ስእለት

ዲያቆን ገብረሥላሴ ሽታሁን

የካቲት ፱ ቀን ፳፻፲፫ ዓ.ም

ስእለት ማለት ልመና፣  ምልጃ፣ ጸሎት፣ ጥየቃ እንደሆነ አለቃ ኪዳነ ወልድ ክፍሌ በመጽሐፈ መጽሐፈ ሰዋስው ወግስ ወመዝገብ ቃላት ሐዲስ ገልጸዋል፡፡ ሰዎች በተለያዩ ምክንያቶች ስእለት ይሳላሉ፡፡ ለምሳሌ ‹‹እግዚአብሔር የልቤን ጭንቀት ቢፈጽምልኝ እንዲህ አደርግለታለሁ፡፡ እመቤቴ ማርያም ስእለቴን ወይንም ልመናዬን ብትሰማኝ ለቤተ ክርስቲያን እንዲውል ጃን ጥላ አስገባለሁ››  ብለው ይሳለሉ፤ ወይንም አቅማቸው የፈቀደውን ነገር እንደሚሰጡ ቃል ይገባሉ፡፡ ስእለታቸውም ሲደርስ ‹‹እመቤታችን እንዲህ አድርጋልኛለች›› ብለው ለክብሯ መገለጫ ድባብ ወይንም የተሳሉትን ነገር ለቤተ ክርስቲያን ይሰጣሉ፡፡(ገጽ ፰፻፵፪)

ነቢዩ ዳዊት እንዲህ ሲል ተናግሯል፤ ‹‹በሕዝብ ሁሉ ፊት ስእለቴን ለእግዚአብሔር እሰጣለሁ፡፡›› የዚህም የመጀመሪያው ፍቺ ልመናዬን አቀርባለሁ ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ የሚታይ የሚዳሰሰውን ለቤተ መቅደስ አገልግሎት የሚውለውን ንዋየ ቅዱሳት እሰጣለሁ ማለት ነው፡፡ (መዝ. ፻፲፭፥፱)

በተጨማሪም ነቢዩ ዳዊት  ‹‹ለእግዚአብሔር የምስጋናን መሥዋዕት ሠዋ፥ ለልዑሉም ጸሎትህን ስጥ፤›› በማለት እንደተናገረው የተሳልነውን ስእለት ለእግዚአብሔር መስጠት ተገቢ ነው፡፡ ከሚሰጡት ስእለቶች ውስጥ አንዱ ደግሞ የበኲር ወይንም የመጀመሪያ ልጅ ብፅዓት /አገልጋይ/ አድርጎ መስጠት ነው፡፡ (መዝ. ፵፱፥፲፬)

ነገር ግን የስእለትን ትክክለኛ ትርጒሙን ወይንም ምክንያቱን የተረዳንንም ሆነ ያልተረዳን ሰዎች ልንኖር እንችላለን፡፡ ስለዚህም ስእለቶቻችንን ከመሳላችን በፊት ምን ብለን መሳል እንዳለብን ማወቅ እና መመርመር አለብን፡፡ ልመና ስናቀርብ ከነፍስ ጋር ማዋሐድ ቢጠበቅብንም እኛ ግን ለሥጋችን ድሎት ብቻ በማሰብ ምሳል ሰዎች አለንና፡፡ ለምሳሌ አንዲት እናት ልጇ በትምህርት ቤት ውስጥ የሚፈተነው ፈተና እንዲያልፍላት መሳል በጎ ነው፡፡ ሆኖን ግን ሰርቆ እንዲያልፍልኝ የሚል ከሆነ ግን ኃጢአት ይሆንባታል፡፡

የልጇ ኑሮም እንዲሻሻልላት፣ ከሱስ እንዲላቀቅ፣ ክፉ እንዳይገጥመው ስእለት መግባት መልካም ነው፤ ነገር ግን ‹‹እንዲያው ከዚህች ድኃ ሀገር ተላቆ ሰው የሠለጠነበት ክፍለ ዓለም ይሂድልኝ›› ብሎ መሳል ኃአጢአት ነው፡፡

ስእለትን የፈጸሙ ወይንም የተገበሩ ደጋግ አባቶችና እናቶች እንዲሁም ወንድሞችና እኅቶች  እንዳሉ ግን መዘንጋት የለበትም፡፡ አባታችን አብርሃም የተባረከ ትዳር ካላቸው ቅዱሳን ሰዎች ውስጥ የመጀመሪያው ነው፡፡፡ እርሱም እስማኤል፣ ኬጡራ ደግሞ ስድስት ልጆች ወልዷል፤ ነገር ግን ቅድስት ሣራ የወለደችው ልጅ አንድ ይስሐቅን ብቻ ነው፡፡ አብርሃምም የእግዚአብሔር ትእዛዛ ያከብር ዘንድ ይገባልና ከሣራ የወለደውን አንድ ልጁን ይሠዋ ዘንድ ታዞ ነበር፡፡  በብሉይ ኪዳንም  አምልኮተ እግዚአብሔር የሚፈጸምበት መሥዋዕት ነውና፡፡  ሆኖም እግዚአብሔር አምላክ አብርሃም ለእርሱ የታመነ እንደሆነ ስላወቀ ልጁን ማረለት፤ ከእርሱም የዘር ሐረግ እንዲወለድ ትንቢት ተነገሯልናም ዘሩን አበዛለት፤ ባረከለትም፡፡

የጌታችን መድኃታችንን ኢየሱስ ክርስቶስ እናት ትሆን ዘንድ የተመረጠችው ንጽሕተ ንጹሓን ቅድስተ ቅዱሳን ቅድስት ድንግል ማርያምን የወለደች ቅድስት ሐናም ከደጋገች እናት መካከል ናት፡፡ ለብዙ ዘመናት ልጅ ሳትወለድ በመኖሯ አምላኳን እግዚአብሔርን ትማጸንም ነበር፡፡ እናታችን ቅድስት ሐና ፈጣሪዋን ወርቅ፣ ንብረት ወይንም ሀብት እንዲሰጣት አለመነችውም፡፡ ምክንያቱም ይህ ለዘለዓለማዊ ሕይወታችን የምንጠቀመው ሳይሆን ለኩነተ ሥጋ የምንጠቀመው ነገር ብቻ ነው፡፡ ‹‹እባክህ የማሕፀኔን ፍሬ ስጠኝ፤ የሰጠኸኝንም ፍሬ ለእግዚአብሔር አገልጋይ አደርገዋለሁ›› ብላም ስለተሳለች ከተቀደሱ የተቀደሰች ከተከበሩ የተከበረችውን እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያምን ወልዳለች፡፡  ቅድስት ሐናም በተሳለችው መሠረት ልጇ ቅድስት ማርያም በሦስት ዓመቷ ገና ጡት መጥባት ስታቆም ወደ ቤተ መቅደስ ወስደው ሰጥተዋታል፡፡ (መጽሐፈ ስንክሳር ነሐሴ ፯)

በሀገራችን ኢትዮጵያም ውስጥ በዘመናት የኖሩ ደጋግ አባቶች እና እናቶች ተስለው ያገኟቸውን ልጆች ለቤተ ክርስቲያን አገልጋይነት ይሰጡ እንደነበር ታሪክ ያወሳናል፡፡ እኛም የተሳልነው ስእለት ቢደርስልን እንደነርሱ ማድረግ እንችል እንደሆነ በደንብ ልናስብበት ይገባል፡፡ ምክንያቱም እግዚአብሔር አምላክ የሚሳነው የለምና ልመናችንን ሰምቶና መማጸኛችንን ተቀብሎ ስእለታችንን ሲፈጽምልን ‹‹እንዲሁ እስኪ ልሞክር እና ስእለቴ ከደረሰ የሚሆነውን አደርጋለሁ ወይንም እዚሁ ከእኔ ጋር ሆኖ አምላኩን ቢያገለግል ችግር የለውም›› ብሎ አስቦ ስእለትን ማስቀረት በኋለኛው ዘመን ያስጠይቀናል፡፡ በተለይም ሥርዓቱ እንደሚያዘው የበኲር ልጅን ለቤተ ክርስቲያን አገልጋይነት መስጠት ለበረከት እንደሆነ ሁሉ ለመስጠት መሰሰት ደግሞ ያስቀጣል፡፡ ‹‹አንድ ልጄን እንዴት አሳልፌ እሰጣለሁ›› ብሎ ልክ ለሞት አሳልፈው እንደሚሰጡ ያህል የሚሰማቸው ሰዎች ጥቂት አይባሉም፡፡

በቤተ ክርስቲያን አገልግሎትና ሥርዓት ማደግ የተቀደሰ እና የተባረከ ነገር ነው፤ ብዙዎቻችን ግን ይህ አልገባንም፤ በሥርዓተ ቤተ ክርስቲያን ማደጋችንን ቀለል አድርጎ ማየት ተገቢ አይደለም፡፡ ሥራችን የሚባረክልን፣ ኑሯችን ውስጥ ሰላም እና ደስታ የሚኖረን  እና የተባረከ ትዳርም የምንመሰርተው እግዚአብሔርን ማገልገል ስንችል ነው፡፡ የስእለት ልጅ መሆናችን ለቤተ እግዚአብሔር አገልጋይ ለመሆን ያበቃናልና ልንኮራበት ይገባል፡፡

በአሁኑ ጊዜ ቤተሰቦቻችን ተስለው የወለዱን ልጆች እንኖራለን፤ ለቅዱሳን አባቶች ወይንም እናቶች ለስእለት የተሰጠን አለን፡፡ ስእለታቸው ግን ልጅ ከሰጣቸው ለቤተ ክርስቲያን አገልጋይ እንደሚሰጡት ቃል መግባት ሳይሆን በዚያ ፈንታ ሌላ ነገር ይሰጣሉ፡፡ ይህም ቅድስት ሐናንና ቅድስት ሣራን ተምሳሌት አድርጎ ባለመውሰደቻው የተነሣ የፈጸሙት ስሕተት እንደሆነና የመንፈሳዊ አቅም ማነስ መሆኑን መረዳት ያሻል፡፡

ስእለታችን እንደ ስእለተ ቅድስት ሐናንና ስእለት ቅድስት ሣራ እንዲሁንልን ቅዱስ ፍቃዱ ይሁንልን፡፡