ጾመ ገሀድ

ታኅሣሥ ፳፮ ቀን ፳፻፲፬ .

የከበሩ አባቶቻችን ሐዋርያት የጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የልደትና የጥምቀት በዓል በረቡዕ ወይም በዓርብ ቀን ቢሆን በበዓለ ኃምሳ የሚበላውን የጥሉላት መብል በጥዋት በመብላት ምእመናን ሁሉ በዓሉን እንዲአከብሩ አዝዘዋል፤ ይህም ጾመ ገሀድ ነው፡፡ እነዚህ ሁለቱ የእግዚአብሔር ታላላቅ በዓላቶቹ ናቸውና።

እኛ በዚህ በኃላፊው ዓለም ተድላ ደስታ ደስ የሚለን ለሌሎች እንዳይመስላቸው እንደ አይሁድና እንደ አረማውያን  በዓል በመብልና በመጠጥ ብቻ እንዳናደርግ፤ ስለዚህ ከልደትና ከጥምቀት በዓል በዋዜማ ያሉትን ሁለቱን ዕለታት እንድንጾም አዘዘን፡፡ የልደትና የጥምቀት በዓል  በረቡዕና በዓርብ ላይ በሚሆን ጊዜ በረቡዕና በዓርብ ፈንታ እንድንጾማቸው ይገባልና፡፡ በዚህም   ሁለት ሥራ ይፈጸምልናል፤ የጾም ሥራና የበዓል ማክበር ሥራ  ነው። እንዲሁም በግብጻውያን አብያተ ክርስቲያን የተሠራ ነው።

በይረሙን በእሑድ ወይም በአይሁድ ሰንበት ቀን ቢሆን ይህም ጌታ የተገለጸበት ጥር ዐሥር  ቀን ነው፤ በዋዜማው ዐርብ  እስከ  ምሽት  ይጹሙ! አስቀድመን እንደተናገርን ጥሉላት አይብሉ፤  የልደትና  የጥምቀት በዓልም ሰኞ ቀን ቢሆን በሰንበት ቀን  ይጾሙ ዘንድ  አይቻልም፡፡ ነገር ግን ጥሉላትን ከመብላት ይጠበቁ።

በጥምቀትም  ዕለት ከእኩለ ሌሊት በፊት  ተነሥተው  በውኃው  ላይ ይጸልዩና  ይጠመቁ፤ ሕፃናትም  በሚጠመቁ ጊዜ በውኃ  እንዳይገድፉ ካህናቱም ከመንጋቱ በፊት ቀድሰው ቀርባኑን ያሳርጉ፤ እጅግም ማልደው በጥዋት ከቤተ ክርስቲያን ይውጡ፤ በከበረ ሥርዓታቸው ጌቶቻችን ሐዋርያት  እንዳዘዙ።

የመለካውያን ወገኖች ግን የልደትና የጥምቀት ዋዜማ በቅዳሜ ቀን ወይም በእሑድ ቀን  ቢሆን በሦስት ሰዓት ይቀድሳሉ፤ ከወደዱም የተባረከ ኅብስት ተመግበው ውኃ ይጠጣሉ፤ ከዚህም በኋላ  ካህናቱ በቤተ  ክርስቲያን ውስጥ ሁነው በየሰዓቱ በመጸለይ ለበዓሉ የሚገባውን የነቢያትን  ትንቢቶች ያነባሉ፤ በዚያም ቀን በምሽት  ይኸውም  ጥር  ዓሥር  ነው  በውኃው ላይ ይጸልያሉ፤ ይህም አባቶቻችን ሐዋርያት እንዳዘዙት  አልሆነም። እርሳቸው የኤጲፋንያን  በዓል  እንዲአክብሩ አዘዋል፡፡ ይኸውም መድኃኒታችን  የተገለጠበት ካኑን በሚባል በሮም ሁለተኛ ወር በሰባት ይህም ጥር ዐሥራ አንድ ቀን ነው፡፡

መለካውያን ግን የከበሩ አባቶች የቤተ ክርስቲያን መምህራን ያዘዙትን ይተላለፋሉ በልደትና በጥምቀት በዓል ዓርብም ረቡዕም ቢሆን አስቀድመው በእርሱ ፈንታ ሳይጾሙ በጥዋት ተነሥተው ይበላሉና።

እኛንም ከበደላችን ያነጻን ዘንድ  በዮርዳኖስም ወንዝ እንደገለጸ የጌትነቱን ክብር በልቡናችን  ይገልጥልን ዘንድ የክብር ባለቤት የሆነ ጌታችንን ኢየሱስ ክርስቶስን እንለምነው፤ ጌትነት ክብር ስግደት  ለእርሱ ይገባልና፤ ከቸር አባቱ ጋር ይቅር  ባይ ከሆነ መንፈስ ቅዱስም ጋር  ዛሬም ዘወትርም ለዘላለሙ አሜን።