅሉ እና ከጥላው በታች ስለተቀመጠበት ቦታ ተደሰተ፡፡ ሆኖም እግዚአብሔር አምላክ ዮናስ የተጠለበበትን ቅል ትል እንዲመታውና እንዲደርቅ አደረገ፡፡

በቀጣዩ ቀን ነፋስ እና ፀሐይ ዮናስን አሳቃየው፡፡ ይህም የእግዚአብሔር ትእዛዝ ነበር፤ ዳግምም ዮናስ ተስፋ በመቍረጥ ሞቱን ተመኘ፡፡ ከዚያም እግዚአብሔር እንዲህ አለው፤ ‹‹አንተ ትበቅል ዘንድ ላልደከምክባት፥ ላላሳደግሃትም፥ በአንድ ሌሊት ለበቀለች፥ በአንድ ሌሊትም ለደረቀችው ቅል አዝነሃል፡፡ እኔስ ቀኛቸውንና ግራቸውን የማይለዩ ከመቶ ሃያ ሺህ የሚበልጡ ሰዎችና ብዙ እንስሶች ላሉባት ለታላቂቱ ከተማ ለነነዌ አላዝንምን?›› አለው፡፡ ነቢዩ ዮናስ ያኔ ወንዶች፣ ሴቶች እና ትናንሽ ሕፃናት ሁሉ በእግዚአብሔር ፊት ውድ መሆናቸውን፣ የእርሱን ሕልውና የማያውቁትን እንኳን እንደሚያውቃቸው ተረዳ፡፡ (ዮና.፬፥፲-፲፩)

እኛም ይህን ጾም እንደነነዌ ሰዎች ከልባችን ብንጾም ከእግዚአብሔር ይቅርታንና ምሕረተን ለማግኘት ይረዳናል፡፡ ከበደላችን ብንመለስ እና ንስሓ ብንገባ ፈጣሪያችን እግዚአብሔር ይቅርታና ምሕረትን የባሕርይ ገንዘቡ ስለሆነ ‹‹ወደ እኔ ተመለሱ፤ እኔም ይቅር እላችኋለሁ፤›› ብሎ ይቅር ይለናል፡፡ ከዚህም ባሻገር አሁን ካለንበት የችግር አረንቋ፣ ቸነፈር እንዲሁም ጦርነት ይታደገን ዘንድ በጾም እና ስግደት እንማጸነው፡፡ የዚህ ዓመት ‹‹የነነዌ ጾም›› የካቲት ፲፭ ጀምሮ እስከ ፲፯ ድረስ በመሆኑ ሁሉም ክርስቲያን ሊጾመው ይገባል፡፡

አምላካችን እግዚአብሔር ጾሙን በሰላም አስጀምሮ ያስጨርሰን፤ አሜን፡፡

ወስብሐት ለእግዚአብሔር