በዘመናችን የቤተ ክርስቲያን ፈተና

የተከበራችሁ አንባብያን እንደምን ሰነበታችሁ? ባለፉት ተከታታይ ጽሕፎች ላይ በዘመናችን ቤተ ክርስቲያን የገጠማትን ፈተና በተለይ የቤተ ክርስቲያንን ቃጠሎና የይዞታ መነጠቅን በተመለከተ መጠነኛ መረጃ የሚሰጥ ጽሑፍ ማቅረባችን ይታወቃል፡፡ ቀጣዩን ደግሞ እንደማከተለው አቅርበነዋል፡፡

ሀገራችንን የምንወድና ሰላማውያን ከሆንን ቀርበን መወያየት፣ ጥፋተኞችን መገሠጽ፣ አጥፊዎችን ለሕግ ማቅረብና ለተፈጠረው ጥፋት ይቅርታ ጠይቆ ካሳ ካስፈለገ መክፈል ነው፡፡ በሃያ ሰባት ዓመታት በቤተ ክርስቲያን ላይ የደረሰውን እንተውና ለውጥ ከመጣ በኋላ የጥፋት ኃይሎች የፈጸሙትን በመጠኑ ለማቅረብ እንሞክር ቢባል እንኳ ተዘርዝሮ አያልቅም፡፡ ‹‹ሚያዝያ ፳፻፲፩ ዓ.ም ሐረር ሳሮሙጢ በሚኖሩ በአራት ካህናትና በምእመናን ላይ የመግደል ሙከራ ተደርጐ ከባድ ድብደባ ቢፈጸምባቸውም በእግዚአብሔር ቸርነት ተርፈው ሆስፒታል ገብተዋል፡፡›› ይህ የሚያሳየው ጥፋቱ ተጠናክሮ መቀጠሉን ነው፡፡ ይህንን ጥፋት እየፈጸሙ ሰላማውያን ነን ቢሉን ማመን አንችልም፡፡ ሰላም የሚመጣው በተግባር እንጂ በቃል አይደለም፡፡ መንግሥት አጥፊዎችን ለሕግ ያቅርብልን፣ ወደ ፊትም ጉዳት እንዳይደርስብን ጥበቃ ያድርግልን የምንለው ለዚህ ነው፡፡ ጥፋቱ አንድ ጊዘ ተፈጽሞ በመቆሙም አይደለም፡፡ በድሬዳዋ፣ በከሚሴ፣ በኤፍራታና ግድም፣ በሰሜን ሸዋ ሰላሌ፣ በምዕራብ ሸዋ፣ ወሊሶ፡ በጅማ ሊሙኮሳ በተከታታይ የተፈጸመውን በማየት እንጂ፡፡

በድሬዳዋ ሀገረ ስብከት የተፈጸመውም ከዚህ ጋር ተቀራራቢ ነው፡፡ በድሬዳዋ ከተማ ዳር የሚገኘውን ‹‹የመካነ ሕይወት አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ ቤተ ክርስቲያንን ይዞታ እንወስዳለን በማለት ከመጋቢት ፳፻፲፩ ዓ.ም ጀምሮ ተደጋጋሚ ጥቃቶች በእስላሞች ተፈጽመዋል፡፡ የፖሊስ አባላቱ ችግር በተፈጠረበት ቦታ በሰዓቱ ቢደርሱም ጥቃት ፈጻሚዎቹን በመያዝና ወደ ሕግ በማቅረብ ፈንታ እንዲሸሹ ማድረጋቸውን ለማወቅ ችለናል፡፡ በአንጻሩ ደግሞ የቤተ ክርስቲያንን ይዞታ አናስነካም፣ ቤተ ክርስቲያን ጉዳት ሲደርስባት ቆመን አናይም ያሉ ወጣት ክርስቲያኖችን አስረው በመግረፍ የጥቃቱ ተባባሪ ሆነዋል፡፡››

ማኅበረ ቅዱሳን ወንጀል የሠሩ አካላት አይጠየቁ አላልንም፡፡ ጥፋተኛ ተለቅቆ፣ ተጎጂው የሚታሰርበትና የሚሰቃይበት አሠራር ይስተካከል በማለት ግን እንጠይቃለን፡፡ የፍትሕ አካላትም ከአንድ ወገን የሰሙትን ብቻ ይዘው ወደ ውሳኔ ከመግባት ይልቅ ከሃይማኖት ነፃ በሆነና የተቀመጡበትን ኃላፊነት ባገናዘበ መልኩ ሁለቱንም ወገን ፊት ለፊት አቅርቦ እውነቱን በማውጣት አጥፊዎችን ለሕግ ማቅረብ ይኖርባቸዋል ለማለት ነው፡፡ በወቅቱ የቤተ ክርስቲያኑን ይዞታ ለመቀራመት አሰፍስፈው የነበሩ ወገኖች የምኒሊክ ሃይማኖት ይውጣልን በማለት ይጮኹ እንደነበር የደረሰን መረጃ ያመለክታል፡፡ ይህ ድርጊት የሰውን ልጅ የእምነት ነፃነት የሚፃረር ነው፡፡

የቤተ ክርስቲያንን ይዞታ ለመቀራመትና ደኗን ጨፍጭፎ ለማውደም የተሰለፉ ወገኖች ቤተ ክርስቲያኗን ከምኒሊክ ጋር ለማያያዝ ምን ሞራላዊስ ሃይማሃታዊስ ችሎታ ይኖራቸዋል፡፡ ክርስትናም ጌታችን ለሐዋርያት ያስተማረው እንጂ በሰዎች የተፈጠረ ሃይማኖት አይደለም፡፡ ምኒሊክ ከመነሣታቸው ከሁለት ሺህ ዓመታት በፊት ፍጹም አምላክ የሆነው እግዚአብሔር ወልድ ፍጹም ሰው በመሆን የመሠረተው፣ ዓለምን ከጨለማ ወደ ብርሃን ያመጣበት ሃይማኖት ነው፡፡

ቅዱስ ጳውሎስን ሊገድሉ በለስ አልቀናቸው ያሉ አይሁድ የሮማውያን ሕግ የሰጣቸውን መብት በትክክል መጠቀም ሲገባቸው ሕጉን ጠምዝዘው ጳውሎስን ካልገደልን እህል አንበላም፣ ውኃም አነጠጣም ብለዋል፡፡ ታሰሮ የነበረውን ቅዱስ ጳውሎስ ወደ አደባባይ እንዲያወጣላቸው ሀገረ ገዥውን ሕጋውያን መስለው ጠይቀው የግል ጥላቻቸውን በሕግ ሽፋን ለመፈጸም ተማምለው እንደነበር ሁሉ ዛሬም እየተፈጸመ ያለው የጥንቱ ተመሳሳይ ክፍት ነው፡፡ ሕግ የሰጠውን መጠቀም መብት ነው፡፡ ሕግን ጠምዝዞ ግላዊ ፍላጐትን ለማሟላትና ሌላውን ለማጥፋት መሞከር ግን ወንጀል ነው፡፡ የማይገለጥ የተከደነ፣ የማይታወቅ የተሰወረ ጉዳይ ባለመኖሩ ተደብቀን ብናጠፋ ሁለት ቀን ሳናድር እውነቱ ይገለጣል፡፡ የአጥፊዎች አሳብ ታሪክ ምንም ይበል እኛ ብቻ ደኅና ካላሉና ሀገር ብትበተን ምን አገባን ካላሉ በስተቀር ያልተረዱት እውነታ ወደ ሌላው የወረወሩት ቀስት እነሱንም እንደሚወጋቸውና ለሌላው ያነደዱት እሳት ራሳቸውንም እንደሚያቃጥላቸው ነው፡፡

በዚሁ በያዝነው ዓመት ባሳለፍነው የሚያዝያ ወር ሌላም ዘግናኝ ድርጊት በእስልምና እምነት ተከታዮች ጅማ ሀገረ ስብከት ሊሙኮሳ በሚባል ቦታ ተፈጽሟል፡፡ ታሪኩ እንዲህ ነው ‹‹ሚያዝያ አምስት ቀን ፳፻፲፩ ዓ.ም ለሚዘክረው አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ ጽዋ ጉዝጓዝ ቄጠማ ሊያጭድ በሔደበት ሚጡ ወንዝ ዳርቻ አቶ ልየው ጌትነት የተባለን የኦርቶዶክስ ተዋሕዶ  ቤተ ክርስቲያን የእምነት ተከታይ አንገቱን ቀልተዉ በመጸዳጃ ቤት ጉድጓድ ውስጥ ከጣሉት በኋላ በላዩ የከብት ፍግ ጨምረውበታል፡፡ የመጸዳጃ ጉድጓዱ ባለቤት አቶ መሐመድ ሃምዛ የተባሉ ግለሰብ ነው፡፡ ወዳጅ ዘመዶቻቸው ቄጤማ ሊያጭድ ወጥቶ የቀረውን አቶ ልየው ፍለጋ ቢወጡ የደም ነጠብጣብ በማግኘታቸው ነጠብጣቡን ተከትለው ሲሔዱ ለማመን በሚከብድ ሁኔታ ገድለው ከአጨደው ቄጠማ ጋር መጸዳጃ ቤት ውስጥ ጥለውት ተገኝቷል፡፡›› ይህን ወንጀል የፈጸመው አካል ተጠርቶ ወደ ሕግ አልቀረበም፡፡ ከሁለት ዓመት ላላነሰ ጊዜ በደረሰባቸው ተደጋጋሚ ግፍ በአካባቢው ይኖሩ የነበሩ ክርስቲያኖች ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ድንኳን ተክለው መኖር ጀምረዋል፡፡

ቤተ ክርስቲያን ስታስጠልል ዘርና ሃይማኖት እንደማትመርጥ የመካቆሪሾች አባርረዋቸው ለመጡት የመሐመድ ተከታዮች ክርስቲያኑ ንጉሥ አረማህ ተቀብሎ በሰላም እንዲኖሩ የፈቀደላቸው መሆኑን የምንመሰክረው እኛ ብቻ ሳንሆን ምዕራባውያን ጭምር ናቸው፡፡ ይህንንም ጉዳይ አቶ አንዳርጋቸው ፅጌ ‹‹የእነሱ መንግሥታት (ምዕራባውያን) በ፳ኛው መቶ ክፍለ ዘመን እኔን የመሰለ ስደተኛ በሀገሩ መቀበሉን እንደ ትልቅ ሰብአዊ ድርጊት ሲቆጥረው፤ የእኔ ሀገር ንጉሦች የጄኔቫ ኮንቬንሽን (ስምምነት)፣ ሰብአዊ መብትና ዲሞክራሲ የሚባል ነገር በሰው ልጅ አእምሮ ባልታሰበበት ከአንድ ሺህ አምስት መቶ ዓመታት በፊት በእምነታቸው ከዘመኑ የሀገራችን ሰዎች እምነት የተለዩ የነቢዩ መሐመድ ተከታዮች ጥገኝነት መስጠታቸውን፣ እነዚህን ስደተኞች መልሱልን በማለት ዓረቦች ለላኩት መልእክተኛ፣ ንጉሣችን በእያንዳንዱ ስደተኛ ክብደት የሚመዝን ወርቅ ብትሰጡኝ እንኳን አሳልፌ አልሰጣችሁም›› (አንዳርጋቸው፣፳፻፲፩፥፲፱) በማለት መመለሳቸውን ጽፈዋል፡፡

ስለዚህ ጉዳይ በጥልቅ ለማወቅ የፈለገ ሰው የእነ ጆን ሰፔንሰር ትሪሚንግሆምን እስላም ኢን ኢትዮጵያን እና የጎበዜ ጣፈጠን እስልምና በአፍሪካ ማንበብ ይጠቅመዋል፡፡ የቤተ ክርስቲያንን እንግዳ ተቀባይነት በማቃለል ማጣጣል ተገቢ አይደለም፡፡ የኢትዮጵያ ነገሥታት ጠብቀው ባቆዩዋት ሀገር እየኖሩ ነገሥታትን የሚተቹና ቤተ ክርስቲያንን ከነገሥታት ጋር እየደረቡ ለመምታት የሚፈልጉ ወገኖች እንደሚተርኩት ሳትሆን ትክክለኛ በመሆኗ በቅርቡ በለገጣፎም ሆነ በቡራዩ የተፈናቀሉ የእስልምናም የሌላ እምነት ተከታዮች እንጠጋ ብለው ሲመጡባት አታምኑብኝም የምትል ሳትሆን ልጆቼ ኑ ብላ እጇን ዘርግታ የምትቀበል መሆኗን አሳይታለች፡፡ ቤት ፈርሶባቸው ቤተ ክርስቲያን የተጠለሉ ወገኖች በኢሳት የቴሌቭዥን ጣቢያ ሲናገሩ ሰምተናልና፡፡

የሚጠቅመንም ካለፈው መጥፎ ታሪክ እየተጠነቀቅን መልካም ከሆነው ያለፈ ታሪካችን መማር ነው፡፡ ድሮ ተፈጽሟል እያሉ የሐሰት ታሪክ እየደረቱ የጥፋት ነጋሪት መምታት እልቂት እንጂ ሰላም ስለማያማጣ አጥፊዎች ደግመው ደጋግመው ተረጋግተው እንዲያስቡበት ማሳሰብ እንወዳለን፡፡ መንግሥትም አጥፊዎችን እንዲያስታግሥልን ደግመን እንጠይቃለን፡፡ ይህንን ጽሑፍ የምንዘጋው በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የሰንበት ትምህርት ቤት ወጣቶች፣ የመንፈሳዊ ኮሌጅ ደቀ መዛሙርትና ምሩቃን እንዲሁም የመንፈሳዊ ማኅበራት ተወካዮች በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ በሰጡት መግለጫ ነው፡፡ እንዲህ ይላል ‹‹እስከ ዛሬ ሲፈጸሙ በኖሩ ጥቃቶች ላይ ከጥንስሱ ጀምሮ እጃቸውን የከተቱ፣ ያለ አንዳች ፍርሃት በአደባባይ ጭምር በክርስቲያኑ ሕዝብ ላይ ሲሳለቁ እና በል ሲላቸውም ዕልቂትን ሲያውጁ በከረሙና እያወጁ ባሉ ከመንግሥት ጭምር የፈረጠምን ነን ባይ ግለሰቦች እና ተቋማት መንግሥት ለፍርድ እንዲያቀርብልን እንጠይቃለን›› ይህ ቃል ሰላም ወዳድ ከሆነ አስተዋይ አካል የሚነገር ነው፡፡ ጥፋትን በጥፋት መመለስ ለሀገር አይጠቅምምና፡፡

 ይቆየን

 ምንጭ ፤ስምዐ ጽድቅ ጋዜጣ ፳፮ ዓመት ቁጥር ፲፮