ዘመነ ክረምት – የመጨረሻ ክፍል

በዲያቆን ኤፍሬም የኔሰው

መስከረም ፲፮ ቀን ፳፻፲ ዓ.ም

የተወደዳችሁ የማኅበረ ቅዱሳን ድረ ገጽ ተከታታዮች! በክፍል ስምንት ዝግጅታችን ስድስተኛውን የክረምት ንዑስ ክፍል (ዘመነ ፍሬን) በሚመለከት ወቅታዊ ትምህርት ማቅረባችን ይታወሳል፡፡ በዛሬው የመጨረሻ ክፍል ዝግጅታችን ደግሞ ሰባተኛውን ክፍለ ክረምት (ፀአተ ክረምትን ወይም ዘመነ መስቀልን) የሚመለከት ትምህርት ይዘን ቀርበናል፡፡ ትምህርቱን እንድትከታተሉ መንፈሳዊ ግብዣችንን አስቀድመናል፡፡ መልካም የንባብ ጊዜ ይኹንላችሁ!

፯. ፀአተ ክረምት (ዘመነ መስቀል)

ከመስከረም ፲፮ – ፳፭ ቀን ድረስ ያለው ሰባተኛው የክረምት ክፍለ ጊዜ ፀአተ ክረምት ወይም ዘመነ መስቀል በመባል የሚታወቅ ሲኾን ይኸውም የክረምት መውጣት እና በአተ መጸው (የመጸው መግባት) የሚሰበክበት ወቅት ነው፡፡ የፀአተ ክረምት መጨረሻ የሚኾነውም መስከረም ፳፭ ቀን ነው፡፡ ‹ፀአተ ክረምት› የሚለው የግእዝ ቃላት ጥምረት ‹የክረምት መውጣት› የሚል ትርጕም አለው፡፡ የክረምት መውጣት ሲባል ለዘመነ ክረምት የተሰጠው ጊዜ በዘመነ መጸው መተካቱን ለማመልከት እንጂ ክረምት ተመልሶ አይመጣም ለማለት አይደለም፡፡ የሰው ልጅ ምድራዊ ሕይወት እስከሚያበቃበት እስከ ኅልፈተ ዓለም ድረስ የወቅቶች መፈራረቅም አብሮ ይቀጥላልና፡፡ ቅዱሳት መጻሕፍትም ይህንን የወቅቶች መፈራረቅ ለመግለጽ ነው ‹‹መግባት፣ መውጣት›› እያሉ በክፍል በክፍል የሚያስቀምጧቸው፡፡

ጠቢቡ ሰሎሞን ‹‹እስመ ናሁ ክረምት ኀለፈ ወዝናም ገብአ ድኅሬሁ ጽጌ አስተርአየ በውስተ ምድርነ ጊዜ ገሚድ በጽሐ ቃለ ማዕነቅ ተሰምዐ በምድርነ በለስ አውጽአ ሠርጸ አውያን ጸገዩ ወወሀቡ መዓዛ፤ እነሆ ክረምት ዐለፈ፤ ዝናቡም ዐልፎ ሔደ፡፡ አበባ በምድር ላይ ታየ፤ የመከርም ጊዜ ደረሰ፡፡ የቊርዬውም ቃል በምድራችን ተሰማ፡፡ በለሱ ጐመራ፤ ወይኖችም አበቡ፤ መዓዛቸውንም ሰጡ፤›› (መኃ. ፪፥፲፩-፲፫) በማለት እንደ ተናገረው አሁን የክረምቱ ጊዜ አብቅቶ ሌላ ወቅት ዘመነ መጸው ተተክቷል፡፡ መጭው ዘመን የተስፋ፣ የንስሐና የጽድቅ ወቅት እንዲኾንልን እግዚአብሔርን ከፊት ለፊታችን ማስቀደም ይኖርብናል፡፡ እርሱ ከቀደመ መሰናክሎቹን ለማለፍ፣ ፈተናዎችንም ለመወጣት ምቹ ኹኔታዎችን እናገኛለንና፡፡ ክረምቱ አልፎ መጸው ሲተካ ምድር ባገኘችው ዝናም አማካይነት የበቀሉ ዕፀዋት በአበባና በፍሬ ይደምቃሉ፡፡ ምእመናንም በተማርነው ቃለ እግዚአብሔር ለውጥ በማምጣት እንደ ዕፀዋት በመንፈሳዊ ሕይወታችን አፍርተን ክርስቲያናዊ ፍሬ ማስገኘት ይኖርብናል፡፡ በዚህ ፍሬያችን ዘለዓለማዊውን የእግዚአብሔር መንግሥት ለመውረስ እንችላለንና፡፡

አንድ ክፍለ ጊዜ (ወቅት) ሲያልፍ ሌላ ክፍለ ጊዜ ይተካል፡፡ ‹‹ሲሞት ሲተካ፣ ሲፈጭ ሲቦካ›› እንደሚባለው የሰው ልጅ ሕይወትም እንደዚሁ ነው፡፡ አንደኛው ሲሞት ሌላኛው ይወለዳል፤ አንደኛው ሲወለድ ሌላኛው ይሞታል፡፡ ወቅቶችም የጊዜ ዑደት መንገዶች እንደ መኾናቸው ለሰው ልጅ ምቾት እንጂ ለራሳቸው ጥቅም የተዘጋጁ ሕያዋን ፍጥረታት አይደሉም፡፡ በመኾኑም ራሳቸውን እየደጋገሙ ይመላለሳሉ፤ የሰው ልጅ ግን አምሳሉን ይተካል እንጂ ራሱ ዳግመኛ ተመልሶ አይመጣም፡፡ እንግዲህ ክርስቶስ ለፍርድ ሲመጣ እንዳናፍር ዳግም በማናገኛት በዚህች ምድራዊ ሕይወታችን የማያልፍ ክርስቲያናዊ ምግባር ሠርተን ማለፍ ይጠበቅብናል፡፡ ከሞት በኋላ ዘለዓለማዊ ፍርድ እንጂ ንስሐ የለምና፡፡

መንፈሳዊ ዓላማችን ይሳካልን ዘንድም እግዚአብሔርን በጸሎት እንጠይቀው፡፡ እንደዚህ እያልን፤ ‹‹ድኅረ ኀለፈ ክረምት ወገብአ ዝናም፤ ዘአርአይከ እግዚኦ ጽጌያተ ገዳም፤ አፈወ ሃይማኖት ነዓልድ ወፍሬ ምግባር ጥዑም፤ አትግሀነ ለስብሐቲከ ከመ ትጋሆሙ አዳም፤ ለጽብስት ንህብ ወነአስ ቃህም፡፡›› ትርጕሙም፡- ‹‹ክረምት ካለፈ፣ ዝናምም ወደ ቦታው ከተመለሰ በኋላ የዱር አበቦችን ያሳየህ አቤቱ እግዚአብሔር ሆይ! የሃይማኖት ሽቱን እናስገኝና የሚጣፍጥ የምግባር ፍሬን እናፈራ ዘንድ ተወዳጅ እንደ ኾነው የታታሪዋ ንብና የብልሃተኛዋ ገብረ ጕንዳን ትጋት እኛንም ለምስጋናህ አትጋን›› ማለት ነው (መጽሐፈ ስንክሳር፣ የመስከረም ፳፭ ቀን አርኬ)፡፡

በተጨማሪም በዚህ ወቅት (ከመስከረም ፲፮ – ፳፭ ቀን ድረስ ባለው ክፍለ ክረምት) ነገረ መስቀሉን የሚመለከት ትምህርት በቤተ ክርስቲያናችን በሰፊው ይነገራል፡፡ ማለትም ጌታችን አምላካችንና መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለሰው ልጅ ድኅነት ሲል በፈቃዱ በመስቀል ላይ ተሰቅሎ ስለ መሞቱ፣ በሞቱም ዓለምን ስለ ማዳኑ፣ ክርስቶስ ቅዱስ ሥጋውን ክቡር ደሙን ያፈሰሰሰበት ዕፀ መስቅሉ የተቀደሰ ስለ መኾኑ ከሌሎች ጊዜያት በላይ በስፋት የሚነገረውና ትምህርት የሚሰጠው በዚህ ወቅት ነው፡፡

ከዚሁ ዅሉ ጋርም በአይሁድ ቅናት በጎልጎታ ለ፫፻ ዓመታት ያህል ተቀብሮ የቆየው የጌታችን ዕፀ መስቀልን ለማውጣት በንግሥት ዕሌኒ አማካይነት ቍፋሮ መጀመሩ፣ መስቀሉ ከወጣ በኋላም በዐፄ ዳዊትና በልጃቸው በዐፄ ዘርዐ ያዕቆብ ጥረት ወደ ኢትዮጵያ መጥቶ በግሸን ደብረ ከርቤ መቀመጡ የሚዘከረው በእነዚህ ዐሥር የፀአተ ክረምት ዕለታት ውስጥ ነው፡፡ እኛ ምእመናን ይህንን የመስቀሉን ነገር በልቡናችን ይዘን በክርስትናችን ምክንያት የሚገጥመንን ልዩ ልዩ ዓይነት ፈተና በትዕግሥት ማሳለፍ ይጠበቅብናል፡፡

ማጠቃለያ

ትምህርታችንን ለማጠቃለል ያህል ዘመነ ክረምት ስለ ሥነ ፍጥረት ዘርዘር ባለ መልኩ የሚነገርበት፤ ፍጡርን ከፈጣሪ መናን (ምግብን) ከተመጋቢ ለይቶ የሚያሳይ እና የሚያሳውቅ ዘመን ነው፡፡ በዚህ ወቅት የውኃ ባሕርይ ይሠለጥናል፤ ውኃ አፈርን ያጥባል፤ እሳትን ያጠፋል፡፡ ኾኖም ግን ውኃ በብሩህነቱ ከእሳት፤ በቀዝቃዛነቱ ከነፋስ፤ በእርጥብነቱ ከመሬት ጋር ተስማምቶ ከሦስቱ ባሕርያት ጋር ይኖራል፡፡ ይህን ምሥጢር ከሕይወታችን ጋር አያይዘን ስንመለከተው ዘመነ ክረምት የክርስትና ምሳሌ ነው፡፡ በክረምት ወቅት ገበሬው ብርዱንና ዝናሙን ሳይሰቀቅ ለሥራ ይሰማራል፤ በበጋው የእጁን ፍሬ ያገኝ ዘንድ የክረምቱን መከራ ይታገሣል፡፡ ይህም ምእመናን በሰማያዊው ዓለም የምናገኘውን ተድላና ደስታ በማሰብ በምድር ቆይታችን ወቅት የሚደርስብንን ልዩ ልዩ መከራ በትዕግሥት ማሳለፍ እንደሚገባን ያስገነዝባል፡፡

ዘመነ ክረምት ዕፀዋቱ በስብሰው ከበቀሉ፣ ካበቡና ካፈሩ በኋላ የሚጠቅሙት በሪቅ፣ በጎተራ እንደሚሰበሰቡ፤ እንክርዳዶቹ ደግሞ በእሳት እንደሚቃጠሉ ዅሉ እኛም ተወልደን፣ አድገን፣ ዘራችንን ተክተን እንደምንኖር፤ ዕድሜያችን ሲያበቃም እንደምንሞት፤ ሞተንም እንደምንነሣና መልካም ሥራ ከሠራን ወደ እግዚአብሔር መንግሥት እንደምንገባ፤ በኀጢአት ከኖርን ደግሞ በገሃነመ እሳት እንደምንጣል የምንማርበት ወቅት ነው፡፡ በመኾኑም ሰይጣን በሚያዘንበው የኀጢአት ማዕበል እንዳንወሰድና በኋላም በጥልቁ የእሳት ባሕር እንዳንጣል ዅላችንም ቅዱሳት መጻሕፍትና ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን ያዘጋጁልንን የቃለ እግዚአብሔር ዘር በእርሻ ልቡናችን በመዝራት (በመጻፍ) እንደየዓቅማችን አብበን፣ ያማረ ፍሬ አፍርተን መንግሥቱን ለመውረስ መዘጋጀት ይኖርብናል፡፡ ይህንን እንድናደርግም የእግዚአብሔር ቸርነት፣ የእናታችን የቅድስት ድንግል ማርያም አማላጅነትና የቅዱሳኑ ዅሉ ተራዳኢነት አይለየን፡፡

ወስብሐት ለእግዚአብሔር፡፡