ክብረ መስቀል በኢትዮጵያ

መስከረም ፲፮ ቀን ፳፻፱ ዓ.ም 

በዝግጅት ክፍሉ

cross

‹መስቀል› ስንል ሦስት መሠረታዊ ቁም ነገሮችን መጥቀስ ይቻላል፤ የመጀመሪያው ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የሰውን ልጅ ከሞተ ነፍስ ለማዳን ሲል የተቀበለው መከራና የከፈለው መሥዋዕትነት መስቀል ይባላል፡፡ ሁለተኛው በክርስትና ውስጥ የሚያጋጥም ልዩ ልዩ ዓይነት መከራም መስቀል ነው፡፡ ጌታችን ‹‹እኔን መከተል የሚወድ ቢኖር ራሱን ይካድ፤ መስቀሉንም ተሸክሞ ይከተለኝ›› /ማቴ.፲፮፥፳፬/ በማለት መናገሩም በክርስትና ሕይወት ውስጥ የሚደርሰውን ይህንኑ መከራ መታገሥ ተገቢ መኾኑን ሲያመለክተን ነው፡፡ ሦስተኛው ደግሞ ጌታችን የተሰቀለበት ዕፀ መስቀል ሲኾን በሦስቱም ቁም ነገሮች ነገረ መስቀል (የመስቀሉ ነገር) ከክርስትና ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት አለው፡፡ ስለ ክርስትና ሕይወት ሲነሣ ነገረ መስቀልም አብሮ ይታወሳል፡፡ ስለ ክርስትና ሲነገር ክርስቶስ የተቀበለው መከራ፣ የተሰቃየበትና ነፍሱን በፈቃዱ አሳልፎ የሰጠበት ዕፀ መስቀል፣ በክርስትና ሕይወት ውስጥ የሚከሠት ፈተና አብረው የሚነሡ ጉዳዮች ናቸው፡፡

ስለ መስቀል ሲነገር ክርስቶስ ሰውን ለማዳን ሲል በሥጋው የተቀበለው ስቃይ፤ ሰማዕታት በሃይማኖታቸው ምክንያት የሚደርስባቸው ስደት፣ መከራና ሞት፤ ቅድስት ቤተ ክርስቲያን በየዘመኑ በአረማውያንም በውስጥ ጠላቶችም የሚያጋጥማት የዘረፋና የቃጠሎ፣ እንደዚሁም የሰላም እጦትና የመልካም አስተዳደር እጥረት፤ በተጨማሪም በክርስትና ሕይወት ውስጥ የሚከሠቱ የኑሮ ውጣ ውረዶች መስቀልና ክርስትና የማይነጣጠሉ የአንድ ሳንቲም ሁለት ገጽታዎች ለመኾናቸው ማስረጃዎች ናቸው፡፡ ከዚሁ ኹሉ ጋርም መስቀል ሲባል ክርስቶስ መከራ የተቀበለበት፣ ቅድስት ነፍሱን ከቅዱስ ሥጋው የለየበት፣ ድንቅ ተአምራትን ያደረገበት፣ ከኹሉም በላይ ለአዳምና ለልጆቹ ነጻነትን ያወጀበት ዕፀ መስቀልም አንዱ የክርስትናችን አካል ነው፡፡

ቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን በጉልላቷና በሌሎችም ንዋያተ ቅድሳቷ መስቀልን እንደ ምልክት ትጠቀመዋለች፡፡ መሠረቷ፣ የልጆቿ መድኀኒት ክርስቶስ በመስቀል ላይ የከፈለው ዋጋ ነውና ሰንደቅ ዓላማዋ መስቀል ነው፡፡ አባቶች ካህናት ጸሎት ሲያደርጉ ‹‹ከመስቀሉ ዓላማ፣ ከወንጌሉ ከተማ አያውጣን›› እያሉ የሚመርቁትም ስለዚህ ነው፡፡ በእጃቸው ይዘውት የሚንቀሳቀሱት፣ እኛንም የሚባርኩትም በመስቀል ነው፡፡

መስቀል የጠላት ሰይጣን ተንኮል የከሸፈበት፣ የክርስቶስ ቤዛነት የተረጋገጠበት የድኅነት ኃይል ነውና፡፡ በየገዳማቱና በየአብነት ት/ቤቱ፤ እንደዚሁም በክርስቲያኖች መኖሪያ ቤቶች ውስጥ በሚከናወኑ ተግባራት መስቀል ሰፊ ድርሻ አለው፡፡ በቅዳሴ ጊዜ፣ በጠበል ቦታ፣ በጸሎት ጊዜያት፣ ወዘተ ቡራኬ የሚፈጸመው በመስቀል በማማተብ ነው፡፡ የመስቀሉን ምልክት ባዩ ጊዜ አጋንንት ይንቀጠቀጣሉ፤ ካደሩበት ሰው ላይም በፍጥነት ይወጣሉ፡፡ ምእመናን በመስቀሉ ስንዳሰስ ከልዩ ልዩ ደዌ እንፈወሳለን፡፡

ወደ አገራችን ክርስቲያናዊ ባህል ስንመለስ በኢትዮጵያ የመድኀኒታችን የክርስቶስ መስቀል በብዙ ተግባራት ላይ በምልክትነት ጥቅም ላይ ሲውል ይታያል፡፡ ለምሳሌ በቡልኮ፣ ጋቢ፣ ነጠላ፣ ቀሚስ ወዘተ የመሳሰሉ የሸማ ልብሶች፤ እንደዚሁም በጆሮ፣ በአንገት፣ በእጅና ሌሎችም ጌጣጌጦች ላይ የመስቀል ምልክት አለ፡፡ ክርስቲያን ልጃገረዶች (በተለይ በሰሜኑ የአገራችን ክፍል) በግንባራቸው፣ በጉንጫቸው፣ በአንገታቸው፣ በደረታቸውና በእጃቸው ላይ በመስቀል ቅርፅ እየተነቀሱ ያጌጡበታል፡፡

ክርስቲያኖች ከዚህ ዓለም በሞት ስንለይም በመቃብር ሣጥናችን ወይም በሐውልቶቻችን ላይ የመስቀል ምልክት ይቀመጣል፡፡ በቤት ውስጥም ስንተኛና ከእንቅልፋችን ስንነቃ ፊታችንንና መላ ሰውነታችንን በትእምርተ መስቀል እናማትባለን፤ አባቶችና እናቶችም ውሃ ሲቀዱ፣ ሊጥ ሲያቦኩ፣ እንጀራ ሲጋግሩ፣ ምግብ ሲቈርሱ፣ ወዘተ በመስቀል አማትበው ነው፡፡ በአጠቃላይ መስቀል ብዙ ነገር ነው፤ መስቀል በክርስትና ሕይወት ውስጥ በሚደረጉ ተግባራት ኹሉ ያለው ድርሻ ጕልህ ነው፡፡ /ለተጨማሪ መረጃ ግሸን ደብረ ከርቤ የቃል ኪዳን አምባ፣ መስከረም ፲፱፻፺፮ ዓ.ም፤ ገጽ ፺፮-፻፪ ይመልከቱ/፡፡

ከዓለም ክርስቲያኖች በበለጠ ኢትዮጵያውያን ክርስቲያኖች ለጌታችን ለመድኀኒታችን ለኢየሱስ ክርስቶስ መስቀል የተለየ እምነትና አክብሮት አላቸው፡፡ ኢትዮጵያውያን ምእመናን ጌታችን ሰውን ለማዳን ሲል ብዙ ጸዋትወ መከራ የተቀበለበትንና ድኅነተ ሥጋ ድኅነተ ነፍስ ያገኘንበት መስቀልን ለአፍታም ያህል የማያስታዉሱበት ቅፅበት ባይኖራቸውም በዓመት ለአምስት ጊዜያት ያህል በቤተ ክርስቲያንና በዐደባባይ ያከብሩታል፡፡

በዚህም መሠረት በዐፄ ዳዊት ዘመነ መንግሥት ግማደ መስቀሉ ከእስክንድርያ ወደ ኢትዮጵያ የመጣበትን የመታሰቢያ በዓል በየዓመቱ መስከረም ፲ ቀን ቀደም ባለው ወቅት በነገሥታቱ፣ በመሳፍንቱና በመኳንንቱ ፊት በቤተ መንግሥት ያከብሩት ነበር፡፡ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ደግሞ ከካህናትና ከምእመናን ጋር በቤተ ክርስቲያን ዐውደ ምሕረት ያከብሩታል፡፡

እንደዚሁም በ፫ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ንግሥት ዕሌኒ በዕጣን ጢስ አመልካችነት መስቀሉን ከተቀበረበት ቦታ ለማውጣት ቍፋሮ ያስጀመረችበትን የመታሰቢያ በዓል በየዓመቱ መስከረም ፲፮ ቀን ደመራ ደምረው በመለኮስ በታላቅ መንፈሳዊ ሥርዓት በዐደባባይ ያከብሩታል፡፡ በማግሥቱ መስከረም ፲፯ ቀንም ንግሥት ዕሌኒ ቅዳሴ ቤቱን ያከበረችበትን የመታሰቢያ በዓል ታቦት አውጥተው ዑደት በማድረግ በቤተ ክርስቲያን ያከብሩታል፡፡

በማያያዝም መስከረም ፳፩ ቀን ግማደ መስቀሉ በሚገኝበት በግሸን ደብረ ከርቤ ማርያም በታላቅ በዓለ ንግሥ ያከብሩታል፡፡ በተመሳሳይ መልኩ መስቀሉ ከተቀበረበት ተራራ ተቈፍሮ የወጣበት መጋቢት ፲ ቀንም በቤተ ክርስቲያን በደማቅ ሥርዓት ይከበራል፡፡ /ምንጭ፡- የ፳፻፱ ዓ.ም የመስቀል ደመራ በዓልን በማስመልከት በጠቅላይ ቤተ ክህነት ጽ/ቤት የተዘጋጀ ልዩ ዕትም መጽሔት፣ ገጽ ፪/፡፡

በክርስቶስ ደም የተቀደሰው ይህ ክቡር መስቀል ለበርካታ ዓመታት በአይሁድ ምቀኝነት በጎልጎታ ተቀብሮ ከኖረ በኋላ በንግሥት ዕሌኒና በልጇ ቈስጠንጢኖስ ጥረት ከተቀበረበት ወጥቶ ከፀሐይ ብርሃን በላይ አብርቷል፤ ሙት በማስነሣት፣ ሕሙማንን በመፈወስ ብዙ ተአምራትን አሳይቷል፡፡ በመላው ዓለም በሚገኙ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ አብያተ ክርስቲያናት ደመራ ተደምሮ በዓሉ የሚከበረውም ንግሥት ዕሌኒ መስቀሉ የተቀበረበትን ቦታ ለማግኘት ከእግዚአብሔር መልአክ በተሰጣት አቅጣጫ መሠረት ያነደደችውን ዕጣንና የመስቀሉን መገኛ የጠቆማትን ጢስ ለማስታዎስ ነው፡፡

እግዚአብሔር የተመሰገነ ይኹን! በንጉሥ ዳዊትና በልጃቸው በዘርዐ ያዕቆብ አማካይነት ወደ አገራችን የመጣው የጌታችን መስቀል ቀኝ ክፍል በአገራችን ኢትዮጵያ በደቡብ ወሎ ሀገረ ስብከት በግሸን ደብረ ከርቤ ይገኛል፡፡ ከቅዱስ መስቀሉና ከገዳሙ በረከት ለመሳተፍ ብዙ ምእመናን በየዓመቱ ቦታው ድረስ በመሔድ በዓለ መስቀልን ያከብራሉ፡፡

በዓለ መስቀል በቤተ ክርስቲያን ብቻ ሳይኾን በየመንደሩና በየቤቱም ምእመናን ደመራ በመደመር፣ ጸበል ጸሪቅ በማዘጋጀት በድምቀት ያከብሩታል፡፡ በተለይ በደቡቡ የአገራችን ክፍል በዓለ መስቀል በደማቅ ሥርዓት ይከበራል፡፡ ይህም የቀደሙ አባቶቻችን ስለ በዓለ መስቀል ይሰጡት የነበረው ትምህርት ቁም ነገር ላይ መዋሉን የሚያስረዳ መንፈሳዊ ትውፊት ነው፡፡ የአከባበሩ ባህል ከቦታ ቦታ ይለያይ እንጂ በዓለ መስቀል በየዓመቱ በመስከረም አጋማሽ በመላው ኢትዮጵያ በልዩ ድምቀትና በመንፈሳዊ ሥርዓት ይከበራል፡፡

በአጠቃላይ በአገራችን ኢትዮጵያ መስቀልና ክርስትና እንዲህ ሳይነጣጠሉ ተሳስረው ይኖራሉ፡፡ እኛም አባቶቻችን እንዳስተማሩን ይህንን በክርስቶስ ደም የተቀደሰውን መስቀል በዘወትር ጸሎታችን ‹‹… መስቀል ኃይልነ መስቀል ጽንዕነ መስቀል ቤዛነ መስቀል መድኃኒተ ነፍስነ አይሁድ ክህዱ ንሕነሰ አመነ ወእለ አመነ በኃይለ መስቀሉ ድኅነ፤ … መስቀል ኀይላችን፣ ጽንዓችን፣ ቤዛችን፣ የነፍሳችን መዳኛ ነው፡፡ አይሁድ ይክዱታል፤ እኛ ግን እናምንበታለን፡፡ ያመነውም እኛ በመስቀሉ ኀይል እንድናለን፤ ድነናልም›› እያልን ለመስቀሉ ያለንን ክብር እንገልጻለን፤ በክርስቶስ መስቀል ኀይል መዳናችንንም ስንመሰክር እንኖራለን፡፡ ልዑል እግዚአብሔር በመስቀሉ ኃይል ኹላችንንም ከልዩ ልዩ ዓይነት መከራ ይጠብቀን፡፡

ወስብሐት ለእግዚአብሔር፡፡