ቃል

ዲያቆን ዐቢይ ሙሉቀን

ቃል የፊደላት ስብስብ ሆኖ ልናስተላልፈው የፈለግነውን ሐሳብ የሚሸከም የሐሳብ ወካይ መግለጫ ነው፡፡ ቃል የማይታይ፣ የማይዳሰስ፣ በጆሮ ብቻ የሚደመጥ ሲሆን ቋንቋ ትዕምርታዊ በመሆኑ እና ቃል ደግሞ የቋንቋ አንድ መዋቅር በመሆኑ በፊደላት አማካኝነት ይታያል፡፡ ይህ ጸሐፊ ብዕር ቀርጾ፣ ብራና ዳምጦ፣ ቀለም በጥብጦ በልቡናው ያለውን ሐሳብ ሲጽፈው ረቂቁ ይገዝፋል፤ የሚታይ፣ የሚዳሰስም ይሆናል፡፡ ስለዚህ ነው ቃል የፊደላት ስብስብ ሆኖ በልቡናችን ላለና ልናስተላልፈው ለፈለግነው ሐሳብ ወካይ መግለጫ ነው የተባለው፡፡

ቃል ከምልክትነት ወይም ከቋንቋ መዋቅር ብቻ ሳይሆን ከትርጉም ሰጭ መዋቅርነት አንጻር የነገር ሁሉ መጀመሪያ ነው፡፡ ፕሮፌሰር ባየ ይማም በመጀመሪያም ቃል ነበረ የሚለውን በዮሐንስ ወንጌል ዮሐ.፩፥፩ መሠረት አድርገው የቋንቋ ፍች ወይም ትርጉማዊነት መነሻ እንደሆነ ያስረዳሉ፡፡ ትርጉማዊ መዋቅር ከመመሥረት አንጻር ቃልን የሚቀድመው መዋቅር የለም፡፡ ፊደል ብንል ብቻውን ትርጉም ሊሰጠን አይችልም፡፡ ምዕላድ ብንልም ትርጉም አዘል እንላለን እንጂ ሙሉ ትርጉም ሊሰጠን አይችልም፡፡ ሙሉ ትርጉም ሊሰጠን የሚችል መዋቅር ቃል ስለሆነ የትርጉማዊ መዋቅር መነሻ እንለዋለን፡፡

የቃልን ምንነት ፕሮፌሰር ባየ ይማም የአማርኛ ሰዋስው በሚባል መጽሐፋቸው ከቃል የሚያንሰውን የቋንቋ ቅንጣት (ምዕላድን) ከአስረዱ በኋላ ቃልንም እንዲህ ይገልጹታል፡፡

-ትርጉም አዘል አሐድ ነው፡፡

-ራሱን ችሎ መቆም የሚችል ነው፡፡

-በውስጡ ብዙ ጥገኛ ምዕላዶችን ሊይዝ ይችላል፡፡

-ከቃላት ክፍሎች ውስጥ ባንዱ ሊመደብ ይችላል፡፡ ባየ (፳፻፱፥፸፭)

ከላይ የተገለጸው የቃል ብያኔ እንደ ማንኛውም ቋንቋ ነው፡፡ ግእዝም የራሱ የሆነ መለያ ባሕርይ ቢኖረውም እንደማንኛውም ቋንቋ የጋራ የሆኑትን የቋንቋ ባሕርይን፣ ብያኔንና መዋቅርን ይጋራልና የቃል ብያኔ በግእዝ ቋንቋም ከላይ የተገለጸውን እንጠቀማለን፡፡ በራሱ ሥርዓትና አገባብ ለመግለጽ አንድ ምንባብ እንጥቀስና በምሳሌ እናስረዳ፡፡

አቡነ ዘበሰማያት ይትቀደስ ስምከ ትምጻእ መንግሥትከ ወይኩን ፈቃድከ በከመ በሰማይ ከማሁ በምድር ሲሳየነ ዘለለእለትነ ሀበነ ዮም ኅድግ ለነ አበሳነ ወጌጋየነ ከመ ንሕነኒ ንሕድግ ለዘአበሰ ለነ ኢታብአነ እግዚኦ ውስተ መንሱት አላ አድኅነነ ወባልሀነ እምኵሉ እኵይ እስመ ዚአከ ይእቲ መንግሥት ኃይል ወስብሐት ለዓለመ ዓለም፡፡

ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በመዋዕለ ስብከቱ ዕለት ዕለት እንድናመሰግነው ባዘዘንና ዘወትር በምንጸልየው ጸሎት (አቡነ ዘበሰማያት) በርካታ ቃላትን እናገኛለን፡፡ ሐሳብ በቃል ይገለጻል ብለናልና ሐሳባችንን ለመግለጽ ቃላትን ተጠቅመናል፡፡ ቃላቱ በሥርዓት ተዋቅረው ሙሉ መልዕክት እንድናስተላልፍ አድርገውናል፡፡ ቃላቱን በተወሰነ መልኩ ዘርዘር አድርገን እንመልከት፡፡

አቡነ፣ ሰማያት፣ ይትቀደስ፣ ስምከ፣ ትምጻእ፣ መንግሥትከ፣ ይኩን፣ ፈቃድከ፣ ሰማይ፣ ምድር፣ሲሳየነ፣ ዕለት፣ ሀበነ፣ ዮም፣ ኅድግ፣ ለነ፣ አበሳነ፣ ጌጋየነ፣ ንሕነ፣አበሰ፣ ኢታብአነ፣ እግዚኦ፣ ውስተ፣ መንሱት……..ወዘተ እነዚህ ሁሉ ከላይ ፕሮፌሰር ባየ ይማም በገለጹት መንገድ ቃል ለመባል የሚያስችለውን መስፈርት የሚያሟሉ የሐሳባችን ወካዮች ናቸው፡፡

ለምሳሌ አቡነ የሚለው ቃል መልእክት አለው አባታችን የሚለውን ሐሳብ የተሸከመ ነው፡፡ ራሱን ችሎ ይቆማል፤ማለትም ፍች ይሰጣል፤ ምዕላድ ያስጠጋል፡፡ ይህ ማለት በዐሥሩ መራሕያን መርባት ይችላል፡፡ በዐሥሩ መራሕያን ሲረባ ጾታን፣ መደብን፣ ቁጥርን፣ ወዘተ ያመለክታል፡፡  ስለዚህ ዋና ቃሉ አብ የሚለው ሲሆን “ነ” የሚለውን ዘርፍ አመልካች ምዕላድ አስጠግቷል፤ ከቃላት ክፍሎች ባንዱ ይመደባል፤ ይህም ስም በሚለው የቃል ክፍል ገብቶ ይቆጠራል፡፡

“ይትቀደስ” የሚለውንም ቃል ብንወስድ መልእክት አለው ይመስገን የሚለውን ሐሳብ የተሸከመ ነው፡፡ ራሱን ችሎ ይቆማል፤ ሌላ ፊደል ወይም ምዕላድ ሳይፈልግ ፍች ይሰጣል፤ ምዕላድ ያስጠጋል፡፡ ይህም ዋና ቃሉ ቀደሰ የሚለው ሲሆን በግስ እርባታ ሥርዓት “ይት” የሚለውን የሣልሣይ (የትእዛዝ) አመልካች ምዕላድ አስጠግቷል፤ በዐሥሩ መራሕያን መርባት ይችላል፡፡ በዐሥሩ መራሕያን ሲረባ ጾታን፣ መደብን፣ ቁጥርን፣ ጊዜን ወዘተ ያመለክታል፡፡ ከቃላት ክፍሎች ባንዱ ይመደባል፤ ይህም ግስ በሚለው የቃል ክፍል ገብቶ ይቆጠራል፡፡

ሐሳቡ ግልጽ እንዲሆን አንድ ተጨማሪ ምሳሌ እንጥቀስ፡፡ “እኩይ” የሚለው ቃል መልእክት አለው “ክፉ” የሚለውን ሐሳብ የተሸከመ ነው፡፡ ራሱን ችሎ ይቆማል፤ ሌላ ፊደል ወይም ምዕላድ ሳይፈልግ ፍች ይሰጣል፤ ምዕላድ ያስጠጋል ይህም “እምኵሉ” ከሚለው ቃል ኵሉ “እኩይ” ላይ ተቀፅሎ “እም” የሚለው አገባብ (ምዕላድ) የሚያርፈው እርሱ ላይ ነው፡፡ ከዚህም በተጨማሪ በራሱ የአረባብ ሥርዓት እየረባ መደብን፣ ቁጥርን፣ ጾታን ወዘተ መግለጽ ይችላል፡፡ ከቃላት ክፍሎች ባንዱ ይመደባል፤ ይህም ቅፅል በሚለው የቃል ክፍል ገብቶ ይቆጠራል፡፡

የቃል ክፍሎች

በማንኛውም ቋንቋ ቃላት ምድብ ( ክፍል) አላቸው፡፡ የቃላት አከፋፈል እንደየቋንቋው የተለያየ ነው፡፡  በግእዝ ቋንቋ ውስጥ የሚገኙት ቃላት በአምስት ይከፈላሉ እነሱም፡- ስም፣ ቅፅል፣ ግስ፣ ተውሳከ ግስ፣ አገባብ ናቸው፡፡ በእያንዳንዳቸው የቃል ክፍሎች በርካታ ክፍሎች አሉ፡፡ የቃል ክፍሎችን በተናጠል ስናይ የምንመለከታቸው ይሆናል፡፡ ከላይ በጠቀስነው ምንባብ ውስጥ የዘረዘርናቸውን ቃላት በቃላት ክፍል እየዘረዘርን እንመልከታቸው፡፡

ስም፡- አቡነ፣መንግሥትከ፣ ሰማይ፣ ምድር፣ ሲሣይ፣ አበሳ፣ ጌጋይ፣ ወዘተ

ቅፅል፡- እኩይ፣ መንሱት፣ ይእቲ፣ ኵሉ፣ ወዘተ

ግስ፡- ይትቀደስ፣ ትምጻእ፣ ይኩን፣ ሀበነ፣ ኅድግ፣ ንኅድግ፣ ኢታብአነ፣ ወዘተ

ተውሳከ ግስ፡- ዮም፣ ዓለም፣ ኵሉ

አገባብ፡- እስመ፣ ዘ፣ ወ፣ በ፣ ከመ፣ ከማሁ፣ አላ፣ እም፣ ለ፣ ወዘተ

በቤተ ክርስቲያን አስተምህሮ አቡነ ዘበሰማያት አምስት መሠታዊ ጉዳዮችን ይይዛል፡፡ እነሱም ሃይማኖት፣ ተስፋ፣ ፍቅር፣ ተአምኖ ሐጣውዕ (ትሕትና) እና ጸሎት(ልመና) ናቸው፡፡ ይህን ጥልቅና ዘርፈ ብዙ ጽንሰ ሐሳብ ማስተላለፍ የቻልነው፣ ከእግዚአብሔር ጋር መነጋገር የበቃነው በቃል አማካኝነት ነው፡፡ በእርግጥ ሰው ከእግዚአብሔር ጋር ለመግባባት የተዋቀሩ ቃላት፣ የሰዋስው ሥርዓት፣ የቋንቋ ጉዳይ ያስፈልገዋል ማለት አይደለም፡፡ እንደኛ ግን እርስ በእርስ ሰዎች እንድንግባባ ቋንቋ ያስፈልገናል፡፡ ከሰዎች ጋር በመናደርገው ተግባቦት ቋንቋ እንዳስፈለገን ሁሉ በመዋዕለ ስብከቱም እንደኛ ሰው በሆነበት ጊዜ በቋንቋ ከሰው ጋር ተግባብቷል፡፡ ዛሬም በዚህ አንጻር ሐሳባችንን በቃላት አማካኝነት ወደ እግዚአብሔር እናቀርባለን፡፡ ስለዚህ እርስ በእርሳችን ለመግባባት፣ ለእግዚአብሔር ያለንን ታዛዥነት፣ አምልኮታችንን ወዘተ ለሰዎች ለመግለጽ ቋንቋ መሠረት ነው፡፡የቋንቋ መሠረት ደግሞ ቃል ነውና ቃል ማለት ልናስተላልፈው የፈለግነውን ሐሳብ የሚወክልልን የሐሳብ ወካይ መግለጫ ነው በሚል እናጠቃልላለን፡፡

የቃልን ምንነትና የቃላት ክፍሎችን በአጭሩ እንዲህ ከተመለከትን በእያንድዳንዱ የቃላት ክፍሎች ውስጥ የሚኖረውን ክፍፍል (ዓይነት)፣ የቃላቱን ሙያ፣ መዋቅራዊ ሥርዓት ወይም የአገባብ ሥርዓታቸውን በሰፊው በዝርዝር የምንመለከት ይሆናል እስከዚያው ቸር እንሰንብት፤ አሜን፡፡