ኒቆዲሞስ

መምህር አብርሃም በዕውቀቱ
መጋቢት ፴ ቀን ፳፻፲፬ ዓ.ም

በግሪክ ቋንቋ ኒቆዲሞስ የሚለው ቃል ትርጓሜ ድል ማድረግን ወይም አሸናፊነትን የሚያመለክት ነው፡፡ በዘመነ ሥጋዌ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ወንጌልን በሚሰብክበት ጊዜ አንድ ፈሪሳዊ ከአይሁድ አለቆችና መምህራን ወገን የሆነ ኒቆዲሞስ የተባለ ሰው እንደነበረና የጌታችንን ቃል በሌሊት ወደ እርሱ በመሄድ እንደተማረ በወንጌለ ዮሐንስ ተጠቅሷል። (ዮሐ.፩፥፪)

በአይሁድ አለቆች ፊትም ‹‹ሕጋችን አስቀድሞ ሳይሰማ የሠራውንም ሳያውቅ በሰው ይፈርዳልን?›› በማለት ስለ መድኃኔዓለም ክርስቶስ የተናገረ እርሱ ነው። እነርሱ ግን በክርስቶስ ወልደ እግዚአብሔር መሆን ያመኑበት ኦሪትን የማያውቁ ስሑታን እንደሆኑ ያስቡ ስለ ነበር ‹‹አንተም ደግሞ ከገሊላ ነህን? ከገሊላ ነቢይ እንደማይነሣ መርምርና እይ›› አሉት እንጂ አልተቀበሉትም። (ዮሐ.፯፥፵፰-፶፪)

ኒቆዲሞስ የአርማትያስ ሰው ከሚሆን ከዮሴፍ ጋር በመሆን የጌታችንን ቅዱስ ሥጋ በንጹሕ በፍታ ገንዞ በአዲስ መቃብር ቀብሯል። ወንጌላዊው ቅዱስ ዮሐንስ ‹‹ቀድሞ በሌሊት ወደ ጌታችን ኢየሱስ ሄዶ የነበረው ኒቆዲሞስም መጣ፤ ቀብተውም የሚቀበርበትን መቶ ወቄት የከርቤና የሬት ቅልቅል ሽቶ አመጣ›› እንዲል፤ (ዮሐ ፲፱፥፴፱) በዚህም ኒቆዲሞስ ከምክረ አይሁድ ያልተቀላቀለ መሆኑ ይታወቃል።

ኒቆዲሞስ ከቀኑ ክፍለ ጊዜ ይልቅ የሌሊቱን ጊዜ ለትምህርት ለምን መረጠ?
፩. ኒቆዲሞስ መምህር ስለነበር ‹‹ስማር ሰዎች ቢያዩኝ ውዳሴ ከንቱ መምህር መባል ይቀርብኛል›› ብሎ ነው፡፡ እኛስ ዛሬ የዘለዓለም ሕይወት የሚሰጠንን ቅዱስ ቃል በትሕትና መማር ሲገባን ለምድራዊ ክብር ብለን በቀን ጊዜያችን መማር ያልቻልን ስንቶቻችን ነን? ስለዚህ ቀን ጊዜያችንን በአግባቡ ልንጠቀምበት ይገባል። ‹‹ማንም ሊሠራ የማይችልባት ሌሊት ትመጣለችና፡፡›› (ዮሐ ፱፥፬)

፪. ኒቆዲሞስ የአይሁድ መምህር ስለነበር እንዳያዩት ፈርቶ ሌሊት እየመጣ ይማር ነበር፤ እኛስ ዛሬ ልባችን የተረዳውን እውነት በግልጥ እንዳንፈጽም በፍራቻና በይሉኝታ የምንሠውር ስንቶቻችን ነን? ፍጹም ፍቅር ፍርሃት የለውም፤ ፍርሃት ቅጣት አለውና፡፡ (፩ኛዮሐ.፬፥፲፰) ፍርሃትን አስወግደን ለእውነት ልንቆም ይገባል።

፫. ኒቆዲሞስ በሙሉ ልቡ በማስተዋል ለመማር ስለፈለገ ከቀኑ ክፍለ ጊዜ ይልቅ የማታውን መረጠ፤ ዛሬስ ስንቶቻችን ነን ቅዱስ ቃሉን በማስተዋል ከልብ ሆነን የምንማር? የሰማነው ቅዱስ ቃል በሕይወታችን ፍሬ እንዲያፈራ ቅዱስ ቃሉን ከልብ ሆነን በማስተዋል ልንሰማ ይገባናል፡፡ ቃሉን ሰምቶ የሚያስተውል ልብ መልካም መሬት ተብሏል፡፡ ‹‹በመልካም መሬት የተዘራውም ይህ ቃሉን ሰምቶ የሚያስተውል ነው፡፡›› (ማቴ.፲፫፡፥፳፫)
አንዳንዶቻችን ጸሎት እያደረግን እንኳን አንደበታችን የእግዚአብሔርን ቃል ይረሳል፡፡ ልቦናችን ወደ ሌላ ቦታ ይጓዛል፤ በማኅበር ጸሎትም አብረን እየጸልይን በመካከል በተመሳሳይ ሁኔታ ሐሳቦቻችን ወደ ሌላ ነገር የሚሳቡበት አጋጣሚ ይኖራል፡፡

፬. ሌሊት ጨለማ ነው፤ ብርሃን የለም፤ ይህም የኃጢአት ምሳሌ ነው፤ ኒቆዲሞስ በሌሊት መምጣቱ ኃጢአተኛ እንደሆነና ንስሓ ፈልጎ ወደ ጌታችን እንደመጣ ያስረዳናል፡፡ ዛሬስ ስንቶቻችን ነን ቅዱስ ቃሉን ስንሰማ በተአምኖ ኃጢአት በንስሓ ውስጥ ሆነን የምንሰማ? ያለንስሓ የምንሰማው ቃል በሕይወታችን ፍሬ የማፍራት ዕድሉ ጠባብ ነው፡፡ ምክንያቱም በንስሓ ከልባችን ያልጸዱት ክፉ ምኞቶች እንደ እሾህ ሆነው ያንቁታልና፡፡ ‹‹ሌላውም በእሾህ መካከል ወደቀ፤ እሾህም ወጣና አነቀው›› ተብሎ የተጻፈው ለዚህ ነው። (ማቴ.፲፫፥፰)

፭. ሌሊት የቆየው ኪዳን ወይም የብሉይ ኪዳን ምሳሌ ነው፤ ኒቆዲሞስም ‹‹እኔ ምሁረ ኦሪት እንጂ ምሁረ ወንጌል አይደለሁም፡፡ ወንጌልን ካንተ እማር ዘንድ ያስፈልገኛል›› ሲል በሌሊት ለመማር ወደ ጌታችን ይመጣ ነበር፡፡ የብሉያትን ከሐዲሳት መጻሕፍት ጋር ተዋሕደው ሲተረጎሙ ሰሙና ወርቁ ተጣምሮ የሕይወት ትምህርት ያስገኛል፡፡ አንዳንዶች ዛሬ ‹‹ብሉያት ጭራሽ አያስፈልጉም›› ሲሉ ይደመጣሉ፡፡ ነገር ግን እንደ ኒቆዲሞስ ሁለቱን ኪዳናት አዋሕዶ መጓዝ ትክክለኛው መንገድ ነው፡፡ ጌታ ሲያስተምር ‹‹እውነት እላችኋለሁ! ሰማይና ምድረ እስኪያልፍ ድረስ ከሕግ አንዲት የውጣ ወይም አንዲት ነጥብ አታልፍም›› በማለት አበክሮ የተናገረው ለዚህም ነው፡፡ (ማቴ.፭፥፲፰)

ኒቆዲሞስ ምንም እንኳን የቀኑ ክፍለ ጊዜ ባይመቸውም በሌሊቱ ሰዓት ለመማር ችሏል፡፡ እኛም ከእርሱ ተምረን ከልብ ካለቀሱ እንባ አይጠፋምና ምንም ሥራ ቢበዛብን ለቅዱስ ቃሉ ጊዜ አይጠፋም፡፡ ቅዱስ ወንጌል ወደ ዘለዓለማዊ ሕይወት የሚያሻግር የእግዚአብሔር ቃል በመሆኑ ዘወትር ልንማር ያስፈልጋል፡፡

በተለይም በአዘቦት ቀንም ሆነ በሰንበታት ወደ ቤተ ክርስቲያን በማዘውተር በሰርክ፣ በወርኃዊ እና በዓመታዊ በዓላት ላይ በሚደረጉ የዐውደ ምሕረት ጉባኤዎች ላያ በመሳተፍ ቅዱስ ቃሉን መማር ይገባል፡፡ የድኅነት መንገድን ዐውቀንና ተረድተን በጽድቅ ጎዳና ካልተጓዝን መዳን አይቻለንም፡፡ ለኃጢአትም ተጋልጠን ፈጣሪያችንን እናስከፋዋለን፡፡ የእግዚአብሔርንም መንግሥት ከመውረስ ይልቅ ለዘለዓለማዊ ቅጣት እንዳረጋለን፡፡

እግዚአብሔር አምላችን ቅዱስ ቃሉን እንድንረዳ አስተዋይ ልቡና ይስጠን፤ አሜን!

ወስብሐት ለእግዚአብሔር!