ሶርያዊው ቅዱስ ኤፍሬም(ክፍል ሁለት)

ዲ/ን ዮሐንስ ልሳነወርቅ

ከክፍል አንድ የቀጠለ

በቅዱስ ኤፍሬም ሥራዎች ላይ በሚያጠነጥነውና የሚያበራ ዐይን በሚል ርእስ ሰባስቲያን ብሩክ ካዘጋጀው  መጽሐፍ የተገኘው እንዲህ ተተርጉሞ ቀርቦአል። መልካም ንባብ

በዚህ ክፍል ውስጥ የምናየው ፈጣሪና ፍጡር፣/የተሰወረውና የተገለጠው/ሁለቱ ጊዜያትና ነጻ ፈቃድ በሚሉት ርእሶች ስር ቅዱስ ኤፍሬም በግጥም ያቀረበውን ትምህርት ነው።የቅዱስ ኤፍሬም መዝሙራት ከሚያጠነጥኑባቸው ርእሰ ጉዳዮች አንጻር ስያሜ ተሰጥቶአቸዋል። ለምሳሌ በእምነት ዙሪያ የጻፈውን -Faith ፣በቤተ ክርስቲያን ዙሪያ የጻፈውን -Church የሚል ሲሆን ፤በዚህ ጽሑፍም እነዚህ  በእያንዳንዱ መዝሙር ስር ተጠቅሰዋል።

1. ፈጣሪ-ፍጡር (Creator-Creation)

ቅዱስ ኤፍሬም በፈጣሪና በፍጡር መካከል ያለዉን ልዩነት ሁልጊዜ የተረዳ ነው። በእምነት ላይ ከዘመራቸው መዝሙሮች በአንዱ(Faith 69:11) በነዌና አልአዛር (ሉቃ.16፣26) ምሳሌ የተገለጸውን ቃል በማንፀባረቅ ስለ ነገረ ህላዌ(ontology) ያለውን ክፍተት እንደ ሰፊ ልዩነት በመውሰድ ይናገራል። በዚህ ሰፊ ልዩነት ውስጥ ፍጡር ፈጣሪዉን አይደርስበትም።(Faith)ይኽም ማለት የተፈጠረ ማንነት ስለ ፈጣሪ ማንነት ምንም ማለት አይችልም።

ቀድሞ እንዳየነው በፈጣሪና በፍጡር መካከል ያለው ጥርት ያለ  የልዩነት ቦታ የማመልከት ጉዳይ በአራተኛው መቶ ክ/ዘመን ክርክር ነበረበት። ቅ/ኤፍሬም  ሁሉንም የመልአካዊና የቁስ አካላዊ ማንነትን በአንድ ወገን (ፍጡር) ሲያስቀምጥ የፈጣሪ ቃል ከነገረ ህላዌ ልዩነት(ontological chasm) በሩቅ አቅጣጫ በአጽነዖት ያስቀምጠዋል።

ማንኛዉም ፍጡር ይኽንን ሰፊ ልዩነት በማለፍ ፈጣሪ ጋር መድረስ እንደማይችል ከማስተዋል ጋር በተያያዘ (ቅ/ኤፍሬም ከሌሎች ብዙ አባቶች ጋር የሚጋራው ሀሳብ) በሆነ ነገር ዕውቀት ያለው መረዳት ከዕውቀቱ አካል የግድ መብለጥ አለበት የሚለው ግንዛቤ ውጤት ነው።በዚህ መረዳት መሠረት በተመሳሳይ ጊዜ  እግዚአብሔርን ማወቅም መግለጽም ይቻላል የሚል የሰው መረዳት የማይያዘውን (uncontainable) እግዚአብሔርን መያዝ ይችላል እያለ ነው። ስለዚህም የእግዚአብሔርን ማንነት ለመመርመር መሞከር እጅግ አስፈሪ እንደሆነ እንዲህ ይገልጸዋል።

           ማንኛዉም መመርመር(ላልቶ ይነበብ) የሚችል ሰው
           የሚመረምረውን(ነገር) የያዘ (contains) ይሆናል።
           ፍጹም ዕውቀት ያለውን የሚይዝ (contains) ዕውቀት
           ሁሉን ዐዋቂ ከሆነው(ከእግዚአብሔር ) ይበልጣል።
           እርሱን(እግዚአብሔርን) በአጠቃላይ መለካት እንደሚችል አረጋግጧልና።
           ስለዚህም አብንና ወልድን የሚመረምር ሰው ከእነርሱ ይበልጣል!
           አመድና ትቢያ ሲሆን ራሱን ከፍ አድርጎ

አብና ወልድ መመርመር(ጠብቆ ይነበብ) አለባቸው የሚል የራቀ ፣የተወገዘም ይሁን። (Faith 9:16)
የአምላክን መሰወር ስለመመርመርና መጠየቅ (የማይጠየቀውን) የሚሰጠው ምላሽ ማስጠንቀቂያ ቅ/ኤፍሬም   ዝንባሌው ኢ-ምሁራዊ ነው ወደሚለው ሊመራን አይገባም። ከዚህ የራቀ ነው፣ እርሱ እንደሚያየው የሰው መረዳት በተፈጥሮ ውስጥ ብዙ አቅጣጫ(scope) ያለው ሲሆን ድርሻዉም የፈጣሪን እውነታ በከፊል ለመረዳት የሚያስችሉትን ዓይነቶችንና  ምሳሌዎችን ከተፈጥሮ መፈለግ ነው። አስነቃፊ የሚሆነው መረዳቱ የነገረ ህላዌን ልዩነት ማለፍ ሲፈልግ ብቻ ነው።አግባብነት ያለው የመረዳት ጥያቄ የሚያርፍበት ቦታ እግዚአብሔር ራሱን በፍጥረት(በተገለፁ ነገሮች) በገለፀበት ላይ ነው። ስለዚህም በእምነት መዝሙሮች ላይ ቅ/ኤፍሬም ሲገልፅ                                         

                         በቤተ ክርስቲያን የመረዳት ጥያቄ አለ፤
                         የተገለጸውን መመርመር
                         መረዳቱ ያልተፈቀዱ የተሰወሩ ነገሮችን
                         የመመርመር ዝንባሌ አልነበረውም።(Faith 8:9)

ይህም ቅ/ኤፍሬም ደጋግሞ በሚጠቀማቸው የተገለጠና የተሰወረ በሚሉ ቃላት መካከል ያለውን ሚዛናዊነት(tension) ወደሚያሳየው ቀጣይ ርእስ ይወስደናል።

 

2. የተሰወረውና የተገለጠው( The Hidden and The Revealed )

ቅዱስ ኤፍሬም ስውርና ክሱት(ግልጥ) የሚሉ ቃላትን ሲጠቀም ፈጽመው ከተለያዩ ሁለት እይታዎች አንዱን ይገልጻል። አብዛኛውን ጊዜ የሰው እይታ እያልን የምንጠራውን ራሱ እንዲገለጽ ካልፈቀደ በቀር እግዚአብሔር ስውር ነው የሚለውን ይተካል። የእግዚአብሔርን መሰወር ሰው ሊረዳው  የሚችለው እግዚአብሔር በተለያዩ  ሁኔታዎች ራሱን ሲገልጽ ብቻ  ነው።ለፍጡር ህላዌ የእነዚህ እግዚአብሔር ራሱን ለእያንዳንዱ  የመግለጽ ሁነቶች ሁሉ የእግዚአብሔርን መሰወር ወደ ሙሉ መገለጥ አያደርሱትም፤ መገለጡ ሁል ጊዜ በከፊል ነው። ይኽም ማለት ይህ የሰው እይታ በዋናነት እንደየራሱ ነው። እያንዳንዱ ሰው የእግዚአብሔርን መሰወር የሚያቀርበው በተለያዩ የመገለጥ መንገዶች ነው።
የእግዚአብሔር መሰወር ወደ ሙሉነት በቀረበ ሁኔታ ለሰውነት የተገለጠው በሥጋዌ ነው ማለት አስፈላጊ አይደለም፤ያኔም እንኳን የፈጣሪነት መሰወር እንደተጠበቀ ነበር።

                       ለተሰወረው ምሥጋና የማይሰጥ ማነው፡ ከሁሉም ይልቅ የተሰወረ
                       መገለጥን ይከፍት ዘንድ ማን መጣ፡ ከሁሉም ይልቅ የተከፈተ
                       እሱ በሰውነት ላይ ተቀምጦአልና ፤ ህሊናዎች ባይዙትም
                       ሌሎች አካላትም ዳሰሱት (Faith 19:7)
                     
         ወይም ሰፋ ባለ ሁኔታ
                       ጌታ፡ ወደ መገለጥ የመጣውን መሰወርህን 
                       ትኩር ብሎ ማየት ማን ይችላል?
                       አዎ መሰወርህ ወደ መገለጥና ወደ መታወቅ መጥቶአል
                       ምሥጢራዊ ህላዌህ ያለ ገደብ ወደ መገለጥ መጥቶአል
                        የሚፈራ (የሚደነቅ) ማንነትህ ወደ ያዙት እጆች መጥቶአል።
                        ጌታ ይህ ሁሉ በአንተ ሆኖአል ፤ ምክንያቱም ሰው ስለ ሆንክ
                        አንተን ስለላከ ምስጋና ለእሱ(ለአብ)
                        እንዲህ ቢሆንም ፈጽሞ የማይፈራህ ማነው
                        ምክንያቱም ምንም እንኳ
                        ሰው መሆንህ ዳግም ልደትህ የተገለጠ ቢሆንም
                        ከአብ የተወለድከው ልደት የማይደረስበት እንደሆነ ይቀራል።
                        የሚመረምሩትን ሁሉ አስቁሞአል። (Faith 51:2-3)

ከዚህ ሰውአዊና ግላዊ እይታ ጎን ለጎን ሌላ ፈጽሞ የተለየ እይታ አለ፤ ይኽም ቅዱስ ኤፍሬም እውነት እያለ የሚጠራው የፈጣሪ እርግጠኝነት ነው። እዚህ ላይ  መነሻው የሰው እግዚአብሔርን መረዳት አይደለም፤  በራሱ ህልው የሆነ (objectively exists) ግን በተሰወረና   ግላዊ በሆነ መንገድ የሚገለጥ የእግዚአብሔር  እውነተኛ ህላዌ ነው። ከዚህ አቅጣጫ ሲታይ ዓይነቶችና ምሳሌዎች እግዚአብሔር በሚታይ  ፍጥረት  ራስን የመግለፅ ቅጽበቶች አይደሉም ፤ይልቁንም አንድ ቀን የሚገለጥን ነገር የሚያመለክት መሰወር አላቸው፤ በተፈጥሮና በቅዱሳት መጻሕፍት ምሳሌዎች የተሰወረው በክርስቶስ ሥጋዌ ተገልጦአል፤ በ(ቤ/ክ) ምስጢራት የተሰወረ በፍርድ ጊዜ በመንግሥተ ሰማያት ይገለጣል።
ቅዱስ ኤፍሬም በግጥሙ ስለ ተሰወረውና ስለ ተገለጠው ያሉትን እነዚህን ሁለት እይታዎች ድንቅ በሆነ መንገድ ያስተሳስራቸዋል። በሁለቱም ጥጎች ፡ የተሰወረና የተገለጠ ፡እንዲጠበቅ የሚያደርገው ሚዛናዊነት በእግዚአብሔር  ርሑቅነት(transcendence) ና ቅሩብነት(immanence) መካከል ካለው መሳሳብ ሌላ አይደለም።

3. ሁለቱ ጊዜያት (The Two Times)

መደበኛው ጊዜ ቀጥታዊ ነው፤ እያንዳንዱ ነጥብም በጊዜ ውስጥ በፊትንና  በኋላን ያውቃል። በሌላ በኩል ምስጢራዊ ጊዜ በፊትንና በኋላን አያውቅም ዘልዓለማዊ አሁንን ብቻ። ለምሥጢራዊ ጊዜ ጠቃሚ የሆነው  በቀጥታዊ ጊዜ ቅደም ተከተል ላይ ያለው ልዩ ቦታ ሳይሆን ይዘቱ ነው። ይኽም ማለት በታሪካዊ ጊዜ በተለያዩ ወቅቶች የሚገኙ ፣ በነገረ ድሕነታዊ ይዘታቸው አንድነት ያላቸው ድርጊቶች ፡እንደ የክርስቶስ ሰው መሆን/መጠመቅ/መሰቀል/ወደ ሲኦል መውረድ(ነፍሳትን ለማውጣት)ና ትንሣኤ ፡በምስጢራዊ ጊዜ በአንድነት ይሄዳሉ፤ሊተኮርበት የሚቻል አጠቃላይ ነገረ ድሕነታዊ ይዘታቸው  ከእነዚህ ተከታታይ  ነጥቦች በቀጥታዊ ጊዜ በማንኛዉም(በአንዱ) ላይ በማተኮር በሚለው ውጤት። ለምሳሌ ምንም እንኳ በቀጥታዊ ጊዜ የክርስቶስ ጥምቀት ከሞቱ እና ከትንሣኤው በፊት ቢሆንም በሶሪያ ትውፊት እንደራስና ለሁሉም የክርስትና ጥምቀት ምንጭ መሆኑን ወደ መረዳት እንዴት እንደመጡ ይገልጻል።

በቅዱስ ኤፍሬም መዝሙራት የምስጢራዊ ጊዜ እሳቤ ከሌሎች ሁለት ነጥቦች አንጻርም ጠቃሚ ነው።
በመጀመሪያ  ደረጃ ቅ/ኤፍሬም ክርስቶስ ወደ ሙታን ዓለም ሲኦል የመውረድ አስፈላጊነቱን ስለተረዳበት መንገድ የሚያሳይ ስለሆነ። ነገር ግን በመሬት ላይ የክርስቶስ ሥግው ሕይወት ለታሪካዊ ጊዜና ቦታ መግቢያ ነው፡ የመጀመሪያው ክ/ዘመን ፍልስጥኤም፡ ወደ ሲኦል መውረድ ከምሥጢራዊ ጊዜ እና ቦታ ጋር ብቻ የተያያዘ ነው።ይኽ የክርስቶስ ወደ ሁለቱም ኃላፊና መጪ ጊዜ መግባት ነው፤በጂኦግራፊያዊ ቦታ የተከለለም አይደለም። ስዚህም ወደ ሲኦል መውረዱ በነገረ ድሕነት ሂደት ላይ ከጌታ የምድር ቆይታው ጋር እኩል ጠቀሜታ አለው፤ በዚያም እንዲህ ባይሆን ኖሮ ሊነሳ የሚችለው ውሱንነትን (የክርስቶስ ሥራ በታሪካዊ ጊዜና ጂኦግራፊያዊ ቦታ እንደተገደበ መረዳት) ያብራራል።

የክርስቶስ ወደ ሲኦል የመውረድ ዶግማዊ ዓላማ ሥጋዌ(የክርስቶስ ሰው መሆን) ሁሉንም ታሪካዊ ጊዜንና ጂኦግራፊያዊ ቦታን እነደለወጠ(effects) በግልጽ ለማሳየት ነው። ነገር ግን ይኽን ለማግኘት በምስጢራዊ ጊዜና በምስጢራዊ ቦታ  አንጻር ሊነገር ይገባዋል፤ በዚህም መሠረት መውረዱም ታሪካዊ በሚመስልና ግጥማዊ የጥንት ታሪክ በሆነ መንገድ ብቻ ሊገለጽ ይችላል፡ ቅዱስ ኤፍሬም በንጽቢን መዝሙሮቹ ሁለተኛ አጋማሽ ላይ በታላቅ ድራማዊ ውበት እንደገለጸው።

የቅዱስ ኤፍረምን አስተሳሰብ ለመረዳት የምስጢራዊ ጊዜ እሳቤ ጠቃሚ የሆነው ሁለተኛው ነጥብ የሚያጠነጥው በታሪካዊጊዜ የክርቲያኖች የጥምቀትና ቁርባን ምስጢራት ሱታፌና በፍርድ ቀን የእነሱ ሙሉ በሙሉ እውን መሆን ነው። ምክንያቱም የመንግሥተ ሰማያት ሕይወት ለምሥጢራዊ ጊዜ የተገባ ነው። በተለያየ መጠን በምድር ላይ በታሪካዊ ጊዜ ውስጥ ባለ በእያንዳንዱ ሊተገበር ይችላል።

4. ነጻ ፈቃድ (Free will)
በቅዱስ ኤፍሬም አስተሳሰብ ውስጥ ነጻ ፈቃድ እጅግ ጠቃሚ የሆነ ሚና ይጫወታል። በዚህ ርእስ ላይ ያተኮረ መዝሙር  ጌታ፡ትንሿን አካል ነፃ ፈቃድን በመስጠት ከሌሎች ሁሉም ከተፈጠሩ ነገሮች አገዘፍክ። (Heresies 11)የሚል መልስ አለው።

ቀድሞ እንዳየነው አዳም በራሱ ነጻ ፈቃድ ትእዛዛቱን ይጠብቅ ዘንድ መርጦ ቢሆን ኖሮ እግዚአብሔር ከፍ ባለ ሁኔታ  አዳምን ያከብረው ዘንድ በመካከለኛ ሁኔታ ፈጥሮታል ።

         
                  ፍትሓዊ የሆነው(እግዚአብሔር)፡ዘውዱን ለአዳም በከንቱ እንዲሰጠው አልወደደም
                  ምንም እንኳ በገነት ያለ ድካም ደስ ይሰኝ ዘንድ ቢፈቅድለትም
                  አዳም ቢፈልግ ሽልማቱን ማግኘት እንደሚችል እግዚአብሔር አውቆአል።
                  ፍትሓዊው ፡አዳምን ያከብረው ዘንድ ስለወደደ፤ ምንም እንኳ በልዑላዊ ሕላዌዎች ደረጃ
                  በጸጋ ታላቅ ቢሆንም ለሰው አግባብነት ላለው ለነጻ ፈቃድ አጠቃቀም
                  ክብሩ ያነሰ ነገር   አይደለም።(Paradise 12:18)   
አዳም ከገነት የተባረረው በተሳሳተ የነጻ ፈቃዱ አጠቃቀም ነው፤እንዲሁም ቅዱሳን የከበሩት በዚህ ስጦታ ትክክለኛ አጠቃቀም ነው።
                  ትእዛዛቱን ያስቀመጠ እርሱ(እግዚአብሔር) ምስጉን ነው
                  በእነዚያ(ትእዛዛቱ) ምክንያት ነጻ ፈቃድ ይከበር ዘንድ
                  ጽድቅን፣ስለነጻ ፈቃድ የሚጣሩ ምስክሮችን ያበዛ
                  እርሱ(እግዚአብሔር) ምስጉን ነው።(Heresies 11:4,end)
እርሱ ራሱን ባለ ማስከፋት ደስ እናሰኘው ዘንድ እኛን ማስገደድ በቻለ ነበር ፤ግና በምትኩ   በራሳችን ነጻ ፈቃድ በደስታወደ እርሱ እንቀርብ ዘንድ በሁሉም መንገድ ተቸገረ።(Faith 31:5)
የኖህ ትውልድ ስለ ነጻ ፈቃድ ትክክለኛ እና የተሳሳተ አጠቃቀም ለቅዱስ ኤፍሬም ቀዳሚ ምሳሌ ሆኖአል።
                   የኖህን ምሳሌ ውሰድ፤
                   በዘመኑ የነበሩትን ሁሉንንም መገሰፅ ይችላል፤
                   ፈልገው ቢሆን ኖሮ እነሱም እኩል ድል መንሳት ይችሉ ነበር፤
                   በእነሱ የነበረው የእኛ ነፃ ፈቃድ በኖህ ከነበረው ጋር አንድ ነውና።(Chrch 3:9)

የነፃ ፈቃድ ተግባር በሞራል ክልል የተገደበም አይደለም።ለተለያዩ የእግዚአብሔር ራስን የመግለፅ መንገዶች ምላሽ መስጠት ሙሉ በሙሉ እንደኛ ፍላጎት ነው።የእኛ የራሳችን ነፃ ፈቃድ የአንተ ደስታ መክፈቻ ነው።(Church 13:5)
 
ምንም እንኳ በራሳቸው ነጻ ፈቃድ ራሳቸውን ለሃጢአት ባሪያ ባደረጉት ውስጥ በግልጽ ባይታይም ነጻ ፈቃድ በእያንዳንዱ በእኩል መጠን ይገኛል።

ቅዱስ ኤፍሬም ይኽንን በሕክምናዊ ንጽጽር ይገልፀዋል።
                   የእኛ ነጻ ፈቃድ ማንነት በእያንዳንዳችን ውስጥ አንድ ዓይነት ነው።
                   የነጻ ፈቃድ ኃይል በአንዱ ውስጥ ደካማ ከሆነ በሁሉም ውስጥ ደካማ ነው
                   የነጻ ፈቃድ ኃይል በአንዱ ውስጥ ብርቱ ከሆነ በሁሉም ውስጥ አንድ  ነው።
                   የጣፋጭነት ተፈጥሮ ምንነት በጥሩ ጤንነት ላለ ለአንድ ሰው
                   ጣፋጭ ይመስለዋል።
                   ለታመመ ለሌላው ሰው ግን መራራ ይመስለዋል፤
                   ለነጻ ፈቃድም እንዲሁ
                   ከኃጢአተኞች ጋር ታማሚ ነው፤ ከጻድቃን ጋር ግን ጤነኛ ነው።
                   ማንኛዉም ሰው የጣፋጭነትን ጣዕም መቅመስ ቢፈልግ
                   በታማሚ ሰዎች አፍ ውስጥ አይቀምስም ወይም ለመቅመስ ሙከራ አያደርግም፤
                   ጣዕሞችን ለመለየት መቀመጫ የሚሆነው ጤነኛ አፍ ነው።
                   እንደገና ማንም የነጻ ፈቃድን ኃይል መለካት ቢፈልግ
                   በመጥፎ ተግባሮቻቸው በተዳደፉት ውስጥ መሞከር የለበትም
                   ንጹህ የሆነ ጤነኛ ሰው እሱን ለመቅመስ ማደሪያዉን ሊሰጥ ይገባዋል።
                   ሕመምተኛ ሰው የጣፋጭነት ጣዕም መራራ ነው ሊልህ የሚገባ ከሆነ
                   ሕመሙ ምን ያህል እንደጸና ተመልከት፤
                   ስለዚህም የደስታ ምንጭ የሆነውን ጣፋጭነትን አሳስቶአል፤
                  እንደገና ማንም የተዳደፈ ሰው የነጻ ፈቃድ ኃይል ደካማ ነው ሊልህ የሚገባ ከሆነ
                  የሰው ልጅ ገንዘብ ያደረገውን ኃብት ነጻ ፈቃድን ደሀ በማድረግ 
                  ተስፋዉን እንዴት እንደቆረጠው ተመልከት ። (Church 2:18-23)

 
ይቆየን!