ስምና የስም ዓይነቶች

ዲያቆን ዐቢይ ሙሉቀን

የተከበራችሁ አንባብያን ባለፈው ትምህርታችን ላይ የቤት ሥራ የሰጠናችሁ መሆኑ ይታወሳል፡፡ በመሆኑም መልሱን እንደሚከተለው እንሥራ፡፡

፩. ምት፡-  ሠናይት ብእሲት ታቀርብ ማየ እግር ለምታ፤ መልካም ሴት ለባሏ የእግር ውኃ ታቀርባለች፡፡

   ፪. ብእሲት፡- ብእሲ ወብእሲት አሐዱ አካል እሙንቱ፤ ባልና ሚስት አንድ አካል ናቸው፡፡

፫. ሥእርት፡- ሥዕርት ይትረከብ እምላዕለ ርእስ፤ ፀጒር ከራስ ላይ ይገኛል፡፡

፬. ምክዳን፡- ለብሓዊት ገብረት ምክዳነ ለጽሕርታ፤ ሸክላ ሠሪ ለማድጋዋ መክደኛን ሠራች፡፡

   ፭. ክድ፡- ጊዮርጊስ ወሀበ ክሣዶ ለሰይፍ፤ ጊዮርጊስ አንገቱን ለሰይፍ ሰጠ፡፡

   ፮. ገቦ ፡- ገቦ ኢየሱስ አውሐዘ ደመ ወማየ ለመድኃኒተ ኵሉ ዓለም፤ የኢየሱስ ክርስቶስ ጎን ለዓለም  ሁሉ መድኃኒት ደምና ውኃን አፈሰሰ፡፡

ማስታወሻ ፡- ከላይ ለተሰጡት ጥያቄዎች መልሱ ይህ ብቻ ነው ማለት አይደለም፡፡ በዚህ አንጻር ሌላም ተስማሚ ዐረፍተ ነገር እንደሠራችሁም ተስፋ እናደርጋለን፡፡

መራሕያን

መራሕያን ማለት፣ መሪዎች ዋናዎች ማለት ነው፡፡ በነጠላው መራሒ የሚለው መራሕያን ብሎ ይበዛል፡፡ መራሕያን በሌላ አገላለጽ ተውላጠ ስሞች ማለት ነው፡፡

አነ           እኔ                    አንትን      እናንተ

ንሕነ          እኛ                   ውእቱ       እርሱ

አንተ          አንተ                 ውእቶሙ     እነሱ

አንትሙ       እናንተ                ይእቲ        እሷ

አንቲ          አንቺ                 ውእቶን       እነሱ

የግእዝ መራሕያን በቊጥር ዐሥር ሲሆኑ ሁሉም በዐረፍተ ነገር እየገቡ የየራሳቸውን አገልግሎት ይሰጣሉ፡፡ መራሕያን (ተውላጠ ስሞች) በስም ቦታ እየገቡ የስምን ተግባር ያከናውናሉ፡፡ በስም ቦታ ብቻ ሳይሆን በግስ ቦታም እየገቡ ማሰሪያ አንቀጽ በመሆን ያገለግላሉ፡፡ በዚህ ጊዜ ነባር አንቀጽ ይባላሉ፡፡ ማሰሪያ አንቀጽነታቸውን (ነባር አንቀጽነታቸውን) በሌላ ክፍል የምናይ ይሆንና በስም ቦታ እየገቡ የስምን አገልግሎት መያዛቸውን በዚህ እትም እንመለከታለን፡፡

፩. አነ ውእቱ ብርሃኑ ለዓለም፤ ለዓለም ብርሃን እኔ ነኝ፡፡ (ዮሐ.፰፥፲፪)

፪. ንሕነ አባል ወውእቱ ርእስ፤ እኛ ሕዋሳቶች ነን እርሱም ራስ ነው፡፡

፫. አንተሰ አንተ ክመ ወአመቲከኒ ኢየኃልቅ፤ አንተ ግን ያው አንተ ነህ ዓመትህም ከቶ አያልቅም፡፡ (መዝ.፻፩፥፳፯)

፬. አንትሙ ውእቱ ፄዉ ለምድር፤ እናንተ የምድር ጨው ናችሁ፡፡ (ማቴ.፭፥፲፫)

፭. አንቲ ተዐብዪ እምብዙኃት አንስት፤ ከብዙ ሴቶች አንቺ ትበልጫለሽ፡፡ (ውዳሴ ማርያም ዘዐርብ)

፮. አንትን አንስት አሠንያ ማኅደረክን እናንተ ሴቶች ቤታችሁን አሣምሩ፡፡

፯. ውእቱ የአምር ኵሎ፤ እርሱ ሁሉን ያውቃል፡፡

፰. ውእቶሙ ተሰዱ እምሀገሮሙ፤እነርሱ ከሀገራቸው ተሰደዱ፡፡

፱. ይእቲ ተዐቢ እምኪሩቤል፤እርሷ ከኪሩቤል ትበልጣለች፡፡ (ውዳሴ ማርያም ዘረቡዕ)

፲. ውእቶን ደናግል ዐቀባ ማኅፀንቶን እነዚያ ደናግል አደራቸውን ጠበቁ፡፡

መራሕያንን ከዐረፍተ ነገር በዘለለ በአንድ አንቀጽ እንዴት አገልግሎት ላይ እንደሚውሉ እንመልከት፡፡

አነ ሶበ እጼሊ ወትረ አአኵቶ ለእግዚአብሔር እንዘ እብል አምላክ አንተ ለኵሉ ዘሥጋ ወለኵላ ዘነፍስ፤ ወንጼውዐከ በከመ መሐረነ ቅዱስ ወልድከ እንዘ ይብል አንትሙሰ ሶበ ትጼልዩ ከመዝ በሉ፤ ካዕበሂ እኄሊ ከመ አንትሙ ትብሉ ከመ ንሕነኒ ንሕድግ ለዘአበሰ ለነ::

ወኤፍሬምኒ ወደሳ ለድንግል እንዘ ይብል አንቲ ውእቱ ሰዋስው ዘርእየ ያእቆብ፤ እስመ ይእቲ ተነግረት በሕገ ኦሪት፡፡ ነቢያት ወሐዋርያት ሰበኩ ክርስቶስሃ፡፡ እስመ ውእቱ ከሠተ ሎሙ ወውእቶሙ አእመሩ በእንቲአሁ፡፡ ውእቱሂ ከሠተ ምሥጢረ ለአንስት ወይቤሎን አንትን  ሑራ ንግራሆሙ ለአርዳእየ፡፡ ወውእቶን ሰበካ ትንሣኤሁ ለወልድ፡፡

ከላይ በተገለጸው ምንባብ ዐሥሩም መራሕያን አገልግሎት ላይ እንደዋሉ መረዳት ያስፈልጋል፡፡

ይቆየን