በአተ ክረምት

 ዲያቆን ኤፍሬም የኔሰው

በቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን ሥርዓት፣ በሀገራችን ኢትዮጵያ የዘመን አቈጣጠር ስሌት መሠረት ወቅቶች በአራት ይከፈላሉ፡፡ እነዚህም፡- ዘመነ መጸው (መከር)፣ ዘመነ ሐጋይ (በጋ)፣ ዘመነ ጸደይ (በልግ) እና ዘመነ ክረምት ይባላሉ፡፡ ከአራቱ ወቅቶች መካከልም ከሰኔ ፳፮ እስከ መስከረም ፳፭ ቀን ድረስ ያለው ጊዜ (አሁን የምንገኝበት ወቅት) ዘመነ ክረምት ተብሎ ይጠራል፡፡ ቃሉን ለማብራራት ያኽል፣ ‹ክረምት› የሚለው ቃል ‹ከረመ – ከረመ› ካለው የግእዝ ግስ የተገኘ ሲኾን፣ ትርጕሙም የዝናም፣ የአዝርዕት፣ የአረም ጊዜ፣ እንደዚሁም ዕፀዋት፣ አዝርዕትና አትክልት በቅለው፣ ለምልመው የሚያድጉበት፣ ምድር በአረንጓዴ ዕፀዋትና በልምላሜ የምታሸበርቅበት ወቅት ማለት ነው፡፡ ‹ዘመነ ክረምት› ማለትም ይኼንኑ ወቅት የሚያስገነዝብ ትርጉም አለው፡፡

በአተ ክረምት (ዘርዕ፣ ደመና)

ከሰኔ ፳፮ እስከ ሐምሌ ፲፰ ቀን ድረስ ያለው የመጀመሪያው የክረምት ክፍለ ጊዜ ‹በአተ ክረምት› ወይም ‹ዘርዕ፣ ደመና› ይባላል፡፡ ‹በአተ ክረምት› ማለት ‹የክረምት መግቢያ፣ መጀመሪያ› ማለት ነው፡፡ በዚህ ወቅት በቤተ ክርስቲያናችን ስለ ክረምት መግባት፣ ስለ ዘርዕ፣ ስለ ደመና እና ስለ ዝናም የሚያዘክሩ መዝሙራትና ምንባባት ይዘመራሉ፣ ይነበባሉ፡፡ ይህ ወቅት ደመና ሰማዩን የሚሸፍንበት፣ የዝናም መጠን የሚያይልበትና መሬት በዝናም ረክታ ዘር የምታበቅልበት ጊዜ ነውና፡፡

ዘርዕ

ምድር ከሰማይ ዝናምን፣ ከምድርም ዘርን በምታገኝበት ወቅት ዘሩን አብቅላ ለፍሬ እንዲበቃ ታደርጋለች፡፡ በምድር የምንመሰል የሰው ልጆችም ከእግዚአብሔር ባገኘነው ጸጋ ተጠቅመን፣ ከቅዱሳት መጻሕፍት እና ከመምህራነ ቤተ ክርስቲያን የምናገኘውን ቃለ እግዚአብሔር በተግባር ላይ ማዋል እንደሚገባን ከምድር እንማራለን፡፡ ይህን ካደረግን ዋጋችን እጅግ የበዛ ይኾናል፣ ከዚህም አልፎ የእግዚአብሔርን መንግሥት ለመውረስ እንበቃለን፡፡ የተዘራብንን ዘር ለማብቀል ማለትም ቃሉን በተግባር ለማዋል ካልተጋን ግን በምድርም በሰማይም ይፈረድብናል፡፡ ‹‹ምድርም በእርስዋ የሚወርደውን ዝናብ ከጠጣች፣ ያን ጊዜ ስለ እርሱ ያረሱላትን መልካም ቡቃያ ታበቅላለች፡፡ ከእግዚአብሔር ዘንድም በረከትን ታገኛለች፡፡ እሾኽንና ኵርንችትን ብታወጣ ግን የተጣለች ናት፡፡ ለመርገምም የቀረበች ናት ፍጻሜዋም ለመቃጠል ይኾናል፣›› በማለት ቅዱስ ጳውሎስ እንደ ገለጸው (ዕብ. ፮፥፯-፰)፡፡

በቅዱስ ማቴዎስ ወንጌል ፲፫፥፩-፳፫ እንደ ተገለጸው ጌታችን አምላካችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የክርስትና ሕይወትን ከዘርና ፍሬ ጋር በማመሳሰል አስተምሯል፡፡ ይኸውም አንድ ገበሬ ዘር ሲዘራ በመንገድ ዳር የወደቀው ዘር ከመብቀሉ በፊት በወፎች እንደ ተበላ፣ በጭንጫ ላይ የተጣለውም ወዲያውኑ ቢበቅልም ነገር ግን ሥር መስድድ አልቻለምና፡፡ በፀሐይ ብርሃን እንደ ጠወለገ፤ በእሾኽ መካከል የወደቀው ደግሞ ሲበቅል በእሾኽ እንደ ታነቀ፣ ከሁሉም በተለየ መልኩ በመልካም መሬት ላይ የተጣለው ዘር ግን አድጎ መቶ፣ ስድሳ፣ ሠላሳ ፍሬ እንደ ሰጠ የሚያስረዳ ነው፡፡

ይህም ምሳሌ አለው፡፡ ጌታችን ለደቀ መዛሙርቱ እንደ ተረጐመው በመንገድ ዳር የተዘራው ዘር የእግዚአብሔርን ቃል ሰምቶ የማያስተውል (ልብ የማይል) ክርስቲያን ምሳሌ ነው፣ እንደዚህ ዓይነቱ ምእመን ሙሉ እምነት ስለማይኖረው በመከራው ጊዜ አጋንንት ድል ያደርጉታል፡፡ በጭንጫ ላይ የተዘራው ደግሞ ቃሉን ሰምቶ ወዲያው በደስታ የሚቀበል፣ ነገር ግን ተግባራዊ የማያደርግ (የማይተገብር) የክርስቲያን ምሳሌ ነው፡፡ ይህ ምእመንም በጠንካራ እምነት ላይ የጸና አይደለምና በሃይማኖቱ ምክንያት መከራ ወይም ስደት በደረሰበት ጊዜ ፈጥኖ ይክዳል፡፡ በእሾኽ መካከል የተዘራውም ቃሉን የሚሰማ ቢሰማም ግን በዚህ ዓለም ዐሳብና ባለ ጠግነት ተታሎ ቃሉን የማይተገብር ክርስቲያን ምሳሌ ነው፡፡

በመልካም መሬት የተዘራው ደግሞ ቃሉን ሰምቶ ተግባር ላይ የሚያውል ክርስቲያን ምሳሌ ነው፡፡ እንደዚህ ዓይነት ምእመን በተማረው ትምህርት ጸንቶ ይኖራል፣ መልካም ሥራም ይሠራል፡፡ በመልካም መሬት የተዘራው ዘር ስለ አንዱ ፋንታ መቶ፣ ስድሳ፣ ሠላሳ እንደሚያፈራ ሁሉ በክርስቲያናዊ ግብር ጸንቶ የሚኖር ምእመንም ሥራውን በሦስት መንገድ ማለትም በወጣትነት፣ በማእከላዊነትና በፍጹምነት ደረጃ እንደሚፈጽም፣ ዋጋውንም በሥራው መጠን እንደሚያገኝ የሚያስረዳ ነው፡፡ በሌላ በኩል ባለ መቶ ፍሬ የሰማዕታት፣ ባለ ስድሳ የመነኮሳት፣ ባለ ሠላሳ በሕግ ተወስነው በዓለም የሚኖሩ ምእመናን ምሳሌ ነው፡፡ በተመሳሳይ ምሥጢር ሁሉም የፍሬ መጠን በሁሉም ጾታ ምእመናን ሕይወት ውስጥ እንደሚገኝ የትርጓሜ ሊቃውንት ያስተምራሉ፡፡ ስለዚህም በሰማዕትነትም፣ በምንኵስናም፣ በዓለማዊ ሕይወትም ውስጥ የሚኖሩ ምእመናን መልካም ግብራቸው እጅግ የበዛ ከሆነ በባለ መቶ ፍሬ፣ መካከለኛ ከሆነ በባለ ስድሳ፣ ከዚህ ዝቅ ያለ ከሆነ ደግሞ በባለ ሠላሳ ፍሬ ይመሰላል፡፡ (ትርጓሜ ወንጌለ ማቴዎስ፣ ማቴ. ፲፫፥፩-፳፫)፡፡

ደመና

እግዚአብሔር አምላካችን የውቅያኖስ እና የሐኖስ ድንበር ይሆን ዘንድ በውኃ መካከል ጠፈርን ፈጥሮ ከጠፈር በታች (በዚህ ዓለም) ያለው ውኃ በአንድ ቦታ እንዲወሰን አድርጎታል፡፡ ከዚያም ከምድር እስከ ብሩህ ሰማይ ድረስ የነበረውን ውኃ ከሦስት ከፍሎ ሢሶውን አርግቶ ጠፈር ብሎ ሰይሞታል፡፡ ከጠፈር በላይ ያለውን ሢሶውን የውኃ ክፍል ሐኖስ ብሎታል፡፡ ሢሶውንም ይህንን ዓለም ከሰባት ከፍሎ ሰባተኛውን ዕጣ አጐድጕዶ በዚያ ወስኖ ስሙን ውቅያኖስ ብሎ ጠርቶታል፡፡ የብሱን ክፍል ደግሞ ምድር ብሎ ሰይሞታል፡፡ እግዚአብሔር አምላክ ከደረቅ ምድር ደረቅ ጢስን፣ ከርጥብ ባሕር ርጥብ ጢስን አስወጥቶ እንደ ጉበት በለመለመች ምድር ላይ ደመናን አስገኝቷል (ትርጓሜ መዝሙረ ዳዊት፣ መዝ. ፻፴፬፥፯)፡፡

ደመና፣ ዝናምን የሚሸከም የማይጨበጥ፣ የማይዳሰስ ጢስ መሰል ፍጥረት ነው፡፡ በትነት አማካይነት፣ በደመና ተሸካሚነት ከውቅያኖሶች እና ከወንዞች እየተቀዳ ወደ ሰማይ ተወስዶ እንደ ገና ተመልሶ ወደ ምድር የሚጥለው ውኃ ዝናም ይባላል፡፡ ይኸውም በእግዚአብሔር ጥበብ በደመና ወንፊትነት ተጣርቶ ለፍጡራን በሚመችና በሚጠቅም መጠን በሥርዓት ይወርዳል፡፡ ‹‹ያጸንዖ በፍኖተ በድው ከመ ይዝንም ብሔረ ኀበ አልቦ ሰብእ ወኢይነብሮ ዕጓለ እመሕያ፣ ዝናሙን ሰው በሌለበት በምድረ በዳ ያዘንመዋል፤›› እንዳለ ቅዱስ ኤጲፋንዮስ በቅዳሴው፡፡ ይህ ኃይለ ቃል እግዚአብሔር በረዶውን በምድረ በዳ አፍስሶ የጠራውን ውኃ ሰው ወዳለበት እንዲዘንም ማድረጉን የሚያስረዳ መልእክት የያዘ ሲሆን፣ ምሥጢሩም ጌታችን አምላካችንና መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እንበለ ዘርዐ ብእሲ (ያለ ወንድ ዘር) በልዩ ጥበቡ ተፀንሶ ከቅድስት ድንግል ማርያም መወለዱንና በተዋሐደው ሥጋ በምድር ተመላልሶ ወንጌልን ማስተማሩን፣እንደዚሁም ‹‹ሑሩ ወመሀሩ፤ ሒዱና አስተምሩ›› ብሎ ቅዱሳን ሐዋርያትን በመላው ዓለም ለስብከተ ወንጌል አገልግሎት ማሰማራቱን ያመለክታል (ትርጓሜ ቅዳሴ ኤጲፋንዮስ፣ ፪፥፭-፮)፡፡

ዘመነ ክረምት ስለ ሥነ ፍጥረት ዘርዘር ባለ መልኩ የሚነገርበት፤ ፍጡርን ከፈጣሪ መናን (ምግብን) ከተመጋቢ ለይቶ የሚያሳይ እና የሚያሳውቅ ዘመን ነው፡፡ በዚህ ወቅት የውኃ ባሕርይ ይሠለጥናል፣ ውኃ አፈርን ያጥባል፣ እሳትን ያጠፋል፡፡ ሆኖም ግን ውኃ በብሩህነቱ ከእሳት፣ በቀዝቃዛነቱ ከነፋስ፣ በእርጥብነቱ ከመሬት ጋር ተስማምቶ ከሦስቱ ባሕርያት ጋር ይኖራል፡፡ ይህን ምሥጢር ከሕይወታችን ጋር አያይዘን ስንመለከተው ዘመነ ክረምት የክርስትና ምሳሌ ነው፡፡ በክረምት ወቅት ገበሬው ብርዱንና ዝናሙን ሳይሳቀቅ ለሥራ ይሰማራል፣ በበጋው የእጁን ፍሬ ያገኝ ዘንድ የክረምቱን መከራ ይታገሣል፡፡ ይህም ምእመናን በሰማያዊው ዓለም የምናገኘውን ተድላና ደስታ በማሰብ በምድር ቆይታችን ወቅት የሚደርስብንን ልዩ ልዩ መከራ በትዕግሥት ማሳለፍ እንደሚገባን ያስገነዝባል፡፡

በዘመነ ክረምት አዝርዕቱ በስብሰው ከበቀሉ፣ ካበቡና ካፈሩ በኋላ የሚጠቅሙት በሪቅ፣ በጎተራ እንደሚሰበሰቡ፣ እንክርዳዶቹ ደግሞ በእሳት እንደሚቃጠሉ ሁሉ እኛም ተወልደን፣ ተጠምቀን፤አድገን፣ ዘራችንን ተክተን እንደምንኖር፣ ዕድሜያችን ሲያበቃም እንደምንሞት፣ ሞተንም እንደምንነሣና መልካም ሥራ ከሠራን ወደ እግዚአብሔር መንግሥት እንደምንገባ፣ በኀጢአት ከኖርን ደግሞ በገሃነመ እሳት እንደምንጣል የምንማርበት ወቅት ነው፡፡ በመሆኑም ሰይጣን በሚያዘንበው የኀጢአት ማዕበል እንዳንወሰድና በኋላም በጥልቁ የእሳት ባሕር እንዳንጣል ዅላችንም ቅዱሳት መጻሕፍትና ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን ያዘጋጁልንን የቃለ እግዚአብሔር ዘር በእርሻ ልቡናችን በመዝራት (በመጻፍ) እንደየዓቅማችን አብበን፣ ያማረ ፍሬ አፍርተን መንግሥቱን ለመውረስ መዘጋጀት ይኖርብናል፡፡

ወስብሐት ለእግዚአብሔር