ስምንቱ አርእስተ ግሥ

መምህር በትረማርያም አበባው

ታኅሣሥ ፳፮ ቀን ፳፻፲፬ .

ውድ አንባብያን! እንደምን ሰነበታችሁ? ባለፈው የትምህርታችን ክፍለ ጊዜ ‹‹ባለቤትና ተሳቢ›› በሚል ርእስ አስተምረናችሁ ነበር፡፡ በዚህ ሳምንት ደግሞ ለሰጠናችሁ መልመጃ ምላሽና ስምንቱን የግሥ አርእስት እንመለከታለን፤ በጥሞና ተከታተሉን!

መልመጃ

፩) ለሚከተሉት ቃላት ተሳቢያቸውን ጻፍ።

         ሀ) ማርታ

         ለ) መንበር

         ሐ) ትንሣኤ

         መ) ዮሐንስ

         ሠ) ቃለ ሕይወት

፪) የሚከተሉትን ሁለት ሁለት ቃላት ተናባቢ አድርግ፦

        ሀ) አክሊል እና ጽጌ

        ለ) ክብር እና ቅዱሳን

        ሐ) ፍካሬ እና ኢየሱስ

መልሾች

የጥያቄዎች መልስ

  ሀ) ማርታሃ

  ለ) መንበረ

 ሐ) ትንሣኤ

 መ) ዮሐንስሀ

 ሠ) ቃለ ሕይወት

የጥያቄዎች መልስ

     ሀ) አክሊለ ጽጌ

     ለ) ክብረ ቅዱሳን

     ሐ) ፍካሬ ኢየሱስ

የግሥ አርእስት

የግሥ አርእስት የሚባሉት ስምንት ሲሆኑ እነርሱም የሚከተሉት ናቸው፡፡

ግእዝ አማርኛ
ቀተለ ገደለ
ቀደሰ አመሰገነ
ተንበለ ለመነ
ባረከ ባረከ
ማህረከ ማረከ
ሴሰየ መገበ
ክህለ ቻለ
ጦመረ ጻፈ

ቀተለ ደግሞ የሁሉም ርእስ ስለሆነ ርእሰ አርእስት ይባላል። የአንድን ግሥ አርእስት ማወቅ እንዴት እንደሚዘረዘር ፍንጭ ስለሚሰጥ አርእስተ ግሥ የተባሉትን መለየት ያስፈልጋል።

የቀተለ ቤት የሚባለው ላልቶ የሚነበብ በግእዝ የሚጀምር ፍጹም ሳድስ የሆነ ግሥ ነው።

ምሳሌ፦          

ግእዝ አማርኛ
ሀለበ አለበ
ሰበከ አስተማረ

የቀደሰ ቤት የሚባለው ደግሞ በግእዝ የሚጀምር ጠብቆ የሚነበብ ሦስት እና ከዚያ በላይ የሆነ ቃል ነው።

ምሳሌ፦

ግእዝ አማርኛ
ሐወጸ ጎበኘ
ጸውዐ ጠራ
ተፈሥሐ ተደሰተ

የተንበለ ቤት የሚባለው ዐራት ፊደል ባለው ግሥ መነሻው ግእዝ ሆኖ ከመነሻው ቀጥሎ ሳድስ ከሆነ ነው። አምስት ፊደል ባለው ግሥ ደግሞ መካከለኛው ወይም ድኅረ መነሻው ፊደል ሳድስ ሆኖ ሌላው ግእዝ ከሆነ ነው።

ምሳሌ፦

ግእዝ አማርኛ
አእመረ ዐወቀ
አመድበለ አከማቸ
አስቆረረ አስጠላ

ሦስት ፊደል ሆኖ በራብዕ የሚነሣ ከሆነ ደግሞ የባረከ ቤት ይባላል።

ምሳሌ፦

ግእዝ አማርኛ
ናፈቀ ተጠራጠረ
ማሰነ ጠፋ

ዐራት እና ከዚያ በላይ ፊደል ያለው ሆኖ በራብዕ የሚጀምር ግሥ ደግሞ የማህረከ ቤት ይባላል።

ግእዝ አማርኛ
ጻዕደወ ነጭ ሆነ
ማህረከ ማረከ

የሴሰየ ቤት የሚባለው ደግሞ መነሻው ኀምስ የሆነ ግሥ ነው።

ምሳሌ፦

ግእዝ አማርኛ
ዴገነ ተከተለ
ቄቅሐ ፈተገ
ጼወወ ማረከ

የክህለ ቤት የሚባለው ደግሞ መነሻው ሳድስ የሆነ ግሥ ነው።

ምሳሌ፦

ግእዝ አማርኛ
ብህለ አለ
ርእየ አየ
ጥዕየ ዳነ

 የጦመረ ቤት የሚባለው መነሻው ሳብዕ የሆነ ግሥ ነው።

ምሳሌ፦

ግእዝ አማርኛ
ሞቅሐ አሰረ
ሞርቅሐ ላጠ
ኖለወ ጠበቀ

ከዚህ በላይ የዘረዘርናቸው ስምንቱ የግሥ አርእስት ሲሆን አንዳንድ ጊዜ በየቅኔ ቤቱ የተወሰነ ልዩነቶች ሊኖሩ ይችላሉ። ከእነዚህ ከስምንቱ በተጨማሪ አንድን ግሥ ለማርባት የሚጠቅሙን ግሦች ሲኖሩ እነርሱም የሚከተሉት ናቸው፡፡

ግእዝ አማርኛ
ሤመ ሾመ
ቆመ ቆመ
ገብረ ሠራ
ኀሠ ፈለገ

የሤመ ቤት የሚባለው ሁለት ፊደል ሆኖ በኀምስ የሚጀምር ግሥ ነው።

ምሳሌ፦

ግእዝ አማርኛ
ቄሐ ተፋ
ሬመ ከፍ ከፍ አለ

የቆመ ቤት የሚባለው ደግሞ ሁለት ፊደል ሆኖ በሳብዕ የሚጀምር ግሥ ነው።

ምሳሌ፦

ግእዝ አማርኛ
ኖኀ ረዘመ
ሎሀ ጻፈ
ሞዐ አሸነፈ

የገብረ ቤት የሚባለው ደግሞ መነሻው ግእዝ ከዚያ ቀጥሎ ያለው መካከለኛው ሳድስ መድረሻው ግእዝ የሆነ ቃል ነው።

ምሳሌ፦

ግእዝ አማርኛ
ሠምረ ወደደ
ኀብረ አንድ ሆነ

ሁለት ፊደል ያላቸው ‹‹ኀሠ››ን የመሰሉ መነሻቸውም መድረሻቸውም ግእዝ የሆኑ ቃላት ደግሞ ብዙ ጊዜ መድረሻ ፊደሉን ሁለት ጊዜ ደግመው ሊነገሩ የሚችሉ ናቸው። ለምሳሌ ኀሠ ብሎ ፈለገ ይላል። እንደገና መድረሻውን ደግሞ ኀሠሠ ብሎ ፈለገ ይላል።

ተጨማሪ ምሳሌ፦

ግእዝ አማርኛ
ነደ ነደደ
ጠበ ብልሀተኛ ሆነ

ከዚህ በላይ ያየናቸው ቃላት ካሁን በኋላ ለምንማረው ትምህርት መሠረታዊ የሆኑ ናቸው።

ሠራዊት

አርእስታቸውን ወይም አለቃቸውን የሚመስሉ ነገር ግን የተወሰነ የፊደላት አቀማመጥ ልዩነት ያላቸው ቃላት ሠራዊት ይባላሉ። ለምሳሌ ቀተለ አርእስት ነው። ነገር ግን የቃሉ ሆሄያት አደራደር ‹‹ቀተለ›› ከሚለው ቃል የተለዩ ሆነው አረባባቸው ግን ቀተለን የሚመስሉ ቃላት የቀተለ ሠራዊት ይባላሉ። እነዚህም የሚከተሉት ናቸው፤

ግእዝ አማርኛ
ኀቤተ አገለገለ
ተኬሰ መታ፣ጠመጠመ
ሰኮተ ወለወለ፣ ሠራ (የመንገድ)

ከዚህ እንደምንመለከተው ኀቤተ እና ተኬሰ መካከላቸው ኀምስ ነው። ሰኮተ ደግሞ መካከሉ ሳብዕ ነው። በሆሄያት አደራደር ከቀተለ የተለየ ቢሆንም ነገር ግን ቀተለን መስለው ስለሚረቡ የቀተለ ሠራዊት ተብለዋል። የቀደሰ ሠርዌ የሚባለው ደግሞ የሚከተለው ነው።

                ግእዝ………አማርኛ

                ፩) አንገለገ…….አከማቸ

የቀደሰ ሠርዌ አንድ አንገለገ ብቻ ነው። ይህ ምንም እንኳ የሆሄያት አደራደሩ የተንበለን ቤት መስሎ ቢገኝም ባረባብም ባነባበብም ቀደሰን መስሎ ስለሚገኝ የቀደሰ ሠርዌ ይባላል። የተንበለ ሠራዊት የሚባሉት ደግሞ የሚከተሉት ናቸው።

ግእዝ አማርኛ
ቀበያውበጠ ቀላወጠ
ቀንጦሰጠ ተሰለፈ/አሰለፈ
ዘርዜቀ ነፋ (የወንፊት)

ከዚህ እንደምታዩት ከተንበለ የሆሄያት አደራደር የተለየ አደራደር ቢኖራቸውም ተንበለን መስለው ስለሚወርዱ የተንበለ ሠራዊቶች ተብለዋል። የማህረከ ሠራዊቶች ደግሞ የሚከተሉት ናቸው።

ግእዝ አማርኛ
አንቃዕደወ አንጋጠጠ
ሰካዕለወ መነጠረ
አናሕሰየ አቃለለ/ይቅር አለ

ከላይ እንደገለጥነው የማህረከ ቤቶች በራብዕ ይጀምራሉ ብለን ነበር። ነገር ግን እነዚህ ሠራዊቶች በግእዝ ጀምረዋል። ነገር ግን አረባባቸው ወይም አወራረዳቸው ማህረከን መስሎ ስለሚረባ የማህረከ ሠራዊት ይባላሉ። የሴሰየ ሠራዊቶች ደግሞ የሚከተሉት ናቸው።

ግእዝ አማርኛ
አሌለየ ማለደ/ገሠገሠ
አቅዜዘየ ቅዝዝ ቅዝዝ አለ
አንጌገየ ተቅበዘበዘ

ይህም የሴሰየ ቤቶች በኀምስ ይነሳሉ ብለን ነበር። እነዚህ ሠራዊቶች ግን በግእዝ ተነሥተዋል። አረባባቸው ግን የሴሰየን ስለሚመስል የሴሰየ ወይም የዴገነ ሠራዊት ተብለዋል። የጦማረ ሠራዊቶች ደግሞ የሚከተሉት ናቸው።

ግእዝ አማርኛ
አልኆሰሰ ሹክ ሹክ አለ
አክሞሰሰ ፍግግ ፍግግ አለ
ሶርየመ ለምድ አወጣ
ጎርየመ አገመ

እነዚህ ደግሞ የጦመረ ሠራዊቶች ናቸው። ሶርየመ እና ጎርየመ መነሻቸውም ጦመረን ይመስላል። አልኆሰሰ እና አክሞሰሰ ግን መነሻቸው ግእዝ ነው። ቢሆንም ግን ጦመረን መስለው የሚረቡ ስለሆነ የጦመረ ሠራዊት ይባላሉ። የክህለ እና የባረከ ሠራዊት የላቸውም። ማለት በሆሄያት አደራደርም ራሳቸውን የመሰለ ቃል እንጂ በሆሄያት አደራደር ተለይቶ ሲረባ ግን እነርሱን የሚመስል ቃል የለም ማለታችን ነው። እኒህን ጠንቅቆ ማወቅ ለቀጣዩ ትምህርታችን ወሳኝነት  ስላለው ጠንቅቀን መላልሰን እናንብበው።

 መልመጃ

፩) የሚከተሉትን ቃላት አርእስታቸውን ለዩ!

    ግእዝ……………..አማርኛ

ሀ) ከሠተ……………..ገለጠ

ለ) ርእሰ………………አለቃ ሆነ

ሐ) ሠለሰ……………ሦስት አደረገ

መ) ጋህግሀ…..ክፍትፍት አደረገ

ሠ) ሰንሰለ…………አያያዘ/አቆራኘ

ረ) ሌለየ……………ለየ

፪) ከሚከተሉት ቃላት የሤመን፣ የቆመን እና የኀሠን ቤቶች ለዩ!

                 ግእዝ………አማርኛ

                 ሀ) ጼሐ……..ጠረገ

                 ለ) ሞተ……..ሞተ

                 ሐ) ከበ……..ከበበ

                 መ) ሮዘ…….ወለወለ

ረድኤተ እግዚአብሔር አይለየን!