መንፈሳዊነት
ኦርቶዶክሳዊነት ርትዕት ሃይማኖት፣ ጽኑ እምነት፣ መልካም ምግባርና መንፈሳዊ እውቀት በአንድነት የተዋሐዱበት፤ አርአያ እግዚአብሔርን አጽንቶ በሐዋርያዊ የሕይወት ተጋድሎ እግዚአብሔርን በግብር ወደ መምሰል የሚታደግበት ፍጹም ሰማያዊ ሕይወት በመሆኑ፤ አባላት በየትኛውም ቦታ፣ ጊዜና ሁኔታ በማሰብ፣ በመናገር እና በመሥራት/በተግባር በሚገለጽ ክርስቲያናዊ ሥነ ምግባር ታንጸው፣ ፍኖተ አበውን ተከትለው፣ በታማኝነት እና በፈሪሐ እግዚአብሔር ቤተ ክርስቲያንን በቅንነት ያገለግላሉ::
ማኅበረ ቅዱሳን ከስደት ተመላሾችን ለመደገፍ እንደሚሠራ አስታወቀ
ኅዳር 24 ቀን 2006 ዓ.ም.
በእንዳለ ደምስስ
ማኅበረ ቅዱሳን ከሳውዲ አረቢያ ተመላሽ ወገኖቻችንን ለመደገፍ ቀጣይ ሥራዎችን እንደሚሠራ አስታወቀ፡፡
ማኅበረ ቅዱሳን ከሳውዲ አረቢያ በመመለስ ላይ ለሚገኙ ከ2ሺሕ በላይ ኢትዮጵያዊያን ስደተኞች ኅዳር 23 ቀን 2006 ዓ.ም. ቦሌ በሚገኘው የስደተኞች ጊዜያዊ መቀበያ ጣቢያ በመገኘት የምሳ ግብዣ ባደረገበት ወቅት የማኅበረ ቅዱሳን ዋና ጸሐፊ አቶ ተስፋዬ ቢሆነኝ ማኅበሩ በዚህ በጎ አድራጎት ተግባር ላይ ለመሳተፍ የተነሣበትን ምክንያት ሲገልጹ “ማኅበረ ቅዱሳን እንደ ክርስትናም፤ እንደ ዜግነት የወገኖቻችን በዚህ ሁኔታ ላይ መገኘት ያስጨንቀዋል፡፡ ችግሩንም ለመፍታትና ወገኖቻችንን ለመደገፍ ማኅበራችን የበኩሉን ድርሻ መወጣት እንዳለበት በማመን በመንቀሳቀስ ላይ ይገኛል፡፡ ይህ የምሳ ግብዣ የመጀመሪያ ምዕራፍ ሲሆን ወንድሞቻችንና እኅቶቻችንን ለመደገፍ ምእመናንንና አባላትን በማስተባበር ቀጣይ ሥራዎችን እንሠራለን፡፡” ብለዋል፡፡
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በዝርወት ክፍል ሦስት
በዲ/ን ዶ/ር መርሻ አለኸኝ
ባለፈው ዕትማችን የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ በዝርወት /ከኢትዮጵያ ውጪ/ ያደረገችውን ረዥም ሐዋርያዊ ጉዞ የሚዳስስ ጽሑፍ ማውጣታችን ይታወሳል፡፡ ቀጣዩን ደግሞ እንደሚከተለው አቅርበነዋል፡፡
1.1. ውስጣዊ ችግሮች
ቤተ ክርስቲያን በረጅሙ የታሪክ ጉዞዋ ያጋጠሟት ችግሮች ወደ ኋላ ሲቃኙ በብዛት ከልዩ ልዩ አረማውያንና አላውያን ነገሥታት የመጡባት ውጫዊ ፈተናዎች በርከት ብለው ይታያሉ፡፡ እሷን ለመፈተን የማይታክተው ዲያብሎስ በዚህ ዘመን ደግሞ ከውጫዊው ፈተና ባልተናነሰ መልኩ አንዳንድ ክፍተቶችን በመግቢያነት እየተጠቀመ ቤተ ክርስቲያኗ በተለያዩ ውስጣዊ ችግሮች እንድትፈተን በማድረግ ላይ ይገኛል፡፡ እነዚህን ችግሮች አንድ በአንድ እንደሚከተለው እንዳስሳለን፡፡
በንብና ነብር የምትጠበቀው ሥዕለ ማርያም “ወይኑት”
ኅዳር 10 ቀን 2006 ዓ.ም.
በእንዳለ ደምስስ
ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ታላላቅ ገዳማት መካከከል በምሥራቅ ጎጃም ሀገረ ስብከት ውስጥ የሚገኙት የመርጡለ ማርያም እና ደብረ ወርቅ ገዳማት በግንባር ቀደምትነት ይጠቀሳሉ፡፡ ሁለቱም ገዳማት ጥንት መሥዋዕተ ኦሪት ይከናወንባቸው የነበረና ታላላቅ ታሪካዊ ቅርሶችንም ለትውልድ በማስተላለፍ ረገድ ትልቁን ድርሻ ከያዙት ቅዱሳት መካናት መካከል ይመደባሉ፡፡
መስከረም 29 ቀን 2006 ዓ.ም. በምሥራቅ ጎጃም ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ አቡነ ማርቆስ ጥሪ መሠረት በብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ፓትርያርክ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት የሚመራና ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት የሚገኙበት የልዑካን ቡድን መርጡለ ማርያም ገዳም አዲስ ለሚሠራው ሕንፃ ቤተ ክርስቲያን የመሠረት ድንጋይ ለማኖር፤ እንዲሁም በደብረ ወርቅ ማርያም ገዳም የተገነባውን መንበረ ጵጵስና ለመመረቅና ለዘመናዊ ትምህርት ቤት ግንባታ የመሠረት ድንጋይ ለማኖር ከሄደው ልዑክ ጋር ተጉዣለሁ፡፡
ከስደት የመመለሱ ምሥጢር
ኅዳር 5 ቀን 2006 ዓ.ም.
ሊቀ ሊቃውንት ስምዐ ኮነ መልአክ
እግዚአብሔር በሐዲስ ኪዳን ሊያደርገው ያሰበውን ነገረ ድኅነት አስቀድሞ በብሉይ ኪዳንና ቅድመ ብሉይ ኪዳን ለሕዝቡ በተለያየ መንገድ መግለጹን ቅዱሳት መጻሕፍት ይመሰክሩልናል ዕብ 1÷1:: ምክንያቱም ፈታሒነቱና መሐሪነቱ የማይነጣጠሉ በመሆናቸው ነው ይሏል፡፡ የሰው ልጆች በዚያ ዘመን እግዚአብሔር ፈታሒነቱን በተከፈላቸው የኃጢአት ደመዎዝ የተረዱ ሲሆን መሐሪነቱን ደግሞ በተለያየ ኅብረ አምሳል መግለጹ አልቀረም:: ከእነዚያ ብዙ ከምንላቸው ኅብረ አምሳላት አንዱ እንዲህ የሚለው ነው “በዚያም ወራት እንዲህ ሆነ፤ ሙሴ ጎበዝ መሆን በጀመረ ጊዜ ወንድሞቹን ሊጎበኛቸው ወደ ወንድሞቹ ወጣ የግብፅም ሰው የወንድሞቹን የዕብራውያንን ሰው ሲመታ ተመለከተ” ዘጸ.2÷11፡፡ በፈርዖን ቤተ መንግሥት ላደገው ለዚያ ሰው የተነገረለት ቃል በዕውነት አስደናቂ ነው፡፡ ዕድሜው በአባቶቻችን አነጋገር አርባ ዓመት ሆኖት የነበረው ይህ ሰው በጉብዝናው ወራት ወደ ወገኖቹ ሲመጣ ከተማው መከራ የበዛበት፤ ሕዝቡ ለቅሶና ዋይታ የጸናበት አስቸጋሪ ወቅት ሆኖ ነበር የጠበቀው፡፡ የሰው ልጆች ከአስገባሪዎቻቸው የተነሣ እስከ ጽርሐ አርያም ዘልቆ የሚሰማ ጩኸታቸውን አሰምተው የጮሁበት፤ እግዚአብሔርም የሰውን ጩኸት የሰማበት ጊዜ ነበር፡፡ በሌላ አነጋገር የመከራው ማለቂያ፤ የመጎብኘቱ ዘመን መግቢያ ነበር ማለት ነው፤ በመከራ ዘመን የሚጎበኝ ወዳጅ ታማኝ ወዳጅ ነውና፡፡
የማይስማሙትን እንዲስማሙ አድርጎ ፈጠራቸው
ሊቀ ሊቃውንት ስምዐኮነ መልአክ
እግዚአብሔር ሰውን ሲፈጥረው ከሰባት እርስ በርሳቸው ከማይስማሙ ነገሮች ፈጥሮታል:: አራቱ ባሕርያት እግዚአብሔር በጥበቡ ካላስማማቸው በቀር መቼም የማይስማሙ ባላንጣዎች ናቸው፡፡ ምን አልባት ተስማምተው ከተገኙም በጽርሐ አርያም ባለው የእግዚአብሔር ማደሪያ ብቻ ሊሆን ይችላል፡፡ በዚያ ግን ባለጠጋው እግዚአብሔር የውኃ ጣራ፤ የእሳት ግድግዳ ያለው አዳራሽ ሠርቷል፤ ዓለም ከተፈጠረ እስከ ዛሬ ተስማምተው ይኖራሉ እንጂ አንዱ ባንዱ ላይ በክፋት ተነሳስቶ ውኃው እሳቱን አሙቆት፤ እሳቱም ውኃውን አጥፍቶት አያውቅም፡፡ ይህ ትዕግስታቸው በፍጥረት ሁሉ አንደበት ሠሪያቸውን እንዲመሰገን አድርጎታል::
በታች ባለው ምድራዊ ዓለምም ያለው ብቸኛው የእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ የሰው ልጅ ነውና እነዚህ እርስ በእርስ የማይስማሙ መስተጻርራን ነገሮች ተስማምተው የሚኖሩበት ዓለም ሆኗል፡፡ እሳት ከውኃ፤ ነፋስ ከመሬት ጋር የሚያጣብቃቸውን የፍቅር ሰንሰለት የሰው አዕምሮ ተመራምሮ ሊደርስበት የማይችል ታላቅ ምሥጢር ነው፡፡ ግን እንዴት ይሆናል? ነፋስ መሬትን ሳይጠርገው፤ መሬትም ነፋስን ገድቦ ይዞ መላወሻ መንቀሳቀሻ ሳያሳጣው፤ ተስማምተው እንዲኖሩ ያደረገ እግዚአብሔር ታላቅ ነው፡፡ ውኃና እሳት ተቻችለው አንድ ቤት ውስጥ መኖር ችለዋል፤ የጥንት ጠላትነታቸውን በጥበበ እግዚአብሔር አስታራቂነት እርግፍ አድርገው ትተው ከሞት በቀር ማንም ላይለያቸው በቃል ኪዳን ተሳስረዋል፡፡
“አትሮንስ” የመጻሕፍት ውይይት መርሐ ግብር ሊጀመር ነው
ጥቅምት 26 ቀን 2006 ዓ.ም.
በእንዳለ ደምስስ
ማኅበረ ቅዱሳን የቅዱሳት መጻሕፍት የንባብ ባሕልን ለማዳበር በየደረጃው ከሚሠራቸው ተግባራት በተጨማሪ “አትሮንስ” የተሰኘ በመጻሕፍት ላይ የሚደረግ የውይይት መርሐ ግብር ኅዳር 1 ቀን 2006 ዓ. ም. በማኅበሩ ኤዲቶሪያል ቦርድ አስተባባሪነት ይጀመራል፡፡
ንባብ ዕውቀትን ለማዳበር፤ አስተሳሰብን ለማስፋት፤ ሚዛናዊ ብያኔን ለመሥጠት፤ የአባቶችን ሕይወትና ትምህርት ለማወቅ ያለው አስተዋጽኦ ከፍተኛ መሆኑን የሚገልጸው የኤዲቶሪያል ቦርድ ክፍል፤ መንፈሳዊ መጻሕፍትን ማንበብ ዘላለማዊ ሕይወት ማግኛ መንገድን የሚጠርግና ጠቀሜታው የላቀ መሆኑን በመገንዘብ ተግባራዊ እንደሚደረግ አስታውቋል፡፡
ትኩረት ለፊደላት
ጥቅምት 25 ቀን 2006 ዓ.ም.
በዳዊት ደስታ
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ለሀገራችን በርካታ ነገሮችን አበርክታለች፡፡ ከዚህም ካበረከተቻቸው ነገሮች ውስጥ አንዱ ኢትዮጵያ የራሷ ፊደል እንዲኖራት በማድረግ ነው፡፡ የቅርሳቅርስ ጥናት ሊቃውንትና ታሪክ ጸሐፊዎች እንደሚያረጋግጡት የአጻጻፍ ስልት በኢትዮጵያ የተጀመረው ከጌታ ልደት በፊት እንደነበር ነው፡፡ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን አጭር የታሪክ የሃይማኖትና የሥርዐት መጽሐፍ ይገልጻል፡፡ /ገጽ. 9-11/
በአክሱም ዘመነ መንግሥት የሳባውያንና የአግዓዝያን ፊደላት በኅብረት ይሠራባቸው ነበር፡፡ በአክሱም ዘመነ መንግሥት ግን የግእዝ ፊደልና የግእዝ ቋንቋ እያደገ ስለመጣ በክርስቲያን ነገሥታት በአክሱም ዘመነ መንግሥት በሐውልቶችና በሌላም መዛግብት የተጻፉ ጽሑፎች በግእዝ ፊደልና በግእዝ ቋንቋ ተጽፈው እናገኛለን፡፡ የጽሑፍ መሠረት የሆነው ፊደልና የጽሑፍ ስልት በደንብ የታወቀው የክርስትና ሃይማኖት ማለት የኦርቶዶክስ ተዋሕዶ እምነት በኢትዮጵያ መስፋፋት በጀመረበት ወቅት መሆኑ ግልጽ ነው፡፡
ማእከሉ Tewahedo/ተዋሕዶ /የተሰኘ የስልክ አፕ አዘጋጀ
ጥቅምት 22 ቀን 2006 ዓ.ም. በዳዊት ደስታ የማኅበረ ቅዱሳን የሰሜን አሜሪካ ማእከል የቤተ ክርስቲያን አገልግሎት ዘመኑን የዋጀ እንዲሆን Tewahedo /ተዋሕዶ የተሰኘ የስልክ አፕ/ በአይቲ ክፍል አዘጋጀ፡፡ በማእከሉ የተዘጋጀው አፕ የኢትዮጵያና የጎርጎሮሳዊያንን የዘመን አቆጣጠር አጣምሮ የያዘ ነው፡፡ የፈለጉትን ዓመት የበዓላት እና አጽዋማት ቀናት በቀላሉ ማየት ያስችላል፡፡ የየቀናቱን የቅዳሴ ምንባብ በመጽሐፈ ግጻዌ መሠረት ያሳያል፡፡ […]
የቅዱስ ሲኖዶስ ምልዐተ ጉባኤ ልዩ ልዩ ውሳኔዎችን በማሳለፍ አጠናቀቀ፡፡
ጉባኤው ከጥቅምት 11 ቀን 2006 ዓ.ም. ጀምሮ ላለፉት 10 ቀናት ተወያይቶ ያሳለፋቸውን ውሳኔዎች አስመልክቶ ዛሬ ከሰዓት በኋላ ቅዱስ ሲኖዶስ አባላት በተገኙበት በብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርኩ ጋዜጣዊ መግለጫ ተሰጥቷል፡፡ የመግለጫውን ሙሉ ቃል እንደሚከተለው አቅርበነዋል፡፡
የሐዊረ ሕይወት መርሐ ግብር እንደሚካሔድ ተገለጸ
ጥቅምት 19 ቀን 2006 ዓ.ም.
በእንዳለ ደምስስ
ማኅበረ ቅዱሳን ሐዊረ ሕይወት /የሕይወት ጉዞ/ የተሠኘውንና ምእመናንን በማሳተፍ በተመረጡ ቅዱሳት መካናት የሚያካሒደውን መርሐ ግብር ታኅሣሥ 6 ቀን 2006 ዓ.ም. በደብረ ዘይት ደብረ መድኀኒት ኢየሱስ ክርስቶስ ቤተ ክርስቲያን እንዳዘጋጀ የመርሐ ግብሩ አስተባባሪ ኮሚቴ ገለጸ፡፡
አቶ ግርማ ተሾመ የማኅበረ ቅዱሳን ምክትል ዋና ጸሐፊና የሐዊረ ሕይወት መርሐ ግብር አስተባባሪ ኮሚቴ ሰብሳቢ ዝግጅቱን አስመልክቶ በሰጡት ማብራሪያ በመርሐ ግብሩ ላይ ከ5000 በላይ ምእመናን ይሳተፋሉ ተብሎ እንደሚጠበቅና የቲኬት ሽያጩንም በማሰራጨት ላይ እንደሚገኙ ገልጸዋል፡፡ ምእመናን ቲኬቱን በማኅበረ ቅዱሳን ዋናው ማእከል ጽ/ቤት፤ በማኅበሩ የንዋያተ ቅዱሳት ማከፋፈያና መሸጫ ሱቆች እንደሚያገኙ የተናገሩት አቶ ግርማ የቲኬት ሽያጩም ኅዳር 25 ቀን 2006 ዓ.ም. እንደሚጠናቀቅ አሳውቀዋል፡፡