በዲ/ን ተመስገን ዘገየ
መስጠትና መቀበል በሁለትና ከዚያ በላይ በሆኑ አካላት መካከል ይፈጸማል፡፡ይህም ያለው ለሌለው መስጠት የሌለው ካለው መቀበልና እርስ በእርስ መመጋገብ ነው፡፡ በመጽሐፍ ቅዱስ ተመዝገቦ እንደምናገኘው ‹‹ከሚቀበል ይልቅ የሚሰጥ ብፁዕ ነው››(ሐዋ.፳፥፴፭) ይላል፡፡ በዚህ ኃይለ ቃል ላይ የሚሰጥ አለ ደገሞ የሚቀበል አለ፡፡ በዚህ ግንኙነት ውስጥ የሚሰጠው ከሚቀበለው ይልቅ ዋጋው ታላቅ ነው፡፡ ስለዚህ በክርስቲያናዊ ሕይወት መስጠት ብፅዕና የሚያስገኝ ስለሆነ ባለን ነገር ሁሉ መስጠትን ልንሻ ያስፈልጋል፡፡ እግዚአብሔር ለእያንድንዳችን የተለያየ ጸጋ ሰጥቶናል፡፡ ከእኛ የሚጠበቀው ባለን ጸጋ መጠን ማገልገል ነው፡፡
ለዚህም ነው ሐዋርው ቅዱስ ጳውሎስ በመልእክቱ፡- ‹‹እግዚአብሔር በሰጠን ጸጋ መጠን ልዩ ልዩ ስጦታ አለን ትንቢት የሚናገር እንደ እምነቱ መጠን ይናገር የሚያገለግልም በማገልገሉ ይትጋ የሚያስተምርም በማስተማሩ ይትጋ የሚመክርም በመምከሩ ይትጋ የሚሰጥም በልግስና ይስጥ የሚገዛም በትጋት ይግዛ የሚመጸውትም በደስታ ይመጽውት››(ሮሜ.፲፪፥፮)እንዲል፡፡ ከመልእክቱ እንደተረዳነው መስጠት ብዙ አይነት ነው፡፡ ከነሱም ውስጥ ለምሳሌ ያህል የተወሰኑትን እንደሚከተለው ለማየት እንሞክራለን፡፡
1.ፍቅርን መስጠት
ክርስቲያናዊ ፍቅር ከልብ የተተከለ የመውደድ ኃይል አለው፡፡የክርስቲያኖች የመጀመሪያው ፍቅር የቤተሰብ ፍቅር ነው፡፡ፍቅር የሚጀምረው ከቤተሰብ ነውና፡፡”ነገር ግን በእርሱ ስለሆኑት ይልቁንም ስለቤተሰቦቹ የማያስብ ማንም ቢሆን ሃይማኖቱን የካደ ከማያምን ሰው ይልቅ የከፋ ነው(1ኛጴጥ5÷8) ፍቅር የምግባራት ሁሉ ራስ ነው፡፡ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ የመንፈስ ፍሬ በማለት ከዘረዘራቸው መካከል የመጀመሪያው ፍቅር ነው (ገላ፭÷፳፪) በዘመናችን ግን ይህ የመንፈስ ፍሬ ከሰው ልጆች ልቡና ጠፍቷል፡፡ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስን ደቀ -መዛሙርቱ በደብረ ዘይት ስለ ዓለም ፍጻሜ በጠየቁት ጊዜ ምልክቱን ሲነግራቸው ከሰው ልጅ ዘንድ ፍቅር እንደሚቀዘቅዝ አሳስቧቸዋል፡፡ ”ከዐመፃ ብዛት የተነሣ የብዙ ሰዎች ፍቅር ትቀዘቅዛለች” በማለት (ማቴ24÷12) የፍቅር ሸማ ከሰው ልጆች ልቡና ውስጥ ተገፍፎ ወድቋል፡፡
“ዳሩ ግን የነገር ሁሉ መጨረሻው ቀርቧል እንግዲህ እንደ ባለአእምሮ አስቡ ትጸልዩም ዘንድ በመጠን ኑሩ ፍቅር የኀጢአትን ብዛት ይሸፍናልና ከሁሉ በፊት እርስ በእርሳችሁ ተዋደዱ ”ይላል (፩ኛጴጥ፬÷፯) ወጥ ማጣፈጫው ጨውና ቅመም እንደሆነ ሁሉ የሰው ማጣፈጫውም ሃይማኖትና ፍቅር ነው፡፡የፍቅር ምንጩ ክርስቶስ ነው፡፡ አምስት ሺህ አምስት መቶ ዘመን ለተራቡ ሥጋውን አብልቶ ደሙን አጠጥቶናልና“ወአጽገቦሙ እምበረከቱ ለርኁባን፤ የተራቡትንም በቸርነቱ አጠገባቸው(ሉቃስ1፥53) ዘለዓለማዊ ሕያው አምላክ እግዚአብሔር በቃላት ከመነገርና በልቡና ከመታሰብ በላይ የሆነውን ጥልቅ ፍቅሩን የገለጠው በመስቀል ነው፡፡በአዳም በደል ምክንያት“እኛ ሁላችን እንደ በጎች ተቅበዝብዘን ጠፋን እያንዳንዳችንም በየመንገዳችን ነጎድን”(ኢሳ፶፫÷፮)፡፡ ነገር ግን የሰው ልጆች በኃጢአታችን ምክንያት ከእግዚአብሔር ተለይተን እንዳንቀር አምላካችን ኢየሱስ ክርስቶስ በደል ሳይኖርበት የእኛን በደል ተሸክሞ እኛን ለማዳን በመስቀል ላይ በመሞት ፍቅሩን ገልጾልናል፡፡ ሊቁ አባ ሕርያቆስም ይህንኑ ሲመሰክር “ፍቅር ሰሐቦ ለወልድ ኃያል እመንበሩ ወአብጽሖ እስከ ለሞት፤ፍቅር ኃያል ወልድን ከዙፋኑ አወረደው እስከ ሞትም አደረሰው” ብሏል (ቅዳሴ ማርያም)፡፡
እግዚአብሔር አብ ለሰው ልጅ ያለውን ፍቅር በልጁ በኩል ገልጦልናል፡፡ እርሱም ቅድመ ዓለም የነበረ የባሕርይ ልጁ ኢየሱስ ክርስቶሰ ነው፡፡ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ፍጹም ፍቅሩን ካሳየን በኋላ ‹‹እኔ እንደወደድኋችሁ እርስ በርሳችሁ ትዋደዱ ዘንድ ትእዛዜ ይህች ናት››(ዮሐ.፲፭፥፲፪) በማለት እርሱ እንዲሁ እንደወደደን እኛም እንዲሁ እንዋደድ ዘንድ አዞናል፡፡ ለዚህም ነው ሐዋርያው ቅዱስ ዮሐንስ ” ማንም እግዚአብሔርን እወዳለሁ እያለ ወንድሙን የማይወድ ያላየውን እግዚአብሔርን እንዴት ሊወድ ይችላል? (፩ኛዮሐ ፬÷፰-፲፪) በማለት ያስተማረን፡፤ ስለዚህ ነገ ነፍሳችን ልብሰ ጸጋዋን ተገፋ ከክርስቶስ ፊት እራቁቷን እንዳትቆም ዛሬ በዚህ ዓለም ሳለን የፍቅር ሸማኔ ሁነን ልብሰ ጸጋ ልንሠራላት ይገባል፡፡ድሩን ሃይማኖት ማጉን ፍቅር አድርገን የክብር ልብስ የሠራንላት እንደሆነ ሞገስ ታገኛለች፡፡
ሰው ለፍቅር ዘወትር የጋለ ብረት ምጣድ ሁኖ ከተገኘ ዕድሉ የቀዘቀዘና የፈዘዘ አይሆንበትም”ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስም “በሰዎችና በመላእክት ልሳን ብናገር ፍቅር ግን ከሌለኝ እንደሚጮኽ ናስ ወይም እንደሚንሸዋሽዋ ጸናጽል ሆኜኛለሁ….”(፩ኛቆሮ፲፫÷፩-፰) ቅዱስ ጳውሎስ እምነትን፣ተስፋንና ፍቅርን ከዘረዘረ በኋላ የሚበልጠው ፍቅር ነው ይላል፡፡ ክርስቲያኖች የሚኖረን ፍቅር እንደ ፀሐይ እንጂ እንደ ጨረቃ መሆን የለበትም፡፡ፀሐይ ሁል ጊዜ ሙሉ ነች የእኛ ፍቅር ወጥ መሆን አለበት እንጂ ጥቅም ስለምናገኝ ብቻ ሰዎችን የምናፈቅር ከሆነ ጨረቃ ሁነናል ማለት ነው፡፡”በቃልና በኑሮ በፍቅርም፣በእምነትም በንጽሕናም ለሚያምኑቱ ምሳሌ ሁን “(፩ኛጢሞ፬÷፲፩-፲፪)ክርስትና የምንተርከው ታሪክ ሳይሆን በፍቅር የምንኖረው ሕይወት ነው፡፡ፍቅር ለሌሎች በመስጠት ክፉ የሚያስቡትን በፍቅር ማሸነፍ ይገባል፡፡
 2..ምጽዋትን መስጠት
ምጽዋት ሥርወ ቃሉ የግእዝ ቋንቋ ነው፡፡ትርጓሜውም ስጦታ፣ችሮታ፣ልግስና ማለት ነው፡፡ ሰዎች በሰዎች ላይ የሚያዩትን ችግር በማገናዘብ የተቸገሩትን መርዳት ከፍጹም ፈቃድና ርኅራኄ የሚያደርጉት ስጦታ ምጽዋት ይባላል፡፡ በፍትሐ ነገሥት ፍትሕ መንፈሳዊ አንቀጽ ፲፮ ቊ125-127 እንደተገለጠው ምጽዋት ምሕረት ነው፡፡እግዚአብሔር ከሰጪዎች ጋር የሚሰጥ ከተቀባዮች ጋር ሁኖ የሚቀበል በመስጠትና በመቀበል በሰዎች መካከል መተሳሰብና መረዳዳት እንዲኖር ሀብትን ለሀብታሞች የሚሰጠው ከእነርሱ የሚያንሱትን እንዲያስተናግዱበት ነው፡፡ብላቴን ጌታ ኅሩይ ወልደ ሥላሴ ምጽዋትን የተረጎሙት እንዲህ በማለት ነው “ምጽዋት ማለት የዕለት ምግብና የዓመት ልብስ ለቸገራቸው ሰዎች ገንዘብ መስጠት ነው ደግሞም ምክር ለቸገራቸው መምከር፣ትምህርት ለቸገራቸው ማስተማር ምጽዋት ነው(ጎሐ ጽባሕ ገጽ ፳፬)፡፡
ምጽዋትን ለተቸገረ ሰው የሚሰጥ ሰው ለእግዚአብሔር መስጠቱ ነው፡፡ ጠቢቡ ሰሎሞንም” ለደሀ ቸርነትን የሚያደርግ ለእግዚአብሔር ያበድራል በጎነቱንም መልሶ ይከፍለዋል፡”ይላል(ምሳ፲፱÷፲፯)ምጽዋት ብልሆች ሰዎች በእግዚአብሔር ዘንድ የሚያስቀምጡት አደራ ነው፡፡ ደካሞችን በጉልበት፣ያልተማሩትን በዕውቀት የሙያ ርዳታ የሚስፈልጋቸውን በሙያ መርዳት ምጽዋት ነው፡፡ምጽዋት መስጠት አስፈላጊ እንደሆነ ምጽዋት ሰጪዎችም በእግዚአብሔር ዘንድ የሚጠብቃቸው ከፍተኛ ዋጋ እንዳላቸው በብሉይና በሐዲስ ኪዳናት በሰፊው ተገልጦ ይገኛል፡፡”ድሆች ከምድር ላይ አይታጡምና በሀገር ውስጥ ላለ ደኃ ለተቸገረውም ወንድምህ እጅህን ትከፍታለህ ብዬ አዝዝሃለሁ”(ዘዳ፲፭÷፲፩)
“ወንድምህ ቢደኸይ እጁ ቢደክም አጽናው እንደ እንግዳ እንደመጻተኛ ካንተ ጋር ይኑር”(ዘሌ፳፭÷፴፭) ልዑል እግዚአብሔርም ከመሥዋዕት ይልቅ ምጽዋትን አብልጦ እንደሚወድ በነቢያቱ አንደበት ተናግሯል፡፡“……እኔ የመረጠሁት ጾም …እንጀራህን ለተራበ ትቆርስ ዘንድ ስደተኞች ደሆችን ወደ ቤትህ ታገባ ዘንድ የተራቆተውን ብታይ ታስበው ዘንድ አይደለምን?(ኢሳ፶፯÷፯) መጥምቀ መለኮት ቅዱስ ዮሐንስ በትምህርቱ ተማርከው ለመጠመቅ የመጡትን ሰዎች እንዲህ በማለት የምጽዋትን አስፈላጊነት አስተምሯቸዋል፡፡ ”ሁለት ልብስ ያለው ሰው ለሌላው ያካፍል ምግብም ያለው እንዲሁ ያድርግ “ይላል (ሉቃ፫÷፲፩)፡፡
ክርስቲያኖች የሚመጸውቱት ከተረፋቸው ሳይሆን ካላቸው ነው (ሉቃ፳፩÷፩-፬)ለዚህም ምክንያቱ ደግሞ አስቀድመን እንዳየነው ምጽዋት ትልቅ የክርስትና ቁልፍ በመሆኗ ነው፡፡ብዙዎቻችን የኃጢአት ሥር በተባለው በገንዘብ መውደድ ልባችን ስለታሰረ ምጽዋት የሚመስለን ከተትረፈረፈው ኪሳችን አንድ ብር ለነዳይ መስጠት ነው፡፡ምጽዋት ብድሩ ከልዑል እግዚአብሔር ይገኛል በሚል እምነት ለተቸገሩ ሰዎች የሚሰጥ ልግስና እንደመሆኑ አቀራረቡ ከግብዝነትና ከከንቱ ውዳሴ የጠራ መሆን እንዳለበት ጌታችን አስተምሯል፡፡ የድሆችን ጩኸት ሰምቶ በችግራቸው በመድረስ ምላሽ የሚሰጥ እሱ በተቸገረ ጊዜ በጎ ምላሽ ከእግዚአብሔር ዘንድ ያገኛል፡፡ምጽዋት የክፉ ጊዜ ዋስትና ነው፡፡
ቅዱስ ዳዊት ”ብፁዕ ዘይሌቡ ላዕለ ነዳይ ወምስኪን እምዕለት እኪት ያድኅኖ እግዚአብሔር፣እግዚአብሔር የዐቅቦ ወያሐይዎ ወያበፅዖ ዲበ ምድር፤ለችግረኛና ለምስኪን የሚያስብ ምስጉን ነው እሱንም እግዚአብሔር ከክፉ ቀን ያድነዋል”(መዝ፵÷፩-፪) ጠቢቡ ሰሎሞንም “ፈኑ ኅብስተከ ውስተ ገጸ ማይ እስመ በብዙኅ መዋዕል ትረክቦ፤እንጀራህን በውኃ ፊት ላይ ጣለው ከብዙ ዘመን (ቀን) በኋላ ታገኘዋለህና”(መክ ፲፩÷፩) እንዴት ሰው ዐይኑ እያየ እንጀራውን በውኃ ላይ ጥሎ ከብዙ ቀን በኋላ ያገኘዋል ልንል እንችላለን እንጀራህን በውኃ ላይ ጣለው ማለት ምጽዋትህን ለተቸገሩት ለድሆች ስጥ ማለት ነው፡፡ ከብዙ ቀን በኋላ ታገኘዋለህ ማለት የምጽዋቱን ዋጋ በገነት በመንግሥተ ሰማያት ታገኘዋለህ ማለት ነው፡፡በውኃ ውስጥ የጣሉት እንዳይታይ ሰውረህ ሳትታይ ምጽዋት ስጥ ውኃ የበላው እንዳይገኝ ከዚያ ተመጽዋች ዋጋ አገኛለሁ ሳትል ምግብህን በከርሠ ርኁባን መጠጥህን በጕርዔ ጽሙኣን አኑር ማለት ነው (ዘዳ15÷7)
ምጽዋት የሚመጸውቱ ሰዎች የሚጠቀሙትን ያህል የማይመጸውቱ ሰዎች ይጎዳሉ፡፡ብዙ በረከትንም ያጣሉ፡፡
በመጨረሻ የፍርድ ጊዜም ወቀሳ ተግሣጽ ፍዳ ይጠብቃቸዋል፡፡ ሰው ከሚረገምባቸው የጥፋት ሥራዎች አንዱ ለድሆች አለማዘንና አለመራራት ነው፡፡እስመ ኢተዘከረ ይግበር ምጽዋተ ሰደደ ብእሴ ነዳየ ወምስኪነ፤ምጽዋትን ያደርግ ዘንድ አላሰበም ችግረኛና ምስኪን አሳዷልና“ይላል (መዝ፻፰÷፲፭)ምጽዋት በመስጠት ሰው ፈጣሪውን በሥራ ይመስለዋል፡፡ለሰው ማዘን መራራት ገንዘብ መስጠት ከአምላክ ባሕርይ የሚገኝ ነውና”ወበምጽዋት ይትሜሰሎ ሰብእ ለፈጣሪሁ እስመ ውሂበ ምፅዋት ወተሣህሎ እምነ ጠባይዕ አምላካዊ “እንዳሉ (፫፻.) ፡፡
ምጽዋት መስጠት ለአምላክ ማበደር ነው፡፡ከአምላክ ጋር የሚነግዷት ንግድ ናት፡፡“ወምጽዋትሰ ልቃሕ አምላካዊት ወይእቲ ካዕበ ተናግዶ አምላካዊት ማእምንት ርብሕት“እንዲሉ ፫፻.ዳግመኛም ቍርባን ናት በከርሠ ነዳያን የምትቀርብ ናት ”ወይእቲ ካዕበ ቍርባን ውክፍት በኀበ መቅደስ ነባቢት “እንዳሉ( ፫፻.) ራሱን መርዳት የሚችል ሰው የሰውን ገንዘብ አይቀበል ወጥቶ ወርዶ ራሱን ይርዳ፡
ቅዱሳን ሐዋርያትም ገንዘብ እያለው ምጽዋት የሚቀበል ወዮለት ብለዋል፡፡ምጽዋት ከክፉ ታድናለች፤ኃጢአትን ታስተሠርያለች፡፡ውኃ እሳትን እንዲያጠፋ ምጽዋትም ኃጢአትን ታጠፋለች” ለእሳት ዘትነድድ ያጠፍኣ ማይ ወከማሁ ምጽዋትኒ ታኀድግ ኃጢአተ “እንዳለ ሲራክ ፫÷፳፰፡፡ ሊቁ ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ ደግሞ “ወእመ ትብሎ አንሰ ወሀብኩከ ብዙኀ ጊዜ እብለከ ኢትበልዕኑ አንተ በኵሉ ጊዜ፣ብዙ ጊዜ ሰጠሁት ይበቃሃል አትበል አንተ ጠዋት ማታ ትበላ የለምን ?እንደራስህ አታየውምን ?”ይላል፡፡
ምጽዋት የሚሰጠው ለሰዎች መልካም ነገር በማድረግ ከእግዚአብሔር መልካም ነገር ለማግኘት ነው፡፡”ስጡ ይሰጣችኋል“ተብሏልና (ማቴ.፲፥፰፣2ኛቆሮ.፱፥፯—፲፪) በምጽዋት የተጠቀሙ ብዙዎች ናቸው፡፡ምናሴ ጠላቶቹ ከመከሩበት መቅሠፍት የዳነው ምጽዋትን በመመጽወቱ ነበር
የጌታን ትእዛዝ፣ፈቃድና ትምህርት መሠረት አድርገው ያስተማሩ ቅዱሳን ሐዋርያትም “ካለው የሚሰጥ ብፁዕ ነው ”በሚል ኃይለ ቃል የምጽዋትን ነገር ትኩረት ሰጥተውታል (የሐዋ.ሥራ ፳÷፴፮) ዕዝ ፱÷፭)ምጽዋትንበፍቅር መመጽወት ይገባል፡፡አበው “ከፍትፍቱ ፊቱ“እንዲሉ፡፡ቅዱስ ያዕቆብ “በጎ ለማድረግ ዐውቆ ለማይሠራው ኃጢአት ነው“(ያዕ፬÷፲፯) ይህን በጎ ምግባር ሠርተን እንዲንጠቀም የእጃችንን እስራት አምላካችን ይፍታ በእርግጥ የእግዚአብሔር ስጦታውን በቃላት ተናግረን አንጨርሰውም (፪ኛቆሮ፱÷፲፭)
    3.ለሚጠይቁን ተገቢ የሆነ ምላሽ መስጠት
ሐዋርያው ቅዱስ ጴጥሮስ “በእናንተ ስላለ ተስፋ ምክንያት ለሚጠይቋችሁ ሁሉ መልስ ለመስጠት የተዘጋጃችሁ ሁኑ ነገር ግን በቅንነትና በፍርሀት ይሁን”ይላል( ፩ጴጥ፫÷፲፭ )
ሰሎሞንም“ ልጄ ሆይ ጠቢብ ሁን ልቤንም ደስ አሰኘው ለሚሰድቡኝ መልስ መስጠት ይቻለኝ ዘንድ”ይላል( ምሳ፳፯÷፲፩) “በውኑ ለቃል ብዛት መልስ መስጠት አይገባምን?ወይስ ተናጋሪ ሰው እንደ ጻድቅ ይቈጠራልን?ትምክህትህስ ሰዎችን ዝም ያሰኛቸዋልን?…(ኢዮ፲፩÷፪)
ዘመናችን ከየትኛውም ጌዜ በተለየ በእምነት ስም የተቋቋሙ ድርጅቶች ከቀን ወደ ቀን የበዙበትና እንደ አሸን የሚፈሉበት መሆኑን በዐይናችን እያየን በጀሯችን እየሰማን ነው፡ በአፍሪካ ቀንድ የምትገኘውን የሦስት ሺህ ዓመታት የሃይማኖት ባላ ታሪክ ሀገራችንን ኢትዮጵያንም በየዘመኑ ከመፈታተን ያረፉበት ጊዜ የለም፡፡ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን ግን ጥያቄዎችን በትሕትና በመቀበል ለመናፍቃኑ ተገቢውን ምላሽ ሲሰጡ በመቆየታቸው እናት ቤተ ክርስቲያን ከሥር መሠረቷን ከላይ ጉልላቷን ለማፍረስ የመጡት ሳይሳካላቸው እነርሱ ፈራርሰው ቀርተዋል፡፡ይህን የመናፍቃን ክዶ የማስካድና ተጠራጥሮ የማጠራጠር የኑፋቄ ዘመቻ ለመግታት የክርስቶስን የባሕርይ አምላክነት በጉባኤ በማስተማር መናፍቃን ለቃቅመው ላመጡት ጥያቄ ኦርቶዶክሳውያን አባቶቸች በየዘመናቱ ተገቢውን ምላሽ በመስጠት አሳፍረው መልሰዋቸዋል፡፡ በእምነት ስም በየጓዳው የሚቋቋሙ የመናፍቃን ድርጅቶች ዓላማ የኢትዮጵያውያንን የሃይማኖት መሠረት በማናጋት ሕዝቡ የራሴ የሚለውን እምነቱንና ሥርዓቱን መንፈሳዊ የሆኑ ነገሮችን እንዲያጣ ማድረግ ነው፡፡ስለዚህ ምእመናን ነቅተውና ተግተው ሊጠብቁ ይገባቸዋል፡፡
በመሆኑም እነዚህንና መሰል በጎ ምግባራትን ማድረግ ከአንድ ክርስቲያን የሚጠበቅ ሃይማኖታዊ ግዴታ መሆኑን መገንዘብ ያሻል፡፡ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በወንጌል ‹‹በከንቱ የተቀበላችሁትን በከንቱ ስጡ››(ማቴ.፲፥፰) ብሎ እንዳስተማረን በተሰጠን ጸጋ ያለ መሰሰት ማገልገልና በልግስና መሥጠት ያስፈልጋል፡፡ ይህንን ብናደርግ ዋጋችን ታላቅ ነው፡፡
ምንጭ ሐመር መጽሔት 26ኛዓመት ቁጥር 3 ሐምሌ 2010ዓ.ም