ge awd 2006 2

“ለሁለንተናዊ የቤተ ክርስቲያን እድገት የድርሻችንን እንወጣ” ዐውደ ርዕይ ተከፈተ

ሰኔ 28 ቀን 2006 ዓ.ም.

አውሮፓ ማእከል የጀርመን ቀጠና ማእከል

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የማኅበረ ቅዱሳን የአውሮፓ ማእከል የጀርመን ቀጠና ማእከል በፍራንክፈርት ከተማ ኢኮነን ሙዚየም ያዘጋጀው ዐውደ ርእይ ተከፈተ፡፡ge awd 2006 2

 

ከሰኔ 27- 29 ቀን 2006 ዓ.ም./July 4-6, 2014/ እንዲታይ የተዘጋጀው ዐውደ ርእይ ጥሪ የተደረገላቸው ካህናትና ምእመናን በተገኙበት በልዩ ልዩ ዝግጅቶች ተከፍቷል፡፡ ጸሎተ ወንጌል በቦታው በተገኙ ካህናት ተደርጓል፤ የዐውደ ርእዩን የዝግጅት ሒደትና ይዘት አስመልክቶም አቶ ቃለ አብ ታደሰ የዝግጅት ኮሚቴው ሰብሳቢ የመክፈቻ ንግግር አድርገዋል፡፡

እንደ አቶ ቃለ አብ ገለጻ የጥንታዊቷንና የሐዋርያዊቷን ቤተ ክርስቲያን ታሪክ፣ ባሕልና ትውፊት ማስተዋወቅን ዓላማው ያደረገው ዝግጅቱ በሦስት ዋና ዋና ክፍሎች ተከፋፍሎ የተዘጋጀ ነው፡፡ የመጀመሪያው ክፍል የቤተ ክርስቲያኗን ታሪክ በአጭሩና ተመልካች በቀላሉ ሊረዳው በሚችለው መንገድ የቀረበበት የቤተ ክርስቲያን ታሪክ ነው፡፡  ሁለተኛው ደግሞ የዕውቀትና የጽድቅ እንዲሁም የልማት መሠረቶች የነበሩት ገዳማትና አድባራት እንዲሁም አብነት ት/ቤቶች ያደረጉትን አስተዋጽዖና በአሁኑ ወቅት እያጋጠማቸው ያለው ተግዳሮቶች በዝርዝር የቀረቡበት ነው፡፡ የመጨረሻው ደግሞ ከግንቦት 1984 ዓ.ም ጀምሮ ሰፊ መንፈሳዊና ማኅበራዊ አገልግሎቶችን ሲሰጥ የቆየውና ወደፊትም የሚሰጠው ማኅበረ ቅዱሳን ታሪክ፣ አገልግሎትና በየጊዜው ያጋጠሙት ችግሮች የቀረቡበት ክፍል ነው፡፡ ቤተ ክርስቲያን በአውሮፓ ያላት የአገልግሎት ታሪክ የተዳሰሰበት አንዱ የመርሐ ግብሩ አካል ነበር፡፡

 

ge awd 2006 1በክብር እንግድነት ተገኝተው ዐውደ ርዕዩን በጸሎት የከፈቱት መልዐከ ፀሐይ ቆሞስ አባ ሲራክ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ምስራቅና ምዕራብ አውሮፓ ሀገረ ስብከት የፍራንክፈርት ደብረ ፀሐይ ቅድስት ማርያም ቤተ ክርስቲያን አስተዳዳሪ ናቸው፡፡ መልአከ ፀሐይ በመክፈቻ መርሐ ግብሩ ላይ የተከፈተው ዐውደ ርዕይ በፍራንክ ፈርት ከተማ ለአራተኛ ጊዜ እንደኾነ በማውሳት፤ ሁሉንም ዐውደ ርእዮች አዘጋጅቶ ለፍራንክፈርት ከተማና አካባቢው ሕዝብ ለዕይታ ያቀረበው በማኅበረ ቅዱሳን የጀርመን ቀጠና ማእከል ምስጋና ይገባዋል ብለዋል፡፡ ማኅበሩ ለቤተ ክርስቲያን እየሰጠ ያለው አገልግሎት ሰፊና ጠቃሚ ነው ያሉት መልአከ ፀሐይ ቆሞስ አባ ሲራክ፤ ለዚሁ ደግሞ እኔ ራሴ ምስክር ነኝ በማለት በቅርብ ጊዜ ወደ ኢትዮጵያ ሔደው ማኅበሩ በአቡነ  ቶማስ ዘደብረ ሃይዳ ገዳም እያደረገ ያለውን የልማት እንቅስቃሴ በአብነት ጠቅሰዋል፡፡

 

የዐውደ ርእዩን መከፈት አስመልክቶ አስተያየት እንዲሰጡ የተጠየቁት ምእመናንም በዝግጅቱ እንደተደሰቱ ገልጸዋል፡፡ በፍራንክፈርት ከተማ ነዋሪ የኾኑት አቶ ነቢዩ የማነ፤ ላለፉት ሦስት ጊዜያት የቀረቡትን ዝግጅቶች እንደተመለከቱ አውስተው «ይኸኛውም ዝግጅት ብዙ ያላወኳቸውን ነገሮች አሳውቆኛል፡፡ ይልቁንም የቤተ ክርስቲያኗ ልጆች ምን ያህል ሓላፊነታችንን እንዳልተወጣን አስገንዝቦኛል፤ ይህም በእውነት ቁጭት ፈጥሮብኛል፡፡  ማኅበረ ቅዱሳን በሀገር ቤትም ይሁን በውጭ የሚሰጠው አገልግሎት በእጅጉ እየጠቀመን ነውና ሁሉም ቢደግፈው» በማለት ጥሪያቸውን አስተላልፈዋል፡፡

 

በተመሳሳይ ሁኔታም በከተማው ነዋሪ የኾኑት ወ/ሮ እጥፍ ወርቅ ወልዴ ባዩት ዝግጅት ብዙ ነገር እንዳወቁና «ሁሉም በውጭ የሚኖረው ምእመን በሀገራችን በችግር ላይ ያሉትን ገዳማትንና አድባራትን እንዲሁም አብነት ት/ቤቶችን ለዕረፍትም ይሁን ለልዩ ልዩ ጉዳዮች ወደ ሀገር ቤት ስንሔድ በአካል በመገኘት ልናያቸው ይገባል፤ አይተንም መርዳት ይጠበቅብናል፤» ብለዋል፡፡  አቶ ኤልያስ መሸሻ ደግሞ በስዊዘርላን ነዋሪ የኾኑና ዝግጅቱ ብቁ ቁም ነገሮችን እንዳሳወቃቸው ጠቅሰው፤ «ይህን መሰሉ ድንቅና ጠቃሚ ዝግጅት በሁሉም የአውሮፓ ከተሞች ተዘዋውሮ ሊታይ ይገባዋል» ብለዋል፡፡

 

እስከ እሑድ ሰኔ 29 ቀን 2006 ዓ.ም. /July 6, 2014/ ድረስ የሚቆየውና በበርካታ ምእመናንና ጀርመናውያን እንደሚጎበኝ የሚበሚጠበቀው በዚህ ዝግጅት ጥናታዊ ጽሑፎችና የቤተ ክርስቲያኗን ልዩ ልዩ ባሕሎች የሚያስተዋውቁ ትዕይንቶችና ስብከተ ወንጌል ይቀርባሉ፡፡

 

በሀገረ ጀርመን አስራ አንድ አብያተ ክርስቲያናት የሚገኙ ሲኾን ሁሉም በደቡብ ምስራቅና ምዕራብ አውሮፓ ሀገረ ስብከት ስር የታቀፉና አገልግሎት የሚሰጡ ናቸው፡፡ መንበረ ጵጵስናውን በፍራንክፈርት ከተማ ያደረገው ሀገረ ስብከቱ ሊቀ ጳጳስም ብፁዕ አቡነ ሙሴ ናቸው፡፡