ሰማዕቱ ቅዱስ መርቆሬዎስ

ኅዳር ፳፬ ቀን ፳፻፲፬ ዓ.ም

የቅዱስ መርቆሬዎስ ወላጆቹ አስሊጥ ከምትባል ሀገር ቢሆኑም እርሱ ግን ተወልዶ ያደገው በሮሜ ከተማ ነው፤ አያቱና አባቱ ሥራቸው አውሬ ማደን ስለነበር አንድ ቀን እንደልማዳቸው አውሬ ሲያድኑ ከገጸ ከለባት ወገን የሆኑ ሁለት ወንዶች አግኝተዋቸው የመርቆሬዎስን አያት በሉት፤ አባቱንም ሊበሉት ሲሉ የታዘዘ መልአክ ከለከላቸው፤ ዙሪያቸውንም በእሳት አጥሮ ከበባቸው፤ እነርሱም በተቸገሩ ጊዜ ለመርቆሬዎስ አባት ሰገዱለት፡፡

በዚያን ጊዜም እግዚአብሔር ፍጥረታቸውን ወደ ገራምነት ለወጠውና እንደበጎች የዋሆች ሆነው አብረውት ወደ መንደር ገቡ፤ ከዚህም በኋላ ቅዱስ መርቆሬዎስ ተወለደና ስሙ ፒሉፓዴር ተባለ፡፡ የውሻ መልክ ያላቸውም በእርሱ ዘንድ ብዙ ዘመናት ኖሩ፤ ከዚህም በኋላ ክርስቲያኖች ሆኑ፡፡

የቅዱስ መርቆሬዎስም ወላጆች አስቀድመው አረማውያን ነበሩና የክርስትና ጥምቀትን በጸጋ ተቀበሉ፤ አባቱንኖህ እናቱንም ታቦት ብለው ሰየሟቸው፤ ቀድሞ ፒሉፓዴር የነበረውም ስሙ ተለውጦ መርቆሬዎስ ተባለ፡፡ ‹መርቆሬዎስ› ማለትም የአብ ወዳጅ ማለት ነው፤ ዳግመኛም የኢየሱስ ክርስቶስ አገልጋይ ማለት ነው፡፡ የውሻ መልክ ያላቸው ግን መልአኩ በተገለጠላቸው ጊዜ እንደነገራቸው ለቅዱስ መርቆሬዎስ አባት የሚታዘዙና የሚያገለግሉ ሆኑ፡፡ (መጽሐፈ ስንክሳር ዘወርኃ ኅዳር፤ ገጽ ፫፻፵፭)

ንጉሡም የመርቆሬዎስን አባትና የውሻ መልክ ያላቸውን ዜናቸውን ሲሰማ ወታደሮቹን ልኮ በፊቱ አቆማቸው፤ እግዚአብሔርም የቀድሞ ፍጥረታቸውን መልሶላቸው አራዊት አደረጋቸውና ንጉሡን እጅግ አስፈሩት፡፡ ንጉሡም የቅዱስ መርቆሬዎስን አባት የአራዊት ተፈጥሮአቸውን ያርቅለት ዘንድ ለመነው፤ የቅዱስ መርቆሬዎስም አባት በለመነ ጊዜ ተፈጥሮአቸውን መልሶላቸው ገራሞች ሆኑ፡፡

ንጉሡም የመርቆሬዎስን አባት ገዥና የሠራዊቱ አለቃ አድርጎ ሾመው፤ የውሻ ፊት ያላቸውም አብረው ያገለግሉት ስለነበር ሁሉም ይፈራው ነበር፡፡ ንጉሡም የመርቆሬዎስን አባት ወደ ጦርነት ከላከው በኋላ ሳይመለስ ስለቀረ ሚስቱን ሊያገባት አሰበ፤ የመርቆሬዎስ አባትም የመርዶሳውያን አገሮች ሁሉ ገዢ በነበረው ንጉሥ ተይዞ ቢማረክም ገዥው ክርስቲያን መሆኑን አይቶ አከበረው፤ ቆይቶም በሀገሩ ላይ ሾመው፤ ሚስቱም ጠፍታ ከሀገሯ ወጥታ ሄዳ ስለነበር ከባሏ ተገናኝተው በዚያው መኖር ጀመሩ፡፡

መርቆሬዎስም አባቱና እናቱ ከሞቱ በኋላ ንጉሡ በአባቱ ፈንታ በመርዶሳውያን አገር ላይ ሾመው፤ መርቆሬዎስ መኰንንነት በተሾመም ጊዜ ገጸ ከለባቱ አብሮት ነበር፤ ለመዋጋትም በወጣ ጊዜ የቀድሞው የአራዊት የሆነ ተፈጥሮውን እግዚአብሔር ይመልስለት ስለነበር ማንም አይቋቋመውም ነበር፡፡ ለቅዱስ መርቆሬዎስ ታላቅ የድል አድራጊነት ኃይል ተሰጠውና ዜናው በሁሉም ሀገሮች ተሰማ፤ በሮሜ ሀገር ጣዖትን የሚያመልከው ዳኬዎስ የተባለውም ንጉሥ የበርበር ሰዎች ጋር ጦርነት ሊገጥም በወጣ ጊዜ እጅግ ሲበዙበት ፈራ፡፡

ቅዱስ መርቆሬዎስም በጦሩ መካከል የተሳለ ሰይፍ የያዘ የእግዚአብሔርን መልአክ ስላየ ንጉሡን ‹‹እግዚአብሔር ያጠፋቸዋልና አትፍራ›› አለው፤ መልአኩም ሰይፉን ለቅዱስ መርቆሬዎስ ሰጠውና ‹‹ጦርነቱን ድል ባደረግህ ጊዜ እግዚአብሔርን አስበው›› አለው፤ ጦርነቱን ድል አድርጎ ሲጨርስም መልአኩ ድጋሚ ተገልጦለት ‹‹ለምን የፈጣሪህን ስም መጥራት እረሳህ›› አለው፤ ከጦርነቱም በኋላ ንጉሥ ዳኬዎስ ለጣዖታቱ ዕጣን በማሳረግ በዓልን አደረገ፡፡

ቅዱስ መርቆሬዎስም በዚያ ስላልተገኘ ለጣዖታቱ ዕጣን በማሳረጉ እንዳልተባበረ ንጉሡ ሲያውቅ መልእክተኞችን ልኮ አስመጣው፤ ንጉሡም ‹‹ከእኔ ጋር ለምን አታጥንም›› ባለው ጊዜ ቅዱስ መርቆሬዎስ ትጥቁንና ልብሱን አውልቆ ከወረወረለት በኋላ ‹‹ክብር ይግባውና አምላኬ ኢየሱስ ክርስቶስን ፈጽሞ አልክደውም ለረከሱ ጣዖቶችህም አልሰግድም፤›› አለው፤ ንጉሡም ተናዶ ልዩ ልዩ በሆኑ ሥቃዮችም እጅግ አሠቃየው፡፡ ንጉሡም ስለ መርቆሬዎስ ብለው የሀገሩ ሰዎች እንዳይነሡበት ፈርቶ በብረት ችንካር ቸንክሮ የቀጵዶቅያና የእስያ ክፍል ወደሆነች ወደ ቂሳርያ ከደብዳቤ ጋር ላከው፡፡ በዚያም እጅግ ካሠቃዩት በኋላ ንጉሡ ዳኬዎስ እንዳዘዘ ኅዳር ፳፭ ቀን አንገቱን በሰይፍ ቆረጡትእና የሰማዕትነት ተጋድሎውን ፈጸመ፤ የሕይወትንም አክሊል ተቀዳጀ፤ በዓለሙ ሁሉ አብያተ ክርስቲያናት ታነጹለት፤

እግዚአብሔርም ድንቅ ድንቅ የሆኑ ተአምራትን በቅዱስ መርቆሬዎስ ስም አደረገ፡፡
ከብዙ ተአምራቱም አንዱ የቂሳርያውን ሊቀ ጳጳስ ባስልዮስን ረድቶ ከሃዲውን ዑልያኖስን የገደለበት ነው፤ ዑልያኖስ ነግሦ የክብር ባለቤት ጌታችንን ክዶ ጣዖታትን ማምለክና ክርስቲያኖችን ማሠቃየት ጀመረ፡፡ የቂሳርያው ሊቀ ጳጳስ ባስልዮስም አስተምሮ ሊመልሰው ወደ ንጉሡ ቢመጣ ክብር ይግባውና ዑልያኖስ ጌታችንን ሰድቦ ባስልዮስንም አሠረው፡፡
ባስልዮስም በእሥር ቤት ሳለ በቅዱስ መርቆሬዎስ ሥዕል ፊት ጸለየ፤ ሥዕሉም ወዲያው ተሠወረው፤ ያንጊዜም ወደ ከሃዲው ንጉሥ ዑልያኖስ ዘንድ ሄዶ በጦር ወግቶ ገደለውና ወዲያው ወደ ቦታው ተመለሰ፤ ከጦሩም አንገት ደም ይንጠፋጠፍ ነበር።

ቅዱስ ባስልዮስም ከሃዲውን ንጉሥ እንደገደለው ዐውቆ ‹‹የክርስቶስ ምስክር ጌታዬ ሆይ የእውነት ፀር የሆነ ዑልያኖስን ገደልከውን›› አለው፤ ሥዕሉም ያን ጊዜ አዎን እንደሚል ራሱን ዘንበል አደረገ። ቅዱስ ባስልዮስም ደስ ብሎት እግዚአብሔርን አመሰገነ፤ ሌላው ሰማዕት ቅዱስ መርቆሬዎስ በተአምሩ ከእስልምና እምነት መልሶ ክርስቲያን ያደረገው አንድ እስላም ሰው አለ፡፡ ይኸውም የቅዱስ መርቆሬዎስ ቤተ ክርስቲያኑ በተሠራችበት በምስር ሀገር የሚኖር ከመሳፍንት ወገን የሆነ ወጣት ነበረ፤ ከብዙ ሰዎችም ጋር ሆኖ ወደ መሐመድ መቃብር ለመሄድ እንዳሰበ ለአባቱ ሲነግረው ስንቅ ሰንቀው በሰላም ወደ መካ መዲና ሸኙት፤ መካ ደርሰውም ሥራቸውም ፈጽመው ወደ ቤታቸው እየተመለሱ ሰባት ቀን ተጓዙ፤ በሌሊትም ሲጓዙ ስለ ሥጋዊ ግዳጁ ያ እስላም ወጣት ከግመል ላይ ወርዶ ለመጸዳዳት ዘወር አለ፡፡ እነርሱም አብሯቸው የሚጓ መስላቸው ስለነበር ባልንጀሮቹም በበረሃው ውስጥ ትተውት ሄዱ፤ እርሱም ወዴት እንደሚሄድ ስላላወቀ አራዊትም እንዳይበሉት ፈርቶ እጅግ ደነገጠ፡፡በዚያም ጊዜ በምስር አገር በአባቱ ቤት አቅራቢያ ያለች የሰማዕቱ የቅዱስ መርቆሬዎስን ቤተ ክርስቲያን አስታውሶ በልቡ ቅዱስ መርቆሬዎስን እንዲያድነው በመለመን ተሳለ፤ ወዲያውም ቅዱስ መርቆሬዎስ በፈረሱ ተቀምጦ ወደ እርሱ መጣና ‹‹ከወዴት ነህ ከዚህ በረሃ ውስጥስ እንዴት ጠፋህ?›› አለው፤ ወጣቱ እስላምም የሆነውን ነገረው፡፡

ቅዱስ መርቆሬዎስም ‹‹ና በኋላዬ በፈረሱ ላይ ተፈናጠጥ›› አለውና በአየር ላይ እየበረረ በምስር ሀገር ወዳለች የቅዱስ መርቆሬዎስ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ እንደ ዐይን ጥቅሻ አደረሰውና እንደተዘጋች በውስጧ አስገባውና ከእርሱ ተሰወረ፡፡ይህም ወጣት በኋላ አምኖ ተጠምቆ ብዙ ሰማዕትነት ተቀብሏል፤ ገዳምም ገብቶ ብዙ ከተጋደለ በኋላ እንደገና ወደ ሀገሩ ተመልሶ ብዙዎችን ወደ ክርስትና መለሰ፡፡

የሰማዕቱ ቅዱስ መርቆሬዎስ አማላጅ ተራዳኢነት አይለየን፤ አሜን፡፡

ምንጭ፤ መጽሐፈ ስንክሳር ዘወርኃ ኅዳር