በዚህች ዕለትም ቅዱስ ሚካኤል ያደረገው ተአምር ይህ ነው!

እስክንድርያ በምትባል ከተማ አክላወ ባጥራ የተባለች ንግሥት የንጉሥ በጥሊሞስ ልጅ ዙሐል በሚባል ኮከብ ስም ያሠራችው ታላቅ ምኵራብ ነበረና በየዓመቱ ሰኔ በባተ በዐሥራ ሁለት ቀን በዚያ ምኵራብ ሕዝቡ ተሰብስቦ ታላቅ በዓል ያደርጉ ነበር፡፡ በዚያም ምኵራብ ውስጥ ዙሐል የሚሉት ታላቅ የነሐስ ጣዖት ነበረና በዓሉ በሚከበርበት ዕለት ብዙ ፍሪዳዎችን ያርዱለት ነበር፡፡

አባ እለእስክንድሮስም እስከተሾመበት ዘመን ድረስ ለዚያ ጣዖት እንዲህ ሲያደርጉ ኖሩ፡፡ ይኸውም ሦስት መቶ ዓመተ ምሕረት ተፈጽሞ በአራተኛው ምዕት ውስጥ ነበር፡፡

አባ እለእስክንድሮስ በእስክንድርያ ከተማ ሊቀ ጵጵስና በተሾመ ጊዜ ጻድቅ ቆስጠንጢኖስም በነገሠ ጊዜ የክርስትና ሃይማኖት ስለ ተስፋፋች ያን ጣዖት ሊሠብረው ወድዶ ሳለ ጐስቋሎች ሰዎች ከለከሉት እንዲህም አሉት፤ እኛ በዚህ ቦታ ይህን በዓል ማክበርን ለምደናል፤ እነሆ ከአንተ በፊት ዐሥራ ስምንት ሊቃነ ጳጳሳት አልፈዋል፤ ይህን ልማዳችንንም አልለወጡብንም፡፡

አባ እለእስክንድሮስ ግን ገሠጻቸው፤ አስተማራቸውም፤ ስሕተታቸውንም በመግለጥ እንዲህ ብሎ፤ ‹‹አስተማራቸው ይህ ጣዖት የማይጎዳና የማይጠቅም ነው፤ እርሱንም የሚያመልክ ሰይጣናትን ያመልካቸዋል፤ ምክሬንስ ብትሰሙ ቀድሞ እንደ ነበረ አድርጌ ይህን በዓል እሠራላችኋለሁ፡፡ ይኸውም ጣዖቱን እንድንሰብረው፣ ምኵራቡንም እንድንባርከውና በከበረ መልአክ በመላእክት አለቃ በቅዱስ ሚካኤል ስም ቤተክርስቲያን አድርገን እንድንሰይመው ነው፤ እኛም ይህን ታላቅ በዓል እንሠራለን፡፡ የሚታረዱትም ላሞችና በጎች፤ ለድኆችና ለጦም አዳራዎች፤ ለችግረኞችም በከበረው መልአክ ስም ምግብ ይሁኑ፡፡ እርሱ በእግዚአብሔር ዘንድ ባለሟልነት ያለው ስለሆነ ስለእኛ ይማልዳልና፡፡›› ይህንንም ብሎ በዚህ በጎ ምክር አስወደዳቸው፤ እነርሱም ታዘዙለት፡፡

ከዚህም በኋላ ያንን ምኵራብ አድሰው በዚህ የከበረ መልአክ የመላእክት አለቃ ሚካኤል ስም ቤተክርስቲያን አደረጉት፤ በዚችም ዕለት አከበሩዋት፤ እርሷም የታወቀች ናት፡፡ እስላሞችም እስከ ነጉሡበት ዘመን ኑራ ከዚያ በኋላ አፈረሱዋት፡፡

ይህም ባሕል ተሠራ፤ እስከ ዛሬም ጸንቶ ይኖራል፡፡

ዳግመኛም በዚች ዕለት እግዚአብሔር የመላእክት አለቃ ቅዱስ ሚካኤልን በነገዱ ውስጥ በመላእክት ሁሉ ላይ በብዙ ክብር ሾመው፡፡

ይህም የከበረ መልአክ ክብር ይገባውና በጌታችን ፊት ስለ ሰው ልጆችና ስለ ፍጥረትም ሁሉ ይለምናል፤ ይማልዳልም፡፡

የዚህ የከበረ የመላእክት አለቃ ቅዱስ ሚካኤል ተአምራቱ ብዙዎች ናቸው፡፡ ከእነርሱም አንዱ ይህ ነው፡፡ እግዚአብሔርን የሚፈራ አንድ ሰው ነበረ፤ እርሱም የከበረ የሚካኤልን የበዓሉን መታሰቢያ በየወሩ በዐሥራ ሁለተኛው ቀን ይልቁንም በሰኔና በኅዳር ወር አብልጦ ያከብር ነበር፡፡

በጐረቤቱም ርኅራኄ የሌለው አንድ ባለጠጋ ሰው ነበረ፡፡ ይህን እግዚአብሔርን የሚፈራውን ሰው የከበረ መልአክ የቅዱስ ሚካኤልን በዓል በሚያደርግበት ጊዜ ይጠላውና ያቃልለው ነበር፤ ለድኆች ስለ መራራቱም ይዘባበትበት ነበረ፡፡

የሕይወቱ ዘመንም ተፈጽሞ የሚሞትበትና ከዚህ ከኃላፊው ዓለም ድካምም የሚያርፍበት ጊዜ ሲቀርብ የክቡር መልአክ ሚካኤልን የበዓሉን መታሰቢያ ታደርግ ዘንድ ምጽዋት ሰጭም ትሆን ዘንድ ሚስቱን አዘዛት፡፡

ከዚህም በኋላ አረፈና ገንዘው ቀበሩት፤ ሚስቱም ፀንሳ ነበረች፤ የመውለጃዋ ጊዜም ደርሶ ምጥ ያዛት፤ በታላቅ ጭንቀት ውስጥ ሳለችም እንዲህ ብላ ጸለየች፤ ‹‹የእግዚአብሔር መልአኩ ሆይ ራራልኝ በእርሱ ዘንድ ባለሟልነት አለህና በእግዚአብሔር ዘንድ ስለ እኔ ለምንልኝ፡፡›› 

ይህንንም በአለች ጊዜ በቤቷ ውስጥ ብርሃን በራ፤ ከችግርም ዳነች፤ መልኩ ውብ የሆነ ወንድ ልጅንም ወለደች፤ የእግዚአብሔርም መልእክተኛ ቅዱስ ሚካኤል ከሰማይ ወርዶ ሕፃኑን እንዲህ ብሎ ባረከው፤ ‹‹ርኅራኄ የሌለውን የዚህን ባለጸጋ ገንዘብና ሀብት ጥሪቱንም ሁሉ ይህ ሕፃን እንዲወርስ እግዚአብሔር አዝዟል፤›› ባለጸጋውም በቤቱ በዐልጋው ላይ ሳለ ጌታ ጆሮውን ከፍቶለት ይህን ነገር ከመልአኩ ሰማ፡፡

ይህንን በሰማ ጊዜ ታላቅ ኀዘን ደረሰበት፤ ሕፃኑንም የሚገድልበትን ምክንያት ይፈልግ ጀመረ፤ ነገር ግን ክብር ይግባውና ጌታ ይጠብቀው ነበር፡፡

ከዚህ በኋላ ያ ባለጸጋ ምክንያት አዘጋጅቶ ‹‹የሚያገለግለኝ ልጅ ይሆነኝ ዘንድ ልጅሽን ስጪኝ፤ እኔም እየመገብኩና እያለበስኩ አሳድገዋለሁ፤ ለአንቺም ሃያ ወቄት ወርቅ እሰጥሻለሁ›› አላት፡፡

ይህንንም ነገር ከባለጸጋው በሰማች ጊዜ ስለችግሯ እጅግ ደስ አላት፤ ልጅዋንም ሰጠችው፤ እርሱም ሃያውን ወቄት ወርቅ ሰጣት፤ ልጅዋንም ወሰደው፤ የምሻው ተፈጸመልኝ ብሎ ደስ አለው፡፡

ከዚህም በኋላ በልጁ ቁመት ልክ ሣጥን አሠርቶ ሕፃኑን በሣጥኑ ውስጥ አስገብቶ ዘጋበት፤ እስከ ባሕርም ተሸክመው ወስደው በባሕር ጣሉት፤ ክብር ይግባውና በጌታችን ፈቃድ ያ ሣጥን ሳይሠጥም ከዚያች አገር የሃያ ቀን መንገድ ያህል ርቃ ወደምትገኝ ወደ አንዲት አገር ወደብ እስከ ሚደርስ በባሕሩ ላይ ተንሳፈፈ፡፡

በባሕሩም አካባቢ በጎቹን አሰማርቶ የሚጠብቅ አንድ ሰው ነበርና ሣጥኑን በውኃ ላይ ተንሳፎ አየው፤ እርሱም ከባሕሩ አውጥቶ ወደ ቤቱ ወሰደው ይህን ሣጥን እንዴት እንደሚከፍተው ያስብ ጀመረ፤ ይህንም ሲያስብ ወደ ባሕሩ ይሄድ ዘንድ ጌታችን በልቡናው ኃሳብ አሳደረበት፤ ወዲያውኑም ተነሥቶ ወደ ባሕሩ ሔደና አንድ ዓሣ የሚያጠምድ ሰው አገኘ፡፡

ዓሣ አጥማጁንም ‹‹መረብህን በኔ ስም ጣል፤ ለሚያዘውም ዓሣ ዋጋውን እሰጥሃለሁ፤›› አለው አጥማጁም እንዳለው አደረገ፤ ያን ጊዜም ታላቅ ዓሣ ተያዘ፤ ዋጋውንም ይዞ ወደቤቱ ሔደ፤ ለራትም ይጠብሰው ዘንድ አረደው፤ በሆዱም ውስጥ መክፈቻ አገኘ፡፡ በልቡም ይህ ‹‹መክፍቻ ይህን ሣጥን ይከፍተው ይሆን?›› አለ፤ በሣጥኑ ቀዳዳም በአስገባው ጊዜ ፈጥኖ ተከፈተ፤ በውስጡም ይህን ታናሽ ብላቴና አገኘ፡፡ ልጅ የለውም ነበርና ታላቅ ደስታ ደስ አለው ጌታችንንም አመሰገነው፡፡ ሕፃኑንም በመልካም አስተዳደግ አሳደገው፤ ሕፃኑም አድጎ ጐልማሳ ሆነ፡፡

ከብዙ ዘመናትም በኋላ ያ ባለ ጸጋ ተነሥቶ ወደ ዚያ አገር ሔደ፤ በመሸም ጊዜ ወደ በግ ጠባቂው ደጅ ደረሰ፤ በግ ጠባቂውን ‹‹እስከ ነገ የምናድርበት ማደሪያ በአንተ ዘንድ እናገኛለን፤ ኪራዩንም እሰጥሃለሁ›› አለው፤ በግ አርቢውም እንዳልክ ይሁንና እደር አለው፤ ባለጸጋውም በዚያ አደረ፡፡

ራት በሚቀርብም ጊዜ ሕፃኑን ባሕራን ብሎ ጠራው፤ ባለጸጋውም ሰምቶ ‹‹ልጅህ ነውን?›› ብሎ ጠየቀው፤ በግ ጠባቂውም ‹‹አዎን፤ ታናሽ ሕፃን ሁኖ ሳለ ከባሕር አግኝቼዋለሁና እግዚአብሔር የሰጠኝ ልጄ ነው›› አለው፤ ባለጸጋውም ‹‹በምን ዘመን አገኘኸው?›› አለው፤ እርሱም ‹‹ከሃያ ዓመት በፊት›› ብሎ መለሰለት፡፡ ያን ጊዜም እርሱ ወደ ባሕር የጣለው መሆኑን አውቆ እጅግ አዘነ፡፡

በማግሥቱም ጎዳናውን ሊጓዝ በተነሣ ጊዜ ሰይጣናዊ ምክንያት አመካኝቶ በግ ጠባቂውን እንዲህ አለው፤ ‹‹ዕገሊት ወደምትባል አገር በቤቴ የረሳሁት ጉዳይ ስለአለ እንድልከው ልጅህን ትሰጠኝ ዘንድ እሻለሁ፤ እኔም የድካም ዋጋውን ሃያ ወቄት ወርቅ እሰጥሃለሁ፤›› አለው፡፡ የብላቴናውም አባት ስለገንዘቡ ደስ ብሎት ልጁ ባሕራንን ሰጠው፤ እንዲህም ብሎ አዘዘው፤ ‹‹ልጄ ባሕራን ይህ የከበረ ሰው ስለ ጉዳዩ ወደ ቤቱ ይልክህ ዘንድ ና ወደ ቤትህም በሰላም ትመለሳለህ፡፡››

ያን ጊዜም ባለጸጋው ወደ መጋቢው እንዲህ ብሎ ደብዳቤ ጻፈ፤ ‹‹ይህችን ደብዳቤ በምታነባት ጊዜ ደብዳቤዋን ይዞ የመጣውን ገድለህ በጉድጓድ ውስጥ ጣለው፤ ማንም አይወቅ፤››  በመካከላቸውም የሚተዋወቁበትን ምልክት ጽፎ አሸጋት፡፡ ለባሕራንም ሰጠው፤ ለመንገዱም የሚሆነውን ስንቅ ሰጠው፤ ባሕራንም ተነሥቶ ጉዞውን ጀመረ፤ ሲጓዝም ሰንብቶ የአንዲት ቀን ጉዞ ሲቀረው እነሆ የመላእክት አለቃ የከበረ መልአክ ሚካኤል በንጉሥ ጭፍራ አምሳል በነጭ ፈረስ ላይ ተቀምጦ ‹‹አንተ ጐልማሳ የያዝኸው ምንድነው?›› አለው፤ ባሕራንም ‹‹ወደ ዕገሌ አገር ወደ ቤቱ ለማድረስ ከአንድ ባለጸጋ የተጻፈች መልእክት ናት›› አለው፤ ‹‹ያቺን ደብዳቤ አሳየኝ›› አለው፤ እርሱም ስለ ፈራ ሰጠው፡፡

በዚያን ጊዜም የከበረው መልአክ ሚካኤል ያቺን የሞት መልእክት ደመሰሳት፤ በእርሷ ፈንታም በንፍሐት ለውጦ እንደህ ብሎ ጻፈ፤ ‹‹ይቺን ደብዳቤ ይዞ ለመጣ ባሕራን ለሚባል ይቺ ደብዳቤ ደርሳ በምትነበብበት ጊዜ ልጄ ዕገሊትን አጋቡት፤ በውስጥና በውጭ ያለ ንብረቴንና ጥሪቴን ወንዶችና ሴቶች ባሮቼን ጠቅላላ ንብረቴንም አውርሼዋለሁና፤ የፈለገውንም ሊያደርግ ሥልጣን ሰጥቼዋለሁና፤ እኔን አትጠብቁኝ፡፡ እኔ ብዙ እዘገያለሁ፤ የኔ ሹም እገሌ ሆይ! በእኔና በአንተ መካከል ይቺ ምልክት እነኋት፤›› ከዚህ በኋላ አሽጐ ለባሕራን ሰጠውና ‹‹ወደ ባለጸጋው ቤት ሒደህ ይቺን ደብዳቤ ለሹሙ ስጠው፤ በጎዳናም እኔ እንደ ተገናኘሁህ አትንገረው፤ እንዳይገድልህም ይህን የሞት ደብዳቤ ለውጨልሃለሁ›› አለው፡፡ ባሕራንም ‹‹እሺ ጌታዬ፤ ያዘዝኸኝን ሁሉ አደርጋለሁ›› አለ፡፡ (ስንክሳር ዘሰኔ ፲፪)

ባሕራንም ወደ ባለጸጋው ቤት በደረሰ ጊዜ ያቺን ደብዳቤ ለሹሙ ሰጠው፤ በአነበባት ጊዜ በመካከላቸው ያለውን ምልክት አገኘ፤ አስተውሎም እርግጠኛ እንደሆነ አወቀ፡፡

ከዚህም በኋላ በባሕራን ሠርግ አዘጋጅቶ እንደሚገባ በቤተ ክርስቲያን ሥርዓት በተክሊል የባለጸጋውን ልጅ አጋቡት፤ አርባ ቀን ያህልም ደስታና ሐሴት እያደረጉ ኖሩ፡፡

ከዚህ በኋላ ባለጸጋው ከሔደበት መመለሻው ጊዜ ሁኖ በደስታ የሆነውን የመሰንቆና የእንዚራ ድምፅ ሰምቶ ‹‹ይህ የምሰማው ምንድነው?›› ብሎ ጠየቀ፤ እነርሱም ‹‹ስሙ ባሕራን ለተባለ የአንተን ደብዳቤ ላመጣ ጐልማሳ ሰው ልጅህ ዕገሊትን አጋቡት፤ እነሆ ለአርባ ቀናት በሠርግ ላይ ነው፡፡ ገንዘብህንና ጥሪትህን ሁሉ ወንዶችና ሴቶች ባሮችህን አንተ እንዳዘዝክ ሰጥተውታል›› አሉት፡፡ ይህንንም በሰማ ጊዜ ደንግጦ ከፈረሱ ላይ ወደቀ፤ በድንገትም ሞተ፡፡

ባሕራንም በጎ ሥራዎችን የሚሠራ ሆነ፤ የተገለጸለትና ከመገደል ያዳነው የመላእክት አለቃ የከበረ መልአክ ሚካኤል እንደሆነ፤ ሊገድለው የሚሻውን የባለጸጋውን ጥሪቱን ሁሉ ያወረሰውም እርሱ እንደሆነ ተረዳ፤ የዚህንም የከበረ መልአክ የመላእክት አለቃ ሚካኤልን መታሰቢያ በየወሩ ያደርግ ጀመረ፡፡ ቤተክርስቲያንም ሠራለት፤ የቅዱስ ሚካኤልን ሥዕሉን አሥሎ በቤተክርስቲያኑ ውስጥ አደረገው፤ ከእርሱም ብዙዎች ድንቆች ተአምራቶች ተገለጡ፡፡ ባሕራንም ቅስና ተሹሞ እስከ ዕለተ ሞቱ በዚያች ቤተክርስቲያን ውስጥ የሚያገለግል ሁኖ ኖረ፤ በዚህ በከበረ የመልአክት አለቃ ሚካኤል አማላጅነት ከእናቱና ከአባቱ ከልጆቹም ጋራ የዘላለም ሕይወትን ወረሰ፡፡

ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በተነሣባትም ቀን ይህ ክቡር መልአክ ሚካኤል ከውስጠኛው መጋረጃ ውስጥ ገብቶ በክብር ባለቤት ፊት እንዲህ እያለ ይለምናል፤ ‹‹እውነት ስለሆነ ቃል ኪዳንህ በምድር መታሰቢያዬን የሚያደርጉትን ትምርልኝ ዘንድ ፈጣሪዬ ሆይ እኔ አገልጋይህና መልእክተኛህ ከቸርነትህ እለምናለሁ፤ አንተ መሐሪና ይቅር ባይ ነህና፡፡››

የክብር ባለቤት ጌታችንም እንዲህ ብሎ ይመልስለታል፤ ‹‹የመንፈሳውያን ሰማያውያን መላእክት አለቃቸው ሚካኤል ሆይ! መታሰቢያህን የሚያደርገውን ሁሉ መሸከም እንደምትችል ከሲኦል ሦስት ጊዜ በክንፎችኛ ተሸክመህ እንድታወጣ እነሆ እኔ አዝዤሃለሁ፡፡››

ይህንንም ቃል በሰማ ጊዜ እጅግ ደስ ብሎት የበዓሉን መታሰቢያ ከሚያደርጉት በክንፎቹ ተሸክሞ የእሳቱን ባሕር አሳለፋቸው፤ እነርሱንም ከብቻው ጌታ በቀር የሚቆጥራቸው የለም፡፡

ስለዚህም የዚህን ታላቅ የከበረ የመላእክት አለቃ ሚካኤልን የበዓሉን መታሰቢያ ለማድረግ መታገል ይገባናል፤ እርሱ ከሰይጣን ወጥመድ ያድነን ዘንድ፤ በዘመናችን ሁሉም ይጠብቀን ዘንድ፤ ኃጢአታችንንም ያስተሠርይ ዘንድ፤ መከራችንንም ያርቅ ዘንድ፤ የምድራችንንም ፍሬ ይባርክ ዘንድ፤ ፈቃዱንም ለመሥራት ይረዳን ዘንድ፤ ከእኛ ወገን የሞቱትን ዕረፍተ ነፍስ ይሰጥ ዘንድ፤ ወደ መንገድ የሔዱ አባቶቻችንና ወንድሞቻተንን ወደ ቤቶቻቸው በሰላም በጤና ይመልሳቸው ዘንድ፤ በመካከላችንም ፍቅር ያደርግልን ዘንድ፤ እስከ መጨረሻዪቱም ሕቅታ ድረስ በቀናች ሃይማኖት ያጸናን ዘንድ፤ በእግዚአብሔር ፊት ስለ እኛ ይለምናልና፡፡

የክርስቶስ ወገኖች የሆኑ መኳንንቶቻችንንም ጠብቆ በወንበሮቻቸው ላይ ያጸናቸው ዘንድ የሳቱትንም ወደ ቀናች ሃይማኖቱ ይመልሳቸው ዘንድ፡፡

ዳግመኛም በዚህች ቀን በየወሩ ሦስት በዓላቶችን ማለትም የጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የልደቱ መታሰቢያ በየወሩ በሃያ ዘጠኝ፤ የእመቤታችን የቅድስት ድንግል ማርያም በዓል መታሰቢያ በየወሩ፤ በሀያ አንድ የከበረ የመላእክት አለቃ የሆነ የቅዱስ ሚካኤል በዓል መታሰቢያም በየወሩ በዐሥራ ሁለት እያከበረ የሚኖር እግዚአብሔርን የሚፈራ አስተራኒቆስ የተባለ ሰው ነበር፡፡

የሚሞትበትም ጊዜው ሲቀርብ እርሱ ሲሠራው የነበረውን ምጽዋት ይልቁንም እሊህን ሦስቱን በዓላት እንዳታስታጉል ሚስቱን ቅድስት አፎምያን አዘዛት፡፡

እርሷም የከበረ የመልአኩ የሚካኤልን ሥዕል ያሥልላት ዘንድ ባሏን ለመነችው፤ እርሱም አሠርቶ ሰጣትና በቤቷ ውስጥ በክብር አኖረችው፡፡

ባሏም ከአረፈ በኋላ ባሏ ያዘዛትን መሥራት ጀመረች፤ ሰይጣን ግን ቀናባት፤ በመበለት ሴት መነኵሲት ተመስሎ ከእርሷ ጋር ተነጋገረ፤ እንዲህም አላት፤ ‹‹እኔ አዝንልሻለሁም፤ ገንዘብሽ ሳያልቅ፤ የልጅነትሽም ወራት ሳያልፍ አግብተሽ ልጅ ትወልጂ ዘንድ እመክርሻለሁ፤ ባልሽም መንግሥተ ሰማያትን ወርሷል፤ ምጽዋትም አይሻም፡፡››

አፎምያም እንዲህ ብላ መለሰችለት ‹‹እኔ ከሌላ ሰው ጋራ ላልገናኝ በእግዚአብሔር ፊት ቃል ኪዳን አድርጌያለሁ፤ ርግቦችና መንጢጦች እንኳ ሌላ ባል አያውቁም፤ በእግዚአብሔር አርአያ ከተፈጠሩ ሰዎች ይህ ሊሆን እንዴት ይገባል፡፡››

ምክሩንም ባልሰማች ጊዜ አርአያውን ለውጦ በላይዋ ጮኸባት፤ እንዲህም አላት፤ ‹‹እኔ በሌላ ጊዜ እመጣለሁ፤›› እርሷም የከበረ የመልአኩ የሚካኤልን ሥዕል ይዛ አሳደደችው፡፡

ከዚህም በኋላ ሰኔ ዐሥራ ሁለት የከበረ የመልአኩ የሚካኤል በዓል በሚከብርበት ዕለት እርሷም የበዓሉን ዝግጅት ስታዘጋጅ ሳለች ብርሃናዊ መልአክ መስሎ መጣ፤ ‹‹አፎምያ ሆይ ሰላም ላንቺ ይሁን፤ እኔ የመላእክት አለቃ ሚካኤል ነኝ፤ ጌታ ወደ አንቺ ልኮኛልና እርሱም ይህን መመጽወትሽን ትተሽ ለአንድ ምእመን ሚስት ትሆኚ ዘንድ ጌታ አዞሻል፤›› ባል የሌላት ሴት መልሕቅ የሌለውን መርከብ እንደምትመስል ዕወቂ፤ እንደ አበርሃምና ያዕቆብ እንደዳዊትም እንደእነርሱ ያሉ ብዙ ሴቶችን እንዳገባ እግዚአብሔርንም ደስ እንዳሰኙት ከብሉይ ኪዳን መጻሕፍት ጥቅሶችን ያመጣላት ጀመረ፡፡

ቅድስት አፎምያም መልሳ ‹‹አንተ የእግዚአብሔር መልአክ ከሆንክ የመስቀል ምልክት ከአንተ ጋር ወዴት አለ? የንጉሥ ጭፍራ የሆነ ሁሉ የንጉሡን ማሕተም ሳይዝ ወደ ሌላ ቦታ አይሔድምና›› አለችው፡፡

ሰይጣኑም ይህንን በሰማ ጊዜ መልኩ ተለወጠና አነቃት፤ እርሷም ወደከበረው መልአክ ወደ ሚካኤል ጮኸች፤ ወዲያውኑም ደርሶ አዳናት፡፡ ያንንም ሰይጣን ይዞ ይቀጣው ጀመረ፤ ሰይጣኑም ጮኸ ‹‹ማረኝ፤ ያለ ጊዜዬ አታጥፋኝ፤ እግዚአብሔር እስከ ዓለም ፍጻሜ ታግሦናልና›› እያለ ለመነው፤ ከዚያም ተወውና አበረረው፡፡

የከበረ መልአክ ሚካኤልም እንዲህ አላት ‹‹ብፅዕት አፎምያ ሆይ! ሄደሽ የቤትሽን ሥራ አዘጋጂ፤ አንቺ ዛሬ ከዚህ ዓለም በሞት ትለዪአለሸና እነሆ እግዚአብሔርም ዐይን ያላየውን፣ ጆሮም ያልሰማውን፣ በሰው ልብም ያልታሰበውን አዘጋጅቶልሻል፡፡›› ይህንንም ብሎ ሰላምታ ሰጣት ወደ ሰማያትም ዐረገ፡፡

የበዓሉንም ዝግጅት እንደሚገባ ከፈጸመች በኋለ ወደ ኤጲስቆጶሱና ወደ ካህናቱ ሁሉ ላከች፤ ወደርሷም በመጡ ጊዜ ለድኆችና ለጦም አዳሪዎች ይሰጧቸው ዘንድ ገንዘቧን ሁሉ አስረከበቻቸው፡፡

ከዚህም በኋላ ተነሥታ ጸለየች፤ የከበረ የመልአኩ የቅዱስ ሚካኤልንም ሥዕል አንስታ ታቅፋ ሳመችው፤ ያን ጊዜም በሰላም አረፈች፡፡

ምንጭ፡ስንክሳር ዘሰኔ ፲፪