ከእነዚህ ታናናሾች አንዱ እንኳ ይጠፋ ዘንድ በሰማያት ባለው አባቴ ፊት አይፈቀድም(ማቴ. ፲፰፥፲፬)

መጋቤ ሐዲስ ምሥጢረ ሥላሴ ማናየ

ሚያዚያ ፳፱ ቀን ፳፻፲፫  ዓ.ም

ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የሰዎች ልጆችን ከሞት ለማዳን ከሰማየ ሰማያት ወርዶ፣ ከእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ከሥጋዋ ሥጋ ነፍሷ ነፍስ ነሥቶ በሥጋ ተገለጸ፡፡ አምላካችን ወደ ምድር የመጣበት ዋና ዓላማውም የጠፋውን የሰው ልጅ ከጠፋበት ለመመለስ ነው፡፡

የማቴዎስ ወንጌልን ከቁጥር ዐሥራ አንድ ጀምረን ስናበብ እንዲህ የሚል ቃል እናገኛለን፤ የሰው ልጅ የጠፋውን ሊፈልግ፣ የተጎዳውን ሊያድን መጥቷልና፤ ምን ትላላችሁ? መቶ በጎች ያለው ሰው ቢኖር ከመካከላቸውም አንዱ ቢጠፋው፥ ዘጠና ዘጠኙን በተራራ ላይ ትቶ የጠፋውን ሊፈልግ ይሄድ የለምን? እውነት እላችኋለሁ፤ ባገኘው ጊዜ ካልጠፉት ከዘጠና ዘጠኙ ይልቅ ጠፍቶ ስለ ተገኘው ፈጽሞ ደስ ይለዋል፡፡ እንዲሁም ከእነዚህ ታናናሾቹ አንዱ እንኳ ይጠፋ ዘንድ በሰማያት ባለው አባቴ ፊት አይፈቀድም፡፡ (ማቴ. ፲፰፥፲፩-፲፬)

ይህ የጌታችን ቃል የሚያመልክተን ከነገደ መላእክት ተለይቶ፣ ከሥላሴ ልጅነት ወጥቶ የጠፋውን አዳምን ሊፈልግ አምላካችን እንደመጣ ነው፡፡ በደሉን ለመደምሰስና በኃጢአት የተነሣ የተሰደበትን ልጅነት ለመመለስ መድኃኔዓለም ክርስቶስ ወደዚህ ዓለም መጥቶ መከራ እንደተቀበለልንና በመስቀል እንደተሰቀለልንም ያመለክታል፡፡

ታናናሾች የተባሉት የተናቁት፣ የተጠቁት፣ ዓለም ሥፍራ ያልሰጣቸው፣ በደዌ ዳኛ በአልጋ ቁራኛ የታሠሩ፣ ምድር ለስማቸው ዝና፣ ለማንነታቸውም ክብር መስጠት ያልቻለች፤ ነገር ግን አምላካቸው እግዚአብሔር እነርሱን ለማክበር ከሰማየ ሰማያት የወረደላቸው፣ ክቡር ደሙን አፍስሶ ሥጋውን ቆርሶ ሊያድናቸው ዋጋ የከፈለላቸው ናቸው፡፡

አምላካችን ማንም እንዲጠፋ አይፈቅድም፤ እኛ ወደንና ነፃ ፈቃዳችንን ተጠቅመን ልንጠፋ እንችላለን፡፡ ቃሉን ሰምተን ወደ እርሱ መምጣት ቢሳነንም እርሱ ግን ዘወትር እኛን  ከመፈለግ አቋርጦ አያውቅም፡፡ እግዚአብሔር ቸር ጠባቂ እንጂ ክፉ እረኛ አይደለም፡፡ ምክንያቱም ክፉ የሆነ እረኛ በጎቹን አስሮ ስለ እነርሱም ሳይጨነቅ እርሱ በተመቸውና በፈለገው ቦታ ይውላል፡፡ እንዲሁም በጎቹ ጉዳት ያደርስባዋል፡፡ በጎቹንም ሲጠብቅና ሲያሰማራ በለመለመ መስክና በጠራ ውኃ ከማሰማራት ይልቅ ደረቅ ኮሮኮንች የበዛበት ቦታ ላይ ሰብስቦ ሊያስተኛቸው ይችላል፤ በለመለመ መስክ የሚያመለክተው ንጹሕ ቃለ እግዚአብሔር ባለበት ያልተበረዘ፣ ያልተበከለ ቃሉን መስማት በምንችልበት ሥፍራ ነው፤ የአምላካችን ጥበቃ እንደ ቸር እረኛ በመሆኑ በለመለመ መስክ ላይ ያሰማራናል፡፡

ነቢዩ ቅዱስ ዳዊት እግዚአብሔር እረኛዬ ነው፤ የሚያሳጣኝ የለም፤ በለመለመ መስክ ያሳድረኛል፤ በዕረፍት ውኃ ዘንድ አሳደገኝ፡፡ ነፍሴን መለሳት፥ ስለ ስሙም በጽድቅ መንገድ መራኝ፡፡ በሞት ጥላ መካከል እንኳ ብሄድ፥ አንተ ከእኔ ጋር ነህና ክፉን አልፈራም፤ በትርህና ምርኩዝህ እነርሱ ያጽናኑኛል፡፡ በፊቴ ገበታን አዘጋጀህልኝ፥ በሚያሠቃዩኝ ሰዎች ፊት ለፊት ራሴን በዘይት ቀባህ፥ ጽዋህም የተትረፈረፈ ነው፥ ያረካልም፡፡ ምሕረትህ በሕይወቴ ዘመን ሁሉ ይከተለኝ፤ በእግዚአብሔር ቤት ለረዥም ዘመን እኖር ዘንድብሎ ፈጣሪውን አመስግኗል፡፡ (መዝ. ፳፪፥፩-፮)

አምላካችን እግዚአብሔር ለእኛም ይህን ነገር ዘወትር ያደርግልናል፡፡ የጠፋን እንድንመለስ፣ ያልጠፋን ደግሞ እንዳንጠፋ በምርኩዙ ደግፎና አጽንቶ የሚያኖረን እርሱ በመሆኑ ልናመሰግነው ይገባናል፡፡ ይህን እኛ በማናውቀው ድንቅ ጥበቡ የሚያደርገው ከቸርነቱ የተነሣ ማንም እንዳይጠፋ መፈለጉን የሚገልጽበት መንገድ ነው፡፡

በዚህ ዓለም ላይ በግ የሚያረቡና የሚያሰማሩ የበግ እረኞች ለበጉ ብለው ሳይሆን የሚያረቡት ለራሳቸው ጥቅም ነው፡፡ የለመለመ ሳርና የጠራ ውኃ ቢያቀርቡ እንኳን ለበጎቹ አዝነው አይደለም፡፡ አርብተው፣ አስብተው፣ አብዝተው በበዓል ወቅት ሸጠው ገንዘብ ያተርፉበታል፡፡

የዚህ ዓለም የበግ ጠባቂ በጉ ቢጠፋ የሚፈልገው፣ ቢወድቅ የሚያነሣው፣ ቢታመም የሚያሳክመው፣ ቢሰበር የሚጠግነው ለበጉ አዝኖ አይደለም፡፡ የራሱ ጥቅም እንዳይቀርበት ነው እንጂ፤ በግ አርቢው በግ ያረባል፤ ያሰባል፤ ያበዛዋል፤ በመጨረሻ ግን ለበጉ ሳይሆን ለራሱ ጥቅም ያውለዋል፡፡ ሲፈልግ አርዶ ሥጋውን ይበላል፤ ካልሆነ ደግሞ ሸጦ ያተርፍበታል፤ በቆዳዋ ልብስ አሰፍቶ ይለብሳል፡፡

ነገር ግን እግዚአብሔር አምላክ እኛን ሲጠብቀንና ስንጠፋ የሚፈልገን ለእኛ እንጂ ለእርሱ ጥቅም አይደለም፤ ይህ እውነት በፍጥነት ላይረዳንና ላይገባን ይችላል፡፡ አእምሮአችንና ልቡናችን በተለያዩ በዓለማዊ ነገሮች ይደነዝዛል፤ የእግዚአብሔርን መግቦት፣ ጠባቂነትና ለእኛ ያደረገውን ነገር በሙሉ እንረሳዋለን፡፡ ሰሚ ጆሮ ተሰጥቶን፣ አስተዋይ አእምሮ ተፈጥሮልን ያንን መጠቀም ያቅተናል፡፡ ሰብሰብ ብለን ስናገለግል እግዚአብሔርን የጠቀምነው የሚመስለን ብዙዎች ነን፡፡ የምናገለግለው ግን ለአምላክ ሳይሆን ለራሳችን ጥቅም ነው፡፡ ያመሰገነ፣ ያገለገለ፣ ቃሉን የተናገረ፣ የሰማ፣ የጸለየ ጥቅሙ ለራሱ እንጂ ለእግዚአብሔር አይደለም፡፡ እኛ ብንጠፋ አምላክ የሚያገለግሉት እልፍ አእላፍ መላእክት በሰማያት እንዲሁም ቅዱሳን ሰማዕታትና የመንፈስ ቅዱስ ልጆች በገነት አሉት፡፡ ክብሩን መውረስ ስሙን መቀደስ ይቀርብናል እንጂ ምስጋናው አይጎድልበትም፤ ምክንያቱም ምስጋና የባሕርይው ነው፡፡ ጠፍተን ስለፈለገን፣ ወድቀን ስላነሣን፣ በድለን ይቅር ስላለን ብናመሰግነው ተጠቃሚዎች እኛ እንጂ እርሱ አይደለም፡፡ ስለዚህ ወደንና ፈቅደን ልናገለግለው ይገባል፡፡ ሆኖም ወዶ ማመስገን ክብር አለው፤ ተገዶ ማመስገን ግን ማመስገናችን ባይቀርም ክብሩ ግን ይቀርብናል፡፡ በመሆኑም እንድናመሰግነው ከጠፋንበት ይፈልገናል፤ ከወደቅንበት ያነሣናል፤ ይህንም ሲያደርግ ግን እርሱ በጣም ደስ ብሎት ነው፤ እኛን ሊያድን ስለመጣ፣ ሥጋውን ስለቆረሰልን፣ ደሙን ስላፈሰሰልን፣ ለእኛ ራሱን አሳልፎ ሰጥቶ ቤዛ ስለሆነልን እያመሰገንን ልናገለግለው፣ እያገለገልን ልናሰመግነው ያስፈልጋል፡፡

አምላካችን እግዚአብሔር እንድንጠፋ ስለማይፈልግ የሕይወትና የድኅነት በር አዘጋጅቷል፡፡ የምሕረት እጆቹን ዘርግቶ ሊቀበለን ፈቃደኛ ነው፡፡ አብ የሚሰጠኝ ሁሉ ወደ እኔ ይመጣል፤ ወደ እኔ የሚመጣውንም ከቶ ወደ ውጪ አላወጣውም፤ ከሰማይ የወረድሁ የላከኝን ፈቃድ እንጂ፥ ፈቃዴን ላደርግ አይደለምና፤ የላከኝ የአብ ፈቃድም ይህ ነው፤ ከሰጠኝ ሁሉ አንድስ እንኳ ቢሆን እንዳይጠፋ ነው፤ ነገር ግን እኔ በኋለኛይቱ ቀን አስነሣዋለሁይለናል እግዚአብሔር፡፡

የሁላችንም አባት አዳም ሰሚ ጆሮ፣ አስተዋይ አእምሮ፣ እግዚአብሔርን ያህል ጌታ፣ ገነትን ያህል ሥፍራ ተሰጥቶት፣ በአርአያውና በአምሳሉ ከፍጥረታት በተለየ መልኩ ከብሮ የተፈጠረ፣ ነገር ግን ያንን ያላወቀና ያልተጠቀመ ሰው ነው፡፡ ከበደልና ከመርገም ከጥፋት ሊፈልገው በመጣው ሥጋውን ሥጋው ባሕርይውን ባሕርይ ያደረገለት በዓለም መድኃኒት ድኗል፤ ከወቀሳ ግን ዛሬም አልዳነም፡፡ እኛ እንደጥፋታችን ሰበብ የምናደርገው አዳምን ነው፡፡ የእርሱን ደካማ ባሕርይ ይዘን ሊፈልገን የመጣውን አምላካችን የቸርነቱን ሥራን አድርጎልንና ድኅነቱን አመቻችቶልን መፈለግ ባለመቻላችን ጥፋተኛ አድርገን የምንወቅሰው አዳምን ነው፡፡ ነገር ግን የእርሱ ጥፋተኝነት ጎልቶ ይነገራል እንጂ ለባዊነቱ (አስተዋይነቱ) እጅግ የላቀ ነው፡፡ በገነት በነበረበት ጊዜም ሲሳሳት የመከረውም ሆነ ያስተማረው መምህር አልነበረም፡፡ እግዚብአብሔር የሰጠውን አስተዋይነቱንና ዐዋቂነቱን ተጠቅሞ ራሱን ከጥፋት ለማዳን ጥረት አድርጓል፡፡ አምላክም ሲፈልገው ዕርቃኑን ሆኖ እንደሆነ ወደ ፈጣሪው ለመቅረብና ራሱን ለመክሰስ ፈቃደኛ ነበር፡፡ ኃጢአቱንም በደሉንም አስቧል፡፡ ቅጠል ለብሶ አትብላ የተባለውን ዕፀ በለስ ስለበላና ስለተሳሳተ እንተደበቀም ተናግሯል፡፡ (ዮሐ. ፮፥፴፯-፵፣ ዘፍ.፩፥፲፩-፲፪)

ከዚህም በኋላ ኃጢአቱን እያሰበ ለመቶ ዘመን ያህል አልቅሷል፤ ከኀዘኑ ብዛት የተነሣ ይኖርበት የነበረውን የገነት ተድላ ደስታ ጣዕሙን እስኪረሳ ድረስ አለቀሰ፡፡ በተፈጥሮም በተሰጠው ዕውቀት እራሱን የሚዘልፍ ብፁዕ ነው የሚለው ቃል ከሚገልጽባቸው ሰዎች የመጀመሪያው አዳም ነው፡፡ አዳም ጠፍቶ ነበር፤ ከጠፋበትም ለመገኘት ፋላጊው ሲፈልገው ግን ፈቃደኛ ነበር፡፡ ከበለስ እግር ሥር ቢደበቅ፣ ቅጠል ቢያገለድምም አዳም ወዴት አለህ ሲባል  እዚህ ነኝ ከማለት ግን ወደኋላ አላለም፡፡ ፈጣሪው ፈለገው እርሱም ተገኘ፡፡ ዛሬ ፈጣሪያችን እየፈለገን ያልተገኘንና የተደበቅንበት የኃጢአት ዋሻ ጥልቀቱና ስፋቱ የማይታወቅ ብዙዎች ነን፡፡ እግዚአብሔር ግን በምሕረቱ እኛን አሁንም እየፈለገን ነው፡፡ (ዘፍ.፩፥፱-፲)

ያን ጊዜ የሰው ኮቴ እያሰማ ወደ አዳም መጥቷል፤ ዛሬ ሕያው የሆነ ቃሉን እያሰማ ዕለት በዕለት ወደ እኛ ይመጣል፤ ለጸሎት ስንቆም፣ ስንተኛ፣ ስንጠፋ፣ ስናገለግል፣ ስንደክም እንዲሁም ስንበረታ ይመጣል፤ እኛን ያልፈለገበት ጊዜ የለም፡፡ ምን አልባት እኛ እንደ አዳም አስተውለን ከዚህ ነን ብለን መመለስ ወይንም መንቃት አቅቶን ይሆናል፡፡

አዳም በሠራው ኃጢአት የተነሣ ከገነት ተባሮ ወደ ምድር ከመጣ በኋላ የኖረው ፱፻፴ (ዘጠኝ መቶ ሠላሳ) ዓመት ነው፤ አንድ ሺ ሊሞላ ፸ (ሰባ) ዓመት ሲቀረው ሞተ፤ በልጁ በአቤል ሞትን ቢያይም አዳም ትንሣኤ ሙታንን ተስፋ አድርጎ እስከ ዕለተ ሞቱ ኖሯል፡፡ ይህም ጸጸትንና መመለስን ገንዘብ ያደረገና አእምሮውን የተጠቀመ ሰው ስለነበረ ነው፡፡ እኛም አእምሮ አለን፤ የተፈጠርነው አዳምን መስለን ነው፡፡ ስለዚህም እርሱን እንጂ ዲያብሎስን መምሰል የለብንም፡፡ መውደቅ፣ መሳሳት፣ መድከም አዳማዊ ባሕርይ ነው፤ ወድቆ መቅረት ግን ዲያብሎስን መምሰል ነው፡፡ ወድቀንና፣ ጠፍተን ባለመቅረት፣ አምላካችን ሲፈልገንና ስንጠራ አቤት በማለት አባታችን አዳምን መስለን፣ ከውድቀታችን ተምረን፣ የፈለገንን አምላካችንን አመስግነን፣ ተስፋ ትንሣኤን በልቦናችን ሰንቀን መኖር አለብን፡፡ እንደ አዳም ተጸጽተን፣ አልቅሰንና ተመልሰን፣ አገልግለን ከኖርን ክርስቶስን መምሰል እንችላለን፡፡ ስለዚህም አምላካችን ከእነዚህ ታናናሾቹ አንዱ እንኳ ይጠፋ ዘንድ በሰማያት ባለው አባቴ ፊት አይፈቀድምብሎናል፡፡ የመጀመሪያው አዳምን እንደፈለገ ዛሬም ሰውን እንደሚፈልግን በዚህ እንረዳለን፡፡

በአሁኑ ጊዜ በሞት ጥላ ሥር ስንሆንና በሽታ በነገሠበት ዓለም በሕይወተ ሥጋ እንድንቆይ የጠበቀን አምላካችን እግዚአብሔር ነው፡፡ ስለዚህ ይህንን ዐውቀንና ተገንዝበን እናገልግለው፤ እንድንጠፋ የማይፈልግ አምላክ ሲፈልገን በድፍረት እኛ አንፈልግምልንለው አይገባም፡፡

አዳምም ዕለተ ዕረፍቱ በደሰበት ጊዜ ልጆቹ ሴትንና ወንድሞቹን ጠርቶ ከገነት ፊት ለፊት ከነበረው ደብረ ቅዱስ ከተባለው ሥፍራ እንዳይወርዱ ትእዛዝ ከሰጣቸው በኋላ ዐርፏል፡፡ ለእኛ ደግሞ ሁለተኛው አዳም ወንጌልን ሰጥቶናል፤ በገነት ፊት ለፊት መኖር ማለት የሰማነውን ወንጌል በልቡናችን ሰሌዳ ላይ መዝግበን፣ እንደ ምግብ ተመግበነው፣ እንደ መጠጥ ተጥተነው፣ በኃጢአት ሳንወድቅ ከቅድስናው ሕይወት ሳንወጣ እንድንኖር ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ አዞናል፡፡ ሞትን ለሰው ልጆች ያመጣው የመጀመሪያው አዳም ልጆቹን ነፍሰ ገዳይ ከሆኑት እንደ ቃየል ዓይነት ሰዎችን እንዳይቀላቀሉና ኃጢአትና በደልን እንዳይፈጽሙ፣ ከተራራው እንዳይወርዱና ከቅድስናው ሥፍራ እንዳይለዩ ትእዛዝ ሰጥቷቸዋል፡፡ እኛንም አምላካችን ከእግረ መስቀሉ፣ ከቃለ ወንጌሉ እንዳንጠፋ በሐፁረ መስቀሉ ታጥረን፣ በቅድስናው ተራራ ላይ እንድንኖር ትእዛዝ ሰጥቶናል፤ ይህንንም ስናከብር እኛ ታናናሾቹ የተባልነው አንጠፋም፤ ከክብር ወደ ክብር፣ ከልዕልና ወደ ልዕልና ከፍ እያልን የምንሄደው በዚህ በቅድስናው ተራራ በአገልግሎት መኖር ስንችል ነው፡፡

በኖኅ ዘመን መርከብ ስትሠራ እንደ ታቦት ከመካከል ላይ ያደረጉት የእርሱን ዐፅም ነበር፡፡ ትእዛዙን በልቡናቸው ጽላት፣ ዐፅሙን በመርከቡ መካከል አድርገው ከሥጋ ጥፋት መዳን ችለዋል፡፡ ለእኛ ድኅነት ደግሞ የጌታችን ክርስቶስ ሥጋና ደም በቤተ ክርስቲያን ይፈተታል፤ አማናዊ ታቦትም በቤተ መቅደስ ዙሪያ አለ፤  በዚያ መጠቀም ግን አቅቶናል፡፡ እንድንኖርበት ከታዘዝንበት ደብር ቅዱስ ቤተ መቅደሱ በኃጢአት እየወረድን ከነፍሰ ገዳዮች ከክፉዎች ጋር በቃል፣ በሐሳብና በምግባር አንድ ሆነን ከበደለኞች ሳንለይ ዘር በመቁጠር፣ በቋንቋ፣ በድንበር ተከፋፍለን በተለያዩ ኃጢአት ታጥረናል፡፡ እነዚያ በአዳም ዐፅም ተጠቅመዋል፤ እኛ ግን ሥጋው ወደሙን መቀበል አቅቶናል፡፡ ቅዱስ ቁርባን ከሞት ወደ ሕይወት እንድንሻገር የሚያደርገን በመሆኑ ዘወትር ይቀርብናል፡፡ ነገር ግን እኛ ከክርስቶስ ክቡር ሥጋና ቅዱስ ደም እየራቅን ነው፡፡ ቤተ መቅደስ እየኖርን የምንረክስ፣ በቅዱሰ ሥፍራው እየተመላለስን ሕያው የሆነ ቃሉን እየሰማን የተቀደሰ ሕይወት የለንም፤ አምላካችን ግን ዛሬም እየፈለገን ነው፤ ይህንንም ዕድል ሰጥቶናልና ወደ ቅድስናው ተራራ ቤተ መቅደሱና ሥጋ ወደሙ በንስሓ እንቅረብ፡፡ እኛ እንደ አዳም ፱፻፴ ዓመት ስለማንኖር በተሰጠን አጭር የምድራዊ ሕይወት ዕድሜ እንዳንጠፋ የሚፈልገንን፣ እንዳንወድቅ የሚደግፈንን አምላካችን እግዚአብሔርን እየፈለግን ዘወትር መኖር አለብን፡፡

አምላካችን እግዚአብሔር ዕድሜያችን ሳናባክን እንድንጠቀምበት ይርዳን፤ ከጥፋት ያድነን፤ ሀገራችን ኢትዮጵያን ይጠብቅልን፤ አሜን፡

ወስብሐት ለእግዚአብሔር