ሰሙነ ፋሲካ

ሚያዚያ ፳፭ ቀን ፳፻፲፫ ዓ.ም

በሰሙነ ፋሲካ ከትንሣኤ እሑድ ጀምሮ እስከ ሳምንቱ እሑድ ድረስ የሚገኙት ዕለታት የተለያየ ስያሜ አላቸው፤ እነርሱም፡-

፩. ሰኞማዕዶት (ፀአተ ሲኦል)

በትንሣኤ ማግሥት ዕለተ ሰኞ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ነፍሳትን ከሲኦል ሚውጣቱንና ወደ ገነት መመለስና በማሰብ በዕለተ ዓርብ የተፈጸመች ድርጊት በዕለተ ሰኞ ተሰጥቶ ማዕዶትወይም ፀአተ ሲኦል በመባል ተሰይሟል፤ ትርጓሜውም መሻገሪያ፣ መሻገር ማለት ነው።

ማዕዶት ቀድሞ እስራኤላውያን ባሕረ ኤርትራን ተሻግረው ምድረ ርስት መግባታቸውንም ያመለክታል፡፡ በታሪኩ ውስጥም በተጠቀሰው መሠረት ፈርዖን የዲያብሎስ፣ ሠራዊቱ የሠራዊተ ዲያብሎስ፣ ግብፅ የሲኦል፣ ባሕረ ኤርትራ የባሕረ ሲኦል፣ እስራኤል የምእመናን፣ ሙሴ የወልደ እግዚአብሔር፣ በትረ ሙሴ የመስቀል እንዲሁም እስራኤላውያን በሙሴ መሪነት ተሻግረው ምድረ ርስት እንደገቡ ነፍሳትም በክርስቶስ መሪነት ባሕረ ሲኦልን ተሻግረው ገነት የመግባታቸው ምሳሌ ነው። (ዘፀ. ፩፥፴፩)

፪. ማክሰኞ-ቶማስ

ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በዕለተ ትንሣኤው ሐዋርያት ተሰብስበው በነበረበት በዝግ ቤት ገብቶ ሲገለጽላቸው ሐዋርያው ቶማስ ከእነርሱ ጋር አልነበረም፡፡ ሐዋርያትም የጌታችንን ከሙታን ተለይቶ መነሣት ቢነግሩት ‹‹እኔ ሳላይ አላምንም›› አላቸው፡፡ በሚቀጥለው ሳምንትም ጌታችን ቶማስ በተገኘበት በድጋሜ  ተገለጠላቸው፡፡ ጌታችንም ሐዋርያው ቅዱስ ቶማስን ‹‹ጣትህን ወደዚህ አምጣና በጎኔ አግባው፤ ያመንህ እንጂ ያላመንህ አትሁን›› ብሎ በጦር የተወጋ ጎኑን ፥ በችንካር  የተቸነከረ እጁንና እግሩን እንዲዳስሰው በማድረግ ትንሣኤውን  አረጋገጠለት፡፡ ቶማስም ሲዳስሰው እጅ ከእሳት እንደገባ ጅማት ስለተኮማተረ‹‹ጌታዬ አምላኬም›› ብሎ መሰከረ፡፡  በኋላ ግን ፈውሶታል፤ ኢየሱስም ‹‹ስለ አየኸኝ አምነሀል ሳያዩ የሚያምኑ ብፁዐን ናቸው›› አለው፡፡  ምንም አንኳን ድርጊቱ የተፈጸመው በዳግም ትንሣኤ ቢሆንም የሐዋርያው መታሰቢያ ሆኖ ዕለተ ማክሰኞ ቶማስ ተብሎ ተሰይሟል፡፡ (ዮሐ. ፳ ፥ ፳፬ -፴)

 

፫. ረቡዕ-አልዓዛር

ዕለተ ረቡዕ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በአራተኛው ቀን ከመቃብር ጠርቶ ከሞት ባስነሣው በአልዓዛር ተሰይሟል፡፡ የጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ አልዓዛርን ከሞተ ማስነሣቱ አይሁድ በእርሱ ላይ እንዲቀኑና እንዲገድሉት ካደረጉ ምክንያቶች አንዱ ነው፡፡ አልዓዛርን በቃሉ ጠርቶ ከመቃብር ያስነሣው በሞቱ ሞትን ድል አድርጎ የተነሣ አምላካችን ለሰው ዘር ትንሣኤና ሕይወት በመሆኑና የምናምንበትን ሁሉ ትንሣኤ ዘለክብር የማያምኑበትን ደግሞ ትንሣኤ ዘለሐሳር ማስነሣት የሚቻለው እርሱን ቤተ ክርስቲያን ይህን ዕለት ስያሜ ሰጥታ ታመሰግነዋለች፡፡ (ዮሐ. ፲፩ ፥ ፴፰-፵፮)

፬. ሐሙስ- የአዳም ሐሙስ ወይም አዳም

አምላካችን እግዚአብሔር አዳምን ሊያድነው ፈቅዶ ‹‹ከአምስት ቀን ተኩል በኋላ (አምስት ሺሕ ከአምስት መቶ ዓመት ሲፈጸም) ከልጅ ልጅህ ተወልጄ አድንሃለሁ›› ብሎ ቃል የገባለትን በማሰብ ዕለተ ሐሙስ የአዳም ሐሙስ ወይም አዳም ተብሎ ተሰይሟል፡፡ አዳምም ተስፋው ተፈጽሞ ከነልጅ ልጆቹ ወደ ቀደመ ክብሩ ለመግባቱ መታሰቢያ ይሆን ዘንድም ዕለቱ ይከበራል፡፡ (ሉቃ. ፳፬ ፥፳፭-፵፱)

ለጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከእመቤታችን ከቅድስት ድንግል ማርያም ከሥጋዋ ሥጋ ከነፍሷ ነፍስ ነሥቶ ሰው ለመሆኑ ተቀዳሚ ምክንያት ጸሎተ አዳም ወሔዋን ነው፡፡ አምላካችን በገባላቸው ቃል መሠረት ርደተ ሲኦልን፣ ጽልመተ ሲኦልን በብርሃነ መለኮት አስወግዶ ሞተ ሥጋ ወነፍስን አስቀርቶላቸው ‹‹ኃጢአት ከበዛች ዘንድ ጸጋ እግዚአብሔር ትበዛለች›› ብለው ያመሰገኑበት መታሰቢያ ዕለተ ነው፡፡

አዳምና ሔዋን ከሲኦል የወጡት በዕለተ ዓርብ ቢሆንም የቤተ ክርስቲያን አበው ሊቃውንት  የአምላካችን የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ቸርነት በማሰብ ዝክረ አዳም ሐሙስ እንዲከበር በወሰኑት መሠረት የተሰየመ ነው። በዕለቱም አባታችን አዳም በተሰጠው የተስፋ ቃል የሁላችን ድኅነት ስለመፈጸሙ፣ አዳም ከነልጆቹ በጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሞትና ትንሣኤ ነፃ ስለ መውጣቱ ይዘመራል።

፭. ዓርብ-ቤተ ክርስቲያን

ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከዕለተ ጽንስ ጀምሮ እያከናወነው የመጣውን የማዳን ሥራ በዕለተ ዓርብ ፈጽሟል። የቤተ ክርስቲያን ሁለንተናዊ ምሥጢር የተፈጸመበት ዕለት በመሆኑም ዕለተ ዓርብ ቤተ ክርስቲያን የሚል ስያሜ ተሰጥቶታል። በዚህም የቤተ ክርስቲያን ጉልላቷ የመስቀል ምልክት ሆኗል፤  የሕንጻዋ መሠረት ቀራንኒዮ ተተክሎላታል፤ የምትፈትተው ሥጋ መለኮት በቀራንዮ ተቆርሶላታል፤ ደሙም ፈሶላታል፡፡ ልጆቿን ከማኅጸነ ዮርዳኖስ ከአብራከ መንፈስ ቅዱስ እንዲወለዱ የምታደርግበት ማየ ገቦ ተሰጥቷታል፤ ስብከት፣ ትምህርት፣ ተአምራት፣ ትንሣኤ ተደርጎላታል። እነዚህን ሁሉ ምሥጢራተ ቤተ ክርስቲያን የተፈጸሙበት ዕለተ ዓርብ በመሆኑ ዕለተ ዓርብ ቤተ ክርስቲያን ተብሎ ይጠራል፤ የዓርብ ትርጓሜው የመና ፍጻሜ፤ መካተቻ ነውና ። (መጽሐፈ ስዋሰው ወግስ ወመዝገበ ቃላት ገጽ ፯፻፰)

፮. ቀዳሚት ሰንበት-ቅዱሳት አንስት

ቀዳሚት ሰንበት ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ መስቀሉን ተሸክሞ ሲሄድ እስከ ቀራንዮ ድረስ እያለቀሱ ለተከተሉት፣ በትንሣኤው ዕለትም በሌሊት ወደ መቃብሩ ሽቱ ይዘው  ለገሰገሡት ጌታችንም ከሁሉ ቀድሞ ለተገለጸላቸው ቅዱሳት አንስት መታሰቢያ ሁና ቅዱሳት አንስት ተብላ ተሰይማለች፡፡ (ማቴ. ፳፭ ፥፩-፲፩፣ ሉቃ. ፳፫ ፥ ፳፯-፴፫፣፳፬ ፥፩-፲)

ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከሙታን ተለይቶ መነሣቱን መግደላዊት ማርያም ቀድማ ስለማየቷ፣ ቅዱሳት አንስት የእርሱን አካል ሽቱ ለመቀባት ወደ መቃብሩ እንደሄዱ፣ የእግዚአብሔር መልአክም ተገልጦ ስለ ትንሣኤው እንዳበሠራቸው ቤተ ክርስቲያን ታስተምራለች። (ማቴ. ፳፰ ፥፩-፲፭፣ ማር.፲፮ ፥፩-፰፣ ሉቃ.፳፬ ፥፩-፲፪፣ ዮሐ. ፳ ፥፩-፲፰)

፯. እሑድ-ዳግም ትንሣኤ

ቅዱሳን ሐዋርያት በተሰበሰቡበት የጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ትንሣኤ ዕለት ማታ ጌታችን በዝግ ቤት ገብቶ «ሰላም ለእናንተ ይሁን» ብሎ ትንሣኤውን ሲያበሥራቸው ሐዋርያው ቅዱስ ቶማስ ከእነርሱ ጋራ አልነበረም፡፡

ቶማስም ከሄደበት ሲመለስ ጌታችን እንደ ተነሣ እና እንደ ተገለጸላቸው ሐዋርያት በደስታ ነግሩት፤ እርሱ ግን «የችንካሩን ምልክት በእጁ ካላየሁ፥ ጣቴንም ወደ ተቸነከሩበት ካልጨመርሁ፥ እጄንም ወደ ጎኑ ካላገባሁ አላምንም»  አላቸው፡፡ በሳምንቱም ዕለተ እሑድ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ቅዱሳን ሐዋርያት በአንድነት ሳሉ በድጋሚ በዝግ ቤት ገብቶ «ሰላም ለእናንተ ይሁን» አላቸው፤ ቶማስንም «ጣትህን ወዲህ አምጣና እጆቼን እይ፤ እጅህንም አምጣና ወደ ጎኔ አግባ፤ እመን እጂ ተጠራጣሪ አትሁን» አለው፤ ቶማስም «ጌታዬ አምላኬም» ብሎ መለሰ፡፡ (ዮሐ. ፳፩ ፥ ፳፩-፴)

ይህም ማለት ጌታችን ዳግም ለሐዋርያት የተገለጠበት ዕለት በመሆኑ ዳግም ትንሣኤ ተብሎ ይጠራል፤ ይከበራልም:: ለብርሃነ ትንሣኤው ያደረሰን አምላካችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለብርሃነ ዕርገቱም በሰላም ያድርሰን፤ አሜን፡፡

ምንጭ፤  መጽሐፈ ጾመ ድጓ ዘቅዱስ ያሬድ/ድጓ ዘቤተልሔም-ዘዘመነ ፋሲካ/፣ ፍትሐ ነገሥት አንቀጽ ፲፱፥፮፻፴፩-፮፻፴፯