ምልአተ ባሕር

ዲያቆን ዘክርስቶስ ፀጋዬ

የበአተ ክረምት ሁለተኛው ክፍል ምልአተ ባሕር ይባላል፡፡ ይህም ከሐምሌ ፲፱ እስከ ነሐሴ ፲ ድረስ ያለው ወቅት ሲሆን ዝናም ምድርን የሚያለመልምበት፤ የተዘራው የሚበቅልበት፤ በፀሐይ ሐሩር የደረቁ ዛፎች ሁሉ የሚያቆጠቁጡበት ወቅት ነው፡፡ በተለይ ከሐምሌ ፲፱ እስከ ሐምሌ ፳፱ መባርቅት የሚበርቁበት፤ ባሕርና አፍላጋት የሚሞሉበት ወቅት ነው፡፡

መብረቅና ነጎድጓድ

መብረቅ ማለት የእሳት ሰይፍ፤ የእሳት ፍላፃ፤ በዝናም ጊዜ ከደመና አፍ የሚመዘዝ የሚወረወር ነው፡፡ (ራእ ፬፥፭፤ ኤር ፲፥፲፫፤ ኢዮ. ፴፯፥፬) የመብረቅ ተፈጥሮ ውሃው በደመና አይበት ተቋጥሮ ሲመጣ በነፋስ ወደል ጋዝ ተጭኖ ፤ ደመናና ደመና በተጋጨ ጊዜ የሚፈጠር ነው፡፡ ወተት ሲገፋ ቅቤ እንደሚወጣው አይነት ማለት ነው፡፡

ነጎድጓድ ማለት ታላቅ ግሩም ድምፅ፤ የሚያስፈራ፤ የሚያስደነግጥና የሚያንቀጠቅጥ ሲሆን (መዝ. ፸፮፥፲፰፤ ኢዮ. ፵፥፬)፤ መብረቅ ከወረደ በኋላ የሚሰማ ድምፅም ነው፡፡ (ኢዮ. ፴፯፥፪-፭፤ መዝ. ፳፰፥፫) ነገር ግን ለማስደንገጥ ወይም ለመዓት ብቻ የተፈጠረ አይደልም፤ ማኅፀነ ምድርን በመክፈት ውኃው ሠርፆ እንዲገባና አዝርዕትና አትክልት እንዲበቅሉ፤ እንዲያብቡና እንዲያፈሩ የሚያደርግ ጭምር ነው፡፡(ሄኖ.፮፥፩)

የክረምትን ኃይልና ብርታት ጥግ አድርገው የሚከሠቱ የተፈጥሮ ኃይላት ዑደትም ይጸናበታል፡፡ መብረቅ፤ ነጎድጓድ፤ ባሕርና አፍላጋት (ወንዞች) ይሠለጥናሉ፡፡ጥልቅ የሆኑ ቦታዎች መጠናቸው ያድጋል፤ ምንጮች ይመነጫሉ፤  የወንዞች ሙላት ይጨምራል፡፡

በቅድስት ቤተክርስቲያን በዚህ ክፍለ ክረምትና ንኡስ ክፍል ዘርዕን፤ ደመናን፤ ዝናምን የሚያዘክሩ እና የመብረቅን፤ የነጎድጓድን፤ የባሕርን፤ የአፍላጋትን፤ የጠልን ጠባይዓት የሚያመለክቱ መዝሙራት ይዘመራሉ፤ ምንባባት ይነበባሉ፤ ስብከት ይሰበካል፡፡

ኢትዮጵያዊ ቅዱስ ያሬድም ይህን ወቅት አስመልክቶ በድጓው ላይ በገለጸው መሠረት ‹‹ደምፀ እገሪሁ ለዝናም ሶበ ይዘንም ዝናም ይትፌሥሑ ነዳያን፤ ይጸግቡ ርኁባን ምድርኒ ርእየቶ ወአእኰተቶ ባሕርኒ ሰገደት ሎቱ፡፡ የዝናም ድምፅ ተሰማ፤ ዝናብም በዘነመ ጊዜ ድሆች ደስ ይሰኛሉ፤ ረኃብተኞችም ይጠግባሉ፤ ምድር አየችው፤ አመሰገነችውም፤ ባሕርም ሰገደችለት›› የሚለው ዜማ ይዜማል፡፡

ቅዱስ ዳዊት ደግሞ በመዝሙሩ ‹‹ዘይገለብቦ ለሰማይ በደመና፤ ወያስተዴሉ ክረምተ ለምድር፡፡ ዘያበቊል ሣዕረ ውስተ አድባር፡፡ ወሐመልማለ ለቅኔ እጓለ እመሕያው፡፡ ‹‹ሰማይን በደመና የሚሸፍን፤ ለምድርም ዝናምን የሚያዘጋጅ፣ ሣርን በተራሮች ላይ ልምላሜውንም ለሰው ልጆች አገልግሎት የሚያበቅል›› (መዝ.፻፵፮፥፰፤መዝ.፻፴፬፥፮፤መዝ.፸፮፥፲፰፤ መዝ.፷፬፥፱) ሲል ዘምሯል፡፡

እግዚአብሔር በነጎድጓድና በመብረቅ፤ በባሕርና በሐይቅ ሁሉ ላይ ሥልጣን ያለው አምላክ መሆኑን፤ የሚታዩና የማይታዩ ፍጥረታት ሁሉ የኃይሉ መገለጫዎች እንደሆኑ የሚያስተምሩ መዝሙራት ይዘመራሉ፡፡ ምንባባትም ከቅዱስ ወንጌልና ከቅዱስ ጳውሎስ መልእክታት እንዲሁም ከሐዋርያት ሥራ ክረምቱን በተመለከተ የተዘጋጁት ይነበባሉ፡፡