‹‹መገሠጽስ እግዚአብሔር ገሠጸኝ፤ ለሞት ግን አሳልፎ አልሰጠኝም›› (መዝ. ፻፲፯፥፲፰)

ሊቀ ጠበብት ዘውገ ዐሥራት

ታኅሣሥ ፱ ቀን ፳፻፲፫ ዓ.ም

ተግሣጽ የሚለው ቃል እንደየገባበት ዐውድ እና እንደየተነገረበት ዓላማ የተለያየ ፍቺ ቢኖረውም በመዝገበ ቃላት ደረጃ ቤተ ክርስቲያናችን ካፈራቻቸው ሊቃውንት አንዱ የሆኑት አለቃ ኪዳነ ወልድ ክፍሌ መጽሐፈ ሰዋስው ወግስ ወመዝገብ ቃላት ሐዲስ በተሰኘ መጽሐፋቸው (ገጽ ፫፻፳፯) ‹‹ተግሣጽ›› ማለት ትምህርት፣ ብርቱ ምክር፣ ምዕዳን፣ ኀይለ ቃል፤ እና ቁጣ ብለው ተርጉመውት ይገኛል፡፡

ተግሣጽን በሁለት ዐውድ ከፍለን ሥጋዊና መንፈሳዊ ተግሣጽ ልንለው እንችላለን፡፡ ሥጋዊ ተግሣጽ የምንለው ወላጅ ልጁን ቀጥቶ የሚያሳድግበት መንገድ በሥጋ እንደሚቀርጸው  ሲሆን መንፈሳዊ ተግሣጽ የምንለው ደግሞ አምላካችን እግዚአብሔር በመንፈሳዊነት እንድናድግ በመምህራን አድሮ በቃሉ የሚያስተምርበትና የሚመከርበት እንደሆነ መጽሐፍ ቅዱስ ያስረዳናል፡፡ ነቢዩ ኤርምያስ ‹‹ቃሌን ትሰሙ ዘንድ ተግሣጽን አትቀበሉምን? ይላል እግዚአብሔር›› በማለት ነግሮናል፡፡ ይህም ተግሣጽ ከሚያስደነግጥና ከሚያጠፋ ቁጣ ያነሰ፤ ከቀዝቃዛ ምክር ደግሞ የበረታ እንደሆነ እንረዳለን፡፡ (ኤር. ፴፭፥፲፫)

ለዚህም ምሳሌ ቅዱስ ገብርኤል የመጥምቀ መለኮት ቅዱስ ዮሐንስን አባት ዘካርያስን በሚያበሥርበት ጊዜ የገሠጸበትን መንፈሳዊ ተግሣጽን መጥቀስ ይቻላል፡፡ ካህኑ ዘካርያስ ወደ ቤተ መቅደስ ገብቶ ዕጣን በማሳረግ ላይ ሳለም የእግዚአብሔር መልአክ በዕጣኑ መሠዊያ ቀኝ ቆሞ ጸሎቱ እንደ ተሰማና ሚስቱ ቅድስት ኤልሳቤጥ እንደምትወልድ፤ ስሙንም ዮሐንስ እንደሚለው፤ በመወለዱም ብዙዎች እንደሚደሰቱ፤ ልጁም በእግዚአብሔር ፊት ታላቅ እንደሚሆን እንዲሁም ከእናቱ ማኅፀን ጀምሮ መንፈስ ቅዱስ እንደሚሞላበት ነገረው፡፡ (ሉቃ.፩፥፰-፲፯)

ካህኑ ዘካርያስም ‹‹እኔ ሽማግሌ ነኝ፤ ሚስቴም በዕድሜዋ አርጅታለችና ይህን በምን አውቃለሁ?›› አለው፡፡ መልአኩም ‹‹እኔ በእግዚአብሔር ፊት የምቆመው ገብርኤል ነኝ፤ እንድናገርህም ይህችን የምሥራች እንድሰብክልህ ተልኬ ነበር፡፡ እነሆም በጊዜው የሚፈጸመውን ቃሌን ስላላመንህ ይህ ነገር እስከሚኾን ቀን ድረስ ዲዳ ትሆናለህ፤ መናገርም አትችልም›› አለው፡፡ (ሉቃ.፩፥፲፰-፳፩)

በዚህ መሠረት እግዚአብሔር አምላክ ከጥንት ጀምሮ ዛሬም ድረስ በቅዱሳን ላይ አድሮ ሥርዓቱን ስናጎድል ለማንቃት ሕጉን ስንተላለፍ ለመመለስ ሲል ይገሥጸናል፡፡

በዚህም ስለ ዐሥርቱ ትእዛዛት አበው አባቶች ሕግና ሥርዓት በማለት ለሁለት እንደሚከፈል ይናገራሉ፤ እነርሱም ማድረግ ያለብንና የሌለብንን የሚገልጹ ናቸው፡፡ መፈጸም ያለብንን ነገር የሚያመለክቱ ሕጎች  ‹‹ከኔ በቀር ሌሎችን አማልክት አታምልክ፤ የእግዚአብሔር አምላክህን ስም በከንቱ አትጥራ፤ የሰንበትን ቀን አክብር፤ አባትና እናትህን አክብር እና ባልንጀራህን እንደራስህ ውደድ›› የሚሉት ናቸው፡፡ ማድረግ የሌለብንን የሚገልጹት ሥርዓቶች ደግሞ ‹‹አትግደል አታመንዝር፤ አትስረቅ፤ በሐሰት አትመስክር፤ የባልንጀራህን ቤት አትመኝ›› የሚሉት ናቸው፡፡ ትእዛዛትን ከመፈጸም የሰነፍን እንደሆነ የሚያነቃ ሕግጋቱን የተላለፍን ከሆነ እንድንመለስ የሚያደርጉ ተግሣጾች መሆናቸውን ያስረዳሉ፡፡

ነቢየ እግዚአብሔር ዳዊት የፈጣሪን ሕግ በተላለፈ ጊዜ ሊመልሰው፤ ሥርዓቱንም ባጎደለ ጊዜ ሊያነቃው የእግዚአብሔር ተግሣጽ ወደ እርሱ እንደመጣ፤ ይህም ተግሣጽ ሊያጠፋ ሳይሆን ሊያስተምረው እንደሆነ በተረዳ ጊዜ ‹‹መገሠጽስ እግዚአብሔር ገሠጸኝ፤ ለሞት ግን አሳልፎ አልሰጠኝም›› በማለት ተናግሯል፡፡ (መዝ. ፻፲፯፥፲፰)

ሰው በሕይወት ዘመኑ በአንድም ሆነ በሌላ ምክንያት ትእዛዛትን ሳይፈጽም ሕግጋትን ሊተላለፍ ይችላል፡፡ ነቢዩ ዳዊት በሕይወት ዘመኑ ሕጉን በመተላፉም ይሁን በማጉደሉ ሲገሠጽ የተመለሰ ሰው ነው፡፡

እግዚአብሔር አምላክም ለዳዊት ቸርነትን እንዳልነፈገው ሁሉ እኛን ደግሞ በልዩ ልዩ ተግሣጾች እየመከረን እና እያስተማረን እንዲሁም ምልክቶችን እያሳየን ነው፡፡ የእግዚብሔር  ተግሣጽ ሁሉ እኛ እንድመከርበት፣ እንድመለስበት ደግሞም ሰንፈን ከሆነ እንድንነቃበት እና እንድንጠቀምበት ነው፡፡ በተለየ መልኩ ግን ተግሣጽ የእግዚአብሔርን ቃል መስማት፣ ለእግዚአብሔር መታዘዝ፣ እግዚአብሔርን ማድመጥ እንደሆነ እንረዳለን፡፡ ይህም ደግሞ በእጅጉ የሚጠቅም እና የሚረባን እንደሆነ ልናውቅ ይገባል፡፡

ነቢዩ ዳዊት የአምላኩን ተግሣጽ ምክንያት ማወቅና መቀበል ብቻ ሳይሆን ‹‹ገሠጸኒ በጽድቅ ወተዛለፈኒ በምሕረት፤ በጽድቅ ገሥጸኝ በምሕረትህም ዘልፈኝ›› እያለ አምላኩን ይማጸን ነበር፡፡ ሆኖም ግን ተግሣጾችን አስተውሎ እና ተቀብሎ መመለስ አለመቻል ለበለጠ ቁጣ እና ማዓት ያጋልጣል፡፡

በዚህ ዘመን ከምንኖር ሰዎች የእግዚአብሔርን ሕግ ከጠበቅነው ይልቅ የተላለፍነው፤ ትእዛዛቱንም ከተገበርነው ይልቅ ከመፈጸም የሰነፍነው እንበዛለን፡፡ ለነቢዩ ዳዊት የተሰጠች ማስተማሪያ ተግሣጽ ዛሬም ለበጎ እንደተላከች ናት፤ የምናስተውለው ግን ስንቶቻችን ነን? ለምሳሌ ያህል ከአንድ ዓመት በፊት ጀምሮ በሀገራችን እና በቤተ ክርስቲያናችንም ላይ የተከሰቱ ልዩ ልዩ ችግሮች ምን ያህል አስጨናቂ እንደነበሩ የቅርብ ጊዜ ትዝታችን ነው፡፡ በተለይም በተከሰተው ወረርሺኝ የመጀመሪያ ሰሞን እጅጉን ተጨንቀን ነበር፤ ቤተ ክርስቲያን ተገኝቶ ቅዱስ ቃሉን መስማት፣ ማስቀደስ መቀደስ፣ ማቁረብ መቁረብ ብንሻም እንኳን ከቅጥረ ቤተ ክርስቲያን ደርሰን እፎይታ እንድናገኝ ዕድሉን ስላጣን እጅጉን ተከፍተን ነበር፡፡ ዕድሉን ስናገኝ ግን እግዚአብሔርን ያመሰገንን ጥቂቶች እንሆናለን፡፡ ይብሱን በዚህ ሰሞን ደግሞ ህንድ ሀገር ሌላ ያልታወቀ ወረርሽኝም እንደተነሣ በማኅበራዊ መገናኛዎች እየሰማን ነው፡፡ አንዱን ተግሣጽ አይተን ካላስተዋልን፤ በዚያ ካልተማርንና ካልተገሠጽን ለሌላ ችግር መጋለጣችን አይቀሬ እንደሆነ በዚህ እንረዳለን፡፡ የነበረውን ሁኔታ ተመልሰን ብናጤን ብዙ ተግሣጾች እንደነበር ማወቅ፣ ያንን አይተንና ተግሣጾችንም ተቀብለን ያለፈጸምናቸው ትእዛዛት ካሉ ለመፈጸም የነቃን፣ ደግሞም የተላለፍነው ሕግ ካለ ለመጠበቅ የተመለስን ግን አለን ብሎ ማሰብ ያዳግታል፡፡ ነቢየ ዳዊት ግን በቶሎ ተመልሷል፤ ገሥጾ ለሞት አሳልፎ ላልሠጠው እግዚአብሔር ምስጋናን ያቀርብ ዘንድም ‹‹መገሠጽስን እግዚአብሔር ገሠጸኝ፤ ለሞት ግን አሳልፎ አልሰጠኝም›› ብሎ ከመናገሩ በተጨማሪ የእውነት ደጆችን፤ የጽድቅ በሮችን እንዲከፍትለት ተማጽኗል፡፡ በተግሣጹ ተምረን ሥርዓቱን ብንፈጽም እና ሕጉን ብንጠብቅ በብዙ እንጠቀማለን፡፡ (መዝ. ፻፲፯፥፲፰)

ተግሣጽ ከጥፋት ያድነናል

በትንቢተ ኤርምያስ ላይ እንዲህ የሚል ቃል አለ፤ ‹‹ኢየሩሳሌም ሆይ፥ ነፍሴ ከአንቺ እንዳትለይ፥ አንቺንም ባድማና ወና እንዳላደርግሽ፥ ተግሣጽን ተቀበይ፡፡›› ኢየሩሳሌም በግፍ የተመላች ምድር በነበረችበት ወቅት መቅሠፍትም እንደሚላክባት ነገር ግን ባድማና ወና እንዳትሆን ተግሣጻትን እንድትቀበል ታዛለች፡፡ ይህ ቃል ሁላችንንም የሚመለከት ነው፤ ተግሣጽን ሰምተን ወደ እግዚአብሔር ተመልሰን ቢሆን ኖሮ ሌላ ለጥፋት ለሚዳርግ ክስተት አንጋፈጥም ነበር፡፡ ተግሣጻትን አይቶ የተመለሰ ሰው ከማንኛውም ጥፋት ይድናል፡፡ (ኤር.፮፥፰)

ተግሣጽን መስማትና መቀበል ጠቢባን እና ዐዋቂቆች ያደርገናል

‹‹ተግሣጽን የሚወድ ዕውቀትን ይወድዳል፤ ተግሣጽን የሚጠላ ግን ሰነፍ ነው›› እንደተባለው ኀጢአትን ትቶ ጽድቅን ለመከተል ዐዋቂ ጠበበኛ መሆን ያስፈልጋል፤ ከጥፋት ጎዳና ርቀንና በመልካሙ ጎዳና ለመጓዝ መንፈሳዊ ጥበብ እና ዕውቀት ማግኘት ይኖርብናል፡፡ (ምሳ. ፲፪፥፩)

ተግሣጽን የሚቀበል ሰው ጠቢብ እና ዐዋቂ ይሆናል፡፡ በመሆኑም ሁላችንም ተግሣጽን ሰምተን መቀበል አለብን፤ ጥበበኛ የተባለው ሰሎሞን በመጽሐፈ ምሳሌ እንዲህ ይላል፤ ‹‹ምክርን ስማ ተግሣጽን ተቀበል፤ በፍጻሜህ ጠቢብ ትሆን ዘንድ፡፡››  (ምሳ.፲፱፥፳)

ተግሣጽ በሕይወት መንገድ እንድንሄድ ይረዳናል

ተግሣጽን የሚቀበል ሰው በሕይወት መንገድም ይሄዳል፡፡ መንገድ ሲባል በእግረ ሥጋ የምንሄድበት ብቻ ነው ማለት ባይሆንም በዚህም ቢሆን ሕይወታችን የተጠበቀ እንዲሆን በጽድቁ ጎዳና መጓዝ አስፈላጊ ነው፡፡ ይህ የተጠቀሰው ቃል ግን ስለምድራዊ ሳይሆን ስለ ሰማያዊው፣ ስለሚያስፈልገውና ዘለዓለማዊ ስለሆነው ሕይወት ነው፡፡ ክርስትና ዘለዓለማዊ ሕይወት እንደመሆኑ በመንገዱ እስከ መጨረሻው ለመጓዝ እና በሕይወት ለመመላለስ ከሚያስፈልጉት ነገሮች አንዱ ተግሣጽን መቀበል መሆኑን ልናስተውል ይገባል፡፡

ምድራዊ መንገድ በእግረ ሥጋ የምንሄደው መንገድ በመሆኑ ትርፉ ድካም ነው፤ ነገር ግን እውነትም ሕይወትም የሆነውን ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በሰጠን በክርስትና ሕይወት ውስጥ ልንኖርና ልንጓዝ እንደሚገባ ማወቅ ይኖርብናል፡፡ ተግሣጽን የሚጠብቅ በሕይወት መንገድ ይሄዳልና፡፡ ‹‹ተግሣጽ የሕይወትን መንገድ ይጠብቃታል፤ በተግሣጽ የማይዘለፍ ግን ይስታል›› እንዲል፤ (ምሳ. ፲፥፲፯)

ትእዛዛቱን ቸል ከማለት ይልቅ የሚፈጽማት፤ ሕጉን ከመተላለፍ ይልቅ የሚጠብቃት ሰው እርሱ ተግሣጽን የተቀበለ ነው፡፡ ያ ሰው በሕይወት መንገድ ይሄዳል፤ ስለዚህ ነቢዩ ዳዊት የተገሠጸንበትን መልካም ተግሣጽ እያሰብን በእርሷ ተመልሰን ለሞት ተላልፈን ከመሰጠታችን በፊት ሕግጋቱን እየመጠበቅን ትእዛዛቱን እንፈጽም፡፡ በዚህም ውስጥ መንፈሳዊ ዕውቀትን ማግኘት እንችላለን፤ ተግሣጽን መጠበቃችን ደግሞም በሕይወት መንገድ እንድንሄድ ይረዳናል፡፡

ከስንፍናችን ስለመንቃትና ሕጉን ከመተላለፋችን ስለመመለስ የሚላከውን ተግሣጽ በአኮቴት በመቀበል ተምረንና ተመክረን በመንቃትና በመመለስ ከጥፋት እንድንድን፤ ጠቢባንና አዋቂዎች እንድንሆን እና በሕይወት መንገድ እንድንጓዝ የመድኃኒዓለም ቸርነትና የእናቱ ቅድስት ድንግል ማርያም አማላጅነት አይለየን፤ አሜን፡፡