ዕግትዋ ለጽዮን

በመዝሙርና ኪነ ጥበባት አገልግሎት ክፍል 

ኅዳር፤፳፻፲፬ ዓ.ም

እጅግ ያስጨንቃል የጠላት ሰበቃው ኵናቱ

እስራኤላዊነት ካሕዛብ መለየቱ

በሺህ ቢደበደብ አይታክት እውነቱ

እስራኤል ቢወረር ጽዮን አምባይቱ!

እርሱ እንዲሁ ላይተዋት ጽዮንን ወደዳት

በውስጧ ሲወለድ ዘለዓለም ሲሾማት

እግሩ ላረፈበት በከርስ ላደረበት

አምባነቷን አውቆ ሕዝብ ሰገደላት!

የኪዳናት መሐል ተራራ አምባ ላይ

አለቂም ታርቀዋል ምድርና ሰማይ

ይህች መሸሸጊያ ውስጧ ሰው ተገኝቷል

ብርሃን ለናፈቀው ዘለዓለም አብርቷል!

ጽዮን ሆይ ..

ከሀገርሽ ኮረብቶች ውበትሽ ማርኮኛል

ሰማይ ለወደደሽ ከእቅፍሽ ጠርቶኛል

ከክፉ ፍላጻ መከታን ሰጥቶኛል

ዶፉን ለመሻገር ጥላዬ ሆኖኛል!

ሕዝብማ አከበረሽ በልብ አይቶሻላ

ፍቅርሽን ሲቀምስ ከማርሽ ወለላ

“እምነ ጽዮን” ጧት ማታ ጸሎቱ

ተመስጦ ውበትሽ ’ርቆለት ስሜቱ

ያወቀብሽማ በፍቅርሽ ተነድፎ ዘመረ

ኃይልሽን ፊት ሰድዶ ጠላቱን ሰበረ!

እኔማ…

ያ የአባቴ ሀብቱን ጸጋውን ሸጫለሁ

ሞገሴን ቀብሬ በጥላ ቀን አለሁ

ምግባሬ ላይሰምረኝ ጥላሸት ሆኛለሁ

ጎትቶ ላይቀናኝ ገደል ገብቻለሁ!

ጽዮን ሆይ …

እነዚያ ያበዱ ተዳፍነው ክብርሽን የናቁ

ሀፍረት የሳላቸው ድንዙዝ ሲሳለቁ

ያ አሸዋ ቤቱ ላይጠገን በነፋስ ተመታ

ጎርፍ ሳይደርስበት በትንሽ ተረታ!

የተውሽ ጫማሽ ሥር ናፍቋቸው በእሪታ ቀወጡ

ሲገለጥም ክብርሽ ማረፊያውን አጡ

የዛሬ ስላቁ ከንቱ እንባ ’ምንጫቸው

በእሳት ሊጫወቱ ድግድጋት ሰጣቸው!

ጽዮን ሆይ…

ቅዱስ ዝማሬሽን ለውሻ ባካፍል ለባዕድ ብሰጠው

ጉሮሮዬ ደርቆ ምላሴን ያጣብቀው

ብረሳሽ ያንችን ውለታ እንደ ጧት ጥላዬ ብዘነጋ

ራሴነቴን ጥያለሁ ርጉም ልሁን ጉሮሮዬ ይላጋ!

የጽዮን ልጆች …

እንዚራን አቅርቡ መሰንቆን አውርዱ

የተመስጦን ቃና ዝማሬ ዳዊትን ልመዱ

በልጅ አባት ውዳሴ “ለምኝልን” በሏት

አክብሯታልና ውዳሴዋን ስጧት!

“ዕግትዋ ለጽዮን ወሕቀፍዋ

ወተናገሩ በውስተ ማኅፈዲሃ

ደዩ ልበክሙ ውስተ ኀይላ”

ያች ያማረ ወርቅን የተጫማች

እንደአጥቢያ ጨረቃ ብርሃን የተመላች

ለክረምቱ ስደት መጠለያ ሆነች

ጽዮንን ክበቧት ሰማይ ታደርሳለች!

ጽዮን ሆይ…

የውዳሴሽ ማማር አርጋኖን ክሂሎቱ

“ሰአሊ ለነ” ሲሉሽ ጥላሽ ሥር ሲከቱ

ኪዳንሽን አምነው ተራራን ሲወጡ

ወርቁን አግኝተውት ከጎርፍ አመለጡ!

በቃ!

እፉኝት ዘንግቶ ጌታዋ ካሰባት

ጭፍሮች ሲተብቱ አዶናይ ከሾማት

ያህች ብርሃናዊት ጨረቃ አማረባት

መዝጊያው ሳይዘጋ ጽዮንን ክበቧት!